June 21, 2016

በአሜሪካ/በውጩ ዓለም ያሉት አባቶች ወዴየት እያመሩ ነው?!


(ተረፈ ወርቁ):- "... እንደው እነዚህ በአሜሪካ የሚገኙት አባቶች እንደምንም ብለው ተጠናክረው በአገራችን በኢትዮጵያ በእነርሱ በሚመራው በአሜሪካው "ሲኖዶስ" ሥር ያለ/የሚመራ አንድ እንኳን ቤተ ክርስቲያን መመሥረት ቢችሉ በየቦታው ተበታትኖ ያለውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ አንድ ማድረግ መምራት ይቻል ነበር እኮ ...።"

ይህ ቁጭት፣ ምሬት አዘል ቃል በአንድ  ወቅት የኢትዮጵያን ቤ/ን እናድሳለን ብለው ከተነሡ ሰዎች መካከል ማህበር አቋቁሞና ከአንዳንድ ስለ ሃይማኖታቸው በቂ የሆነ መሠረት ከሌላቸውና የእውነት ዕውቀትን በፍቅር ካልተቀበሉና እንደ "ዘመነ መሳፍንቱ" - የባላባቶች ዘመን "አወዳሽና አንጋሽ" ፈላጊ በሆኑ ባለ ጠጋዎች፣ ወይዛዝርት፣ ነጋዴዎች ምጽዋትና እንዲሁም ከውጭ አገር በሚላክለት ዶላር (በተለይ ከዱባይና ከአሜሪካ) በዐሥር ሺዎች የሚገመት ዘመናዊ ቤት/አዳራሽ ተከራይቶ የተሐድሶን እንቅስቃሴ ለማስፋፋት ላለፉት 20 ዓመታት እየደከመ ያለ ሰው የተናገረው ምሬት ያዘለ ቃል ነው። ለነገሩ ይህ ማህበር በነጋ ጠባ ራሳቸውን በሾሙ በጎበዝ አለቆች የሥልጣን ይገባኛልና በጥቅም ግጭት ሲፈርስ ሲሠራ የኖረ፣ እንዳሰቡትና እንዳለሙት እንኳን የኢትዮጵያን ቤ/ን ሊወርሱ ቀርቶ የሕልም ዳቦቸውን እየገመጡ በቀቢፀ ተስፋ ተውጠው ነው ያሉት።

ይህን የተሐድሶ አራማጆች፣ "ተጠሪነቱ  ለአሜሪካው "ሲኖዶስ" የሆነ ቤ/ን በአገር ቤት ቢያቋቁሙ" የሚለው የጥፋት፣ የክፋት ሐሳብ/የሕልም ዓለም ምኞታቸውን ያነሳሁት አለምክንያት አይደለም። በአሜሪካ የሚገኙት ራሳቸውን "ሕጋዊው የኢትዮጵያ ቤ/ን "ሲኖዶስ"/ስደተኛው "ሲኖዶስ" በሚል የሚጠሩ አንዳንድ አባቶችና አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና ያላቸው የተዛባ ምልከታ፣ አፍቃሪ-ፕሮቴንስታዊ/Pro-Protestant አስተምህሮአቸው የተነሳ የተሃድሶ አራማጅ ነን ከሚሉ ሰዎች ጋር "የጡት ልጅን" ያህል በጥብቅ ተዛምደዋል፤ ተጣብተዋል። ይህ ደግሞ አለምክንያት የሆነ አይደለም።

እስቲ እነዚህ የተሃድሶ አራማጅ ነን ባዮችን ዓይናቸውን ወደ ምዕራቡ ዓለም/አሜሪካ እንዲያነሡ ያደረጋቸውንና በአሜሪካ ያለው "ሲኖዶስ"ም - "እልል በቅምጤ" እንዲሉ እነዚህን ሰዎች በደስታ እጃቸውን ዘርግተው እንዲቀበሉ ያደረጋቸውን ምክንያቶቹን በጣም በጥቂቱ ለማየት እንሞክር።

ለረጅም ዓመታት በኖሩበት የምዕራቡ ዓለም የዘቀጠ ባህል ተፅዕኖ ስር የወደቁ የአሜሪካው ስደተኛ "ሲኖዶስ" አንዳንድ "Liberal" ነን ባይ አባቶችና አገልጋዮች በፕሮቴስንታታዊ አስተምህሮአቸውና ሥርዓት አልበኝነታቸው በአገር ቤት የተለዩ ሰዎች መጠለያና መሸሸጊያ መሆናቸው ነገር መቼም ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምስጢር ነው።

"ወንድሜን ሥጋ መብላት የሚያሰናክለው ከሆነ ለዘላለሙ ሥጋን አልበላ።" የሚሉ ቅዱሳን አባቶችና ሐዋርያት ባለፉባት ቤ/ን ስለ "አሳማ ሥጋ" እና ስለ "ኦርጋን መሳሪያ" ክርክር እያስነሡ ምእመናንን የሚያለያዩ ትምህርትን የሚያስተምሩ አባቶችንና አገልጋዮችን የታዘብነው በዚሁ በአሜሪካው "ሲኖዶስ" ነው።

ቁሳዊነት/Materialism፣ ደስታን የማሳደድ የሕይወት ዘይቤ/Hedonism፣ ግላዊነት/Individualism፣ ዘመናዊነት/Modernism ...ወዘተ በገነነበት ዓለም የሚኖሩ እነዚህ አንዳንድ አባቶችና አገልጋዮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የምዕራቡን ዓለም መንፈሳዊ ተቋማት ከመገዳደር አልፈው እያፈራረሷቸው የሚገኙትን እነዚህን ዓለማዊ የሆኑ አስተሳሰቦችንና የኑሮ ዜይቤዎችን በዘመናዊነት ካባ ወደ ቤ/ን ለማስገባት እየተጣጣሩ ነው።

በዛን ሰሞን በአሜሪካው "ሲኖዶስ" የሚገኙ አባቶችና አገልጋዮች፣ "በኦርጋን መዘመር አለበት!" በሚል መግለጫ እስከማውጣት የዘለቁበት አካሔዳቸው - የአገራቸው/የማንነታቸው መግለጫ፣ የባህል መሳሪያዎቻችን ከሆኑት ከእነ በገና፣ ማሲንቆ፣ ክራር፣ እምቢልታና መለከት ...ወዘተ ተለያይተው ምን ያህል በምዕራቡ ዓለም ባህል ተጠልፈውና ተጠላልፈው እንደወደቁ አንድ ትልቅ ማሳያ ነው።

እነዚህ ሰዎች አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ለሺ ዘመናት የትናንትና  ታሪካችን፣ የሥልጣኔያችንና የማንነታችን መገለጫና መታወቂያ ከሆነና የቅዱስ ወንጌል መሠረት ካለው ክርስቲያናዊ ባህላችንና ትውፊታችን፣ ወግና ሥርዓታችን ትውልዱን በማናወጥ የማንነት ቀውስ/Identity Crisis ውስጥ እንዲገባ የማድረግ ዘመቻ ውስጥ እየተዘፈቁ ነው።

ሌላኛዉ ምክንያት የአሜሪካው ሲኖዶስ የአባላቱን ቁጥር ከፍ በማድረግ ሀያልነቱን ለማሳየት ሲባል ወደ እነርሱ የሚመጡትን ሰዎች/አገልጋዮች ብዙም ጥያቄ ሳያበዙ ነው የሚቀበሏቸው። ለነገሩ ይህን ለማድረግም ጠንካራ የሆነ እንደ ሊቃውንት ጉባኤ ያለ መንፈሳዊ ተቋም አለመኖሩም ሌላኛው ጉዳት ነው። ስለዚህም ይህ ጥብቅነት የሌለው ብዛትን እንጂ ጥራትን ከቁጥር ውስጥ ያልሰገባው አሠራር አንዳንዶችን የራሳቸውን አስተምህሮ እንደፈለጋቸው ለመዝራት እንዲችሉ አስችሎአቸዋል።

እዚህ ጋር አባላትን ከማብዛት አንፃር በደቡብ አፍሪካ የሆነ አንድ ታሪክ ላንሳ። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ቤ/ን በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ያላት ስም ትልቅና የከበረ ነው። ደቡብ አፍሪካውያን ለኢትዮጵያ ቤ/ን ያላቸው ይህ ፍቅርና ክብር ከመቶ በላይ ዓመት ያስቆጠረው ለነፃነት ያበቃቸው ANC ፓርቲያቸው የተመሠረተው ቄስ ጆን ዱቤ በተባሉ የቤተ ክርስቲያናችን አባልና ተከታዮቻቸው ነው።

ይህ ታሪክ እውነታ የኢትዮጵያን ቤ/ን በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ጠንካራ መሠረት እንዲኖራት አድርጓል። እናም ቤተ ክርስቲያናችን በደቡብ አፍሪካ ምድር ከአምስት የሚልቁ ቤ/ን፣ በማህሌታዊው ቅዱስ ያሬድ ስም የተመሰረተ አንድ ገዳምና ከሃያ በላይ መንፈሳዊ ጉባኤያት አሉ። ታዲያ ከእነዚህ ጉባኤያት መካከል ማፊኬኔ በተባለ ከተማ ያለ አንድ ጉባኤ በወያኔ በሚመራ ሲኖዶስ እንዴት ትመራላችሁ በሚል የፖለቲከኞች ስብከት፣ መንፈሳዊ፣ አስተዳደራዊ ጥያቄና ብሶት ምክንያት ራሳቸውን ለይተው ግንኙነታቸውን በአሜሪካው ሲኖዶስ ስር በሚመራው ቤ/ን ስር ሆነው ነበር።

ይሁን እንጂ በአሜሪካው ሲኖዶስ ስር ያሉ አባቶችና አገልጋዮች መንፈሳዊ አገልግሎታቸው በዋና ከተማው በጆሃንስበርግ፣ በፕሪቶሪያና በአካባቢው ብቻ የተወሰነ በመሆኑ እነዚህ ከጆሃንስበርግ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀው የሚገኙት የማፊኬኔ ጉባኤ የ"እኛ አባል ናቸው" ከሚል ንግግር ባለፈ ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎትና አስተዳደራዊ መመሪያ ለመስጠት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም። በሂደትም የጉባኤው አባላት እንዳሰቡት መንፈሳዊ አገልግሎት ባለማግኘታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካውያን መካከል እየተስፋፋች መምጣቷ ያሳደረባቸው ባይተዋርነት የተነሳ በመጨረሻ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ኢትዮጵያ ቤ/ን የተመለሱበትን ታሪክ አስታውሳለሁ።

በመጨረሻም ለማንሳት የምፈልገው ምክንያት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አስተዳደር ውስጥ እጃቸውን የሚያስረዝሙ ፖለቲከኞቻችን የፈጠሩት ክፍተት፣ በዘመነ ኢሕአዴግ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች መካከል የተለያዩበትን አሳዛኝ የታሪክ አጋጣሚ ለመጋፈጥ ተገደናል።  ከዚሁ ጋር ተያይዞም  ለአብነትም በአሜሪካ በስደት ላይ የሚገኙ አባቶቻችን በግንቦቱ ሲኖዶስ ስብሰባቸው ያወጡትን ባለ 15 ነጥብ የአቋም መግለጫ መመልከት በቂ ነው። የቤተ ክርስቲያን ሳይሆን የአንድ የመንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ ያወጣው ሊያውም ስሜት አልባና አደናጋሪ የአቋም መግለጫ ነው የሚመስለው።

ሌላው በጣሙን የገረመኝ ነገር ደግሞ የአሜሪካው ሲኖዶስ በዚሁ መግለጫቸው ከወያኔ መንግሥት ጋር ተባብሮ የሚሠሩትንም ሰዎችን ሁሉ አውገዘናል የሚለው ዐርፍተ ነገር ደግሞ ይበልጥኑ አስገረመኝ፣ አሳዘነኝም። ይሄ ማውገዝ፣ መወጋገዝ በቃ ባህል ሆነ ማለት ነው?!

ከጥቂት ዓመታት በፊትም የአሜሪካው ሲኖዶስ አንድ ሊቀ ጳጳስ የሆኑ አባት፣ "በወንጌል እመኑ፣ ንስሓ ግቡ።" ከሚለው እጅግ በከከበረው የዐዲስ ኪዳን የጌታችንና የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አገልግሎት ወርደው፣ "በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳትጓዙ፣ የወያኔ ሽርኮች የሚያስመጡትን በርበሬና ሽሮ እንዳትገዙ ... ወዘተ በማለት በየቦታው ሲቀሰቅሱ ብናያቸው በጣሙን አፈርንም፣ ተሳቀቅንም።

የባለፈው ሰሞንም በአሜሪካ ያሉ አባቶች በኦርጋን ይዘመር ዘመቻም የዚህችን ጥንታዊት፣ ባለ ታላቅ ታሪክና የገናና ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች የአገራችንና የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክና ቅርስ፣ ማንነትና ባህል፣ ሥርዓትና ትውፊት ለማጥፋት፣ ለመናድ ከሚደረግና እንዲሁም በዘመናዊነትና በሥልጣኔ ስም የምዕራቡን ዓለም ባህል ለመጫን/ለማራገፍ ከሚደረግ እኩይ ዘመቻ/ሴራ ተለይቶ የሚታይ እንዳልሆነ ነው የታዘብኩት።

ወደ ሲኖዶሱ መግለጫ ስመለስም በእውነት ያሳፍራል፣ ያሳቅቃልም። ይህ መግለጫ የጥላቻና የፅንፈኝነት መንፈስ ከሚነዳቸው፣ ዕድሜ ዘመናቸውን ከደምና ከቂም በቀል ትርክት መውጣት ካልቻሉት የ60ዎቹ ትውልድ የፓርቲ ስብስብ ማብቂያ የሌለው፣ የነጋ ጠባ የፖለቲካ መግለጫቸው እምብዛም የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም።

ለመሆኑ የተሸከምነው ወንጌል የፍቅር፣ የሰላም መልዕክት እንጂ የጥላቻና የመለያየት ወንጌል ነው እንዴ ...?! ሌላው የሲኖዶሱ መግለጫ ከበርካታ የፊደል ግድፈቶቹ፣ እዚህም እዛም የተደነገሩት ትርጉም የለሽ ቃላቶች በላይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችንን/የግእዙን ቋንቋ አጻጻፍ ሥርዓት የተከተለ አይደለም። ለአብነትም በሐመሩ "ሐ" መጻፍ ያለበት በሀሌታው "ሀ" ተጽፏል፣ ለአልፋው "አ" መጻፍ ያለበት በዓይኑ "ዐ"፣ ሌላም ሌላም የማይጠበቁ ስህተቶች ያሉበት መግለጫ ነው።

እንግዲህ በዚህ ሁሉ ውዝግብ ውስጥ - ፖለቲካው፣ ዘረኝነቱ፣ የአስተምህሮ ችግሩ፣ መለያየቱ፣ መከፋፈሉ ... ወዘተ ገና ይሄ ነው የሚባል መፍትሔ ሳይበጅለት በአሜሪካ የሚገኙ አባቶች ኤጲስ ቆጶሳት ሹመቱን ተያይዘውታል። ሊያውም ደግሞ በአስተምህሮአቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጥያቄ የሚነሳባቸውን ሰዎች ሳይቀር ለዚህ ታላቅ ለሆነ መንፈሳዊ ሓላፊነት ሹሞአቸዋል። ይህ ከመንፈሳዊ ቅናት ይልቅ የእልክ የሚመስል የአባቶቻችን ጉዞ ፍጻሜው ምን ሊሆን እንደሚችል የምናየው ነው የሚሆነው።

አንድ ስለምታደርግ ሥጋውና ደሙ እግዚአብሔር በይቅርታው አንድ ያደርገን ዘንድ ሰላምን እንማልዳለን።
እስከ ፍጻሜያችን ድረስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አንድነት ይጠብቀን ዘንድ ስለ አንድነታችን እንማልዳለን። የሚለው ዘወትር በሥርዓተ ቅዳሴያችን የምንጸልየው ጸሎት ትርጓሜው ምን ማለት ይሆን ግን ...?!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!    

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)