June 13, 2016

የማኅበረ ቅዱሳን የ፭ኛ ዙር ዐውደ ርእይ አጭር ቅኝትእንደ መንደርደሪያ

(ተረፈ ወርቁ):- ከጥቂት ዓመታት በፊት የለንደኑ ተነባቢ መጽሔት ‹‹ዘታይምስ›› ስለ ሩሲያዊው፣ የዓለማችን ታላቅ የፖለቲካ ሰው ቭላድሚር ፑቲን ሃይማኖተኝነት አስመልክቶ አንድ ሰፋ ያለ ዘገባ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ ዘታይምስ ይህን ዘገባ ይዞ የወጣበት ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የሩሲያ ጠቅላይ / የነበሩት፣ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በእስራኤል ይፋዊ ጉብኝት ያደርጉ ስለነበር ነው፡፡

የዛሩን ዘውዳዊ ሥርዓት መሬት አንቀጥቅጥ በኾነው የጥቅምቱ ታላቁ አብዮት የገረሠሠችው አባት አገር ሩሲያ በቀጣይ ‹‹ኅብረተሰባዊነትን›› ከፍ የሚያደርግ ሶሻሊስታዊ ሥርዓትን ነበር ያነበረችው፡፡ ይህ ኮሚኒስታዊ ሥርዓት፣ ‹‹Religion is Opium/ሃይማኖት ሕዝብን ማደንዘዣ ዕፅ ነው፡፡›› በሚል ‹‹እግዜር የለሽ›› መፈክር በሩሲያ የኦርቶዶክስ / ላይ ብርቱ ክንዱን ነበር ያሳረፈባት፡፡ በርካታ መቶ ዓመታትን ያስቆጠሩ ታሪካዊ ገዳማት እንዲዘጉ፣ ሀብት ንብረታቸው እንዲወረስ፣ ታላላቅ ካቴድራሎች ወደ ቤተ መዘክርነት እንዲቀየሩ አዋጅ ከማውጣት ባለፈ ይህንኑ አዋጅ ተግባራዊ አድርጎት ነበር፡፡

በዚህች ‹‹እግዚአብሔር የለሽ›› ሥርዓትን በምታራምድ አገር የተወለዱትን የዛሬውን የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ወላጅ እናታቸው አጥባቂ ክርስቲያን ነበሩና በሕፃንነታቸው ወራት በምሥጢር አንድ ራቅ ወዳለ / ወስደው አስጠምቀዋቸው ነበር፡፡ በሩሲያ ኦርቶዶክስ / የተጠመቁት ፑቲን ወደ ሁለተኛ ደረጃ /ቤት ሲገቡ በሕፃንነታቸው ሲጠመቁ በአንገታቸው ላይ የታሰረላቸውን መስቀል ያለበት ማኅተማቸውን አውልቀው ለእናታቸው፣ ‹‹እኔ የሩሲያ ሶሻሊስት ወጣቶች ማኅበር አባል ኾኛለኹ፣ ሃይማኖት ሕዝብን ማደንዘዣ ዕፅ ነው፡፡›› እናም እናቴ ሆይ ይህ መስቀል የሚያስፈልግሽ ከኾነ በማለት ሰጧቸው፡፡ የፑቲን እናትም ይህን የልጃቸውን የጥምቀት ማኅተም የኾነ መስቀል የከበሩ ንብረቶቻቸውን ከሚያስቀመጡበት ሣጥናቸው ውስጥ ለብዙ ዓመታት ጠብቀው አኖሩት፡፡

 ከበርካታ ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር የለሽ ሥርዓት ከሩሲያ ምድር ብቻ ሣይሆን ፍዳ መከራዋን ካስቆጠራት አገራችንን ጨምሮ በበርካታ አገራት ግብዓተ መሬቱ ተፈጸመ፡፡ በአገረ ሩሲያም ተገልላ፣ ተዋርዳና ተረግጣ የነበረችው የሩሲያ ኦርቶዶክስ / ለአገራቸው የረጅም ዘመን ታሪክ፣ ታላቅ ሥልጣኔ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ማንነትና ማኅበራዊ መስተጋብር ያላት ግዙፍ የኾነ አስተዋጽኦም ታምኖበት ዳግመኛ ተገቢውን ክብርና ስፍራ እንድታገኝ ተደረገ፡፡ በተለይ የፑቲን ወደ ፖለቲካ ሥልጣን መምጣት ቤተ ክርስቲያኒቱ በሩሲያዊ ታሪክና ቅርስ በክብር ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ረገድ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፣ አሁንም እየተጫወቱ ነው፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቅላይ / ፑቲን የመጀመሪያውን ይፋዊ ጉብኝት ወደ እስራኤል ባደረጉበት ወቅት ዕድሜ የተጫጫናቸው እናታቸው ፑቲን የኮሚኒስት አባል በኾኑበት ጊዜ ከአንገታቸው አውልቀው የሰጧቸውን መስቀል በእናትነት ፍቅርና መንፈሳዊ ቅናት ዳግመኛ አበረከቱላቸው፡፡ ዘታይምስ መጽሔት በሰፊው ዘገባው እንዳሰፈረው ፑቲን ያን በሕፃንነት ዘመናቸው በጥምቀታቸው ጊዜ የታሰረላቸውን ታሪካዊ መስቀል በአንገታቸው አድርገውት ነበር ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዙት፡፡

ዛሬ ዛሬ በታላላቅ መገናኛ ብዙኃን ጣቢያዎች እንደምናየው ፑቲንና ታላላቅ ባለ ሥልጣኖቻቸው በሩሲያ ኦርቶዶክስ / መንፈሳዊ በዓላት ላይ መገኘት ብቻ ሣይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ በሩሲያ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ማንነትና በዕለት ተዕለተ የሕዝባቸው ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ያላትን ደማቅ የኾነ አሻራ፣ ጉልህ አስተዋጽኦ በክብር ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲዘልቅ ተግተው እየሠሩና ሕዝባቸውን በተለይ ወጣቱን ሃይማኖቱን እንዲጠብቅና እንዲያከብር እያበረታቱት ነው፡፡ማኅበረ ቅዱሳንን በጨረፍታ

በዚህ ከላይ በመንደርደሪያነት ባቀረብኩት የፕሬዝዳንት ፑቲንና የሩሲያ ኦርቶዶክስ / ግንኙነት አጭር ማስታወሻ የማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረት በተመለከተ ከአገራችን የቅርብ እግዚአብሔር የለሽ የአገራችን ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ታሪክ አንጻር ወደቃኘኹበት አጭር ቅኝት ልለፍ፡፡

በቅርብ ታሪካችን እንደምናውቀው የሩሲያ/የምሥራቁ ዓለም አብዮት ግልባጭ የኾነው የ፲፱፻፷፮ቱ አብዮት በአገራችን ያደረሰው ውድመት፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅል፣ ስደትና ሞት፣ የእርስ በርስ ጦርነትና እልቂት፣ የኢኮኖሚ ቀውስና የፖለቲካ ዝብርቅርቅ፤ እንዲሁም ከዚህም አልፎ የወርኻ የየካቲቱ አብዮት በመንፈሳዊ ተቋማት በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጉዳት የቤተ ክርስቲያኒቱን አባትና መንፈሳዊ መሪ የኾኑትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በግፍ እስከማጋዝና ፍጹም ሰብአዊነት በጎደለው አኳኃን በደርግ ልዩ ኮማንዶዎች በገመድ ታንቀው እንዲገደሉ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና በግልጽ እስከመዳፈር የተደረሰበት ነበር፡፡

በተውሶ የሩሲያ አብዮት አቅሉን ያጣው ትውልድም እንደ ሩሲያና አልባኒያ ወጣቶች ኹሉ፣ ‹‹ሃይማኖት ሕዝብን ማደንዘዣ ዕፅ ነው!›› ‹‹እግዚአብሔር የለም!›› ‹‹ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስር እናውላለን!›› በሚሉ መፈክሮች አገራችን ለዘመናት ፀንታ ከኖረችበት የታሪኳና የባህሏ መሠረት አናውጧት፡፡ ሕዝቡም ከኖረበት ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ጨዋነት፣ ወግና ባህል ፈጽሞ ሊነጻጸር በማይችል መንገድ የገዛ ወገናቸውን በወላጅ እናቶቻቸው ፊት በጥይት እሩምታ እየገደሉ፣ ‹‹ለፀረ አብዮተኛው ልጅሽ ላባከንነው ጥይት ብር ክፈሉ›› የሚሉ፣ ፈጽሞ ሰብአዊነት የጎደላቸው ጨካኝ አውሬዎች አገሪቱን የደም መሬት/አኬልዳማ አደረጓት፡፡ በአገሪቱ የረኻብና የእርስ በርስ ጦርነት፣ የእልቂት ምድር ኾነች፡፡

በዚህ ኹሉ ዋይታና ጭንቀት ውስጥ የነበረችውን ኢትዮጵያን እንደ እግር እሳት እየለበለባት ካለው ለዐሥርት ዓመታት ለዘለቀው የወንድማማቾች የእርስ በርስ ጦርነት እንድትወጣ ሰላማዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ብቸኛ መፍትሔው ‹‹አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስከሚቀር መዋጋት ነው! ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!›› ያለው የደርግ መንግሥትም በፍጻሜ ዘመኑ አካባቢ በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት/ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተማሪዎችን ወደ ብላቴን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ አስገብቶአቸው ነበር፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ / በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ማኅበረ ቅዱሳን ምስረታ ጅማሬው- ፅንሰቱና ውልደቱ በዚህ ወታደራዊ ማስልጠኛ ጣቢያ ውስጥ ነበር፡፡

የዛን ጊዜዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩት ወጣቶች የቤተ ክርስቲያናቸው ብቻ ሣይሆን፣ ‹‹የደም ምድር/አኬልዳማ፣ የረኻብ፣ የጦርነትና የእልቂት ምድር›› በሚል ቅፅል በመላው ዓለም የምትታወቀው የአገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታም በእጅጉ ያሳስባቸው ነበር፡፡

ለኹለት ዐሥርተ ዓመታት ገደማ ‹‹እግዚአብሔር የለሹ›› ሥርዓት በሕዝቡ ሥነ ልቦና ውስጥ የፈጠረውን ቀውስ፣ የሞራል ድቅቱንና ዝቅጠቱን፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅሉን፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ እረፍት የነሳቸውና የእፍረትን ማቅ የደረበባቸው እነዚህ የነገይቱ ኢትዮጵያ ተስፋ የኾኑ ምሁራን ወጣቶች እንደ አንድ ክርስቲያን- ለአገራችን፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለወገናችን አንድና ጥቂትም ነገር ቢሆን የድርሻችንን ማበርከት ይኖርብናል በሚል ብርቱ ቁጭትና መንፈሳዊ ቅናት ነው ይህን ክርስቲያናዊ መንፈሳዊ ማኅበር ዕውን ለማድረግ የበቁት፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል- ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከመንፈሳዊ አባቶችና መሪዎች በተሰጠው ሕግ፣ ደንብና መመሪያ መሠረት የተጣለበትን መንፈሳዊና ግዴታና ሓላፊነቱን ለመወጣት እየሞከረ ነው፡፡ በመሠረቱ የዚህ ጽሑፍ ዋንኛ ትኩረት ማኅበሩ ያዘጋጀውን ዐውደ ርእይ በአጭሩ መቃኘት በመሆኑ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ለመግባት አልሞክርም፡፡ ስለሆነም በአጭሩ ለመዳሰስ ወደ ወደድኹት ወደ ዐውደ ርእዩ ርዕሰ ጉዳይ ልለፍ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ላለፉት ኹለት ዐሥርት ዓመታት የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ (ዶግማና ቀኖናዋን) ታሪክ፣ ቅርስ፣ ወግና ትውፊት በሚገባ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላላፍ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንዳለ መኾኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ባለፈው ሳምንት ለ፭ኛ ጊዜ የቀረበው ዐውደ ርእይም የዚሁ ጥረቱ አንድ አካል ነው፡፡

ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ዕውቀትና ጥብብ፣ የተጠና ዝግጅት፣ በከፍተኛ ወጪ፣ ድካምና ርብርብ፣ በወቅቱ የተጋረጡበትን ፈተናዎችና ተግዳሮቶች በድል ተወጥቶ ለዕይታ የበቃው ዐውደ ርእይ የሕዝብ ጎርፍ ነበር ሊባል በሚችል ደረጃ በሚደንቅ ኹኔታ በበርካታ ሰዎች ተጎብኝቷል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ ፋይዳውና ተግዳሮቶቹ በአጭሩ

ይህች የምንኖርባት አገራችን ኢትዮጵያ ትናንትና የተፈጠረች አገር አይደለችም፡፡ ዘመናትን ያስቆጠረች የረጅም ዘመን ታሪክን፣ ግዙፍ ሥልጣኔን ያስተናገደች አገር ናት፡፡ በዚህ በአገራችን የረጅም ዘመን የታሪክ ጉዞና ታላቅ ሥልጣኔ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ / አሻራ እጅግ የደመቀና የጎላ መሆኑን ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገራት ያሉ ተጓዦችና አሳሾች፣ ጎብኚዎች፣ የታሪክ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች ደጋግመው ምስክርነታቸውን የሰጡበት እውነታ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገሪቱ አንድነት- ታሪክና ቅርስ፣ ሥልጣኔና ባህል፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ ሕግና ፍትሕ፣ ትምህርት- ሥነ-ጽሑፍና ኪነ-ጥብብ፣ በአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት/Green Development/Economy እንዲሁም በአጠቃላይ በሕዝባችን የዕለተ ተዕለተ ማኅበራዊ ኑሮ መስተጋብር ውስጥ በጉልህ ደምቃ፣ ገዝፋ የምትታይ መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ደማቅ የኾነ አሻራ ከአገራችን አልፎ ድንበር ሳያግደው- በአፍሪካ፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በካረቢያንና በጃማይካ ሕዝቦች ድረስ የተሻገረ፣ የዘለቀ ነው፡፡

ዘንድሮም ማኅበረ ቅዱሳን ለ፭ኛ ጊዜ ‹‹ኦርቶዶክሳዊት  ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ!!›› በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ዐውደ ርእይም ይህን ታሪክ እውነት በመጠኑም ቢሆን በጽሑፍ፣ በገለጻና፣ በምስል ወድምፅ ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡

በዐውደ ርእዩ በአጭሩ እንደተገለጸውም የኢትዮጵያ / ‹‹እንግዶችን ለመቀበል ትጉ፤ ቢቻላችሁስ ከሰዎች ኹሉ ጋር በሰላም ኑሩ፡፡›› በሚለው መንፈሳዊ አስተምህሮዋ መሠረት በማድረግ ወደ እርስዋ የመጡትን ኹሉ በፍቅርና በሰላም ተቀብላ በማስተናገድ መጠለያና ከለላ የሰጠች ኹሉም የሚመሰክርላት ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ኩላዊት የኾነች ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡

የኢትዮጵያ / ታሪክ እንደሚያወሳው ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ እርስዋ የሚመጡትን- የማን ዘር ነህ፣ የትኛው ቋንቋ ተናጋሪ ጎሳ ነህ፣ ትውልድህና ነገድስ ከወዴት ነው የሚል ጥያቄ ፈጽሞ አልነበራትም፡፡ በዚህም የተነሳ ከመካለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓና ኤዥያ የመጡ የሃይማኖት ስደተኞችን ሣይቀር ኹሉንም በፍቅር ተቀብላ በሰላም አሰተናግዳለች፣ መኖሪያ ቤታቸውም ኾና ቆይታለች፡፡

ለአብነትም ከእኛው ጥቁር አፈር የተገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን እስኪመስሉን ድረስና ግን ደግሞ እጅግ በሚበልጠው በጌታችንና በመድኃኒታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ ፍቅርና ርኅራኄ የተዛመድናቸውና ቤተሰብ የኾናቸው እጅጉን የምናከብራቸውና ምንወዳቸው እንደ መጀመሪያው የአክሱም ጳጳስ- አቡነ ፍሬምናጦስ (በኢትዮጵያዊ ስማቸው- አባ ሰላማ፣ ከሳቴ ብርሃን) አባ ዘሚካኤል (በኢትዮጵያዊ ስማቸው አቡነ አረጋዊ) አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ/አቡዬ/አቦወዘተ ያሉ መንፈሳዊ አባቶች ከውጭ አገር በስደት፣ በግዞትና ለመንፈሳዊ አግልግሎት የመጡ ቅዱሳን ናቸው፡፡

ይህ ሰዎች ኹሉ ከአንድ ወገን በመኾናቸው በፍቅርና በሰላም ተስማምተው በአንድነትና በኅብረት እንዲኖሩ መንፈሳዊ ግዴታና ሓላፊነት ከተሠጣትና ካለባት፣ ይህንም በቃልና በተግባር በማስተማርና በመተርጎም ረገድ የኢትዮጵያ / ሰፊ ታሪክ ያላት ተቋም ናት፡፡ ይህ በመለኮታዊ ፍቅር የጸና የመንፈስ አንድነትና ውህደት ሰዎች በምድር ላይ ሲኖሩም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ተግተው ተግባራዊ እንዲያደርጉትም የበኩላን ሚና ተጫውታለች፣ አሁንም እየተጫወተች ነው፡፡

በሰው ልጆች መካከል ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን የምትጋደል፣ ለሰው ልጆች ኹሉ ከፈጣሪ ለተሰጠ ነጻነት ጠበቃ የኾነች፣ አንድነትንና ኅብረትን የምትሰብክ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ካለፈችበት ውስብስብ የታሪክ ጉዞ አንጻር ለአንዳንዶች የተለየ ስያሜና ትርጓሜ እየተሰጣት እንደኾነ በተለያዩ ጊዜያት አስተውለናል፡፡ በተለይ ቤተ ክርስቲያቱ በኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት ላይ ያላት ጽኑ የኾነ አቋም ጋር በተያያዘ ማኅበረ ቅዱሳን በውስጥም ኾነ በውጭ ያለበትን ጫና ተቋቁሞ- በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላትን ጽኑ አቋም ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት ሕዝቡን አስተባብራ ያደረገችውን ታላቅ ውለታ በእንዲህ ዓይነቶቹ ዐውደ ርዕዮችና በተለያዩ መድረኮች ደጋግሞ መዘከሩና ማንጸባረቁ አንዳንዶችን የሚያስደስት እንዳልኾነ ደጋግመን አሰተውለናል፡፡

ዛሬ ዛሬ በአገሪቱ ላይ ያለ ቅጥ በተራገበው የብሔር ፖለቲካ ቤተ እምነቶች ድረስ ሳይቀር ዘልቆ ገብቶ መንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችን ከሰማያዊ ዜግነት፣ እንዲያም ሲል ደግሞ ከተሰደዱበት የትውልድ አገራቸው/ዜግነታቸው አውርደን፣ በመንፈሳዊ ፍቅር የተሳሰሩበትን ኢትዮጵያዊነትን የፍቅር፣ የአንድነት ገመድ በጥሰን ጥለን በሚያሳዝን ኹኔታ ኢትዮጵያዊነትን እንኳን ነስተናቸው በአንዳንዶቻችን ዘንድ ‹‹የእኛና እነርሱ›› በሚል የገባንበት አሳፋሪ መንፈሳዊ ዝቅጠትና የጎጠኝነት አስተሳሰብ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለኹለት ከከፈለበት የቤተ ክርስቲያኒቱ የጨለማ ታሪክ ዘመን ጀምሮ አሁን እስካለንበት መንፈሳዊ ቀውስ እየተጋፈጥነው ያለ የቤተ ክርስቲያኒቱ ከባድ ተግዳሮትና ፈተና እየኾነ ነው፡፡

በዘረኝነት ጎሳዊ/ጎጣዊ አስተሳሰብ ሕሊናቸው የተበላሸባቸው፣ አማሳኞች፣ በጥቅም የተሳሰሩና ሃይማኖትን ንግድና ማትረፊያ ያደረጉ መንፈሳዊ ከባን ከደረቡ በግልና በቡድን የተደራጁ ሰዎች የዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሣይሆን የአገሪቱም ከባድ ፈተና እየኾኑ ነው፡፡ ሃይማኖት አለን በምንለውና በዓላማውያኑ መካከል ያለው የልዩነት ድንበር ደብዝዞ መለየት እስከሚሳን ድረስ የተፈጠረው መቀላቀልና ውህደት የመንፈሳዊ ሕይወት ማራኪ ውብትን እጅጉን አድብዝዞታል፡፡ ይህ ኹኔታ እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው፤ ለውጥ ያስፈልጋል በሚል ድምፁን እያሰማ ያለው ማኅበረ ቅዱሳንም ከውጭም ሆነ ከውስጥ ፈታኝ የኾኑ ተግዳሮቶች በየጊዜው እያጋጠሙት እንደኾነ በግልጽ እያየን ነው፡፡

ተምሳሌት የሚኾነውና ባለ ራእይ የኾነ መንፈሳዊ መሪና አባት ያጣው ትውልድም በአገሩ ፖለቲካዊም ኾነ ሃይማኖታዊ ተቋማት ክስረትና ውድቀት እጅጉን አዝኖና ተክዞ ያለ በቀቢጸ ተስፋ የተዋጠ ትውልድም እጅጉን  እየተበራከተ ነው፡፡ ይህን የባዘነ ትውልድ- ሃይማኖቱን በሚገባ አውቆና ተረድቶ ለቤተ ክርስቲያኑ የሚጠቅም፣ ለነገው ትውልድ ተስፋ የሚኾን፣ ለአሩና ለወገኑ ፍቅርና ተቆርቋሪነት ያለው ባለ ራእይ ትውልድ እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ በሚል መርሕ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በኤግዚቢሽን ማእከል አዳራሽ ባዘጋጀው ዐውደ ርእይ ይህንኑ ዕውን ለማድረግ በኹሉም ዘርፍ እያደረገ የለውን ጥረቱን በከፊልም ኾነ የሚገልጹ አስደናቂ ትዕይንቶችን አስተውለንበታል፡፡

ሌላው በዚህ በዘመነ ሉላዊነት/ግሎባላይዜሽን በዘመናዊነት ካባ ተሸፍነው ‹‹ለውጥ›› ያስፈልገናል በሚል የኢትዮጵያን / እናድሳለን በሚል የተነሡ በቁጥር በርካታ የኾኑ በምዕራባውያን የገንዘብ እርዳታ የሚንቀሳቀሱ፣ የኢትዮጵያን / ታሪክና ቅርስ፣ ትውፊትና ሥርዓት ለመለወጥ ‹‹የተሐድሶ አራማጅ ነን›› የሚሉ ግለሰቦችና ማኅበራት ሌላኛው የቤ/ ችግርና ተግዳሮት መኾናቸውም ተዳሶበታል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን እነዚህ ግለሰቦችና በማኅበራት የተደራጁ የተሐድሶ አራማጆች የምዕራባውያኑን ባህል በማስረጽ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ልጆች ከእምነታቸው፣ ከታሪካቸውና ከማንነታቸው እንዲኮበልሉ እያደረጉት ያለውን ስውርና ግልጽ እንቅስቃሴ በመከታተል፣ በማጋለጥ፣ እንዲመለሱ፣ ተገቢው እርማትና ርምጃ እንዲወሰድባቸው በማሳሰብ ረገድ የሔደበትን መንገድና ትውልዱ ሃይማኖቱን በሚገባ የሚያውቅ፣ ለታሪኩና ለቅርሱ፣ ለአባቶቹ ወግና ሥርዓት የሚቆረቆር እንዲሆን እያደረገ ያለው ጥረቱንና ውጤቶቹን፣ ፈተናዎቹንና ተግዳሮቶቹን በዚህ ዐውደ ርእይ በተጨባጭ ማስረጃዎች ለማሳየት ሞክሯል፡፡

በመሪ ቃሉ በግልጽ እንደተቀመጠው የዚህ ዐውደ ርእይ ዓላማ- እንደ አንድ ክርስቲያን መንፈሳዊ ልደትን ባገኘኹባት /ን፣ እንደ ተማረ ዜጋ ደግሞ በአገራችን ላሉ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች/ተግዳሮቶች ተግባራዊ ምላሽ እንዲያገኙ፤ የእኔ ድርሻ ምን ሊኾን ይገባዋል በሚል- እያንዳንዱ ሰው ራሱን እንዲጠይቅና ሓላፊነቱንና ግዴታውን ምን እንደኾነ ጠይቆ ራሱን የመፍትሔ አካል አድርጎ ማቅረብ እንዳለበት የተጠየቀበት ዐውደ ርእይ ነው፡፡

ከዚህ ዐውደ ርእይ ጎን ለጎንም በማኅበረ ቅዱሳን ምርምርና ጥናት ማእክል በሁለት ተጋባዥ ምሁራን የጥናት ወረቀት አቅራቢነት ለግማሽ ቀን የተደረገው የውይይት መድረክም- በቤተ ክርስቲያናችንም ኾነ በአገር ደረጃ እየተፈታተኑን ያሉ ፈተናዎች የተነሡበት፣ ሰፋ ያሉ ምሁራዊ ትንታኔ የተሰጡባቸው፣ አስተያየት፣ ክርክርና መፍትሔ ሐሳቦች የተነሱባቸው የውይይት መድረክ ነበር፡፡

የዓለም የዕርቅና ሰላም ግብረ ሰናይ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተርና የምጣኔ ሀብት ምሁር የኾነው ወጣቱ / ጸጋዝአብ ለምለም- ‹‹የቤ/ ወቅታዊ ፈተና፣ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርእስ ባቀረበው የጥናት ወረቀት፣ / በዓለም ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሔ የምትሰጥ፣ አንዳንች መላን የምታመላክት የመንፈስ ልእልና የተጎናጸፈች፣ ፍጹም የኾነች፣ መንፈሳዊና ሰማያዊት ተቋም እንጂ በተቃራኒው ለሚያጋጥሟት ችግሮችና ፈተናዎች፣ በዘመናችንም እንደምንታዘበው ሰላምን፣ እውነትን፣ ፍትሕንወዘተ ፍለጋ የዓለማውያኑን ደጅ የምትጠና ተቋም አይደለችም፡፡

ጥንትም ኾነ አሁን እያየነው ያለው የቤተ ክርስቲያን ፈተና፣ ተግዳሮቶች ምንጫቸው ጥንተ ጠላት፣ ክፉው ዲያብሎስ መኾኑን የጠቀሰው ጸጋዝአብ፣ እነዚህ ፈተናዎች ለመቋቋም፣ የጨለማውን ክፉ ሥራ/ተግዳሮቶች በጽድቅ ብርሃን የሚገልጽና የሚያሸንፍ፣ መንፈሳዊ ጨው የመኾን ክርስቲያናዊ እሴቶችን የተላበሰ መንፈሳዊ ማንነት ዋናውና አስፈላጊ አገር እንደኾነ አስምሮበታል፡፡ ከራስዋ አልፋ ለምድራችን፣ ለዓለም ኹሉ ብርሃንና ጨው የመኾን ጸጋ የተሰጣት / ፈተናዎቿን በድል ለመወጣት እንድትችል የሚያነባ፣ በብርቱ የሚቃትት፣ የነገ ብሩሕ ተስፋን የሚያሳይ መፍትሔን የሚወልድ/የሚያዋልድ መንፈሳዊ አርበኛ የኾነ ባለ ራእይ ትውልድ እንደሚያስፈልግ በጥናታቸው በስፋት ገልጸውታል፡፡

ሌላው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ሚና ሙስናን ከመዋጋት አንጻር›› በሚል ርዕስ የጥናት ወረቀታቸውን ያቀረቡት የሕግ ባለሙያው አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በጥናታቸው ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንጠቀምባቸው የሥነ ምግባር መርሕዎችና ደንቦች ምንጫቸው ቅዱሳት መጻሕፍት መኾናቸውን በማስታወስ ከኢትዮጵያ / አስተምህሮ አንጻር ሰፋ ያለ ገለጻ ነበር ያደረጉት፡፡

አቶ ፊሊጶስ ዛሬ በአገራችንና በአኅጉራችን አፍሪካ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ የኾነው ሙስና፣ ጉቦ መስጠትና መቀበል እንዲሁም በአጠቃላይ የመልካም አስተዳደር እጦት መፍትሔው ወደ ጥንቱ የክርስትና አስተምህሮና የሥነ ምግባር ደንቦች መመለስ እንደኾነ በስፋት አንስተውታል፡፡ ከዚህም ጋር የኢትዮጵያ / መምህራንና መጻሕፍት በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ጉቦንና ሙስናን የሚጸየፍ፣ ለእውነትና ለፍትሕ የሚቆም ትውልድን በማፍራት- ለአገራቸው ክብር፣ ለወገናቸው ኩራት የኾኑ ሀገራዊ ግዴታቸውን የሚወጡ ዜጎችን በማፍራት ረገድ የኢትዮጵያ / የማይናቅ ቀዳሚ ድርሻ  እንዳላት ነው ባቀረቡት የጥናታት ወረቀታቸው ድምዳሜ ላይ የተናገሩት፡፡

በስተመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ / ሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ተጋድሎ፣ ወቅታዊ ፈተናዎቿን እና ተግዳሮቶቿን፣ የወሰደችውንና እየወሰደች ያለውን ርምጃዎችን፣ ዓለም አቀፍ የኾነ ሐዋርያዊ ተልእኮዋንና አገልግሎቷን፣  እንዲሁም ደግሞ የኢትዮጵያ / እና የአገራችንን የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህልና ቅርስ በማስተዋወቅ ረገድ ማኅበሩ እየሔደበት ያለውን ጉዞውን በማጠናከር ለወደፊቱ የጎደለውን አሟልቶ ከዚህ በተሻለ ዐውደ ርእይና ውይይት መድረክ እንደምናገኘው ተስፋ በማድረግ ልሰናበት፡፡

ሰላም!

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)