April 28, 2016

ስቅለትን በስግደት ወይስ በሙግት?

·         የ2008 ዓ.ም በዓለ ስቅለት በእመቤታችን ቀን ውሏል። እናም ይሰገዳል? ወይስ አይሰገድም?
·         ይኸው ገጠመኝ በ1913 ዓ.ም ተከስቶ በነበረበት ወቅት አበው ጉዳዩን እንዴት ፈቱት?
(መምህር ጳውሎስ መልክአ ሥላሴ):- በተወሰኑ ዓመታት መካከል የስቅለት ዕለት በየጊዜው ዘንድሮ እንደሆነው ሲገጥም ክርክር ይነሳል። አስታውሳለሁ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪ ሳለሁ እንዲሁ ስግደት በእመቤታችን ዕለት በመዋሉ ምክንያት በተለያዩ አድባራት ተበታትነን በዓሉን የምናሳልፍ ተማሪዎች እንደየደብሩ አለቃ ስሜት ወይም ግንዛቤ አሳልፈን ተመልሰናል። ማለትም አንዱ ጋር ይሰገዳል አንዱ ጋር አይሰገድም። ይህ ክርክር ዘንድሮም ቀጥሏል። ቅዱስ ሲኖዶስ የማያዳግም ምላሽ ቢሰጥበት መልካም ነው። በቅድሚያ ጾሙን በጥሩ ሁኔታ የቻላችሁትን ያክል በትጋት ላሳለፋችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ድካም ባለው ተጋድሎዋችሁ ቸርነቱን አክሎበት የልባችሁን መሻት ይስጥልኝ። የጾምና ጸሎታችሁም በረከት ይድረሰን ለብርሃነ ትንሳኤውም በሰላም ያድርሰን እላለሁ።
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ ዘንድሮ ስቅለት በእመቤታችን ቀን ውሏል። እናም ይሰገዳል? ወይስ አይሰገድም? በሕማማት ውስጥ ከትንሳኤ በፊት ያለችው ቅዳሜ የተሻረች ሰንበት ትባላለች (ቀዳሚት ስዑር) ሃይማኖተ አበው እንደሚያዝዘን በቅዳሜ ቀን መጾም ክልክል ነው። ከቀዳሚት ስዑር በቀር ይላል ስለተሻረች የሕማማትን ቅዳሜ እንጾማታለን በሕማማት ውላለችና። ልክ እንደዚሁ በሕማማት ማንኛውም በዓል ቢውል አይከበርም።
የእመቤታችን በዓል ስለሆነ ስግደት የለም ካልንና ካልሰገድን ቅዳሴ ሊኖር ይገባ ነበር። ቅዳሴ ሳይቀደስ የሚከበር የእመቤታችን በዓል የለንምና ስለዚህ የነገው አርብ ይሰገዳል። ይህ የኔ አሳብ አይደለም የአባቶቼ ትምህርት እንጂ። እስቲ የዛሬ ዘጠና አምስት ዓመት ገደማ ስቅለት እንደዛሬ ውሎ የተፈጸመውን ክስተት ላቅርብላችሁ። የታሪኩ ጸሐፊ ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ናቸው። ዓመተ ምህረቱም ሚያዝያ ፳፩ ቀን ፲፱፻፲፫ ዓ.ም( ሚያዝያ 21/ 1913 ዓ.ም ነው)። ምንም ያልተጨመረበትና ያልተቀነሰለት ታሪኩ እንዲህ ይላል።
"የስቅለት በዓል በዚህ ዘመን ሚያዝያ ፳፩ ቀን ላይ ውሎ ነበር። የአዲስ አበባ አድባራት ሊቃውንትም እኩሌቶቹ በማርያም በዓል ምክንያት ስግደት መስገድ አይገባም ሲሉ እኩሌቶቹ መስገድ ይገባል ብለው ነበርና የአሳብ ልዩነት ተፈጥሮ ዋለ።
ግርማዊት ንግሥትና ልዑል አልጋወራሽ በሚገኙበት ቤተ ክርስቲያን በሥዕል ቤት ኪዳነ ምህረት (በዓታ ያለችውን ኪዳነ ምህረት ነው) ባንድ ወገን መምህር ደስታ “መስገድ አይገባም ሲሉ” ግማሹ ሕዝብ እሳቸውን ተከትሎ አንገቱን ብቻ ጎንበስ እያደረገ ጸሎቱን ያደርስ ጀመር። እሳቸው ለማስረጃ ያቀረቡትም “መቅድመ ተአምር የማርያምን በዓላት እንደ እሁድ ሰንበት አድርጋችሁ አክብሩ ይላልና በእሁድ ቀን ምን ጊዜም ስግደት ስለሌለ ዛሬ መስገድ አይገባም” የሚል ቃል ነው።
በሁለተኛው ወገንም አለቃ ገብረ መድኅን “ስግደት መስገድ ይገባል” ስላሉ ግማሹ ሕዝብ እሳቸውን ተከትሎ ይሰግድ ጀመር። ለማስረጃም ያቀረቡት “የዛሬው በዓል በስግደት የሚከበር በዓል ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታ በተሰቀለበት ቀን በመስቀሉ ስር ቆማ እያለቀሰች እና እየተጨነቀች በብዙ ድካም የዋለችበት ቀን ነው። ከዚህም በላይ ከእመቤታችን በዓል ይልቅ የክርስቶስ በዓል ይበልጣልና እንደ አበው ሥርዓት በዓሉ በስግደት ሊከበር ይገባል” የሚል ነበር። ይህ የአለቃ ገ/መድኅን አሳብ በትልቁ መምህር በአለቃ ወልደማርያም የጊቢ ገብርኤል አለቃ ሲደገፍ
የመምህር ደስታም አሳብ በሌሎች አለቆች ተደገፈ።
ከዚህም በኋላ ግርማዊት ንግሥትና ልዑል አልጋወራሽ ይህን የሊቃውንቱን ልዩነት ለማስቀረት እና አንድ ነገር ለማስወሰን ስለፈለጉ ወደ አቡነ ማቴዎስ ሁለት መልእክተኞችን ላኩ። እነርሱም የንግሥት መምህረ ንስሐ መላከ ገነት ተድላና የልዑል አልጋወራሽ መምህረ ንስሐ አባ ወልደማርያም ናቸው። እኔ ራሴ አባ ወልደማርያምን ተከትዬ ሄጄ ነበርና የሆነውን ሁሉ በቅርብ ተከታትዬዋለሁ።
መልክተኞቹ ከሊቀ ጳጳሱ ፊት ቀርበው የነገሩን አኳኋን ካስረዱ በኋላ በዛሬው ቀን ይሰገድ እንደሆነ ወይም አይሰገድ እንደሆነ ለመጠየቅ እና ውሳኔዎን ለመቀበል መጥተናል ብለው ተናገሩ። አቡነ ማቴዎስም ያለምንም ማመንታት ለአልጋወራሽ አሳወቋቸውና ይሰገድ ጀመረ።
የሆነው ሆኖ አብዛኛው ሰዓት በክርክርና በጥያቄ ምክንያት ባክኖ ነበር። እኔም ይህን ታሪክ መጻፌ ወደፊት የዚህ ዓይነት ነገር ቢያጋጥም ማስታወሻ እንዲሆን በማሰብ ነው።”
ምንጭ።- መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ “የሃያኛው ክ.ዘ. መባቻ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት” (1896-1923 ገጽ 237/38።)
++++++

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)