March 9, 2016

ከቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ባሻገርሕዝብና መንግሥት እንዲወያዩ ጥሪ ቀረበ፤ ጸሎትና ምሕላ ታወጀ፤ ስለ ሶሻል ሚዲያና ድርቁ ማሳሰቢያ ተሰጠ!
 (ደጀ ሰላም፤ ማርች 9/2016፤ የካቲት 30/2008 ዓ.ም )፦ የብፁዕ አቡነ ናትናኤልን እረፍትና ቀብር ተከትሎ ከየሀገረ ሰብከታቸው የመጡ አበው የቅ/ሲኖዶስ አባላትን መሰባሰብ ተከትሎ የተጠራው አስቸኳይ ጉባኤ እንደተካሄደ መዘገቡ ይታወሳል። የተሐድሶ ድረ ገጾች “ማህበረ ቅዱሳን ያስጠራው ስብሰባ ነበረ፤ ከሸፈ” ሲሉ ኦርቶዶክሳውያን የጡመራ መድረኮች ደግሞ ፓትርያርኩ የሚያካሒዱትን የቤተ ክህነቱን አስተዳደርና አሠራር እንዲሁም የቅ/ሲኖዶስን የበላይነት የሚያስተሐቅር ርምጃ እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው በሰፊው ዘግበዋል። ከመጋረጃ ጀርባ በዝግ በር ያለው እልህ አስጨራሽ ስብሰባ ካለቀ በኋላ የወጣው መግለጫ ብዙ ቁምነገሮች ይዞ እናገኘዋለን። ከነዚህም ውስጥ ሕዝብና መንግሥት እንዲወያዩ ጥሪ መቅረቡን፤ ጸሎትና ምሕላ መታወጁን፤ ስለ ሶሻል ሚዲያና ድርቁ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ማንሣት ይቻላል።

የፖለቲካው አስተዳደር ከብረት የጠነከረ እጅ ጨምድዶ በያዘው ቤተ ክህነት ውስጥ የሚደረጉ ነገሮችን በላይላይ ንባብ ብቻ አነብንቦ ማለፍ ትክክለኛ ትርጉምን አያስገኝም። ለአገራቸውና ለሃይማኖታቸው ቁርጠኛ የሆኑ አባቶች የሚያደርጉትን እውነተኛ እንቅስቃሴ ሳይረዱ በመቅረት ያልሆነ ትርጉም ወደመውሰድ ሊመራም ይችላል። ከዚህ አንጻር ቅዱስ ሲኖዶሱ የወሰነውና ለሕዝብ ይፋ የተደረገው መግለጫ አበረታች ውሳኔዎችን የያዘ መሆኑን መገንዘብ ይገባናል።

ለአብነት ያህል፤ አሁን በአገራችን ያለውን ቅጥ ያጣ የመንግሥት ጭፍጨፋ እና የንብረት ውድመት፤ እንዲሁም የሕዝብ ተቃውሞ “በአንዳንድ ክልሎችና ከተሞች የሚታየው አለመረጋጋት ሁሉንም የሚያሳስብ ሆኖ አግኝተነዋል” ተብሎ ተገልጧል። ትርጉሙ “ውጥረቱ ከፍያለ ለውጥ ሊወልድ የተዘጋጀ አገራዊ ምጥ ነው” ማለት ነው። መንግሥት በሚዲያዎቹ ዕለት ተዕለት ሊያሳየን ከሚሞክረው ሥዕል ጋር እጅግ የተራራቀ ነው። “አይዟችን፤ አገር አማን ነው” የሚለውን ማሞኛ ሕዝቡም አባቶችም አልተቀበሉትም።

አሁን ያለው ችግር ተራ ችግር ሳይሆን ክቡር የሰው ልጅን ነፍስ እያጠፋ ያለ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ ግሩም የሆነ ግንዛቤ አግኝቷል። “በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የሀብትና የንብረት ውድመት፣ በተለይም የሕዝብ መገልገያ የሆኑ የእምነት ተቋማት መቃጠል የተሰማንን ሐዘን እንገልጻለን” ብለዋል። በርግጥም በየክፍለ ሀገሩ የሚኖሩ አባቶች እንደመሆናቸው ያለውን ችግር በቅርብ ያውቁታል። “ባሳለፍናቸው ሳምንታት በተከሠተው ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች በመሪር ሐዘንና በጸሎት እናስባቸዋለን” ማለታቸው የሕዝቡ ስቃይ ምን ያህል እንደተሰማቸው ማሳያ ነው። መፍትሔውንም አጠይመው ለመግለጽ “ሁላችሁም ልጆቻቸን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳትሉ ችግራችሁን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሚመለከተው እንድታቀርቡ፣ መንግሥትም የሕዝቡን ችግርና ሰላማዊ ጥያቄ በመገንዘብ መፍትሔ በመስጠትና ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን የዕለት ከዕለት ጥረት እንዲቀጥልበት” ጥሪ ማቅረባቸውን ልብ ይሏል። በርግጥ የሕዝቡን ሰላማዊ ጥያቄ በጭካኔ እየጨፈለቀ ያለው ማን መሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም። ነገሩን ለማጠየም መሞከራቸው እንጂ።

ሌላው ይበል የሚያሰኘው የመግለጫቸው አካል መንግሥት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ረሃብ እንደሌላ ለማሳመን የሚዳክርበትን የችጋሩን ጉዳይ ያቀረቡበት መንገድ ነው። “ሕዝባችንና ሀገራችን በርኀብ፣ በድኅነትና በበሽታ ቸነፈር በተቸገረበት ወቅት” የሚለው ሐረግ ብዙ ይናገራል። “ቸነፈር” ተራ ቃል አይደለም። ከባድ በሽታን የሚወክል ቃል ነው። የረሃቡንና የችጋሩን ጽኑዕነት በበሽታው ቃል ለማስቀመጥ የሞከሩ እንጂ ይህንን ያህል ከባድ የሆነ በሽታ ገብቶ ስለርሱ ለመናገር የፈለጉ አይመስልም።

ሶሻል ሚዲያው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውስጥ አንድ ቦታ አግኝቶ የመግለጫ አካል ለመሆን በቅቷል። የሶሻል ሚዲያውን ሁኔታ በንቃት የሚከታተሉ ብዙ ብጹዓን አባቶች እንዳሉ ግልጽ ነው። የሚጻፈውንና የሚነገረውን ነገር በቅጡ ይገነዘባሉ፤ የሕዝቡንም የልብ ትርታ ያውቃሉ ማለት ነው። በርግጥ ፈር የለቀቁ አንዳንድ አፍራሽ የሶሻል ሚዲያ እንቅስቃሴዎች እንዳሳሰቧቸውም ግልጽ ነው። “ኅብረተሰቡን የሚለያይና የሚያራርቅ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) ዕለት ዕለት ብታስነብቡት ትርፉ መራራቅን እንጂ መቀራረብን፤ መለያየትን እንጂ መግባባትን አያመጣም” ማለታቸው በግርድፉ ስናየው ትክክል ነው። ይሁን እንጂ ሶሻል ሚዲያው ባይኖር ኖሮ የመንግሥትን ቅጥ ያጣ ጭፍጨፋ እና ኢሰብዓዊ ተግባሮች ልንረዳ የምንችልበት ምንም አጋጣሚ አይኖርም ነበር። ስለ ጭፍጨፋው አትናገሩ ሳይሆን ጭፍጨፋውን አቁሙ የሚለው መፍትሔ ትክክለኛ ይሆናል።

በአጠቃላይ ብፁዓን አባቶቻችን ያስተላለፉት ውሳኔ ይበል የሚያሰኝ እና ከዚህ ቀደም በጉባኤ እየተናገሩ በመግለጫ ላይ ግን እንዳይገለጽ የሚጣልባቸውን ገደብ አልፈው ሐሳባቸውን ለምእመናቸው ለማድረስ መጣራቸውን የሚያሳይ ትልቅ እመርታ ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩ ከአበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ቢሠሩ እና ምእመናቸውን ከክፉ ለመታደግ ቢሞክሩ ያስመሰግናቸዋል። ከዚህ በፊት እንጀመሩት በማፍረስ ተግባራቸው ቢገፉም የራሳቸውን ስምና ታሪክ ከማጉደፍ ያለፈ የሚያመጡት ለውጥ እንደማይኖር ከቀዳሚያቸው ሊማሩ ይገባቸዋል። ምእመናንም አባቶቻቸው የሚናገሩትን ንግግር ምንነት ለመረዳት በመጣር፣ እነርሱ ያሉበትን ችግር በመገንዘብና አባቶቻቸውን ለመርዳት በመሞከር የልጅነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል። ፈረንጆች “reading between the lines” እንደሚሉት ከተጻፈው ነገር በላይ ያለውን ትርጉምም ለመረዳት መሞከር ይገባቸዋል። “ፊደል ይገድላል ትርጓሜ ያድናል” እንዲል። ዘመኑን በተርታ ንባብ ሳይሆን በትርጉም እንረዳው።ቸር ወሬ ያሰማን፤

አሜን      ================== የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ማንበብ ይቻላል። ======በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ“ኅሡ ሰላማ ለብሔር እስመ በሰላመ ዚአሃ ይከውን ሰላምክሙ”

(የአገርን ሰላም እሹ ፈልጉ የአገራችሁ ሰላም የእናንተ ሰላም ነውና) የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

የሀገርና የወገን ፍቅር ያለው ሕዝብ፥ ሰላም ከእግዚአብሔር መሆኑን ያውቃል፤ ሰላም ለሰው ልጆች ከማናቸውም መሠረታውያን ፍላጎቶች በላይ ተቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ተቻችለውና ተረዳድተው የሚኖሩባት የዓለም ምሳሌ ናት፡፡ ይህን ዓለምን የሚያስደንቅ ገጽታችንን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲከተለው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያት፤

ኢትዮጵያ አህጉረ ሰላም (የሰላም አገሮች) ከሚባሉት ከዓለም አገሮች አንዷ ስትሆን በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ክልሎችና ከተሞች የሚታየው አለመረጋጋት ሁሉንም የሚያሳሳብ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ከዚህም ጋር ባለፍናቸው ሳምንታት በተከሠተው ያልተጠበቀ ችግር፡-

1.በአንዳንድ አካባቢ የሰው ሕይወት ሲጠፋ፤ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፤ የንግድ ተቋማት፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ሲወድም፤ የሕዝባችን የዕለት ከዕለት ኑሮ ሲናጋ ሁሉም ኅብረተሰብ የችግሩ ተጠቂ ሆኗል፤ የዚህ ዓይነቱ ድርጊት በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የሕዝባችን ህልውናና የትውልዱም የወደፊት ዕድል አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡

2.ባሳለፍናቸው ሳምንታት በተከሠተው ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች በመሪር ሐዘንና በጸሎት እናስባቸዋለን፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም ልጆቻቸን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳትሉ ችግራችሁን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሚመለከተው እንድታቀርቡ፣ መንግሥትም የሕዝቡን ችግርና ሰላማዊ ጥያቄ በመገንዘብ መፍትሔ በመስጠትና ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን የዕለት ከዕለት ጥረት እንዲቀጥልበት በቤተ ክርስቲያናችን ስም እናሳስባለን፡፡

3. ሕዝባችንና ሀገራችን በርኀብ፣ በድኅነትና በበሽታ ቸነፈር በተቸገረበት ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት መሠረታዊ ወደሆነው የልማት የሰላምና የድርቅ ጉዳይ በማተኮር መልስ ሰጭ መሆን ይገባዋል ብለን በጽኑ እናምናለን፡፡

4. ወገኖቻችን ሆይ፣ በአሁኑ ጊዜ የወቅቱ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ (ብሎገሮችና የፌስቡክ) ተጠቃሚዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ከሞያችሁ ከዕውቀታችሁ ተጠቃሚዎች የመሆን ምኞታቸው የላቀ ነው፡፡ ሆኖም መልካሙንና ለዕድገት የሚያግዛቸውን ዕውቀት እንጂ ኅብረተሰቡን የሚለያይና የሚያራርቅ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) ዕለት ዕለት ብታስነብቡት ትርፉ መራራቅን እንጂ መቀራረብን፤ መለያየትን እንጂ መግባባትን አያመጣም፤ ከዚህ አንጻር የእናንተም ጥረትና ድካም ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ በመሆኑም የተከበረ ዕውቀታችሁን፣ ሞያችሁን፤ ለሕዝባችን ፍቅርና አንድነት፤ ለሀገራችን ሰላምና ዕድገት እንድታውሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትጠይቃለች፡፡የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን፤

ተቻችሎና ተረዳድቶ የመኖር የተቀደሰ ነባር ባህላችንን የሚያጎድፍ ማናቸውንም አስተሳሰብና እንቅስቃሴ በአንድነት መቋቋም እንደሚገባ አበክረን እየገለጽን፣ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ወገኖቻችን በሙሉ፣ በተለይም አገር ተረካቢ ትውልድ የሆናችሁ ወጣቶች፣ ሁከትና ብጥብጥብን ከሚያስከትሉ መጥፎ ድርጊቶች እንድትቆጠቡ፤ ለአገር ሰላምና ልማት ጠንክራችሁ እንድትቆሙ በልዑል እግዚአብሔር ስም አጥብቀን እያሳሰብን በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የሀብትና የንብረት ውድመት፣ በተለይም የሕዝብ መገልገያ የሆኑ የእምነት ተቋማት መቃጠል የተሰማንን ሐዘን እንገልጻለን፡፡

ይልቁንም ከሁሉም በላይ ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር አምላካችን፤ ለኢትዮጵያ ለሀገራችን ሕዝቦች ሰላሙን፣ ፍቅሩን፣ አንድነቱን ይስጥልን ዘንድ፤ ድርቁን ረኀቡን አስታግሦ መጪው ጊዜ ዝናመ በረከቱን ይሰጠን ዘንድ በያዝነው በዐቢይ ጾም ሱባኤ ጸሎተ ምሕላ በመላ ሀገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፰ ..

አዲስ አበባ


No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)