March 7, 2016

በኢትዮጵያም፣ በአሜሪካም ያለው የተሐድሶ ቡድን ጡንቻውን እያፈረጠመ ነውን?

·        በስደት በሚገኙ አባቶች ጉባኤ አድርገው መግለጫ አውጥተዋል፤
·        “የቤተ ከርስቲያን ችግር” ያሉት በርግጥ ችግር ነውን?
·         ከመካከላቸው ያሉትና በእምነታቸው ነቅ የሌለባቸው አባቶች ለምን ዝምታን መረጡ?
·        “በስደት ባለው ሲኖዶስ ሥር ላሉ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ምእመናን” ከፍ ያለ ታሪካዊ ጊዜ ነው፤

 (ደጀ ሰላም፤ ማርች 6/2016፤ የካቲት 27/2008 ዓ.ም )፦ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እና በዋናው ጠቅላይ ቤተክህነት ስር የሚገኙ የተለያዩ ካህናት “ጊዜው ተመችቶናል” በሚል ጦርነት በከፈቱበት በዚህ ወቅት በስደት በሚገኙ አባቶች የሚመራው ቤተ ክህነት አባላት የሆኑ ካህናትም ሰሞኑን ጉባዔ ማድረጋቸውንና የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን አስታውቀዋል (መግለጫውን በመጨረሻ ያገኙታል):: እነዚሁ “ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ” በሚባለውና በ4ኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ በሚመራው ክፍል ሥር የሚገኙ ካህናት ያደረጉት ጉባዔ ከየካቲት 21-25/2008 ዓ.ም (ከፌብሩዋሪ 29 እስከ ማርች 4/2016 መሆኑ ነው) ድረስ የተካሄደ መሆኑን “ቆሞስ አባ ጽጌ ድንግል ደገፋው፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ” በሚል ፊርማና ማኅተም የወጣው መግለጫ ያትታል። ታዲያ ስለምን ተነጋገሩ? ውሳኔያቸውስ ምን ይሆን?
በሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትምህርት መሰጠቱን ከባለ 4 ገጹ መግለጫ ለማወቅ ተችሏል። “1ኛ. “ትምህርተ ኖሎት”፤ 2ኛ.  “የቤተ ክርስቲያን ፈተና ትላንት እና ዛሬ”፤ 3ኛ. “አምልኮተ እግዚአብሔር እና ሥርዓቱ” በሚሉ ርዕሶች። አስተማሩ የተባሉት እነማን መሆናቸውን መግለጫው ባይጠቅስም ያወጡትን የጋራ መግለጫው በስምንት ቁጥሮች ከፍሎ አቅርቧል። ቁጥር 1 የመግለጫው አካል “ራሱን ማኅበረ ቅዱሳን ብሎ የሚጠራው አካል” በስደት የሚገኙ አባቶች ላይ (በስም ጠቅሶ ደግሞ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ላይ) “በቅርቡ በጀመረው የስም ማጥፋት ዘመቻ፣ በማን አለብኝነት የመከፋፈል ሥራ እየሠራ ይገኛል” ሲል ይከሳል።
በሰሜን አሜሪካ በመካሄድ ላይ ያለውን “ጸረ ተሐድሶ የስልክ ጉባዔዎች” የማኅበረ ቅዱሳን ጉባዔ ነው በሚል በስሕተት ወይም ደግሞ ሆን ብለው “ጠላት መጣባችሁ” በሚል ምዕመናንን ለማስተባበር የተጠቀሙበት ሊሆን እንደሚችል መገመት ቢቻልም ማኅበረ ቅዱሳን “በቅርቡ የስም ማጥፋት ዘመቻ ያደረገው” የት እና በምን ሁኔታ ነው የሚለውን ምንም አላብራሩም።
በቁጥር ሁለት መግለጫቸውም ከላይ በቁጥር አንድ የጀመሩትን በማብራራት “በየአጥቢያችን የተሰገሰጉ የማኅበሩ አባላት ረብሻዎችን ሊያስነሱብን ነው” የሚል ሥጋታቸውንና ጭንቀታቸውን ገልጸዋል። ቁጥር ሦስትም የዚያው ተጨማሪ ሆኖ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያነጣጠረ ውንጀላቸው እስከ ቁጥር 6 ድረስ ይዘልቃል። በሐሳብ ደረጃ ስንመለከታቸው የመግለጫው ፍሬ ሐሳቦች በአዲስ አበባ ሀ/ስብከትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ ባሉ ሙሰኛ እና የተሐድሶ አስተምህሮ አራማጆች ተደጋግመው የሚገለጹትን ውንጀላዎች የደገሙ ሆነው እናገኛቸዋለን።
ቁጥር ሰባት ላይ “የሐሰት ትምህርት የሚያስተምሩ፤ እኛ ክርስቲያን አይደለንም፣ ጠላት ያወጣልን ስም ነው፣” የሚሉ ያሏቸውን ሰዎች ተቃውመዋል። እንዲህ እያሉ የሚያስተምሩት እነማን እንደሆኑ፤ ማንነታቸውን እና ምንነታቸውን ምን እንደሆነ አስረግጠው ሳያስረዱ በደፈናው ይቃወማሉ። ምእመናንን ከእነርሱ ለመጠበቅ በሚል ማስጠንቀቂያ ለመስጠትም ይሞክራሉ። ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ መግለጫ ሰጡ እንዳይባሉ ያስገቡት ይመስልባቸዋል።
በመጨረሻ፣ እንዳይቀር እንዳይቀር በሚል ጉባኤው “ራሳቸውን ተሓድሶ ነን በሚል የፕሮቴስታንቶችን ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ስም የሚያስተምሩ መሆናቸውን በሚዲያ ከለቀቁት የስሕተት ትምህርት ጉባኤው ተረድቷል” ካሉ በኋላ ጉባኤው ስለተረዳው ነገር እና ስለ አቋሙ ገለጥ አድርጎ ሳያብራራ በደፈናው “ትምህርታዊ መልስ በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ተግቶ ለመሥራት ጉባኤው ተስማምቷል” በሚል ቤተ ክርስቲያናችንን በማመስ ላይ ስለሚገኘው ተሐድሶ ለማንሣት ይሞክራሉ።
ጉባኤው ለየትኛው ጉዳይ ክብደት ሰጥቶ ተነጋገረ? ዋናው የጉባኤው ዓላማስ ምን ነበር የሚለውን ለመረዳት ከስምንት ነጥቦች (መግቢያውን ሳይጨምር) መላልሶ ያነሣውን ጉዳይ መረዳት በቂ ነው። ይህንንም በማያሻማ ሁኔታ “በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን የተጋረጠባት ትልቅ አደጋ ምንድነው” ብሎ ይጠይቅና “ራሱን ማኅበረ ቅዱሳን ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው” ሲል ራሱ ይመልሳል። (ገጽ 2)
ይህ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያነጣጠረው ዘመቻ አስደናቂ የማይሆነው ከጉባዔው ተሳታፊዎች ቀንደኞቹ በተሐድሶ ትምህርታቸው የሚነቀፉት ሰዎች መሆናቸውን ልብ ሲሉ ነው። እነዚህ ግለሰቦች ኢትዮጵያ ከሚገኘውና በዋናው ቤተ ክህነት እግሩን አንሰራፍቶ ከተቀመጠው የተሐድሶ ክፍላቸው ጋር በመቀናጀት በአንድ ሰሞን፣ አንድ ዓይነት መግለጫ በማውጣትና ነገሮችን ከሥሩ አይመረምርም የሚሉትን ምእመን ለማደናገር ሞክረዋል።
ይሁን እንጂ እነርሱ እንዳሰቡት ሳይሆን በተለያየ የፖለቲካ አመለካከታቸው በሀገር ውስጥ ያለውን መንግሥት የሚቃወሙ፣ በፓትርያርክ አባ ማትያስ የሚመራውን ቤተ ክህነት እና ራሳቸውን ፓትርያርኩንም የማይቀበሉ እየመሰሉ ነገር ግን እጅና ጓንት ሆነው እንደሚሠሩ በትክክል አሳይተዋል። በቤተ ክርስቲያናችን የተፈጠረው የአባቶች ልዩነት እና ሁለት ሲኖዶስ የሚባል ችግር እንዳይቀረፍ በዚህም በዚያም ሆነው የሚያከላክሉ ሰዎችን በተሐድሶ ጉዳይ ላይ አብረው ሲሰሩ መመልከታችን “ግርግር ለሌባ ያመቻል” የሚለውን ተረት አስታውሶናል። በአባቶች መለያየት ያተረፈው አካል ማን መሆኑ ግልጽ እየወጣ ነው።
ሌላውን ትልቅ ቁምነገር “በርግጥ የቤተ ክርስቲያናችን ትልቁ ችግር በቃ ይኸው ነው? የገዳማት መበተን፣ የመምህራን መቸገር፣ የምእመናን ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየቆረቆዘ መምጣት፣ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መጠንከር፣ የምእመናን በዘረኛ መንግስት ቁም ስቅላቸውን ማየት፣ ከቀዬያቸው መፈናቀል፣ መታሰር፣ መገረፍ እና መገደል፤ የቤተ ክህነት አስዳደርን የጨበጡ ብዙ ሙሰኛና ዘራፊ ሰዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት በጠራራ ፀሐይ መዝረፋቸው ወዘተ እንደ ችግር እንዴት ሳይታያቸው ቀረ?
በዓላማ የተሐድሶን እምነት የሚያስፋፉትና በዚህ ጉባኤ ላይ መኖራቸውን በፎቶግራፎች ያየናቸው ሰዎች ዓላማቸው ነውና “ያስቸገረን ማኅበረ ቅዱሳን ነው” ቢሉ ብዙም አይደንቅም። ሌሎቹ አባቶች፣ በሃይማኖታቸው የማይጠረጠሩትና ወልድ ዋሕድ ብለው የሚያምኑት ግን አሁንም ዝምታን የመረጡትና አጃቢ ሆነው የቀረቡት በይሉኝታ ነው፣ ባለማወቅ ነው፣ ወይስ በርግጥም የቤተ ክርስቲያን ችግር ምንነቱን አያውቀቱትም ወይም ዘንግተውታል?
ሊሰመርበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ በአገር ቤት ከሕወሐት ወያኔ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ አገራችንን እና ቤተ ክርስቲያናችንን በማፍረስ ላይ ያለው የተሐድሶ ቡድን በውጪ አገር ደግሞ የተቃውሞው ኃይል አካል መስሎ ለመታየት የቻለበት ሁኔታ ነው። በዚህ ዘዴያቸው ከኢትዮጵያውያን ሬዲዮኖች እስከ ድረ ገጾች ድረስ “የነጻነት ኃይል” መስለው ለመታየት ከመቻላቸውም በላይ በፖለቲካ እያሳከሩ እምነታቸውን ለማስፋፋት በመጣር ላይ ይገኛሉ። ይህ ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ወቅት እንኳን ይህ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ምንነት በተንሸዋረረ መልኩ ለማሳየት እና ምእመናን የአቅማቸውን እንዳያደርጉ አቅጣጫ የሚያስቀይር መግለጫ በhttp://ecadforum.com/Amharic/archives/16224/ ድረ ገጽ ላይ ወጥቷል። ሌሎቹም ይከተላሉ፤ ሬዲዮኖቹም ይህንን የተሳሳተ አስተሳሰብ ሲያንጸባርቁ ይገኛሉ።
ነገ ነጻነት በኢትዮጵያ ሲመለስና ሕዝብ የመረጠው አስተዳደር ሲተከል እንኳን ዛሬ “ተቃዋሚ መስለው” የቀረቡት እነዚህ ኃይሎች ቤተ ክህነቱን ለመቆጣጠርና የአገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን መከራ ለማክበድ እነሆ ተዘጋጅተዋል። ነጻነት ናፋቂው ክፍል በዚህ ጸረ ተዋሕዶ ክፍል በመታለል እስከ መቼ የአፍራሽ ተግባራቸው አካል ይሆናል?
እነሆ አሁን “በስደት ባለው ሲኖዶስ ሥር ላሉ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ምእመናን” ከፍ ያለ ታሪካዊ ጥያቄ መቅረቡን ሊገነዘቡት ይገባል። ከወንዝ ልጅነት ባለፈ በመካከላቸው ያለውን ጸረ ተዋሕዶ ቡድን ሊመለከቱ ይገባቸዋል። በርግጥም አሁንም “ተሐድሶ የሚባል የለም፤ ማኅበረ ቅዱሳን ነው የፈጠረው” በሚለው ማባበያ የሚታለሉ አይመስለንም። በርግጥ ይህንን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው ካለፉ እጅግም ባልራቁ ዓመታት ተሐድሶ ምእመናኑን በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ፕሮቴስታንቶች አድርጎ ያገኙታል። ያን ጊዜ ለመመለስ እጅግ ያስቸግራል። ከሕንድ ታሪክ እንማር፤ እንንቃ።
ማስጠንቀቂያ፦ በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኙትን አባቶች በጅምላ ተሐድሶ ናቸው አለማለታችን ግልጽ ቢሆንም ደግመን ለማሳሰብ እንወዳለን። ነገር በማመሳሰል ያልተባለውን ተባለ ለሚሉት መናፍቃን ዕድል አንሰጣቸውም።
መልካም ዐቢይ ጾም
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን      

        
No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)