March 2, 2016

የተሐድሶዎች ዓላማና ግብ ለምን ያደናግረናል? ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት መማር አቃተን?

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ “ተሐድሶ” (ሪፎርሜሽን) ለማካሔድና በእነርሱ እምነት “ተባላሽቷል” የሚሉትን በመቀየር ገሚስ ፕሮቴስታንት ገሚስ ኦርቶዶክስ መሰል እምነት የመፍጠር ዓላማ መኖሩ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ሆኖ “አለ ወይስ የለም?” በሚል ለምን ግር ይለናል? በሃይማኖታቸው ኦርቶዶክሳዊነት የማይጠረጠሩ ብዙ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ልባቸው ይከፈላል። ለማመንም ለመተውም ይቸግራቸዋል። በሌላ አቀራረብ የሚቃወሙትን ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ ትምህርት ለማስፋፋት የሚጥሩትን ተሐድሶዎቹን ሲረዷቸው ይገኛሉ። ይህ የመደናገርና ግርታ ላይ የመውደቅ አባዜ እጅግ ሥር ከመስደዱ የተነሣ በአገር ቤት ያለችውን ቤተ ክህነት እጅግ እግሯን አስሮ ሊቆጣጠራት ምንም አልቀረውም። ከአገር ቤቱ ተገንጥለን የራሳችን ሲኖዶስ አለን የሚሉትንም አባቶች እንዲሁ መጠቀሚያው አድርጓቸዋል። የቤተ ክርስቲያናችን ፈተና የሆነው ይህ “ሪፎርሜሽን/ Reformation” የተባለ አፈንጋጭ አስተምህሮ ሊያመጣ የሚችለው ውጤት ለማይታያቸው ምናልባት የዚሁ ችግር ሰለባ የሆነችውን የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በአጭሩ መጥቀስ አብነት ሊሆን ይችል ይሆን?

የሕንድ ኦርቶዶክሶች ከቅ/ቶማስ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚመዘዝ ረዥም ሃይማኖታዊ ታሪክ አላቸው። ልክ እንደኛዋ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ በ17ኛው መ/ክፍለ ዘመን ወደ አገራቸው የገቡት ፖርቹጋሎች ባመጡት “ኦርቶዶክሳውያንን ካቶሊክ የማድረግ ዘመቻ” ብዙ መከራ ተቀብለዋል። ግማሽ ሕዝባቸውንም አጥተዋል። በእነርሱ እግር የተተኩት አዲሶቹ የሕንድ ገዢዎች እንግሊዛውያን በበኩላቸው ኦርቶዶክሶችን “አንግሊካን” ለማድረግ በነበራቸው ፍላጎት በገንዘባቸው “የቲዮሎጂ ኮሌጅ በማቋቋምና ራሳቸው ረዳት መስለው በመግባት” ኦርቶዶክስ መምህራንን ሊያፈራ የተቋቋመን መንፈሳዊ ኮሌጅ ለራሳቸው ዓላማ በመቀልበስ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውባቸዋል። በዚህም ሰበብ “ማላባር ኢንዲፔንደንት ቸርች፤ ማላንካራ ማር ቶማ ሴሪያን ቸርች እና ሴይንት ቶማስ ኢቫንጄሊካል ቸርች” የተባሉ ሦስት የፕሮቴስታንት እምነት ክፍሎች ሊፈጠሩ ችለዋል።
ከሕንድ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው “ተሐድሶው” የተጀመረው በአንግሊካን እንግሊዞች እርዳታ፣ ቄስ ያውም የቲዎሎጂ መምህር በነበረ ሰው አማካኝነት ነው። ይህ “አብርሃም ማፕላን” የተባለ ግለሰብ ዘመዱ የሆነን ዲያቆን መንበረ ፕትርክናው ወደሚገኘው ወደ ሶሪያ የሐሰት ደብዳቤ አስይዞ በመላክ እና ጵጵስና እንዲቀበል በማድረግ ሐሳቡን ከግብ ለማድረስ ችሏል። ጵጵስናውን ተሳስተው የሰጡት ፓትርያርክ ነገሩ ስሕተት መሆኑን ዘግይተው ቢገነዘቡም የደረሰውን ጥፋት እና ስብራት ለመጠገን ሳይቻላቸው ቀርቷል። ችግሩን ለመፍታት ሕንድ ድረስ ቢጓዙም “የፈሰሰ አይታፈስ” ሆኖባቸው አልፏል።
ዛሬ ተሐድሶዎች በቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም ዘርፍ ተንሰራፍተው ተቀምጠዋል። በአገር ቤትም በውጪውም ሲኖዶሶች አይነኬ ከመሆን ደረጃ ደርሰዋል። የሚያራምዱት እምነት ተሐድሶ መሆኑ በሰፊው እየተነገረ ዲቁናም ቅስናም የሚሰጣቸው ጳጳስ አላጡም። ምንኩስናን እየተቃወሙ ለጊዜው የመነኩሴ ቆብ የደፉትም ጵጵስና ለመቀበል በአገር ውስጡም በውጪውም ተራ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ሰዎች እንደሚፈራው እስከ ጵጵስናው ማዕረግ ለመድረስ ከቻሉ በሕንድ የደረሰው በእኛም ላይ እንደማይደርስ ምንም ማስተማመኛ ማግኘት አይቻልም። የሕንዱ ተሐድሶ (“የማር ቶማ ቸርች”) በእምነት ከአንግሊካኖች ጋር አንድ መሆኑን አውጆ የራሱን ጎጆ እንደቀለሰው ሁሉ የኛዎቹም የራሳቸውን ጎጆ የማይቀልሱበት ምንም ምክንያት የለም። በሕንዶች ከ1880ዎቹ ጀምሮ የተከሰተውን ታሪክ ከ150 ዓመት በኋላ የተፈጠርን ሰዎች ተመልክተን ችግሩን መገንዘብ ለምን ያቅተናል?
የሶሪያው ፓትርያርክ ለተሐድሶዎቹ የመጀመሪያ ጳጳስ ማዕረጉን ተሳስተው እንደሰጡት ሁሉ ዛሬም አውቀውም ይሁን ሳያውቁ መናፍቃኑን ማዕረግ በማዕረግ አድርገው በመንጋው ላይ በእረኛ ፈንታ ተኩላ የሚልኩባቸው ሰዎች ከፍ ያለ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸው ነበር።
በዚህ ወቅት የተሐድሶዎች ክፍል በቤተ ክህነቱ የተፈጠረው የአባቶች መከፋፈል ሰርግና ምላሽ ሆኖት ከዚህ ሲሉት ከዚያ፣ ከዚያ ሲሉት ከዚህ እያጣቀሰ ስሩን እያስፋፋ ሲሆን የአባቶች መከፋፈል እውነት የመሰለው ኦርቶዶክሱ ክፍል በዚህም በዚያም ወገን እየተጎዳ ከሁለት ያጣች ጎመን ሆኖ ተዘልሎ ተቀምጧል። የተሐድሶው ክፍል አገር ቤት ሲገባ ኢሕዴግን፤ ውጪ ሲወጣ ተቃዋሚውን እየመሰለ ዋና ዓላማው የሆነውን የኑፋቄ ስራ በሰፊው ያስፋፋል። “ፓትርያርካችን አቡነ መርቆርዮስ ናቸው” ሲል ይቆይና አቡነ ማትያስ የደገፉት ሲመስለው ተቀልብሶ ሲያመሰግናቸው ያመሻል። “አቡነ ማትያስ ፓትርያርኬ” ሲል የቆየው አገር ቤት ያለው ክንፋቸው ሲመቸው ደግሞ ውጪ ያሉት አባቶች ጋር ራት ሲበላ ይገኛል። በዚህም በዚያም ግን ቤተ ክርስቲያን እየደማች ነው። ይህ አዚም የሚለቀን መቼ ነው? የምንደናገረውስ እስመቼ ነው?
በዚህ ረገድ ፓትርያርክ አባ ማትያስ ቀደምቶቻቸው አድርገውት በማያውቁት መጠን እና ስፋት ቤተ ክርስቲያኒቱን ጅብ እያስበሏት ነው። አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት የተሐድሶዎችና የዚሁ ዓላማ መጋቢ የሆኑ ግብረ በላ ወዳጆቻቸው መጠቀሚያ ሆነዋል። በቤተ ክህነቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስብል ደረጃ ከቅ/ሲኖዶስ ተነጥለው፣ ሲኖዶሳዊቱን ቤተ ክርስቲያን ኢ-ሶኖዶሳዊ አስተዳደር ተክለውባታል። ብዙ ሚሊዮን ሕዝቧ በረሃብና በችጋር የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ በሆነበት ዘመን፤ የኑሮ ምሬት ያንገሸገሸው ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ግዛቶች ምሬቱን በሚያሰማበትና በዚሁ ሰበብ የሚያልቀው ምእመን የቀብሩን ስፍራ ባጣበበት በዚህ ወቅት “አስረሽ ምቺው” የቅንጦትና የዘረፋ ሰደድ ቤተ ክህነቱን አቀጣጥሎታል። ይህ ሁሉ ሰርግና ምላሽ የሆነው ግን ለተሐድሶው ኑፋቄ ነው። ይህ ሁሉ ነገር እንዴት ያደናግረናል? ለምንስ አንነቃም?
                                               
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን። No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)