June 4, 2014

ከአባቶቻችን ለማግኘት የምንመኛቸው


(በፀሐፊው ፈቃድ ከፌስቡክ ተወስዶ የተለጠፈ)፦ ዛሬ ግንቦት 27 30ኛው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ እንደሌሎቹ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኮች ሁሉ ይህንን አባትም የትሩፋቱንና የዕውቀቱን ዜና በሰሙ ጊዜ በእስክንድርያ አገር ያለፍቃዱ ይዘውት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት፡፡ የዕለቱ ስንክሳርወደረሰ ድርሳናተ ብዙኃተ ወአቀመ እግዚአብሔር በመዋዕሊሁ ቀርነ ቤተ ክርስቲያንእንዲል በዘመነ ፕትርክናውም ብዙ ድርሳናትን የደረሰና የቤተ ክርስቲያንን ስልጣን ያጸና አባት ነው፡፡
በዚሁ ዕለትም የማርያምና የማርታ ወንድም የሆነውና ጌታችን ከሞት እንዳስነሳው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ታሪኩ በሰፊው የተጻፈው አልዓዛር የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ይህ አልዓዛርም ጌታ ካስነሳው በኋላ ከሐዋርያት ጋር የአጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ጸጋ የተቀበለ እና በኋላም ሐዋርያት እጅ በመጫን በቆጵሮስ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት የሾሙት ነው፡፡ እርሱም መንጋውን በመልካም አጠባበቅ ጠብቆ በሹመቱ አርባ ዓመታትን ኑሮ በሠላም አረፈ፡፡አረፈየተባለለትም ይኼኛው ዕረፍቱ እንጂ ወደእግዚአብሔር ከመመለሱ በፊት፣ ለአገለግሎት ከመጠራቱ በፊት፣ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከመቀበሉ በፊት እንዲሁም የተሰጠውን የክህነት አደራ ከመወጣቱ በፊት የሞተውሞቱንአይደለም፡፡
እንደቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን እኛም እነዚህን ሶስት ነገሮችን በአባቶቻችን ዘመነ ፕትርክና ለማየት እንናፍቃለን፡፡ እነዚህም ለፍቅረ ሢመት ግድ ሳይኖራቸው ነገር ግን ትሩፋታቸውና ዕውቀታቸው ብቻ ታይቶ ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማሉ ተብለው ሳይወዱ በግድ የሚሾሙ የተሾሙት ለሥራ መሆኑን አውቀው በቃል በመጽሐፍ ምዕመኑን በማስተማር የሚተጉ፣ እንዲሁም በዘመነ ሢመታቸው ሁሉ የክርስቶስን መንጋ በመልካም አጠባበቅ የሚጠብቁ ኤጲስቆጶሳትንና ሊቃለ ጳጳሳትን፡፡
ካህናት አባቶቻችን ሳይወዱ ተገድደው በትሩፋታቸውና ዕውቀታቸው ብቻ የተገባቸው ሆነው ኤጲስቆጶስነት ሹመት የሚበቁበትን ጊዜ የማይናፍቅ እውነተኛ ምዕመን የለም፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ ቦረዳ ገዳምን በአበምኔትነት እያስተዳደሩ እንዳሉት አባት ከአንዴም ሁለቴ ለኤጲስቆጶስነት ታጭተውተውኝ እኔ እዚሁ ጸሎት እያደረኩ ልኑርብለው እምቢ ያሉ ጥቂት ደጋግ እና ቀና አባቶች በዘመናችንም ቢኖሩም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በመጣ ቁጥር ሳይገባቸው ለኤጲስቆጶስነት ሹመት የሚቋምጡና ለዚህም በሥራ ዘርፉ የተሰማሩ እበላ ባዮችን ኪስ እንደሚያደልቡ በተደጋጋሚ የምንሰማው ለጆሮ ግን የሚሰሰቀጥጥ ወሬ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ባልደረሰ የምንልበት ደረጃ ላይ አድርሶናል፡፡
በተጨማሪም የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኮችን ዜና ዕረፍት ስናነብ የብዙሃኑበዘመኑም ሕዝቡን በመልካም አጠባበቅ ጠብቆ በሠላም አረፈይላል፡፡ የእኛስ አባቶች ምን ያህል በበጎ አጠባበቅ ጠብቀውን ይሆን? እርግጥ ነው ለእረኞቻችን የምናስቸግር በጎች እንኖራለን፡፡ ነገር ግን የእኛ እረኞች የሆኑት እነዚህ አባቶችስ ምን ያህል ያስቸገርነውን እኛን ለማቃናት ሞክረዋል? ለስንቶቻችንስ አመጸኛነት ድጋፍ ሰጪ ሆነዋል? ስንቶቻችንን ከተሳሳትንበት መንገድ መልሰውናል? ለስንቶቻችንስ ከመንገድ ፈቀቅ ማለት በአንድም በሌላም ዓይነተኛ ምክንያት ሆነዋል? ስንቶቻቸውስ ከእውነት ጎን ተሰልፈው መንጋውን በመልካም አጠባበቅ በመጠበቅ ክፉ ዘመንን ለማሳለፍ ተግተዋል? ስንቶቻቸውን የበጎቹን ዘመን እጅግ እንዲከፋባቸው አድርገዋል? ስንቶቻቸውስ የተረከቡትን የእረኝነት አደራ እና የገቡትን ቃል አክብረዋል? ስንቶቻቸውስ ለእውነተኛቹ አባቶች እንደሚገባ በጸሎት በመትጋት መንጋቸውን ከሚያገሳው አንበሳ ከዲያብሎስ ጠብቀዋል? ስንቶቻቸውስ በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ለሆነች ለቤተ ክርስቲያንን ልዕልና በጽናት ቆመዋል? ስንቶቻቸውስ ይህንን መንፈሳዊና ሰማያዊ እንዲሁም ክርስቶሳዊ ኃላፊነት ወደኃላ ችላ ብለውታል
እንደ አገባቡ ከሆነ አባቶቻችን ሊቃነ ጳጳሳት ምዕመናንን ከመባረክ፣ የሚነበቡ ሕያዋን መጻሕፍ ናቸውና በኑሮአቸው ከማስተማርም አልፈው ተቀድተው ከማያልቀው ዕውቀታቸው ደካሞችን የምያበረቱበትን ድርሳናት ቢደርልን ምኞታችን ነው፡፡ በተለይ ከቁጥራቸው ማነስና ከምዕመናን ብዛት አንጻር በአካል አግኝተው ትምህርታቸውን ለመከታተል ለማይችሉት እንዲሁም አረፍተ ዘመን ከገታቸው በኋላ ለሚመጣው ትውልድ ሕያው ትምህርት አበርክተው ቢያልፉ ምንኛ ደስ ባለን ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ስድስት ያህል ፓትርያርኮችን የሾመት ቢሆንም ከሌሎች አቢያተ ክርስቲያናት አባቶች አንጻር እነዚህ አባቶች ያበረከቱት ድርሳናት እና መጻሕፍት እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ ለአብነት ያህል በአርባ ዓመት ዘመነ ፕትርክናቸው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ ሳልሳዊ ካበረከቱት ለቁጥር ከሚታክቱ መጻሕፍት አንጻር ሃያ አመታትን በመንበሩ በተቀመጡት በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የተደረሰ ያነበብኩትን አንድም መጽሐፍ አላስታውስም፡፡ በእርግጥ የቀድሞዎቹን ባላውቅም አሁን ያሉት ሌሎች ኤጲስቆጶሳነትን ጨምሮ ብዙዎቹ የእኛ አባቶች የአስተዳደር ሥራ ላይ ብዙ ትኩረት የሚደርጉ ሆነዋል፡፡ እንዲያውም ፓትርያርኮቹማ ደብዳቤ መጻፍና መግለጫ መስጠትን ዋና ሥራቸው ያደረጉ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን ጌታ በመጨረሻ ሲመጣ እኛን ምዕመናንን ስንት መግለጫቸውን እንደሰማን፣ ስንት ደብዳቤአቸውን እንዳነበብን ወዘተ እንደማይጠይቀንና ዋጋ እንደማይሰጠን ሁሉ እኒህ አባቶቻችንም በዚህ ድርጊታቸው አይመዘኑም፡፡ ይልቁንም መንጋውን ምን ያህል ከመናፍቃንና ከቀሳጥያን እንዲሁም ከዘመኑ አላውያን ጠብቃችኋል? ምን ያህልስ የሕይወት ምግብ መግባትኋቸዋል? ተብለው መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ ለሁሉም ቸሩ እግዚአብሔር ይህን መልካም ምኞታችንን እንዲሰጠን አጥብቀን ልንለምነው ይገባል፡፡

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)