April 7, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን በፓርቲ ፖለቲካ የማይጠረጠርባቸው ምክንያቶች (የግል ምልከታ)
Source: Courtesy of www.adebabay.com/  PDF

 ይህ ጽሑፍ የእኔን የግል ምልከታና አስተያየት ብቻ የሚመለከት እንጂ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰውን ማኅበርም ሆነ ከእርሱ ጋር የአገልግሎት ግንኙነት ያላቸውን ተቋማት የማይመለከት መሆኑን አበክሬ በመግለጽ ልጀምር።  

  አንድ ብሒል አለ። ውሸትን ደጋግመው ቢናገሩት እንደ እውነት የሚቀበለው ሰው መፍጠር ይቻላል። ስለዚህም ሐሰተኞች ሐሰታቸውን ሳያሰልሱ በተናገሩት መጠን፦ አንደኛ ራሳቸውንም በሐሰታቸው እውነትነት ያሳምናሉ፤ ብሎም ሌሎችን ማሳመን ይችላሉ። ደጋግሞ የመናገር ጥቅሙ ይኼው ነው።

አንዳንድ እውነት የያዙ ሰዎች ደግሞ “እውነት እስከያዝን ድረስ ደጋግሞ መናገር ለምን ይገባል?” ብለው ያቀርባሉ። እውነት አላቸው። ፀሐይ ሲወጣ ጨለማ መሸሹ፣ ሻማ ሲለኮስ ብርሃን መፈንጠቁ ላይቀር “ጨለማን ማውገዝ ምን ጥቅም አለው?” ይላሉ። ይህም እውነት ነው። “ጨለማን ደጋግሞ ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት” እንደተባለው። ነገር ግን ሐሰት ተደጋግማ በመነገሯ ተከታይ መፍጠር እስከቻለች ድረስ እውነትን ደጋግሞ በመናገር የሚመጣ ምን ችግር አለ? ሻማውንም እየለኮሱ እውነቱንም ደጋግሞ መናገሩስ? ስለዚህ በእውነት ተደጋግሞ መነገር፣ በሻማ መለኮስም አምናለኹ። ደጊመ ቃል እንዲሉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት።

 እንኳን አገር ቤት ያለው አንባቢ ይቅርና እኛ ከአገራችን በብዙ ሺህ ማይሎች ርቀን የምንገኘው ሳንቀር በየዕለቱ የምንኮመኩመው አዲሱ ትኩስ ዜና የማኅበረ ቅዱሳን እና “የተጠመደለት ወጥመድ” ጉዳይ ነው። በማኅበራዊ ድረ ገጾች እና በጡመራ መድረኮች፣ እንዲህ በሕትመት ውጤቶች በሰፊው ሽፋን ያገኘ ጉዳይ ሆኗል። ብዙ ኢትዮጵያውያን (እምነት ሳይለይ) ይህንን ጣልቃ ገብነት በጽኑዕ እየተቃወሙት እያወገዙት ነው። “ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ የሚባል ከሆነ እኔም አክራሪነትን እወደዋለኹ” የሚሉ ሐሳቦች በብዛት ተጽፈው ተመልክቻለኹ።


“የአክራሪነቱ ነገር”፣ ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ በፓርላማ ተናግረውት በነበረ ጊዜ፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ፀሐፍት አስተያየታቸውን የሰጡበት ከመሆኑ አንጻር ወደዚያ መመለስ አይገባ ይሆናል። ማኅበሩ ከፓርቲ ፖለቲካ ጋር ግንኙነት እንዳለው በመንግሥት ሰዎች እና በደጋፊዎቻቸው የሚነሣውን ሐሳብ በተመለከተ ግን የግል አስተያየቴን ላሰፍር እወዳለኹ።

ማኅበሩ ፖለቲካ ውስጥ አለበት? ለመሆኑ ፖለቲካ ውስጥ መግባት/ አለመግባት ምንድነው? ማንኛውም ሰው የተባለ ፍጡር ፖለቲካዊ አመለካከት አለው። ፖለቲካ አልወድም የሚሉ ሰዎች ራሳቸው እንኳን ፖለቲካዊ አቋም አላቸው። ልዩነቱ እያወቁ ማወቅ እና ሳያውቁ መኖር ናቸው። የተለያዩ ሐሳቦች እስካሉ ድረስ፣ አስተዳደሮች፣ ገዢዎችና ተገዢዎች እስካለን ድረስ ፖለቲካዊ አመለካከቶች መኖራቸው ግድ ይመስለኛል። “ፖለቲካ እና ኮረንቲ በሩቅ” የሚለው ሰው ራሱ በኮረንቲ ከመጠቀም፣ ሕይወቱ በፖለቲካ ተጽዕኖ ሥር መውደቁ እስካለ ድረስ ፖለቲካ የማይነካው ኢትዮጵያዊ አይኖርም።

ይኼ በፖለቲካ ምሁራን ሳይሆን እኔን በመሳሰሉ ለፖለቲካው ዕውቀት ተርታ በሆንን ሰዎች ቋንቋ “ፖለቲካ ውስጥ መግባት ወይም አለመግባት” የምንለው የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ማለታችን እንደሆነ ይሰማኛል። ፖለቲከኞች የምንላቸው እንደዚያ ያሉ ሰዎችን ነውና። ማኅበረ ቅዱሳን “ፖለቲካ ውስጥ ገባ/ አልገባም” የሚለውንም የምፈታው በዚሁ አንድምታውና አገባቡ ብቻ ነው።

ማኅበሩ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ አባላት አሉት። አባላቱ ሰዎች እንደመሆናቸው ፖለቲካዊ አመለካከት አላቸው። ማኅበሩን በአባልነት ለመቀላቀል የሚያበቃቸው ግን ይህ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው አይደለም። የአባላቱ የዓላማ አንድነትና መሠረቱ ማኅበሩ የሚያራምደው ቤተ ክርስቲያናዊ አቋም ብቻ ነው። በሃይማኖትና በአገልግሎት ዓላማ አንድ ናቸው እንጂ በፖለቲካ ርዕዮት የተሰባሰቡ አይደሉም። ሲጀመርስ ስለ ፖለቲካ አመለካከታቸው የት ተጠያይቀው? የት ተገማግመው? የት ተለካክተው? በየትኛው ጊዜ?

ስለዚህም ማኅበሩ አንድ ሃይማኖታዊ አቋም ያራምዳል እንጂ “አንድ ፖለቲካዊ አቋም” የሚባል የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ለምን? ምክንያቱም “ፖለቲካዊ አቋምን ለማራመድ” መጀመሪያ ፖለቲካዊ አቋም መያዝ ያስፈልገዋል። ያንን ለማድረግ ደግሞ አባላቱን በሙሉ በዚህ ፖለቲካዊ አቋም ማሳመን ያስፈልጋል፤ ያንን ማድረግ ደግሞ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ማኅበሩ የያዘውን ሃይማኖታዊ አቋም የሚጻረርና ማንም ሳይነካው እንዲፈርስ የሚያደርገው ድማሚት ነው።

እዚህ ላይ መነሣት ያለበት ቁምነገር፤ የማኅበሩ አባላት በሃይማኖታዊም ሆነ በፖለቲካዊ አስተሳሰባቸው ራሳቸውን የቻሉ (ማለትም ማመዛዘን የሚችሉ) ክርስቲያኖች እንጂ የአንድ ቡድን ጀሌዎች አለመሆናቸውን ነው። ራሱን የቻለ አስተሳሰብ ያለው ማንኛውም ሰው፣ አባል የሚሆንበትን ድርጅት ያያል፤ ይመዝናል፣ ያስባል። እንደማይጠቅመውና እንደማይስማማበት ከተረዳ ይተወዋል። ጀሌ ግን የተነገረውን ተቀብሎ እንደ በቀቀን ያስተጋባል፤ ሳያውቅ አባል ይሆናል፤ በጥቂት ጥቅም ይደለላል፣ የሚኖርለትም-የሚሞትለትም ቋሚ መርሕ አይኖረውም።

ማኅበረ ቅዱሳንን እና አባላቱን በአገራችን ላለፉት 40 ዓመታት በጠነነው የፖለቲካ ድርጅት ጀሌነት መገምገም ትክክል የማይሆነው ለዚህ ነው። አባላቱ አገልጋዮች እንጂ ካድሬዎች አይደሉም። አመራር ላይ የሚቀመጡት ሰዎች በተራቸው ለማገልገል እንጂ ከሌላው አባል የተለየ መርሕ ለማራመድ አይችሉም። እናራምድ ቢሉም አባላቱ ጀሌዎች ስላልሆኑ ሊከተሏቸው የሚችሉበት ምንም መንገድ አይኖርም። የአባላቱ አንድነት በሃይማኖት እና በሃይማኖት ብቻ ነው። በበሰለ ሚዛን የሚለካቸው ቢኖር ኖሮ በዘር፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አቋም፣ በትምህርት ደረጃ፣ በዕውቀት፣ በዕድሜ ወዘተ ወዘተ የተለያዩ እንጂ እንደ ሜዳ አህያ አንድ ወጥ እና ልሙጥ አለመሆናቸውን ይገነዘባል።

ስለዚህ አንድ አባል በግልጽ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብቶ የዜግነት ድርሻውን መወጣት ቢፈልግ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። በማኅበሩ ውስጥ ያለውን የአመራር ኃላፊነት ማስረከብ ይኖርበታል። በዚህ ደረጃ በይፋ ከአመራርነታቸው በሰላም ተሰናብተው ወደፈቀዱት ይፋዊ የፖለቲካ መስመር መጓዝ የቻሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ማኅበሩንም የፖለቲካ ድርጅታቸውንም መምራት የሚችሉበት መንገድ አይኖርም። እነርሱ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማቸውን በማኅበሩ ላይ ለመጫን ቢፈልጉም እንኳን “የፍላጎት መላተም” ("conflict of interests") ስለሚኖር ሊሳካላቸው አይችልም። የማኅበሩ አባላት በፖለቲካ መሳተፍ የዜግነት መብታቸው ሲሆን በማኅበሩ አገልግሎት መሳተፍ ደግሞ ሃይማኖታዊ የትሩፋት ሥራ እንደመሆኑ ማቻቻል የአባሉ ፈንታ ነው።

ማኅበሩ በፖለቲካ ውስጥ ገብቷል የሚለው (በተለይ በቤተ ክህነቱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች) ከ1980ዎቹ ጀምሮ ሲያዜሙት የነበረ የሰለቸ ዜማ ነው። የሚነቅፉት ግን ማኅበሩ “ኢሕአዴግን አይደግፍም” ብለው ስላሰቡ እንጂ “ተቃዋሚ ነው ብለው ስላመኑ” ብቻ አይደለም። ለነገሩ እነዚህ መንግሥትን በዱላነት ለመጠቀም የሚፈልጉ፣ በመንፈሳዊም በዓለማዊም ሚዛን ቢመዘኑ ውኃ የማያነሱ ደመናዎች “ፖለቲካ” የሚሉት አጎብዳጅነትን ነው። መንግሥት እነሱን ይጠቀማል። እነሱም በአቅማቸው በመንግሥት ይጠቀማሉ።

ታዲያ ማኅበሩ የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት እንደማይደግፍ ነገሩን ሥራዬ ብሎ ለሚከታተል ለማንኛውም ሰው ግልጽ ሆኖ ሳለ በዚህ ጉዳይ መወንጀሉ ለምን አስፈለገ? ክርስቶስ አምላካችን ራሱ “ግብር አትክፈሉ ይላል? ለቄሳር አትገዙ ብሏል፤ ንጉሣችን ሳይሆን ንጉሥ ነኝ ብሏል” የሚል ፖለቲካዊ ክስ እንደቀረበበት ሃይማኖትን ብለው የሃይማኖት አገልግሎት ላይ የተሠማሩ ሰዎች በየዘመኑ የሚከሰሱበት ጉዳይ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልገናል።

ቅዱስ ሉቃስ “ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም፦ እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር” ሲል እንደጻፈው (ሉቃስ 23፥2)። በሌላው ዓለም ያለውን እንኳን ትተን በአገራችን ያለውን ብናስታውስ፣ ነገር ሰሪዎች በየዘመኑ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችንን ከነገሥታቱ ጋር በማጋጨት በአደባባይ እስከመገረፍ ያደረሱበት ጊዜ፣ በግዞት በእስር እንዲማቅቁ ያደረጉበት ወቅት እንዳለ ታሪክ ያስተምረናል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን እና የደብረ ሊባኖስ እጬጌ ጻድቁ አባ ፊሊጶስን ለአብነት ብናንሣ አባ ጊዮርጊስ እንደተጋዘ፣ አባ ፊሊጶስ በአደባባይ ራቁቱን እንደተገረፈ እናነባለን።

ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ላይ ያለ ማኅበር ትናንት እንደፈላ እንደ ክረምት አግቢ ሊታይ አይችልም። መንግሥት ይኼ ሁሉ ሐቲት አይጠፋውም። ማኅበሩ ተቃዋሚም ደጋፊም እንዳይደለ መግለጹ እስካሁን ጉንጭ አልፋ ከመሆን አልዘለለም። መደገፍ የማይችል አካል፣ ባይቃወምም እንኳን ገለልተኛ መሆኑ ለአደጋ ያጋልጠናል በሚል “ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው” የዶሮ ፍልስፍና የተቃኘ ነው።

ከዚህም ባሻገር አባላቱ ከአንድ ዘርና ቋንቋ፣ ባህልና ፖለቲካዊ አቋም የመጡ አለመሆናቸው፤ ይልቁንም ሕብረ ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው እንቅልፍ የሚነሣቸው አካላት መኖራቸው ግልጽ ነው። “አዳሜ በየቅርጫትህ ግባ” ሲባል አንድ ቅርጫት ውስጥ የማይጨመሩ፣ ከሌላውም ቅርጫት ካለው ጋር ዝምድናና ፍቅር ያላቸው፤ ከቅርጫታቸው ውጪ የሚያስቡ ሰዎች ያሉበት ማኅበር መሆኑ የሚያስፈራቸው አሉ።

በውጪ አገር ባሉ የተለያዩ የመንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ሲጠረጠር እንደኖረ እነርሱም በፈንታቸው “ማኅበረ ቅዱሳን የኢሕአዴግ ደጋፊ መሆን አለበት” ሲሉ ኖረዋል። ለምን እንዲህ አላችሁ ሲባሉ ምክንያቱም “ይህንን የሚያህል ትልቅ ተቋም እንዴት ነጻና ፍፁም ሃይማኖታዊ ብቻ ሊሆን ይችላል? ጠርጥር ጠርጥር” የሚል ጥርጣሬ ያቀርባሉ።

ማኅበሩ አብሯቸው ጀብ ጀብ ላለማለቱ ምክንያቱ ዓላማውና ተፈጥሮው መሆኑን ለመቀበል የአገር ውስጡም የዳያስጶራውም ቡድን፣ እነዚያም እነዚያም ይኸው እንደተቸገሩ አሉ። እነዚያ “የዚያ ደጋፊ ነው” እንዳሉት፣ እነዚያም “የዚያ ደጋፊ ነው” እንዳሉት። ማኅበሩ ደግሞ “አነ ዘክርስቶስ፣ አነ ዘቤተ ክርስቲያን፤ እኔ የክርስቶስ ነኝ፣ እኔ የቤተ ክርስቲያን ነኝ” እንዳለ አለ። መጨረሻውን ደግሞ ዕድሜ ይስጠን እንጂ፣ እናየዋለን።

     ይቆየን - ያቆየን  
(ኤፍሬም እሸቴ)

2 comments:

Anonymous said...

Before any thing else, I appreciate your first words << This is my opinion, not MK and other bodies>> Egziabher Yibarkih....

Yes, we believe and confirm that MK is free from Politics, free means as MK. Individuals except few leaders, who are forbidden to be members of any political party, all are free to follow as they wish. Individuals right is respected unless they do not mix with their ideology with MK. This is what I know, and live for 22 years......Thank you!!!!

Anonymous said...

Thanks Bro, specially I apprciate the word ..“አዳሜ በየቅርጫትህ ግባ” ሲባል አንድ ቅርጫት ውስጥ የማይጨመሩ፣ ከሌላውም ቅርጫት ካለው ጋር ዝምድናና ፍቅር ያላቸው፤ ከቅርጫታቸው ውጪ የሚያስቡ ሰዎች ያሉበት ማኅበር ....this is what i witnessed for MK...May God protect MK forever

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)