February 20, 2013

አስታራቂ ጉባኤው መግለጫ አወጣ

(ደጀ ሰላም፤ የካቲት 13/2005 ዓ.ም፤ ፌብሩዋሪ 20/2013/ PDF)፦ በአባቶች መካከል የተፈጠረውን መለያየት ላማራቅና ዕርቅ ለማውረድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የቆየው የሰላምና አንድነት ጉባኤ ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ አወጣ። የመግለጫው ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ላለፉት ሦስት ዓመታት በአገር ቤትና በውጭው ዓለም የሚገኙ አባቶችን በማስማማት ቤተ ክርስቲያንን አንድ ለማድረግ ያደረገውን ከፍተኛ ጥረት በዝርዝር ለመግለጽና የዕርቁ ሒደት ምን ይመስል እንደነበር በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ለሚኖሩ መላው ኦርቶዶክሳውያን ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምርን እንዲያውቁት ለመግለጽ ነው” ያለው መግለጫ ዝርዝር ሐሳቦችን አካቷል። ሙሉ ቃሉን ከዚህ በታች ተመልከቱ።


በወቅታዊው የቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ።
የካቲት12/2005ዓ.ም
Feb 19/2013

የመግለጫው ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ላለፉት ሦስት ዓመታት በአገር ቤትና በውጭው ዓለም የሚገኙ አባቶችን በማስማማት ቤተ ክርስቲያንን አንድ ለማድረግ ያደረገውን ከፍተኛ ጥረት በዝርዝር ለመግለጽና የዕርቁ ሒደት ምን ይመስል እንደነበር በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ለሚኖሩ መላው ኦርቶዶክሳውያን ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምርን እንዲያውቁት ለመግለጽ ነው።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የማስታረቅ ሥራውን የጀመረው በኢትዮጵያ በኩል በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ፤ በውጭም በኩል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መልካም ፈቃድ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ ነው። የሰላምና አንድነት ጉባኤው በርካታ ምእመናንና አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉለት ሦስት ጉባኤያትን በማዘጋጀት አባቶች ችግሮቻቸውን በጋራ ተነጋግረው በውይይት እንዲፈቱ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። በእያንዳንዱ ጉባኤ ላይም አለመግባባት በተፈጠረባቸው ሐሳቦች ላይ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለዕርቀ ሰላሙ ሥምረት ይበጃል ያለውን የመፍትሔ ሐሳብ እያቀረበ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት አቅም የፈቀደውን ያህል የበኩሉን አስተዋጽዖ አድርጓል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ እስካሁን ያካሔዳቸውን ሦስቱን የዕርቀ ሰላም ውይይቶች አጠቃላይ ገጽታና ሒደት ከዚህ እንደሚከተለው በዝርዝር እናቀርባለን።

የመጀመሪያውጉባኤ
ይህ የመጀመሪያ ጉባኤ የተካሔደው ከሐምሌ 26-28, 2002 .ም በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ማክሊን ሆቴል ሲሆን ከኢትዮጵያና ከውጭው ዓለም የተወከሉ አባቶች እንዲገናኙ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ለዚህ ጉባኤ አለመሰካት ትልቁ ምክንያት ከኢትዮጵያ በኩል ልዑካን ከመሰየማቸው አስቀድሞ በውጭ ካሉት አባቶች ለሰላምና አንድነት ጉባኤው የቀረበ ጥያቄ ነበር። ይኸውም በኢትዮጵያ በኩል በልዑክነት ከተመደቡት ከአንዱ ጋር ከባድ ቅሬታ ስላለን አብረን ቤተ ክርስቲያንን አንድ ለማድረግ የሚያስችል ልባዊ ንግግር ለማድረግ ስለምንቸገር በሌላ ሰው እንዲለወጡ ይደረግልን የሚል ነበር። ይሁን እንጂ ጉባኤው ወደ አዲስ አበባ ደውሎ ለመጠየቅ ከልዑካኑ መሪ ጋር በተነጋገረበት ጊዜ «እኛ የምንመጣው ትልቁን ችግር ልንፈታ ስለሆነ ችግር የለም፤ ስንመጣ እዚያው እንፈታዋለን» የሚል ምላሽ ተሰጠን። ከኢትዮጵያም ሆነ ከውጪው ዓለም የተወከሉት አባቶች ስብሰባው ቦታ እንደተገኙ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ከስብሰባ በፊት ልዑኩን በውጪ ካሉት አባቶች ጋር ያለባቸውን ችግር በመፍታት ወደ ዋናው ድርድር ለመግባት ጥረት ሲያደርግ ከአዲስ አበባ የመጡት ልዑካን ጸሐፊ «ከመመሪያ ውጭ ያደርገናል፤ አይሆንም አሉ።» በወቅቱ ለሰጡት መልስ ያቀረቡት ምክንያት “በጋራ እንድንነጋገር እንጂ በግል ይቅርታ ልንጠያየቅ አልመጣንም” የሚል ነበር። የሰላምና አንድነት ጉባኤው ቀደም ሲል በውጭ ያሉት አባቶች ባቀረቡለት ጥያቄና ጉባኤውም በገባው ቃል መሠረት ልዑኩ ይቅርታ እንዲጠይቁ ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ምክንያት ጉባኤው ሁለቱንም ወገኖች በእንባ ጭምር ቢለምንም የሚሰማ ባለመገኘቱ የመጨረሻ እንደ መፍትሔ አድርጎ ያቀረበው ከኢትዮጵያም ከውጭውም ዓለም የመጡት አባቶች ሊቃውንቱ ቀርተው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሆኑት በሊቃነ ጳጳሳት ደረጃ ብቻ ተነጋገሩ የሚል ሲሆን ይህም ተቀባይነት አላገኘም። ይሁን እንጂ ልዑካኑ ፊት ለፊት ተገናኝተው ባይነጋገሩም ሁለቱም አባቶች በሰላምና አንድነት ጉባኤው አማካኝነት በተዘወዋሪ መልኩ እንዲደራደሩ ተደርጓል። በዚህም ለወደፊቱ ግንኙነት እንቅፋት የሚሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ተስተካክለው የሰላሙ ጉባኤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተስማምተው ነበር።

ሁለተኛውጉባኤ
ሁለተኛው ጉባኤ ከየካቲት 2-11 ቀን 2004 .ም በአሜሪካ ፊኒክስ፤ አሪዞና ከተማ የተካሔደ ሲሆን ከ20 የልዩነት ዓመታት በኋላ አባቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ተነጋግረው በአንድነት የጋራ መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል። በዚህ ጉባኤ ላይ በዋነኛነት ቀርበው የነበሩት የመነጋገሪያ አጀንዳዎች፦

1ኛ/ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በሚመለከት፤
2ኛ/ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በተመለከተ ነበር።

በውይይቱ ወቅት በሰሜን አሜሪካ ያሉት አባቶች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው የወረዱት ተገድደው ነው፤ አቡነ ጳውሎስም አራተኛው ፓትርያሪክ በሕይወት እያሉ በመሾማቸው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ፈርሷል። ስለዚህ የፈረሰውን ቀኖና ለማረምና ለማደስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው መመለስ አለባቸው የሚል ነበር። ከኢትዮጵያ የመጡት ልዑካን ደግሞ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥልጣናቸውን ራሳቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ አልችልም፥ አሞኛል” ብለው ስላስረከቡ ጉዳዩ በምልዓተ ጉባኤ ተወስኖ እርሳቸው ከሥልጣናቸው ከወረዱ በኋላ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የተሾሙ ስለሆነ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አልፈረሰም። ይልቁንም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሌለ ስደተኛ ሲኖዶስ አቋቋምን በማለት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያፈረሳችሁ እናንተ ናችሁ ብለዋል። አያይዘውም “አራተኛው ፓትርያርክ ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም በወሰነው መሠረት ቅዱስነታቸው በፈቀዱት ቦታ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው ይኑሩ፤ ለሾሟቸው ጳጳሳትም ሀገረ ስብከት ይሰጣቸዋል” ብለዋል።

የሰላምና አንድነት ጉባኤው የሁለቱንም አካላት ሐሳብ በሚገባ ካዳመጠ በኋላ አባቶች ይበልጥ በሚያቀራርባቸውና ወደ አንድነት በሚያመጣቸው ሐሳብ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ብርቱ ጥረት አድርጓል። በዚህ መሠረት ለሃያ ዓመታት የቆየውን ችግር በቀላሉ መፍታት ባይቻልም ውይይቱ በመደማመጥና በመከባበር ሊቀጥል ችሏል። ስለሆነም የአሪዞናው ዕርቀ ሰላም ጉባኤ ጽኑ የሰላም መሠረት የተጣለበት ጉባኤ ነውብለው የጋራ መግለጫ ያወጡበትና ቀጣይ ስብሰባ እንዲዘጋጅ ተስማምተው የወሰኑበት ጉባኤ ሆኖ ተጠናቅቋል። የሰላምና አንድነት ጉባኤውም ከውይይቱ ያጠናቸውን ነገሮች መነሻ በማድረግ ባለ ሰባት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ ለሁለቱም ወገን በጹሑፍ አቀርቧል። ለዚህም ልዑካን ሰይሞም ወደ ሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በመላክ ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲያስረዱ አድርጓል። በአሪዞናው ጉባኤ ላይ በተደረሰው የጋራ ስምምነት መሠረት መሠረት ሦስተኛው የዕርቀ ሰላም ድርድር ጉባኤ ዝግጅት ቀጠለ። ይህ በዚህ እንዳለ ግን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ድንገተኛ ዕረፍት መሰማቱ አሳዛኝና አስደንጋጭ ነበር። ስለሆነም የሰላምና አንድነት ጉባኤው በወቅቱ ልዑካንን ልኮ በቅዱስነታቸው ሥርዓተ ቀብር ተገኝተው የጉባኤውን የኃዘን መግለጫ መልእክት እንዲያሰሙ አድርጓል። በዚህም የዕርቀ ሰላሙ ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በአፋጣኝ ለፍጻሜ እንዲበቃም ለቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄውን አቅርቧል።

ሦስተኛው ጉባኤ
በመሠረቱ የሰላምና አንድነት ጉባኤው አንዱን ችግር አሳለፍኩ አሁንስ ሰላም ይገኛል ብሎ ተስፋ ሲያደርግ ሌላ ያልታሰበ ችግር ከፊቱ ይደቀንበታል። ይሁን እንጂ በየጊዜው የሚከሰተውን ችግር ፈትቶ ሂደቱን መልክ ለማስያዝ የሚጠይቀው ጊዜና ድካም ቀላል አልነበረም። በዚህም ሁኔታ ሦስተኛውን ዙር ጉባኤ ከኅዳር 26-30 ቀን 2005 .(Dec. 5-9, 2012) በዳላስ፤ ቴክሳስ ለማካሔድ ተቻለ። ይህ ጉባኤ ከዚህ ቀደም ካሳለፍናቸው ሁለት ጉባኤያት እጅግ በተለየ መልኩ የመቀራረብና የመከባበር መንፈስ የታየበት ልዑካኑ ገና እንደተገናኙ የፍቅር ሰላምታ የተለዋወጡበት ነበር። በጉባኤው ዋዜማ በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ደማቅ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ በአንድ ቤተ መቅደስ ውስጥ ተገኝተው ጸሎተ ኪዳን በጋራ አድርሰዋል። ከሕዝቡ የተደረገላቸውን የአቀባበል ሥነ ሥርዓት በእጅጉ አድንቀውና አመስግነው በደስታ ተቀብለውታል። ጉባኤው ሲጀመርም የጉባኤውን መክፈቻ ጸሎት እርስዎ ይጀምሩ” “የለም እርስዎ ይጀምሩ” እየተባባሉ በፍቅር በመገባበዝ ጀምረውታል።

በውይይቱም ወቅት ሁለቱም ወገኖች ከላካቸው አካል ይዘውት የመጡትን መሠረተ ሐሳብ በሰፊው ተነጋግረውበታል። ይኸውም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገራቸው መመለስ ለዕርቀ ሰላሙ ስኬታማነት ዋነኛ መሠረት መሆኑን በጋራ የተስማሙበት ቢሆንም በሁለቱም ወገን ቅዱስነታቸው እንዴትና በምን ሁኔታ ይመለሱ በሚለው ዐቢይ ጉዳይ ላይ የአቋም ልዩነት ታይቷል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ልዑካን በኩል የቀረበው ዋና ሐሳብ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ቅድስት አገራቸው ገብተው፣ ክብራቸው ተጠብቆና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው እርሳቸው በፈለጉት ቦታ ይኑሩየሚል ነው። አያይዘውም ምክያቱን ሲገልጹ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ቢመለሱ ታሪክ ይፋለስብናል” የሚል ነበር። በአንጻሩ ደግሞ በውጭ አገር ያሉት ልዑካን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ሲባል ቅዱስነታቸው ከነሙሉ ሥልጣናቸው ወደ መንበራቸው መመለስ አለባቸው፤ ፓትርያርክ እያለ ሌላ ፓትርያርክ መሾም ሥርዓት አልበኝነትን ያስከትላልብለዋል። ምክንያቱም «ቅዱስነታቸውን ወደ መንበራቸው እንዳይመለሱ የሚያደርጋቸው ቀኖናዊ በደል ስለሌለባቸውና በአሁኑ ጊዜም መንበሩ ክፍት ስለሆነ ሊመለሱ ይገባል» ብለዋል።

ስለዚህ ልዑካኑ ልዩነት በታየባቸው መሠረታዊ ሐሳቦች ላይ አሁን በራሳችን ለመወሰን ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ሰይሞ ወደላከን አካል ተመልሰን ጉዳዩን በስፋት አስረድተን እንደገና የምንገናኝበትና የዕርቀ ሰላሙን ውይይት የመጨረሻ ምዕራፍ የምናደርስበት ቀጣይ አራተኛ ጉባኤ በቅርቡ ያስፈልገናልሲሉ ለሰላምና አንድነት ጉባኤው ሐሳባቸውን አቅርበዋል። ጉባኤው ከልዑካኑ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት አራተኛው ጉባኤ ከጥር 16-18 ቀን 2005 .(Jan. 24-26/2013) በሎስ አንጀለስ፤ ካሊፎርኒያ እንዲካሔድ ሐሳብ አቅርቧል። የሰላምና አንድነት ጉባኤው ያቀረበውን ሐሳብ የሁለቱም ወገን ልዑካን በአንድ ድምፅ ተቀብለው ተስማምተውበታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የግራ ቀኙን ፍሬ ሐሳብ በጥሞና አዳምጦና በጉዳዩ ላይም በስፋት ተወያይቶ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ሥምረት ይበጃል ብሎ ያመነበትን ባለ አራት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ ለልዑካኑ በጽሑፍ አቅርቦ በንባብ አሰምቷል። ለልዑካኑ ያቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብም በልዑካኑ ስምምነት መሠረት ለሁለቱም ሲኖዶሶች ምልዓተ ጉባኤ በደብዳቤ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርቦ ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ያቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ።
1. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን አስመልክቶ ከምንም በላይ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ሲባል ቅዱስነታቸው ወደ መንበራቸው ተመልሰው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠንቶ በሚጸድቀው የጋራ መመሪያ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ተግባራት ብቻ እንዲያከናውኑ ቢደረግ፤

2. የቤተ ክርስቲያኒቱን የአስተዳደር ዘርፍ በተመለከተ ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠንቶ በሚወጣው መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል በሚመረጥ እንደራሴ ወይም በጋራ ስምምነት በሚሰየም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንዲመራ ቢደረግ፤

3. ከላይ የተገለጸውን የመፍትሔ ሐሳብ ከጠቅላላው የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ አንጻር ለማገናዘብ እንዲቻል የዐራተኛውና የአምስተኛው ዘመነ ፕትርክና እንደ ተጠበቀ ሆኖ በየጊዜው የተከናወኑትን ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተግባራትንም ሙሉ በሙሉ አክብሮ በመቀበል በዕርቀ ሰላሙ አማካይነት የቤተ ክርስቲያናችንን የታሪክ ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚቻል በመሆኑ፤

4. ከዚህም ጋር ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በኋላ በጋራ የሚሾመውን ቀጣይ ፓትርያርክ ስድስተኛ ፓትርያርክ አድርጎ በመሰየም የታሪክ ሒደቱ እንደተጠበቀ ሆኖ እንዲቀጥል ቢደረግ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጥ ይችላል ብሎ ጉባኤው ያምናል።

5. በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያናችን በከባድ ችግር ውስጥ መሆኗንና ዕርቀ ሰላሙ የቅዱስ ሲኖዶስ ተቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንደሚገባው ይታመናል። ስለሆነም ለሦስት ዓመታት ሲካሔድ የቆየው የዕርቀ ሰላም ንግግር ለሠመረ ውጤት እንዲበቃና ሃያ አንድ ዓመታትን ያስቆጠረው አሳዛኝ የልዩነት ታሪክ በአንድነት እንዲተካ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን በጥልቀት ተመልክቶ ለዕርቀ ሰላሙ የመጨረሻ እልባት መስጠት ወቅቱ የሚጠይቀው ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን የሰላምና አንድነት ጉባኤው በእጅጉ ያምናል።

በእንጥጥል ላይ እንዳለ ሳይቋጭ የቀረው የአራተኛው ዙር ጉባኤ እንቅፋቶችና የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዕርቀ ሰላም ሒደት እንዳይሳካ ያደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች፤
1. በኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ አባቶች ከቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ይልቅ ለሢመተ ፓትርያርክ ቅድሚያ በመስጠታቸውና የላኳቸውን ልዑካን ሪፓርት ሳይሰሙ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየማቸው፤

2. የኢ////ክ የሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት በልዑካኑ የስምምነት ውሳኔ መሠረት ወደ አዲስ አበባ ቅዱስ ሲኖዶስ ተሰይመው ከሔዱ በኋላ የተላኩበትን ዐቢይ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዳያቀርቡ እስካሁን ድረስ እንኳን ማንነታቸው ባልታወቀና ባልተረጋገጠ ግለሰቦች ተላለፈ በተባለ ሕገ ወጥ ትእዛዝ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ቅጽረ ግቢ እንዳይገቡ በጥበቃ ሠራተኞች መከልከላቸው፤

3. ከዚህም በላይ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ አንደኛውን ልዑክ ካለአንዳች ምክንያት በግዳጅ ከሀገር እንዲወጡ መደረጉ፤ ሁለተኛውንም ልዑክ በማጉላላትና ወደ ቤተ ክህነት ግቢ እንዳይገቡ በማገድ፤ በቀጠሮ እንኳን ለሚጠብቃቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከላይ የዘረዘርናቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች የያዘውን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ደብዳቤ አቅርበው እንዳያስረዱና ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ እንዳይመክርበት መደረጉ፤

4. ገና ከጅምሩ ጀምሮ ዕርቀ ሰላሙን የማይፈልጉና በግልጽ ይቃወሙ የነበሩ አንዳንድ አባቶች ፈጽሞ የተዛባና ከእውነት የራቀ መሠረተ ቢስ መረጃ ለመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆነ ለኅብረተሰቡ መስጠታቸው፤

5. በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ፍጹም ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ለማድረግ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሔድ የቆየው የዕርቀ ሰላም ጥረት ከዳር እንዲደርስ በማይፈልጉ ጥቂት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አማካይነት ቅዱስ ሲኖዶስ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት ለውጤት እንዲበቃ ባለማድረጉ ምክንያት መንግሥት በቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን ላይ ግልጽ ተጽእኖና ጫና በማድረጉ፤

6. በመጨረሻም ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ስድስተኛ ፓትርያርክ ለመሾም በችኮላ መወሰኑ የሰላሙን በር ከመዝጋቱም በላይ የዕርቀ ሰላሙን ውጤት በጸሎትና በታላቅ ተስፋ ሲጠባበቅ ለቆየው መላው ሕዝበ ክርስቲያን ታላቅ መርዶ ሆኗል።

በዚህ አጋጣሚ በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ አባታዊ ቡራኬና በቅዱስነታቸው በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መልካም ፈቃድ እንዲሁም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አባታዊ ቡራኬና በቅዱስነታቸው በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መልካም ፈቃድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የዕርቀ ሰላሙን ጥረት እንዲያካሒድ በመደረጉ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን። ከዚህም ጋር ጉባኤው በጠየቀው መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መመሪያ ሰጪነት ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ጊዜያት የልዑካኑን የአየር ቲኬት በመሸፈን ስላደረገልን ከፍተኛ ትብብር ጉባኤው ከልብ ያመሰግናል። በአጠቃላይ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ባለፉት ሦስት ዓመታት ባደረገው የዕርቀ ሰላም ጥረት በጸሎታችሁ፣ በሐሳባችሁ፣ በምክራችሁ፣ በገንዘባችሁና በጉልበታችሁ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላደረጋችሁልን አብያተ ክርስቲያናት፣ ምእመናን፣ ማኅበራትና ደርጅቶች ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አምላክ ዋጋችሁን አብዝቶ ይክፈላችሁ እንላለን። አሁንም ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት የተለመደውን ትብራራችሁንና ድጋፋችሁን እንዳታቋርጡ በአክብሮት እናሳስባለን።

ይልቁንም ከኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ልዑካን ሆነው የመጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በልዑካኑ ጸሐፊ አማካኝነት የሚደርስባቸውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ለዕርቀ ሰላሙ አጠቃላይ ሒደት ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት እንዲሁም በውጭ ሀገር ያሉት አባቶች ለዕርቀ ሰላሙ ሒደት ስላደረጉት ቀና ትብብር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል። ምንም እንኳን በጥቂት አባቶች አቀነባባሪነት የሰላምና አንድነቱ በር ለጊዜው የተዘጋ ቢመስልም የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር በጥበቡ ከፍቶ የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት እንደሚያሳየን ተስፋ እናደርጋለን። እነሆ በእግዚአብሔርም ሆነ በሰዎች ዘንድ በግልጽ እንደሚታወቀው ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ስንል እስካሁን ድረስ አቅማችን በፈቀደው ሁሉ የሚቻለንን ያህል ጥረናል። ይሁን እንጂ “ፈደዩኒ እኪተ ህየንተ ሠናይት” እንደተባለው የሰላምና አንድነት ጉባኤው አባላት ፍጹም ሰላማውያን መሆናቸው እየታወቀ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት አብዝቶ መድከም እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል።

እንደሚታወቀው የዕርቀ ሰላሙን ሒደት ለማሰናከል የፈለጉ ጥቂት አባቶችና “የቤተ ክርስቲያን” ባለሥልጣናት የሆኑ ግለሰቦች ለመንግሥት አካላት የተዘባ መረጃ በመስጠት የሰላም ልዑካኑ ከሀገር በግዳጅ እንዲወጡና እንዲጉላሉ ተደርጓል። ከዚህም ጋር በሰላም ልዑካኑ ስም ከሰላሙ በቀር አንዳችም አጀንዳ የሌለውን ጉባኤያችንን የማይወክል የሐሰት ወረቀት በመበተን ያለስማቸው ስም ለመስጠት ተሞክሯል። ለዚህ ሁሉ ግን የቤተ ክርስቲያን አምላክ ራሱ በጊዜው እንደሚመልስና እንደሚፈርድ ወደፊትም ታሪክ እንደሚያስታውሰው ስለምናምን ሁሉንም በአኰቴት እንቀበለዋለን። ነገር ግን ትናንትም፣ ዛሬም ነገም እጅግ የሚያሳስበን የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ነው። በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና መምህራን፣ መዘምራንና ወጣቶች በግልጽ ለማሳወቅና በአጽንዖት ለማሳሰብ የሚፈልገው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እስኪመጣ ድረስ ከመላው ሕዝበ ክርስቲያን ጋር በመሆን እስከ መጨረሻው ጥረቱን የሚቀጥል መሆኑን በአጽንዖት እንገልጻለን።

እግዚአብሔር አምላክ የቤተ ክርስቲያናችንን የሰላምና አንድነት ዘመን እንዲመልስልን ተግተን እንጸልይ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ።

8 comments:

Anonymous said...

Guys,

The main reason it failed because TPLF has a mission to destroy the church by appointing cadre papas and embracing banda amhars like aba abrham. Please read the excerpt below from late TPLF leader himself.

“የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 አመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርሀ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው።...መነኮሳት በመምሰል ደብረ ዳሞ ወደ መሳሰሉት ገዳማት ሰርጎ በመግባት የድርጅቱን እቅድ በማስተጋባት የሚያዳክም አጥኝ ኃይል በስብሀት ነጋ መሪነት ተመሰረተ። "
source:ከቀድሞው የሕ.ወ.ሓ.ት. ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ መጽሐፍ

beewunetkiristian said...

ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ እውነተኛውና ታማኙ ቃል ይህ ብቻ ነው። እርቅንና ሰላምን አሻፈረኝ ብለው ያፈረሱት እነማን እንደሆኑ በግልጽ አየን። የሚሾሙትንም የመንግስት ተላላኪ ለእነርሱው አባት ይሁናቸው። እኛ እውነተኛው አባት እግዚአብሔር አለን። የዋለወድባን መታረስ ሌሎችም የታሰቡትን ቤተክርስቲያንን የማዳከም ስውር እቅድ ለማስፈጸም የሚሾም ነውና እግዚአብሔር ደግሞ ፍርዱን በቶሎ እንደሚሰጥ አንጠራጠርም። ውጊያቸው ከእግዚአብሔር ጋር ሆኗልና የእግዚአብሔር ሰይፍ ሊበላቸው ተፋጥነዋል። ይህንንም በቅርቡ ያሳየናል የታመነ አምላክ ነውና። የዋሕዶ አምላክ ሆይ ፈጥነህ ሰላምንና አንድነትን ስጠን።

Anonymous said...

How trusted is if this commentary is from the negotiators? No logo or stamp or signature??? seems biased towards the end of the blog!

Anonymous said...

መግለጫው ቀደም ሲል እንደሚነገረው ሚዛናዊነት የጎደለው እና አድሎ የሚታይበት ነው ለቤተክርስቲያን ከታሰበ አቡነ መርቆሪዎስ ከነሙሉ ስልጣናቸው ካልተመለሱ ሞተን እንገኛለን ምን ያስብላል እነሱም ለስልጣን ሲንገበገቡ ወያኔ ታዲያ እጁ ላይ ያለውን ስልጣን እንዴት አሳልፎ ይሰጣል ቤተክርስቲያንን እንደሆነ ለስልጣን ብለው ሁለቱም እየገደሉዋት ነው እግዚአብሔር የሰጣቸውን መንጋ ባለመጠበቃቸው ይፈርዳል ምክንያቱም ከመንጋው ይልቅ ራሳቸውን አስቀድመዋልና በጠቅላላ ከእጅ አይሻል ዶማ ነው ስለዚህ ቦ እለ ሞቱ በእንተ ከርሶሙ በእነርሱ ዘንድ ሰውና እግዚአብሔር ቦታ የላቸውም ራሳቸውን ብቻ እየጠበቁ ይኖራሉ አንድ ቀን እግዚአብሔር ማንነቱን ያሳያል

Anonymous said...

Unfair letter and dejeselam is changing her role.

Anonymous said...

Am really sorry to hear this story that even hurt my futur expectation from our church. I think we are too late by now even to have side, they both made mistake. Ok! but do they continue....? Sorry

Anonymous said...

These is unacceptable decision by TPLF for 75000000 when the people make decision we have to pray to get honest leader

Anonymous said...

Some of you are really funny. We all have seen enough of Weyanie for the last 21 years. they already decided to destroy the church. Destroying Waldba a 1600 years old monastry. Dividing the 2000 years old church. What do you need more to believe that what they are doing is wrong. Believe me in the near future our local churchs will be cenima hall and the monastries museum.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)