January 15, 2013

“ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ አገራቸው ይግቡ፣ ግን እንዴት ይግቡ?” የሚለው ቅዱስ ሲኖዶሱን አወያየ

(ደጀ ሰላም፤ ጥር 7/2005፤ ጃኑዋሪ 15/2013/ PDF)፦ ትናንት ሰኞ የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ ላይ  የተገኙ ብፁዓን አበው በዕርቀ ሰላሙ እና በቀጣዩ ፓትርያርክ ጉዳይ ሲነጋገሩ የዋሉ ሲሆን ዕርቀ ሰላም መቅደም እንዳለበት በደምሳሳው ግብብነት እንዳለ ተመልክቷል። ይሁን እንጂ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን በተመለከተ ብፁዓን አበው በቀደመ አቋማቸው ማለትም “ወደ አገር ቤት ገብተው በጡረታ፣ በአንድ ሥፍራ ይቀመጡ” በሚለው እንደጸኑ በትናንትናው ስብሰባቸው አስረግጠዋል ተብሏል፡፡

ምልዐተ  ጉባኤ  በተጠራበት  በትናንት ውሎ  ስብሰባ  ከሰሜን  አሜሪካ  የተመለሱ  ልዑካን  የተጓዙበትን  የሰላም  ጉዞ  በተመለከተ ለጉባኤው አሰምተዋል፡፡ በመቀጠልም በዕርቀ ሰላሙ ዙሪያ በሰፊው ተወያይተዋል፡፡ በዕለቱ አንዳንድ አባቶች በአጽንዖት እንዳሳሰቡት ዕርቀ ሰላሙን ወደ ኋላ አድርጎ ወደ ምርጫ መሔድ በተለይ በውጭው ዓለም የሚገኙ አያሌ ምእመናንን መበተን ነው፡፡ ስለዚህ ከምርጫ በፊት ዕርቀ ሰላም መቅደም አለበት ብለዋል፡፡ በአብዛኛው የቅዱስ  ሲኖዶስ አባላት ዕርቀ ሰላሙ መቀጠል አለበት በሚለው ሲስማሙ እንዴት ይቀጥል የሚለው ግን አነጋጋሪ ሆኖ  ውሏል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በፊትም በነበረው አቋም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ መመለሳቸውንና ወደ አገር ቤት  መግባታቸው ላይ እንደሚስማማ ገልጦ ነገር ግን ተመልሰው በመንበራቸው ይቀመጡ የሚለውን እንደማይቀበለው  መግለጹ ይታወሳል፡፡ በሰኞው የስብሰባ ውሎ በአብዛኛዎቹ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተንፀባረቀው ይኸው ሐሳብ ነው፡፡ ፓትርያርኩ  መመለስ  ይችላሉ፤ በውጭው ሲኖዶስ አማካይነት ለጵጵስና ማዕረግ የበቁ አባቶችም ወደ አገር ቤት  ተመልሰው  መምረጥም ሆነ መመረጥ በሚችሉት ሁኔታ የአገር ቤቱን  ቅዱስ  ሲኖዶስ  የመቀላቀል መብት  አላቸው፡፡ ከዚህ  ባለፈ ግን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ከነሥልጣናቸው ገብተው በፕትርክናው  መንበር ይቀጥሉ የሚለውን  መቀበል ግን በፍጹም የማይሆን ነው በማለት ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡

አንዳንድ አባቶች ከዚህ ጋር በተያያዘ ሲናገሩ “ዕርቀ ሰላሙ የተጀመረው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ  ከማረፋቸው  በፊት ነው፡፡ ያን ጊዜ  ዕርቀ ሰላሙ ጉዞ ተሳክቶ ቢሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ እና   በወደዱት ቦታ በክብር  እንዲቀመጡ ነበር ጥሪ ያስተላለፍነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሁለቱም ፓትርያርኮች ቤተ ክርስቲያኒቱን በአንድ ወንበር እንዲመሩ አልነበረም ሐሳባችን፡፡ ዛሬም ቢሆን  ብፁዕ   ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቢያርፉም  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋ ተመሳሳይ ነው” ብለዋል፡፡ አራተኛው ፓትርያርክ “ከነሥልጣናቸው ይግቡ የሚለውንና በውጭው ሲኖዶስ አባቶች የቀረበውን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ መቀበል ላለፉት ሃያ ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችን በሙሉ እንዳልተሠሩ ማድረግ ነው” የሚል አስተያትም  በተደጋጋሚ ሰንዝረዋል፡፡

በመጨረሻም ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም የሚለውን ሐሳብ  በመያዝ  በዛሬው እለት ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ  በድጋሚ  ተሰብስበው  በውጭ ላለው ሲኖዶስ አባቶች ጥሪ  ስለማቅረብና እና የጀመሩትን ውይይት ለመቋጨት በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ  ለመወያየት  በቀጠሮ ተለያይተዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የውጭው ሲኖዶስ አባላትን ወደ አገር ቤት እንዲገቡና  በአንድነት  እንዲያገለግሉ ጥሪ ለማስተላለፍ ለሰላሙ ያለው መንፈስ ከፍተኛ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ጥያቄ የሆነውና አባቶችን በሰፊው ያወያየው እንዴት ባለ መልኩ ይግቡ የሚለው ነበር፡፡    
         
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)