January 15, 2013

የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ልኡካን ለሰጡት መግለጫ ከሰላምና አንድነት ጉባኤው የተሰጠ ማብራሪያ


 “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን”

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ያወጣውን መግለጫ አስመልክቶ ከአዲስ አበባ የመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ልኡካን ለሰጡት መግለጫ ከሰላምና አንድነት ጉባኤው የተሰጠ ማብራሪያ
 ጥር 3 ቀን 2005 ዓ/ም (January 11/2013)
READ THIS FILE IN PDF
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ታኅሣሥ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫውን እንዲያወጣ ያስገደደው ዋነኘው ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለዕርቀ ሰላሙ ድርድር የላካቸው የሰላም ልዑካን ሳይመለሱና በዳላስ፤ ቴክሳስ የተደረገውን የሦስተኛው ዙር የዕርቀ ሰላም ውይይት ሪፓርት ሳያቀርቡ በአዲስ አበባ በኩል ስድስተኛ ፓትርያርክ ለመምረጥ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ በመሰማቱ እንደነበር ይታወቃል።


በመሠረቱ የሰላምና አንድነት ጉባኤ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከወዲሁ በማሰብ በጥቅምት ወር በተካሔደው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስለ ፓትርያርክ የምርጫ ሕግ ረቂቅ አስመልክቶ ውይይት ስለሚደረግበትና አስመራጭ ኮሚቴ ስለሚሰየምበት ሁኔታ ለኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ  ስብሰባ እንደተጠራ በኢትዮጵያ ያሉት አባቶቻችን በሰጡት መግለጫ ላይ ባየ ጊዜ ጉዳዩ አሳስቦት ወዲያውኑ ሁኔታውን ደብዳቤ ጠይቆ ነበር። ይኸውም ጥቅምት 28 ቀን 2005 ዓ.ም (Nov. 6/2012) በቁጥር 066///2012 በተጻፈ ደብዳቤያችን ላይ 3ኛው የዕርቀ ሰላም ንግግር የሚጠናቀቀው ገና ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በመሆኑ የሰላሙ ሒደት ቅድሚያ ተሰጥቶት ከአንድ ደረጃ ላይ ሳይደርስ በስድስተኛው ፓትርያርክ ሢመት ዙሪያ የሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ለሰላሙ እንቅፋት እንዳይሆኑ በማሳሰብ ጥያቄያችንን ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርበን ነበር።

ይሁንና የፈራነው ነገር አልቀረም። ይኸውም ልዑካኑ ወደ አዲስ አበባ ሳይመለሱ አስመራጭ ኮሚቴ በመሰየሙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት በከፍተኛ ጉጉት የሚናፍቀውን ሕዝበ ክርስቲያንና ለዚህም ስኬታማነት በእጅጉ የሚደክሙትን የሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት በእጅጉ አስደንግጧል። በመሠረቱ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ያሳሰበው እኛን የሰላምና አንድነት ጉባኤውን አባላት ብቻ አልነበረም። ይልቁንም ከኢትዮጵያ የመጡት የሰላም ልዑካን በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳሳ አማካይነት በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ይህ ዓይነቱ አድራጎት “ይሆናል ብለን አናምንም፤ ሆኖ ከተገኘ ግን በጣም እንቃወመዋለን” ማለታቸውን ስንሰማ ከዚህም ጋር ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በተመሳሳይ መልኩ በጥቅምቱ ሲኖዶስ ላይ የተወሳውፓትርያርክ የምርጫ ሕግ ታይቶ ስለሚጸድቅበት ሁኔታ እንጂ ስለ ስድስተኛ ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየም አስመልክቶ ውሳኔ አለመሰጠቱን አውስተው አሁንም ቅዱስ ሲኖዶስ ሁኔታውን እንደገና በማጤን ሊመለከተው እንደሚገባ ሲገልጹ የሰላሙ በር እንዳልተዘጋ ተገንዝበናል ስለሆነም ብዙ የተደከመበትንና በመልካም ሒደት ላይ የሚገኘውን ሰላም በር እንዳይዘጋበት በመስጋቱ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ኃዘኑንና ስጋቱን ለመግለጽ መግለጫ ለማውጣት ተገዷል።

በመሠረቱ የሰላምና አንድነት ጉባኤ መግለጫ ከማውጣቱ በፊት በአዲስ አባባ በኩል የተከሰተውን ሁኔታ በተመለከተ ለማጣራት ከኢትዮጵያ የመጡትን የቅዱስ ሲኖዶስ ልዑካን ለማነጋገር ሞክሮ ነበር። ይልቁንም በልዑካኑ ጸሐፊ በንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በኩል ጥያቄ አቅርቦ ለጥያቄው ተገቢውን መልስ ባለማግኘቱና የጉዳዩንም አሳሳቢነት በመገንዘብ ለሃያ አንድ ዓመታት የቆየው የቤተ ክርስቲያናችን ችግር በውይይት ከመፈታቱ በፊት ለሰላሙ እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውም ነገሮች እንዳይደረጉ ለመጠየቅና ለማሳሰብ ጉባኤው ተስማምቶ መግለጫ አውጥቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከኢትዮጵያ የመጡት ልዑካን ታኅሣስ 13 ቀን 2005 ዓ.ም በተጻፈ መግለጫ የሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላትን ወቅሰውና ተችተው አግባብነት የሌለው መግለጫ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለተነሣበት የሰላም አጀንዳ ቅድሚያ በመስጠት በሦስተኛው ዙር የዕርቀ ሰላም ንግግር ወቅት ከልዑካኑ በቀረበለት ጥያቄና ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በተሰጠው መመሪያ መሠረት በዳላስ፤ ቴክሳስ የተካሔደውን የዕርቀ ሰላም ውይይት አጠቃላይ ገጽታ ለማስረዳትና በተያያዘ መልኩ ጉባኤው በቅርቡ ያወጣውን ወቅታዊ መግለጫና በአንጻሩ ደግሞ ከኢትዮጵያ ልዑካን የተሰጠውን የአጸፋ መግለጫ ለማብራራት፤ እንዲሁም ስለ ዓራተኛው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ቅድመ ዝግጅትም አስፈላጊ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና ተገቢውን የማግባባት ሥራዎች ለመሥራት ሁለት ልዑካንን ማለትም ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁንና መምህር አንዱዓለም ዳግማዊን በአንድ ድምፅ ሰይሞ ልኳል።

ይሁን እንጂ ልዑካኑ ዐቃቤ መንበሩም ሆኑ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊና የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሳያውቁ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ግቢ እንዳይገቡ ከመደረጉም በላይ የጉባኤው ልዑክ የሆኑት ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ፍጹም ሰላማዊ ሰው መሆናቸው እየታወቀ፣ የሰላምና አንድነት ጉባኤ ልዑክ ሆነው በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለሱ መቆየታቸው ግልጽ ሆኖ ሳለ ባልታወቀ ምክንያት በቦሌ ኢሚግሬሽን ባለ ሥልጣን አስቸኳይ የስልክ ጥሪ አማካይነት ተልዕኳቸውን ሳይፈጽሙ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ተገደው ከአገር እንዲወጡ መደረጉና ሌላው ልዑክ መምህር አንዱዓለም ዳግማዊም በደረሰባቸው መጉላላት የሰላምና አንድነት ጉባኤው በእጅጉ አዝኗል። ይህ ጉዳይ በመላው ዓለም የሚገኙ ካህናትንና ምእመናንንም በእጅጉ አሳዝኗል። ይህ በዚህ እንዳለ መምህር አንዱዓለም ዳግማዊ ወደ አሜሪካ በተመለሱ ማግሥት በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ ወረቀት በትነዋል በሚል በሐሰት የተቀናበረ ጽሑፍ በማዘጋጀት መልካም ስማቸውን የሚያጎድፍና የሰላም ተልዕኳቸውን የሚያደናቅፍ ፍጹም አሳፋሪና ኢ-ክርስቲያናዊ ድርጊት መከናወኑንም የሰላምና አንድነት ጉባኤው በቅርቡ ለመረዳት ችሏል።  ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር በቀላሉ ሊያልፈው የማይገባ በመሆኑ ሁኔታውንም በቅርብ ተከታትሎ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው  ይደረግ ዘንድ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰላምና አንድነት ጉባኤ ይጠይቃል

በዚህ አጋጣሚ የሰላምና አንድነት ጉባኤውን ድካምና ያላሰለሰ ጥረት ዋጋ በመስጠት መምህር አንዱዓለም ዳግማዊ ወደ አሜሪካ በሚመለሱበት ዕለት ወደ መንበረ ፓትርያርኩ መጥተው ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተላኩትን መልእክት እንዲያቀርቡና ለጉባኤው መልስ ይዘው እንዲመለሱ ከፍተኛ ትብብር ያደረጉትን ዐቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤልንና የቅዱስ ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን ከልብ ያመሰግናል። እንዲሁም በመልካም ሒደት ላይ ያለውን የዕርቀ ሰላም ጥረት ከፍጻሜ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትንና በማድረግ ላይ የሚገኙትንና የሰላም ልዑካን የሆኑትን ብፁዓን አባቶችና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጉባኤው ልባዊ ምስጋና ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባዔ ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ ነው። ስለሆነም ዋነኛ ግቡ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማየት ነው። አቋሙም በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙትን አባቶች በአክብሮትና በእኩልነት በማየት ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ተግቶ መሥራት ነው። በአንጻሩ ደግሞ ለሰላሙ ሒደት እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውም ነገሮች ሲፈጠሩ  ተገቢውን ማሳሰቢያ ለሚመለከተው አካል በወቅቱ ያቀርባል። ስለዚህም በሰላምና አንድነት ጉባኤው በቅርቡ የተሰጠው ወቅታዊ መግለጫ ለድፍረት ሳይሆን በዕርቀ ሰላሙ ላይ የተፈጠረውን ስጋት በአግባቡ ለመግለጥና ከወዲሁም ለማሳሰብ መሆኑን ሁሉም እንዲገነዘብ ይፈልጋል።

ከላይ እንደገለጥነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ወደ ኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሞ በላካቸው ሁለት ልዑካን አማካይነት የላከው መልእክት ሊደርስ ባለመቻሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ለመላው ካህናትና ምእመናን በያሉበት ስለ ጉባኤው ወቅታዊ መግለጫ ተገቢነትና ሚዛናዊነት ለማስረዳት እንዲሁም ከኢትዮጵያ የመጡት የሰላም ልዑካን አላግባብ ላስተላለፉት መግለጫ ከዚህ በታች የሚከተለውን ማብራሪያ  የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለመስጠት ተገዷል።

1ኛ) የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ነው የሚለውን በተመለከተ

ከኢትዮጵያ የመጡ ልዑካን የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት  የሚጋፋ ነው በማለት ያለአግባብ ተችተዋል። በመሠረቱ የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫ የወጣው የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት ለመዳፈር አይደለም። ለአባቶቻችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ፍጹም ፍቅርና አክብሮት ባይኖረን እኮ የተለያዩትን አባቶች አንድ ለማድረግ ማንም ሳያስገድደን ላለፉት ሦስት ዓመታት ባልደከምንም ነበር። ይልቁንም በቤተ ክርስቲያናችን ያለው ልዩነት ተወግዶ በአንድ መንበር፣ በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የምትመራ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንድትኖር ያላሰለሰ ጥረት የምናደርገውም ለዚህ ነው። ይህንንም ከልዑካኑ የተሻለ የሚረዳ አካል ያለ አይመስለንም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ማንኛውንም የሰላምና አንድነት እንቅፋት ለማስወገድና የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ለማየት በመጓጓት ሁለቱንም አካላት በእኩልነት በማየት ለማገናኘትና ለማስማማት ዘወትር ተግቶ ከመሥራት በቀር ሌላ ዓላማና ተልእኮ የሌለው መሆኑን ለሚመለከተው ሁሉ በአጽንዖት ለመግለጽ እንወዳለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የተዳፈረው የልዑካኑ ጸሐፊ በልዑካኑ ስም ያወጡት መግለጫ ነው። ምክንያቱም 1ኛ) የግል ሐሳባቸውን ብቻ የገለጡበትን መግለጫ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ቅዱስ ሲኖዶስ . . . ያወጣው መግለጫ” በማለት ራሳቸውን በቅዱስ ሲኖዶስ ቦታ ተክተው ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ መግለጫ በማውጣታቸው፤ 2ኛ) ልዑካኑ ወደ ላካቸው አካል ሔደው ሪፓርት ሳያቀርቡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሙሉ ፈቃድና ዕውቅና በሚሠራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ አማካኝነት ለመደራደር ፈቃደኛ እንደማይሆኑ አላግባብ መወሰናቸው፤ 3ኛ) በጋራ መግለጫቸው አክብረው ያመሰገኑትን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በማግሥቱ ቃላቸውን ለውጠው በመተቸታቸው የላካቸውን አካል ቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የተዳፈሩት የልዑካኑ ጸሐፊና መግለጫቸው መሆናቸውን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።

2) የሰላምና አንድነት ጉባኤውን ሚዛናዊ ሥራ በተመለከተ
ልዑካኑ ባወጡት መግለጫ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ሚዛናዊነት የጎደለው ነው በማለት ገልጸዋል፡፡ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ይህን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሥራዬ ብሎ ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ሚዛኑን ጠብቆ የሚሠራና በየጊዜው በሁለቱም አባቶች በኩል ለሚፈጠሩ ማናቸውም የሰላም እንቅፋቶች ተገቢውን መልስ ሲሰጥ የቆየ ነው። ለምሳሌ ያህል በሰሜን አሜሪካ ባሉት አባቶች በኩል ለሰላሙ ሒደት እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውም ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ በአፋጣኝ እያነጋገረ በተደጋጋሚ የማስተካከያ ደብዳቤዎች እንዲጻፉ ማድረጉ በአዲስ አበባ ከሚገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተሰወረ አይደለም። ይህንን በተመለከተ ደግሞ በመግለጫችንም ሳይቀር ጠቅስን የጻፍንበት ጊዜ እንደነበረ ከዚህ በፊት ከወጡት መግለጫዎቻችንና ከፋይሎቻችንም ለመረዳት ይቻላል። በመሠረቱ በሁለቱም ተዳራዳሪዎች በኩል እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል ሲያጋጥም የሰላምና አንድነት ጉባኤው ባለበት ከፍተኛ ኃላፊነት ለሰላሙ ሥምረት ይበጃል ብሎ ያመነበትን የመፍትሔ ሐሳብ እንዲቀበሉ መጠየቅ ከአንድ አደራዳሪ አካል የሚጠበቅ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ጉባኤው ሁልጊዜ ለሚያፈልቃቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ደግሞ ማዕከል የሚያደርገው ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ነው። ምናልባትም የሰላምና አንድነት ጉባኤው የሚሠራው የሽምግልና ሥራ በመሆኑ ሁሉንም  ላያስደስት ይችላል። ስለሆነም ሁለቱም ወገኖች የማዳላት ሥራ ተሠራብን ብሎ ከመናገር ነጻ ይሆናሉ ለማለትም አስቸጋሪ ነው። ጉዳዩን በእውነት መነጽር ለሚያየው ግን የማዳላት ሥራ ሠርቶ ችግርን በጋራ በመፍታት እውነትን ሰላምንና ፍቅርን ለማምጣት የሚያስብ አካል ይኖራል ብሎ ማመን የዋሕነት ነው። የሰላምና አንድነት ጉባኤው ዋነኛ ዓላማና አቋም ለሰላሙ ሥምረት ተገቢውን ጥረት በማድረግ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ መሥራት በመሆኑ ከዚህ በፊት ባደረግናቸው ሦስት ጉባኤያት የሰላምና አንድነት ጉባኤውን ጥረት ከማድነቅ ያለፈ ነገር በቃልም ይሁን በጽሑፍ ከሁለቱም አካላት የደረሰብን ትችት ወይም አስተያይት እስካሁን ድረስ አለመኖሩን ለመግለጽ እንወዳለን።

3ኛ) የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫ አሳሳች ትርጉም ይሰጣል የተባለውን በተመለከተ
ከአዲስ አበባ በመጡት ልዑካን ስም በወጣው መግለጫ ላይ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ያወጣው መግለጫአሳሳች ትርጉም ለመስጠት ነውተብሎ ተተችቷል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አባባል በፍጹም ከእውነት የራቀ ተራ ግምት ነው። በመሠረቱ ይህ ሐሳብ የተሰነዘረው በልኡካኑ የጋራ መግለጫ ተራ ቁጥር 4 ላይ የተወሳውን አቋም አብራርተን በመጻፋችን ይመስላል። ይኸውም በሁለቱም አካላት ዘንድ ማለትም  በውጭ ባሉ አባቶች በኩል ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት፤ በኢትዮጵያ ባሉት አባቶች በኩል ደግሞ የስድስተኛ ሢመተ ፓትርያርክ ከሰላሙ በፊት እንዳይደረግ በጋራ ተስማምተው ያንን የሚወክል ቃል በጋራ ባወጡት መግለጫ ተራ ቁጥር 4 ላይ ያለውን መርጠው “ሰላሙ ለፍጻሜ እስከሚደርስ ድረስ በሁለታችንም በኩል ለሰላሙ መሰናክል የሚሆኑ ማናቸውንም ሥራዎች ከመሥራት ተቆጥበን በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናልሲሉ ተስማምተዋል። ይህንም በጉባኤው ላይ ምን ማለታቸው እንደሆነ ሁለቱም የሰላም ልዑካን በሰፊው የተነጋገሩበት ሲሆን በመግለጫችን የተወሳው እውነት መሆኑን ለመረዳት ካለን የድምጽ  መረጃዎች  በቀላሉ ማረጋገጥ  ይቻላል። የሰላምና አንድነት ጉባኤውም 3ኛው ጉባኤ አበው እንደተጠናቀቀ ኅዳር 30 ቀን 2005 . ባወጣው መግለጫ ላይ ይህንኑ መሠረተ ሐሳብ አብራርቶ ማውጣቱ ይታወሳል። ለተጨማሪ መረጃ የጉባኤውን ድረ ገጽ ይመልከቱ። http://eotc-peace-and-unity.blogspot.com

4ኛ) የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫ ሰላሙን ለማደናቀፍ ነው የሚለውን በተመለከተ
ከአዲስ አበባ የመጡት ልዑካን መግለጫ ጸሐፊ የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫውን ያወጣው ሰላሙን ለማደናቀፍ ነው ሲሉ ጉባኤውን ወቅሰዋል። ይሁን እንጂ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲል ያለ አንዳች ዕረፍት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ባለው ዕውቀት፤ ጊዜና ገንዘብ ተጠቅሞ ላለፉት ሦስት ዓመታት የደከመበትንና ዓላማዬ ብሎ የያዘውን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለማደናቀፍ ማናቸውንም ነገር እንደማያደርግ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ሐቅ ነው፡፡ሰላሙን ለማደናቀፍ ነውበማለት የሰላምና የአንድነት ጉባኤውን የወቀሱበት ምክንያት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ በአጽንኦት ልንገልጽ እንወዳለን። ምክንያቱም ልዑካኑ ለሦስተኛ ዙር በዳላስ፤ ቴክሳስ በተደረገው ጉባኤ አበው መጨረሻ ላይ በጋራ ባወጡት መግለጫ በተራ ቁጥር 5 ላይ “ይህን መሠረታዊና ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ከልብ እናመሰግናለንብለው በአንድ ቃል ያመሰገኑትን ጉባኤ በአጭር ጊዜ  ውስጥ ቃላቸውን እንዲለውጡና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት በብዙ ድካም ላይ የሚገኘውን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የሌለውን ስም መስጠትና መንቀፍ ለምን እንዳስፈለገ ምሥጢሩ አልገባንም። በዚህም ምን አንድምታ ለመስጠት እንደታሰበም ግልጽ አይደለም። በመሆኑም እውነታውን ለአንባብያን ኅሊና፣ ለታሪክና  ለጊዜ ከመሥጠት ያለፈ ለዚህ ሰፊ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ባለመሆኑ በዚሁ እናልፈዋለን። ይሁን እንጂ በሦስተኛው ዙር የዕርቀ ሰላም ውይይት ላይ በተደረሰው ተስፋ ሰጭ የሰላም ሒደት ደስ ያልተሰኙትን አካላት ለማስደሰትና በምክንያት ቤተ ክርስቲያንን በልዩነት እንድትቀጥል ለማድረግ ምክንያት ተፈልጎ እንዳይሆን አሁንም ጉባኤው ያለውን ከፍተኛ ሥጋት ለመግለጽ ይወዳል።

5ኛ) በሦስተኛው ዙር ጉባኤ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ያቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ በተመለከተ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦችን እያፈለቀ ለሁለቱም አካላት ሲያቀርብ ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት ሳሉ ለቤተ ክርስቲያን መለያየት ትልቁ ፈተና በአንድ ዘመን በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ምክንያት ሁለት ፓትርያርኮች መኖራቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ሁለቱም አባቶች በሕይወት ባሉበት ዘመን ቤተ ክርስቲያን ምን ብታደርግ ሰላምን ልታገኝ እንደምትችል የተጠና ባለ ሰባት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለሁለቱም አካላት አቅርቦ ነበር። ቅዱስ ሲኖዶስ በቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ተወያይቶ ተገቢውን ውሳኔ ሳይሰጥበት ቅዱስነታቸው ስላረፉ ጉባኤው ከአሁኑ የቤተ ክርስቲያናችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚገናዘብና ሁለቱንም ይበልጥ ሊያቀራርብና ሊያስማማ የሚችል ወቅቱን ያገናዘበ አዲስ የመፍትሔ ሐሳብ በማጥናትና በማፍለቅ በዳላስ በተደረገው ስብሰባ ላይ  ባለ አራት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረቡ ይታወሳል። ይህ የመፍትሔ ሐሳብ በጥር ወር 2005 ዓ.ም በሎስ አንጀለስ፤ ካሊፎርኒያ ከሚካሔደው አራተኛው ዙር የዕርቀ ሰላም ውይይት በፊት በሁለቱም አካላት በኩል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአስቸኳይ ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያገኝ ተልኳል። እንደሚታወቀው የመፍትሔ ሐሳቡ ዝርዝር በዳላሱ ጉባኤ በልዑካኑ ፊት በንባብ መሰማቱን በመግለጫችን ላይ አትተን ጽፈናል።

ነገር ግን እኛ በአዲስ አበባው ልዑክ መግለጫ ጸሐፊ እንደተባለው በየትኛውም ምክንያት አባቶቻችንን  ለማሳዘን የማይገባ ሥራ አልሠራንም፤ አንሠራምም። ምክንያቱም የምንደክመው የእግዚአብሔር መንግሥት ለሆነቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ነውና። በዚህ አይነት ከባድ ጊዜ በሰላምና አንድነት ጉባኤው ላይ እንዲህ ዓይነቱ ፈታኝ ነገር መሰንዘሩ ካለብን የሥራ ክብደት አንጻር እውነተኛውን ዓላማችንን ከመግለጽና በአኰቴት ከመቀበል ያለፈ ነገር አይኖርም። አሁንም እኛ የምንጮኸው በሁለቱም ወገኖች በኩል ከዕርቀ ሰላሙ የሚቀድም ምንም ነገር እንዳይኖር ነው። ያም ሆነ ይህ የሰላምና አንድነት ጉባኤውን በእጅጉ ያሳሰበውን የሰላም እንቅፋት በማስወገድ ለሰላሙ ስኬታማነት ሁሉም ወገኖች ተገቢውን ሁሉ ካደረጉና ቤተ ክርስቲያንን አንድ ካደረጉ በየትኛውም መንገድ ሰላሙ ይምጣ እንጂ የእኛ መግለጫ ኃይለ ቃል እንቅፋት ሊሆን እንደማይችል እናምናለን። ስለዚህ ከአዲስ አበባ የመጡት ልዑካን በሰላምና አንድነት ጉባኤው ላይ ያለአግባብ ያስተላለፉትን የቅሬታ መግለጫ እንዲያነሡልን በትሕትና እንጠይቃለን። በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶስ ሁኔታውን በስፋት ተመልክቶ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ጥረት ለሠመረ ውጤት እንዲበቃ ያደርግ ዘንድ በአክብሮት እየጠየቅን፦

1)      ሰላሙንም ለማሰናከል ለሚፈልጉ ክፍሎች ይህ ለሰላሙ ሒደት እንቅፋት እንደ ዋና ምክንያት ተደርጎ  እንዳይቆጠር፤

2)    የጉባኤው መግለጫ የቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት እንቅፋት እንዳያጋጥመው የድርሻችንን  ለመወጣት በመሆኑ አሁንም በልዑካኑ የጋራ መግለጫ ላይ “ሰላሙ ለፍጻሜ እስከሚደርስ ድረስ በሁለታችንም በኩል ለሰላሙ መሰናክል የሚሆኑ ማናቸውንም ሥራዎች ከመሥራት ተቆጥበን በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናል” ብለው ልዑካኑ የገቡትን ቃል በማክበርና በማስከበር ከምንም በላይ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ያስቀደመ ሥራ እንዲሠራ ለማድረግ በሁለቱም በኩል ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤

3)    የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ካለን ልባዊ ፍላጎትና ፍጹም ቅንነት አንጻር በመልካም ሒደት ላይ የሚገኘው ሰላም እንቅፋት እንዳያጋጥመው በማሰብ የተሰጠ ማሳሰቢያ መሆኑ እንዲታወቅልን እየገለጥን ከላይ ከተራ ቁጥር 1-5 ከተዘረዘሩትና ከአዲስ አበባ የመጡት ልዑካን ባወጡት መግለጫቸው ካቀረቧቸው ወቀሳዎችና ትችቶች የሰላምና አንድነት ጉባኤው ፍጹም ነጻ መሆኑን በአጽንዖት እንገልጻለን።

4)    በዳላስ፤ ቴክሳስ በተካሔደው ሦስተኛው ዙር የዕርቀ ሰላም ንግግር ላይ በልዑካኑ በተደረሰው የጋራ ስምምነት መሠረት ለዕርቀ ሰላሙ ሥምረት ይበጃሉ ተብለው በሰላምና አንድነት ጉባኤው የቀረቡትን ባለ አራት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት እንዲነጋገርባቸውና እንዲመክርባቸው እንዲደረግና እስካሁን ድረስ ቀደምነት ባላቸው ብፁዓን አባቶች ብቻ የተዋቀረው የሰላም ልዑክ ከልዩነት በኋላ ከተሾሙት አባቶች ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ታክለውበት በአራተኛው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ በተጠቀሰው ቀንና ቦታ እንዲገኙ እንዲደረግልን በትሕትና እንጠይቃለን።

5)     በመጨረሻም የሰላምና አንድነት ጉባኤ ወቅታዊውን ሁኔታ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ የዕርቀ ሰላሙን የሠመረ ውጤት ለማየት ካለው ቅን ፍላጎትና ጉጉት አንጻር እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት ለመዳፈር አለመሆኑን እየገለጽን ማንኛውንም እንቅስቃሴያችንን በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠንን ተገቢውን መመሪያና ምክር ለመቀበል ዝግጁዎች መሆናችንን በትሕትና እንገልጻለን።

“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ።”

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ።

3 comments:

Unknown said...

Thanks for the clarification of some of the important things.

I believe there are some people behind all this peace and unification. Please you guys continue with what you currently doing. But it should not have taken you this long to write such letter. Atleast you have done it now, always never been late.

May GOD be with us, Amen!!!

Anonymous said...

አሁንም መግለጫው "ገርነት"፤ ቅንነትና እውነታን የያዘ አይመስለኝም። "እኔ ትክክል እነሱ ግን አይደሉም።" "የእኔ መግለጫ እንጂ የእነሱ ስህተት ነው"፤ "እመኑኝ እኔ እያደረኩት የነበረውና እያደረኩት ያለሁትም ..." ...

ሲኖዶሱ/ ተወካዮቹ በሰላም ጉባኤ ላይ የትችት መቅለጫ ሲያወጡ ይህ የመጀመሪያ አይደለም። ባልልሳሳት ከዚህ ቀደምም በሶስት ወም በአራት ገጽ ተተችተው እንደነበር ደጀ ሰላም አስነብቦን ነበር።

ቀድሞም እንዳልኩት የሰላሙ ጉባኤተኞች፤ አቅምም ፤ ልምድም፤"ሽምግልና" የተቸሩ አልመሰለኝም። ለምሳሌ በሌላ ሀገር ስለተደረጉት መግባባቶች ብዙም ባላቅ በዳላስ ባለሁበት መንደር ግን የተደገው በአባቶች መሃል "የናፍቆት መወጣጫ" እንደነበረ የአደባባይ ሚስጥር ነው። -- ከሀገር ቤት የመጡት አንዲት ቀጭን መልእክት (አግባብተውም ሆነ ለምነው ፓትሪያርኩ እንዲገቡ ማድረግ)፤ እዚህ ያሉትም ሌላ ተመሳሳይ ("ወይ መንበር እልያም..")። አቡነ መልከ ጼዲቅ በኢሳት"ትኩረት" ያስደመጡንም ይህንኑ ነው።

ነገሩ አሁንም ስላልዘገየ፤ የተነካካው የሰላም ጉባኤ ወርዶ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኗ ተቆርቋሪዎች ካልሆነም እራሳቸው አባቶች በአቸቸው ችግሩን ይፍቱት።

ወ/ኤ ዳላስ-ቴክሳስ

Anonymous said...

«ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው» እንዲሉ ከዚህ በላይ አስተያየት የሰጡት ሰዎች የሰጡት አስተያየት ትክክል አይመስለኝም። ጭፍን ጥላቻ በሰላም ጉባኤው ላይ ያላቸው ናቸው። እነሱስ አረረም መረረም የእነሱን ድርሻ የተወጡ ይመስለኛል። እስኪ እናንተ ደግሞ ሞክሩት፤ እውነት ለመናገር አባቶች ናቸው ሰላምን ያልረጓት። እነ ንቡረ እድ ኤልያስ ለኢያዲግ ያሳዩትን ታማኝነት ያክል ለቤ/ክና ለጌታ ቢያሳዩ ሰላምን በአደባባይ በአባቶች ጉባy መካካል ባልሰቀሏትም ነበር። ምን ይጠቀሙ ይሆን፤ የቤ/ክ አምላክ በእውነት ይፍረድ።

ዘኢየሱስ ሞዓ ከደሴ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)