January 24, 2013

ሁሉም “የማንም አሿሿሚ አልሆንም! የሥልጣን ጥመኞችንም አላገለግልም!” ቢል


(መልዕክተ ተዋሕዶ - ዘሮኪ በተለይ ለደጀ ሰላም እንደጻፉት/ PDF)፦ ደጀ ሰላማውያን እንደምን ሰነበታችሁ? ብዬ መጠየቅ፥ ዛሬ አልፈለኩም። እንዴት እንደሰነበትን፥ ሁላችንም እናውቀዋለንና። ለመላው የቤተ ክርስቲያን  ልጆች እያሳለፍነው ያለው ሳምንት የሐዘንና፥ ተስፋችንን አጨላሚ፥ ሆኖ ነው የሰነበተው። ይህ ሳምንት፥ ለሃያ አንድ ዓመታት ፥ መከፋፈል በተባለ በሽታ ፥ ታማ የነበረችው እናት ቤተ ክርስቲያን  ፥ ስትሰቃይ ኖራ ፥ ያረፈችበት ሳምንት ነው።  ነገር ግን አጥብቀን ከቀድሞው አብዝተን ከጮህን፥ ልክ በወንጌሉ እንደተጻፈው የሞተውን የሚያስነሳው ትንሣኤና ሕይወት የሆነ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ እስትንፋሷን ሊመልሰው ይቻለዋል። በእምነታችንም ጸንተን እያንዳንዳችን ማድረግ ያለብንን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንበል፤ በማለት ሰሞኑን አእምሮዬን ሲሞግቱኝ ወደ ከረሙት ጉዳዮች ተራ በተራ ልግባ።


መጀመሪያ በአሁኑ ወቅት ከበሽታቸው ጋር እየታገሉ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስና ሌሎችም በአጠቃላይ፥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሰጣችሁን፥ ከባድ አደራ በመወጣት ላይ ለሚገኙ አባቶቻችን፥ ለእናንተ ያለን ፍቅርና አክብሮት እጅግ የላቀ መሆኑን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። ያሳያችሁት ጽኑዕ አቋም ብዙዎቻችን ጨርሰን ተስፋ እንዳንቆርጥ ረድቶናል። እያደረጋችሁት ያለውን ጥረትና ተጋድሎም፥ በእኛ በልጆቻችሁ ልቡና ለዘላለሙ ተቀርጾ በሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር ይረዳናል። ዋጋችሁም በማይጠፋው መዝገብ ተመዝግቦ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ እንደምትቀበሉም ሙሉ እምነታችን ነው። ይህ ስሜት የብቻዬ ስላልሆነ ጉዳይ በሚመለከተን የቤተ ክርስቲያን  ልጆች ስምም፥ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።

ከሁሉ ያስደነቀኝ ደግሞ የብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ቆራጥ አቋም ነው። “የማንም አሿሿሚ አልሆንም! የሥልጣን ጥመኞችንም አላገለግልም!” ማለታቸው። ለዚህ የማመስገኛ ቃላት ያጥረኛል። ቤተ ክርስቲያን  ውለታዎንና ተጋድሎዎን መቼም አትረሳውም። ምናለበት፥ እንደርስዎ ሌሎቹም አባቶች ተከትለዎት ቢወጡ ኖሮ ፥ አሰኝቶኛል።  አንዳንዴ እንዲህ ያለ አቋም ቁጭ ብሎ ትርጉም የሌለው ንትርክ ከመነታረክ፥ አስር እጥፍ ይሻላል።  ብፁዓን አባቶቼ፥ መቼም መሣሪያ ደቅነው ከያዙ ጨካኞች ጋር እንደምትጋፈጡ ይገባኛል፥ ነገርግን ቢያንስ የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ፥ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል  ሲወጡ፥ ሌሎቻችሁም ብትከተሉና ፤በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አባቶቻችን በዕርቁ ጉዳይ ሳይስማሙ ተለያዩ ፤ ተብሎ ቢነገረን፥  ይሻል ነበር ብዬ አስባለሁ።

ለነገሩ አሁንም ቢሆን፥ ያለቀ የደቀቀ ነገር ስላልሆነ፥ ከዚህም በኋላ እነሱ በሚያደርጉት ማንኛውም የመሿሿሚያ ስብሰባዎች ራሳችሁን ብትለዩ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ።  አባቶቼ ዝምታም እኮ ተቃውሞ ነው፤  እነ አባ አብርሃምና አባ ሳሙኤል እርስስ በርሳቸው ይሿሿሙ፥ ይሰብሰቡ፥ ነገ እግዚአብሔር ፍርዱን ይሰጣል። ብፁዓን አባቶቻችን ፥ ከቻላችሁ በአቋማችሁ የምትስማሙት አንድ ላይ በመሆን ተቃውሞአችሁን ቀጥሉ፥ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማወቅ ባለበት መጠን አሳውቁ። በመንግሥት አይዞአችሁ ባይነት እየተንቀሳቀሱ ያሉት አባቶች፥ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኝ እረኞች ስለሆኑ እና በሥልጣን ጥመኝነትና በጥላቻ ስለሰከሩ፤ ከዚህ በፊት ለመጠቆም እንደሞከርኩት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከማስፈጸም፥ ወደ ኋላ አይመለሱም። ብፁዓን አባቶች፤ ውሃ ሽቅብ እንደማይፈስ አውቃለሁ። ነገር ግን ሁላችሁም ከእግዚአብሔር ያገኛችሁት ትልቅ መንፈሳዊ ሀብት በእጃችሁ አለ። አስፈላጊውን ማሳሰቢያ ከሰጣችሁ በኋላ፥ በእንቢታቸው ጸንተው፥ የእነ ዓባይ ጸሐዬን ጠመንጃ ተመክተው፥ እንመርጣለን ብለው ከተነሱም፥ በመጨረሻውን ውሳኔ ስጡ! ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ በእጃችሁ ትገኛለችና!

ሁለተኛ፦ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እና ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እባካችሁን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን የወደፊት ህልውናና ስለ እኛ ስለ ተበተንነው ልጆቻችሁ ስትሉ በተደጋጋሚ ያሳያችሁትን ትዕግስት አሁንም ቀጥሉ። ቢያንስ ቢያንስ እነ አባ እንትና በስልጣን ጥመኝነት አእዕምሮአቸውን አጥተው እስኪለይላቸው ድረስ ሕዝቡን የሚያጽናና፣ የሚያረጋጋና አንድነቱን የሚያጠናክርበትን መንገድ በማሳየት በጎቻችሁን በመልካምና በለምለም ሣር ላይ አሰማሩ። እንዲህ ከሆነ ይህን፥ ወይም ያንን፥ እናደርጋለን ከማለት ከእልኸኝነት የሚመነጭ ውሳኔ ተቆጠቡ።

ሦስተኛ፦ የሰላምና አንድነት ኮሚቴም እስከ አሁን ድረስ የደከማችሁትን ድካም ልጆቻችሁ የሆንን ሁሉ እንረዳለን። እግዚአብሔር በሰማያት ዋጋችሁን እንዲከፍላችሁ ጸሎቴ ነው። ከዚህ በኋላ ፥ ያጋጠማችሁን ፈተናና ሰላም እና አንድነቱን ለማምጣት ስትሉ ከመናገር የተቆጠባችሁትን ሁሉ የመግለጽ ኃላፊነት ይጠበቅባችኋል። በአንድነት ምዕመናኑን በመምራት ፥ ለሰላም ይበጃል የምትሉትን ሁሉ ሃሳብ ከመስጠት አትቆጠቡ። አቅማችሁ በቻለ መጠን ከሁለቱም ወገን ይህ መከፋፈል ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ሞክሩ።

አራተኛ፦ለማኅበረ ቅዱሳን አንድ ግልጽ መልዕክት አለኝ። ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመበት ጀምሮ ትኩረቱን በቤተ ክርስቲያን  ብቻ ላይ በማድረግ፤ ከፖለቲካ ነጻ በሆነ መንገድ፥ ስብከተ ወንጌል በማስፋፋት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃንና ከተሐድሶያዊያን በመታደግ፣ አዲሱን ትውልድ ለቤተ ክርስቲያን  የሚገደውና የሚቆረቆር አድርጎ በመቅረጽ ጊዜ የማይሽረው ትልቅ አሻራ ጥሏል። ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን  በምትፈልገው ቦታ ሁሉ ስድብን፣ መታሰርን፣ መጉላላትንና ሌሎች በዚህች ጹሑፍ ዘርዝሬ ልገልጻቸው የማልችላቸውን ፈተናዎች ታግሶ፥ በአዲሱ ትውልድ ላይ፥  በእግዚአብሔር ቸርነት፥ ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆንም በቅቷል። ይህን ሁሉ መከራና ዋጋ የተከፈለላት ቤተ ክርስቲያንና ልጆቿ ያለ መሪ ሲቅበዘበዙ፥ ብፁዓን አባቶቻችን በህቡዕ ሣይሆን በግልጽ ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው፥ ምንም እንዳልተፈጸመ ዝምታችሁ ሊገባኝ አልቻለም።

ቤተ ክርስቲያን  ስትከፈል ደጆቿ ሲዘጉ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት እንዳይዘጋ የምታደርጓቸው ጥንቃቄዎችም አሳዝኖኛል!! ለቤተ ክርስቲያን  የመከራ ቀን ድምጹን አሰምቶ እኛ አለንልሽ ቤተ ክርስቲያን  ካላለ፥ የዚህ ማኅበር ፋይዳው ምንድን ነው? እኔ በበኩሌ ይህ ማኅበር፥ በሰላሙ ሰዓት ብቻ ለስብከተ ወንጌል የሚሯሯጡ ሰባኪያንን ብቻ ሳይሆን፥ በዓላውያን መንግሥታት ፊት አንገታቸውን ለሰይፍ የሰጡትን ሰማዕታትን እነ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚተካ ትውድም የሚያፈራ  አድርጌ እቆጥረው ነበረ።  ከዚህ በላይ ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? አፍቃሬ ማኅበርነት የሚፈለግ ቢሆንም ከሁሉም በላይ አፍቃሬ ቤተ ክርስቲያን  መሆኑን የሚያሳይበት ወቅት አሁን መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ። ለዚህ ወቅታዊ ጥያቄ ምላሽ በአስቸኳይ ያስፈልገዋል!

በመጨረሻም፦ በውጭው ዓለም የምትገኙ የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ልጆች በየቤተ ክርስቲያናችሁ በዚህ ጉዳይ ተሰባስባችሁ አቋማችሁን ዛሬም ለመግለጽ ዛሬም ጊዜ አላችሁ። ከሕሊና ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት ይሻላል። ብዙ አደር ባዮች በበዙበት ዘመን እውነትን ለመናገር ዳተኛ መሆን ከክርስቲያን አይጠበቅም። የፈለገው ይሾም ስም ለመጥራት ዝግጁ ነን፥ ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም ፤ወለም ዘለም አንልም የሚባል ዜማ እያዜሙ የመንግሥትን ሹመኞች እንድንቀበል መድረኩን የሚያዘጋጁ ካህናትና ምዕመናን እየተስተዋሉ ነው። በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ነው የሚባለው ሲኖዶስ ይኼ ነው ወይ? ብፁዕዓን አባቶቻችንን በገዛ ጽሕፈት ቤታችው እያስፈራራቸው ያለው ግለሰብ፥ አባይ ጸሐዬ፥ መቼ ነው የሲኖዶሱ አባል የሆነው? የሚገርመው እነአባ አብርሃም ፓትርያርኩ ያለ መንግሥት ተጽዕኖ ነው መንበር ጥለው የተሰደዱት ይበሉን? እንደው በእመ አምላክ የመንግሥትን ተጽዕኖ መኖር የሚጠራጠር  ሰው ይኖር ይሆንን? እንኳን የዛሬ ሃያ አንድ ዓመት፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን ሲያሳድዱ  ይቅርና ፤ዛሬ ሰላም ነው ተብሎ በሚለፈፍበት ጊዜ እንኳን አዳር ውሎአቸው ቤተክህነት አይደለምን? እኛ እኮ ከሞትን ቆይተናል። የሚቀብረን ነው ያጣነው።

ይቅርታ ይደረግልኝና በታሪክ የምናውቃቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የድሮዎቹ፤ ወኔ የነበራቸው፥ እንኳን ለቤተ ክርስቲያናቸው ቀርቶ ለሃገራችው ለእናት ኢትዮጵያ ሥጋቸውን ለአሞራ የሚሰጡ ነበሩ። ለዚህ መቼም ጥቅስ ፍለጋ አልደክምም። በአጭሩ ግን፥ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  በር ተዘግቶ የካቶሊክ እምነት በር አይከፈትም በማለት፤ በአጼ ሱስንዮስ ዘመን፥ በአንድ ቀን ብቻ፥ ከመላው ኢትዮጵያ ሰማዕትነት አያምልጥህ እየተባባሉ፤ አስር ሺህ ምዕመናን ጎንደር ላይ ሰማዕትነትን የተቀበሉበትንና የቅዱሱን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ሰማዕትነት ለአንባቢ ማስታወስ ግድ ይለኛል።

እንደው ለመሆኑ ሳናውቀው ጥሩ ጥሩ ነገሮች ላይ ብቻ የሚሳተፍ፥ ሀገር ጎብኚ፥ መረር ያለ ነገር ሲመጣ እነእገሌ ይህን ያድርጉ፤ እኔ የለሁበትም የሚል ትውልድ ሆነን እንቅር? እንዲህ እንዲህ ይሸቱ የነበሩት እንኳን መናፍቃኑ ነበሩ።  እረ ጎበዝ ምን ነካን? እዚህ ላይ ይብቃኝ።

አምላከ ቤተ ክርስቲያን  እባክህ ተመልከተን! እኛ ደክመናል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
መልዕክተ ተዋሕዶ - ዘሮኪ

21 comments:

Bilata said...

በመጀመሪያ ጸሐፊው የጻፉት አጀንዳ የሁላችንም አጀንዳ ነው። ሁላችንም በተደረገው ሁሉ አዝነናል። ስንናንፍቀው የነበረው ቀንም (የሰላም እና የአንድነት) እየራቀ ሄደ። ብቻ ምን ይደረግ... እርሱ ይቅር እስኪለን ድረስ...።

በመቀጠል ግን በጽሑፍዎ ላይ ቁጨት፣ ንዴት፣ ብስጭት ይስተዋላል። እውነት ነው ነገሩ ያስቆጫል። ለማንም መሳቂያ መሳለቂያ ስንሆን። ሰላምን እንሰብካለን እያልን በመካከላችን ሰላም ማድረግ ሲያቅተን። ነገር ግን ክርስቲያን በንዴት በቁጨት በብስጭት እንዲያው አዕምሮ ያፈለቀውን ሁሉ መጻፍ አለበት ብየ አላስብም። እናም እስኪ ካነሷቸው ጉዳዮች አንዳንዶች ላይ እኔም ሐሳቤን ልስጥ።
እውነት ነው ሁሉም አባቶች አንድ ሀሳብ አንድ ልብ ሆነው ምዕመኑ የሚፈልገውን ሰላም እና እርቅ ቢያስቀድሙ መልካም ነበር። ግን አልሆነም። አንዳንዶች አባቶች ተቃዎሟቸውን በግልጽ ያሳዩም እንደአሉ፤ እንዲሁም ወደ ምርጫው ነው መግባት ያለብን ብለው የሚሯሯጡ እንዳሉም ሰምተናል። ሁሉም ወደ እርቁና ሰላሙ ነው መሯሯጥ ያለብን ቢሉ ምንኛ መልካም ነበር።
ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም። መቼም ቢሆን ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ሊመራው አይችልም። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት (እንደ ሰዉነታቸው) ሊሳሳቱ ይችላሉ። ቅዱስ ሲኖዶስ ግን አይሳሳትም። ቅዱስ ሲኖዶስ ይሳሳታል ካልንማ መንፈስ ቅዱስም ይሳሳታል ልንል ነው። ይህ ደግም ፍጹም ውሸት ነው። ታዲያ እርስዎ በጽሑፍዎ "በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ነው የሚባለው ሲኖዶስ ይኼ ነው ወይ?" ያሉት ትክክል አይደለም። እንዳሉት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሳሳት ከሆነማ እስከ አሁን ድረስ የሚያውጣቸው ዶግማዎች፣ ቀኖናዎች፣ ስርዓቶችም ሁሉ የተሳሳቱ ናቸው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም።
ሌላው ማኅበረ ቅዱሳን እኮ በቤተክርስቲያን ሥር ያለ እንጂ፣ ቤተክርስቲያንን መሪ አይደለም። ማኀበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያውጣው ስርዓት እና መመሪያ ይመራል እንጂ እንዲሁ እርሱ እንደወደደ የሚንቀሳቀስ አይደለም። ሲወድ የሲኖዶስን ወሳኔ የሚቀበል፣ ሲፈልግ ደግሞ አይ አይሆንም አልቀበልም የሚልም ሊሆን አይችልም። ይህን ካለማ ምኑን ኦርቶዶክሳዊ ማኅበር ሆነውና። ስለዚህ ማኅበሩ ምን ያድርግ። ምናልባት ለእርቁ መሳካት የእራሱን አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችል ይሆናል። ያደረጋልም ብየ አስባላሁ። ከዚህ ውጭ ግን እርቁ ካልተፈጸመ እኔ በሲኖዶስ ህግ አለመራም ይበል? እኔ ባልኳችሁ ተመሩ ይበል ቅዱስ ሲኖዶስን? ይህን ካለማ ኦርቶክሳዊነቱ የት ላይ ነው? ይላላም ብየ አላስብም። ታዲያ እርስዎ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር ያለ፣ በሲኖዶስ ህግ የሚመራ መሆኑን ረስተው ይሁን አውቀው፤ ሥራውን ብቻ ተመልክተው ይህን ማድረግ ነበረበት ሲሉ የሲኖዶስን ህግ የሚሽር አካል አደረጉት። በፍጽም ሊሆን አይችልም። ይህን የሚያደርግ ማኅበር ከሆነም ኦርቶዶክሳዊ አይደለም።
መጨረሻ ላይ ያሉት ሁለት አንቀጾች መልክት አልታየኝም።

Anonymous said...

ሰላም ለጸሐፊው!! ሀሳብዎን በሚገባ ገልጸውታል። መቺም የቤተ ክርስቲያን ችግር ቃላትን በመሰንዘር ብቻ የሚቃለል ሳይሆን ልብ ለልብ አንድ ሆኖ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጾ ችግሩን ለእግዚአብሔር ማመልከቱ ሸክሙን የበለጠ አያቀለው ይመስሎታል? በየድረ ገጹ እንደሚነበበው ከሆነ ግን አባ እገሌ እንዲህ አደረገ አባ እገሌ እንዲህ ሊያደርግ ነው የሚለው አባባል ሌሎቹም ይሉታልና የዚች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሆን ምን ይሁን ምን በአባቶች ላይ ፈራጅ እንዳንሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ፍርዱን ግን ለእግዚአብሔር መተው ይጠበቅብናል። ከምእመናን የሚጠበቀው በየአድባራቱ የጸሎት ምህላ መርሃ ግብር እንዲካሄድ አባቶችን ማሳሰብ ሲሆን ይህ ደግሞ ምሕረትን ያስገኛል ኣዚህ ላይ ጠንከር ማለቱ ጥቅም ይኖረዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የሰው ልጅ እንኳን ዓቅሙ እድሜው ውሱን ስለሆነ አሁን ግን እንደምመለከተው የመከራውን ዘመን እኛው ራሳችን በፍላጎታችን ኣያስረዘምነው እንደሆነ አጥብቀን ልናጤነው ይገባል። ስለ ቤተ ክርስቲያን ህሳብ መሰንዘር መልካም ነው ነገር ግን ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ውጪ እንዳይሆን መመርመር ያስፈልጋል። "እግዚአብሔር ያያል ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ" እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንችንን ይጠብቅልን።

Anonymous said...

ዘሮኪ ሆይ"ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመበት ጀምሮ ትኩረቱን በቤተ ክርስቲያን ብቻ ላይ በማድረግ፤ ከፖለቲካ ነጻ በሆነ መንገድ፥ ስብከተ ወንጌል በማስፋፋት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃንና ከተሐድሶያዊያን በመታደግ፣ አዲሱን ትውልድ ለቤተ ክርስቲያን የሚገደውና የሚቆረቆር አድርጎ በመቅረጽ ጊዜ የማይሽረው ትልቅ አሻራ ጥሏል።" ያሉት ደግ ነው። ግን ይችን ማቆለጳጰስ ማህበሩ ተንግዲህ የስደተኛ ሲኖዶስ አላማ እንዲገፋ የቀረበች መታያ ተመስላለች። ማህበረ ቅዱሳን በሁለት ባላ ያልቆመ፤ ሃገር በቀል የሆነ፤ ስደት ለሚያመጣው የአስተሳሰብ ወልጋዳነት ያልተጋለጠ ማህበር ነው። እዚያ ያለውን ችግር በምናብ ሳይሆን በአካል ያውቀዋል። ማህበረ ቅዱሳን የጥንቱን ካሁኑ አዋህደው የተካኑ የአዲሱ ትውልድ አባላት የሚመሩት ነው። የፈልግነው ባለመሆኑ ድረስልን ተብሎ የሚጠራ "ፈረሰኛ" አይደለም። ስለዚህ "ዝምታችሁ ሊገባኝ አልቻለም" ብለው ማህበሩን በነገር ባይሸነቁጡት ደግ ነው። ማህበሩ ክርስቲያናዊ ግዴታውን እየተወጣ ነው። በእርቀ ሰላሙ ጉዳይም ቢሆን የርስዎ ቅስቀሳ አያስፈልገውም። ማህበረ ቅዱሳን ሥራው እንዲታይ ግጭት ውስጥ የግድ መግባት የለበትም። በነጋ በጠባ መግለጫ ማውጣት አይጠበቅበትም። እኛ ስለጻፍን እየሰራን ነው ማለት አይደለም። ለማንኛውም ውጭ አገር ተቀምጠን ማዘዙ ቢቀርብን መልካም ነው።

Anonymous said...

Selam Zeroki: Ye atse susinios gize yenebrew yehaimanot guday neber. Semaitnetum asfelagi nuw. Yahunu gin yesiltan guday nuw. Ena ebakwon sewun wede tselot enji wede lela bitbit atmiru. Astewaynet nuw enji simetawinet yigodanal. Yemanim dem mefses yelebetim!!!

Anonymous said...

የጽሑፉን መንፈስ እንዴው በደፈናው ስመለከተው ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ከማሰብ የተጻፈ ነው የሚል አመለካከት እንዳይኖረኝ አድርጎኛል፡፡ ምክንያቱም የውጭውን እናስገባለን እየተባለ አገር ቤት ያሉትን አባቶች ለመከፋፈል የሚሞከረው አካሄድ በቁርጡ አዋጊ መኮንን ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም ፡ የተወሰኑትን አባቶች ስም እየዘረዘሩ ማወደስና ሌሎችን ደግሞ መኮነን ለቤተ ክርስቲያናችን አይጠቅማትም ደግሞ ማህበረ ቅዱሳንን ተነሥ እያሉ መቀስቀስ ምን የሚሉት ጉዳይ ነው ፡ ለመሆኑ ከእኛ የተሻለ ግንዛቤ ማህበረ ቅዱሳን አለው ፡ለዚች ቤተ ክርስቲያን የጀርባ አጥንት የሆነውን ማህበረ ቅዱሳንን ሃይማኖት እንደተለወጠ ቤተ ክርስቲያን እንደ ፈረሰች አስመስሎ መቀስቀስ ማህበሩን ወደ አልሆነ አቅጣጫ እንዲሄድ ማድረግ ነው፡፡ ለመሆኑ እነ አቡነ መርቆሬዎስ ከመቸ ወዲህ ነው ለዚች ቤተ ክርስቲያን አስበው የሚያውቁ እናንተ ስለ አቀነቀናችሁ ነው እንዴ፡ እነዚህ ዘረኞች የአንድ ጎጥ ሰፋሪዎች መጡ ቀሩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች የሚጎልባት ነገር የለም ፡ በዚያውስ ላይ ቢሆን የኢትዮጵያውን ሲኖዶስ ብቻ ጥፋተኛ እያደረጉ መኮነን ምን የሚሉት ፡ቋንቋ ነው፡ ሰሜን አሜሪካ ተቀምጦ የማን አባት ገደል ገባ እያሉ ማዋጋት ቤተ ክርስቲያኗን ተጠግቶ በስተጀርባው የተለየ ሚሽን ያለው ይመስላል ደጀ ሰላሞች ቆም ብላችሁ ብታስቡ መልካም ነው ፡

Anonymous said...

በእኔ አመለካከት ጽሑፉን የተጻፈው በቅንነት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንድ አንድ ሊታረሙ የሚገባቸው አገላለጾች ይኖሩታል። በቅንነት እስከተደረገ ድረሰ የተሻለ አመለካከት ያላቸው አንባቢዎች ገንቢ አስተያየት በመስጠት ልንማማርበት እንችላለን። በነገራችን ላይ በየብሎጉ ላይ የሚጻፈው ሁሉ እውነት ነው ብሎ የሚቀበል ሊኖር አይገባም። የድረ ገጾቹም አላማ ውይይት ማድረግ እንጂ እውነትን ማስተማር አይደለምና። እንደዚህ ያሉ ጽሑፎችን በመጻፍ ስለቤተክርስቲያናችንም የሚሰማንን መግለጽ ነውር አይመሰለኝም። እንዲያውም ነውር የሚሆነው ይህ ሁሉ “የተዛባ” አመለካከት ምእመናን እያስጨነቀ ባለበት ዘመን ዝምታን መርጠው የተኙ ሰባኪያንና ሊቃውንት ናቸው። በዚህ ዘመን ትውልዱን የሚያጽናና እና ቤተክርስቲያን ከገባችበት ፈተና እስክትወጣ ድረስ ምእመናን እንዴት በማስተዋልና በጥበብ መኖር እንዳለብን ለማስተማርና ለመምከር አቅም ያጡት ሰባኪያን መምህራ ሁሌም ያስገርሙኛል። በአፍም በመጣፍም ለመምከር በእውኑ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ይኖር ይሆን?

Anonymous said...

ለመሆኑ ደጀ ሰላሞች እንዴው እንጉሮ ገባህ ያለው ሁሉ ነው እንዴ ፖስት የሚያደርግበት ነገርን መርምሩ የማንም ስሜት ቤተ ክርስቲያኗን አይገዛም ጥላቻን ብቻ ከማስፋፋት የሚጠቅመው ነገር የለም ፡ ለማንኛውም ማህበረ ቅዱሳንን ከአባቶች ጋር ለማጣላት የሚደረገው ደባ ጥሩ አይደለም ፡ ወደድንም ጠላንም ወሬው ሰሜን አሜሪካ ብቻ ነው ፡ አርፋችሁ ተቀመጡ ፡ቅዱስ ሲኖዶስ ሥራውን ይሠራል

Anonymous said...

በቅድሚያ ቃለ ህይወት ያሰማልን ከላይ የተጻፈው አስተያየት ሁሉም በአንድ ሰው የተጻፈ ይመስላል ለመሆኑ ለቤተክርስቲያን ተቆርቁሮ መጻፍ ምኑላይ ነው ሃጥያቱ? እስቲ እናስትውልው ቤተ ክርስቲያን እየገጠማት ያለዉን ፈተና እያስተዋልነው አይመስልም ክግል ስሜት ነጽተን ካልተመለከትነው በማህበር ስሜት ብቻ ከተመለከትነው ለስሜታዊነት ይዳርገናል ቤተክርስቲያን ከማህበር በላይ ናት እውነት የማህበረ ቅዱሳን ልጆች ሆነን ከሆነ የጻፍንው ምንው በአንገታችን መስቀል ሲታሰር የገባነው ቃል ረሳነው እንዴ ? ኢየሩሳሌም ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ያልነው ቤተ ክርስቲያን በእንደዚህ ያለ ጊዜ ልንታደግ እንጂ በመልካም ቀንማ ሁሉም ጻድቅ እንደ ሆነ መጻፍ ይነግረናል ስለዚህ ይተጻፈው ጽሁፍ ወቅታዊ እና የታሰበው ምርጫ ከመከናወኑ በፊት ሁላችንም ልንጮህበት የሚገባ ጉዳይ ነው

yemelaku bariya said...

አባ ጳውሎስ ከሞታቸው በኋላ እንኳ ቤተ ክርስቲያን እረፍት እንዳታገኝ ዳዊት ያልደገሙ የአብነት ትምህርት ባለፈበት ያላለፉ ( መኖሩንም የማያውቁ) ምናልባትም በሃሰት በተሰራ ድግሪና ድፕሎማ የተዞሙትን ተክተውልን ሄዱ:: የሚገርም ጠላትነት:: ወያኔዎቹ ጳጳሳት ጊዜው ሲደርስ ምንትሉ ይሆን:: ከወያኔ እኮ ተስፋ የሚደረገው የከተማ ቦታ ነው ቤተ ክርስቲያን ግን የማያልፈውን መንግሥት እንድንወርስ መዘጋጃችን ናት:: እናንተም ለሊዙ እኛም ለመንግሥቱ እንታገላለን:: እግዚአብሔር እንደወያኔ ስላልሆነ መልካሙን ሰርተንበእምነታችን ጸንተን በርሱ ታምነን ከቆየን መንግሥቱን አይነሳንም:: ወገኖቼ ይህ ሁሉ ያልፋል እነሱም ምናልባት የትግራይን ሲኖዶስ ያቋቋሙ ይሆናል ለኛ ግን ግልግል ነው ለመሄድ ከፈለጉ አንከልክላቸው አንለምናቸው ይሂዱ ሰላማችንን አናጣም::

Anonymous said...

በእውነት እጅግ የሚያሳዝን ጊዜ ላይ ደርሰናል እንደእውነቱ ከሆነ ሁሉም ወገን ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት ጊዜ ይመስለኛል። በእውነቱ ጸሐፊው የተሰማቸውን ጽፈዋል የእኛ ክርስትና ጨዋነት የሚለካው አንዱ የተናገረውን አንዱ በመተቸት ሳይሆን የተሻለ ሃሳብ ነው ብሎ የሚያስበውን ቢያመጣ የተሻለ ውጤት ለቤተክርስቲያናችን ልናመጣ እንችላለን። ሲጀመር ጀምሮ ሰዎች ሰዎች ናቸው ዛሬ በውስጥም ሆነ በውጪ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ግድ የሌላቸው እንደሚኖሩ መጠበቅ ይኖርብናል እንጂ ገና ለገና እኛ የምናምነው አባት ተነካ ተብሎ ቡራ ከረዮ ማለቱም አግባብ አይመስለኝም። ምክንያቱም ሁልጊዜ ሰዎችን ሳይሆን መዕከል ማድረግ ያለብን ቤተክርስቲያንን ብቻ ነው። በዚህ ዘመን ሰዎች ትላንት ብዙ መስዋዕትነት ሊከፍሉ ይችላሉ ነገ ደግሞ ማሊያ ቀይረው ቤተክርስቲያንን ሊያፈርሱ ይችላሉ፥ ስለዚህ ትላንት በጎ ሥራ ስለሰሩ ዛሬ ያፍርሱ መባል ያለባቸው አይመስለኝም እንደ ትክክለኛ የቤተክርስቲያን ልጅነታችን ከሆነ። ነገር ግን ተገፍተው ነው፣ ተገደው ነው፣ አቅም ስላጡ ነው እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች ደርድሮ ከአፍራሽ ጋር መቆም እኛንም ከአጽራረ ቤተክርስቲያን ስለማንለይ ድርጊታችን ወይም የምንከተለው ሰው በመጀመሪያ ለቤተክርስቲያን ብቻ የቆመ መሆን ይገባዋል። ነገር ግን ዛሬ ሆኖ ካልተገኘ እንደእውነቱ ከሆነ ልንመክረው፣ ልንነግረው፣ ወይም ልንለየው እንጂ የሚገባን ዝም ብለን በጭፍን ያደረገው ያድርግ ብለን ልንከተለው አይገባም የሚል እምነት አለኝ።
ሌሎች ወገኖች ደግሞ ስለ ማኅበር ይበልጥ ሲቆረቆሩ ይታያሉ እርግጥ ነው ማናችንም እንደምናውቀው ማኅበረ ቅዱሳን የዘመኑ ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ማኅበር ቢሆንም አሁንም ትልቁ ችግር ብዬ የማምነው ማዕከል ማድረግ ያለብን ቅድስት ቤተክርስቲያንን እንጂ ማኅበራችንን መሆን የለበትም፥ ሲጀመር እኮ በማኅበር የተሰበሰብነው ለቅድስት ቤተክርስቲያን ዙሪያ ገባውን ከመናፍቃን ከከሃዲያን እና ከጠላት ልንጠብቃት እንጂ ማኅበራችንን ለመጠበቅ አይደለም። ቤተክርስቲያን ከሌለች እኮ ማኅበር ሊኖር አይችልም፥ ስለዚህ በቅን ልቦና እንመልከተው መታገል ያለብን መቆም ያለብን መጠበቅ ያለብን እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ሁን የሚለቅ ቅሱስ ጳውሎስ ለቤተክርስቲያን እንጂ ለማኅበር መሆን እንደሌለበት መገንዘብ ይኖርብናል ብየ አምናለሁ።
በመጨረሻ መንግሥትን መናገር ወይ ዝም ማለት፤ በጽሁፉ ላይ ጸሐፊው እንደተናገሩት መንግሥት የዚህ ሁሉ ችግር እርሱ ነው፥ ሲጀመር አቡነ መርቆርዮስን ማባረር እና ለራሱ ለአገዛዙ የሚመች ጎጡን ወደ ቤተክርስቲያን ባያመጣብን መልካም ነበር፣ የሆነ ሆነና ላለፉት ሃያ አንድ አመታት ስናለቅስ ስናዝን እና ስንከፋፈል ኖርን። የዚህ ሁሉ ችግር ማዕከል ሰሪና ፈጣሪው መንግሥት እንደሆነ እንኳን እኛ ምራቅ የዋጥነው ዛሬ የናት ጡት የሚጠባ ሁሉ የሚያውቀው እውነታ ነው፤ መንግሥት አሁንም እኔ አውቅላችኋለው ብሎ የራሱን ጎጠኛ ሊያስቀምጥ ሲሯሯጥ እኛም ተቀብለን አብረን መዘመር የለብንም አይሆንም ማለት ይኖርብናል። ማወቅ ያለንን እስከ ዛሬ በሃገራችን እየተሰሩ ያሉት በርካታ ችግሮች በቤተክርስቲያን ላይ እየተዘመተባቸው ያሉት ክስተቶች ሁሉ መንግሥት በአንድም በሌላም እጁ አለበት ለአብነት ያህል
1/ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን ሕልውና እና ተሰሚነት ለማጥፋት በመጀመሪያ ቤተክርስቲያንን ከፈለ፣ በመቀጠል የእስልምና ሃይማኖትን ቁጥራቸውን በውሸት አብዝቶ ብዙ ነን ብለው እንዲያስቡ እና የቤተክርስቲያኒቱን የበላይነት ለማሳጣት ያደረገው ታክቲክ ነው፣ ሌላው ደግሞ በዚህም በተከፋፈለች ቤተክርስቲያን ውስጥ በካድሬዎቹ አማካኝነት በዘር፣ በጎጥ፣ በወንዝ፣ በተራራ፣ ወዘተ በመሳሰሉት ለያይቶን አንዱ አንዱን እንዳያምን እና በጋራ ለዚህች ሀገር እንዳይቆም ወኔያችንን ሰለበው። በአጠቃላይ በከፋፍለህ ግዛው ስልቱ እርስ በእርስ ስንባላ መንግሥት እና የሕዋሃት አባሎች አንጡራ የሆነውን የዚህችን ሃገር ሃብት ዘርፈው በውጪ ባንኮች እና በትግራይ ላይ እያደረጁነው እኛ እርስ በእርሳችን እንባላለን፥ የዚህ ሁሉ ችግር ፈጣሪዎች እነ አቶ አባይ ጸሀይ እና ስብሃት እና በርካታ የትግራይ ሕዋሃት የበላይ እና የበታች ሹማምንቶች አንጡራ የሆነውን የዚህችን ሃገር ሃብት እየዘረፉ ነው ስለዚህ ዝም ማለታችን ይቁም።
ይቀጥላል

ፍኖተ አበው ነኝ

Anonymous said...

ተከታዩ ክፍል እነሆ
2/ በርካታ አድባራት እና ገዳማት ተቃጥለዋል እየተቃጠሉም ነው ታሪክን ለማጥፋት ከሚደረገው ጥረት ዋነኛው ነው ለምሳሌ የአሰቦት ገዳም ተቃጥሏል በተደጋጋሚ፥ መንግሥት እንደመንግሥትነቱ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ግዴታው ሆኖ ሳለ ለምን የምንለውን "ጸረ ሰላሞች" ናችሁ በማለት ስም ይሰጣል ክርስቲያኖች ለምን ይታረዳሉ ሲባል "የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስነሳት የተነሱ አክራሪዎች" ከተባልን እምኑ ጋር ነው የዜግነት መብታችን?
3/ ዝቋላ ገዳማችን ሲቃጠል መንግሥት ሆነ በቤተክህነት ያሉት የመንግሥት ጋሻ ጃግሬዎች መንግሥት ስንቱን ይስራ ይላሉ እሳት እንደማንኛውም ቦታ ተነሳ ተቃጠለ ብለው ባልተገራ ምላሳቸው ይነግሩናል። እውን ይሄ ማደናገሪያ ነው ወይስ ተቆርቋሪነት ነው?
4/ የዋልድባ ገዳም ሲታረስ እና የገዳሙ አባቶች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ፣ በዘር እና በጎጥ ሲታመሱ ለማን ነው አቤት የሚባለው መንግሥት "ጸረ ሰላም እና ጸረ ልማት ሃይሎች " ናቸው ይላል ቤተክህነቱ ስለዋልድባ አያሰማን ይላል ስለዚህ የዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው መንግሥት መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ይሄ ጦርነት ለማስነሳት ወይም እርስ በእርስ ለማጋጨትም አይደለም፣ ጥያቄው አንድ እና አንድ መሆን አለበት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ህልውናዋን ካጠፋ ማዕከል ሆኖ የህዝብን አንድነት የሚናገር አይኖርም ስለዚህ እናውቅልሃለን ባዮቹ አሁንም በተከበረው ስብሰባ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማድረግ ያለባችሁ እንዲህ ነው ካሉን እምኑ ጋር ነው መንፈስ ቅዱስ የመራው ስብሰባ የምንለው?
ወገኖቼ ዝም ብለን ጎጠኝነት ይዞን፣ ወገንተኝነት ይዞን ዛሬ እውነት መናገር ካልቻልን ቤተክርስቲያናችንን እንደዋዛ ልናጣት እንችላለን እንኳን እንዲህ ባለ ሊብራልነት በበዛበት ዘመን ቀርቶ በዘመነ ሰማዕታት እንኳን ጥቂት ሰማዕታት ባይኖሩ ኖሮ ዛሬ ክርስትና እኛ ጋር መድረስ ባልቻለ ነበር። ለቅድስት ቤተክርስቲያን ለዘር ባያስቀርልን ኖሮ ዛሬ ሁላችንም አረማውያን በሆንን ነበር ስለዚህ አሁንም በያለንበት ከወገንተኝነት፣ ከዘረኝነት፣ ከማኅበር ስሜት፣ ወይም ከአጥቢያ ስሜት ወጥተን ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እንቁም፤ ሌላው ቢቀር እንደ ፊተኞቹ ታላቅ ገዳማትንና አድባራትን ባናሳንጽም፣ እንደው በጥቂቱ ያሉትን መጠበቅ እንዴት ይሳነናል? ዛሬ እኮ እንደቀደሙት ሰማዕታት የደም መስዋዕትነት አልተጠየቅንም ነገር ግን እንዴት እውነት ለመናገር ተሳነን። ለቤተክርስቲያን ያልቆመ ከእኛ ሊሆን አይችልም፣ ስለመንጋው ሳይጨነቅ ስለሚያገኘው ምድራዊ ሹመት እና ክብር ለተጨነቀ ስለምን ሰማያዊውን መንገድ ለኛ ይነግረናል?
አባትን ለመውቀስ ብቃት ባይኖረኝም፥ ዛሬም ተረፈ አሪዎሳውያን፣ ተረፈ ንስጥሮስ በመካከላችን መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም።
በመጨረሻ ለማለት የምፈልገው በውጪ የሚኖሩ አባቶችን ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ብላችሁ የስህተት ስህተት አትፈጽሙ እስከ ዛሬ የተሰሩ ስህተቶች ታርመው ህዝብን እና ሃገርን አንድ ለማድረግ መጣጣሩ ለሁላችንም ሞገስ ነው ነገር ግን የሕዋሃት አመራሮች እንደሚያደርጉት እናንተም ከፋፍለህ ግዛው የምትሉ ከሆነ ከእነሱ በምንም ልትለዩ እንደማትችሉ ልታውቁት ይገባል። ቢያንስ እናንተ በሥጋ የወለዳችኋቸው ልጆች ባይኖራችሁም ለሚከተሏችሁ በርካታ ምዕመናን ልጆች ሕጻናት ስትሉ የሰላሙ መንገድ እስከ መጨረሻው ልትጠብቁ ይገባል፣ ዛሬ ጥቂት በሕዋሃት ከህዝብ በዘረፈው ገንዘብ የተታለሉ አባቶች ያሉትን ይዛችሁ እናንተ እንዲህ ካደረጋችሁ እኛም የባሰ እናጠፋለን የሚለውን የሞኞች በትር ስለቅድስት ቤተክርስቲያን ብላችሁ፣ ለማያልፈቅ ቃሉ ብላችሁ ታገሱ እባካችሁ ከትውልድ ወቀሳ፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደማታመልጡም ልታውቁ ይገባል።
ዛሬ ከፋፍላችሁን ብታልፉ ነገ ካለፋችሁ በኃላ ሥጋችሁ እንኳን ሊሸከመው የማይችለው የታሪክ ወቀሳ እና እርግማን እንደሚደርስባችሁ እወቁት ተረዱት።
ሌላው ምዕመናን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምንኖር በሙሉ ዋናው መርሳት የሌለብን ነበር ለማስታወስ ትላንት ቅድስት ቤተክርስቲያንን በብዙ ተጋድሎ ለእኛ ያስረከቡንን አባቶቻችንን እናስታውስ፥ ደሙን በቀራኒዮ አደባባይ አፍስሶ መድኅን የሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ እናስታውስ፥ ሐዋርያት በሰበሰቧት አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት እናስበው፥ ትላንትናም ዛሬም ነገም ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ብለን ለልጆቻችንም እንንገር እኛ እነ እገሌ አይምጡብን እራሳችን እንመሰርታለን፣ እኛ ትክክለኛ ነን፣ የሚሉንን ወግዱ ልንላቸው የሚገባ ጊዜ ላይ ደርሰናል አምላካችን በውስጥም ሆነ በውጪ እንደ መዥገር ተጣብቀው ቤተክርስቲያንን ለመለያየት፣ ለመከፋፈል ምክንያት የሆኗትን አባቶችም ሆነ ምዕመናን ዛሬ የንሰሐ ጊዜ ነው ዝም ብለት ጎጣችንን ሰብስበን ወይም ስለወንዝ እና ምንጭ እምናወራ ከሆነ ድህነት ልናገኝ አንችልም በዙ ጽድቅ የለም ስለዚህ አምላከ ጻድቃን ሰማዕታት በጅራፉ እየገረፈ ከምዕመናን ጀርባ ተደብቀው የሚከፋፍሉንን እስኪለይልን ድረስ በአንድነቷ እንጽና ለበለጠው ክብር እንዘጋጅ ሕዋሃት የሰጠንን የመገነጣጠል ጸበል የመለያት ኪኒን አሽቀንጥረን ጥለን አንድነትን እንስበክ ዛሬም ሆነ ለነገው ትውልድ የሚያስፈልገው አንድነት ብቻ ነው በመለያየት ይሄ ጎጥ ያኛው ወንዝ ወይም ተራራ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ሊያስገባን ቀርቶ ሊያሳየን ስለማይችል ሃክ እንትፍ ልንለው ይገባል።
ይቆየን
ፍኖተ አበው ነኝ

Anonymous said...

ስለ ቤተክርስቲያን ብላችሁ ሁላችንም የማንም ደጋፊ አንሁን
1/ ኢትዮጵያ ያሉት አንዳንድ አባቶች በትክክል ሹመት ፈላጊዎች እንዳሉ እንወቅ
2/ መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ ቆርቶ ተነስቷል
3/ በውጪ ከሚኖሩ አባቶች መካከል ወደ ሃገር ቤት የሚለው ጉዳይ ሁሌ የሚያማቸው እንዳሉ እንረዳ፣ ሰላም ለነሱ እዚሁ እያጭበረበሩ መኖር ነው፣ ሰላም አይፈልጉም ገንዘቡ ያለው በውጪ ስለሆነ ሲበሉ ይኖራሉ፣ ሲሞቱም በቀበሪያ አያጡም። እንዳንዶች እንጂ ሁሉንም ለማለት አይደለም እነሱም ሁሌ ይናገራሉ
4/ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያን ቢቆም ይሻላል፣ ከማኅበርተኝነት መውጣት አለበት ማኅበሬ እንዳይነካ ዝም ልበል፣ የማኅበሬ ጽ/ቤት ካልተነካ እኔ ስራዬ መናፍቃንን መዋገት ነው . . . የመሳሰሉት ትክክል አይደሉም
5/ በውጪ ያላችሁ በሙሉ አጥቢያዬ ስላልተነካ ምን አገባኝ ፣ ብሎ ማለት ተገቢ አይደለም ቤተክርስቲያን የሁላችን ናትና በጋራ እንቁም
6/ መምህራን፣ ሰማሪያን፣ አገልጋዮች በሙሉ መናፍቃን፣ አክራሪዎች በቤተክርስቲያን ላይ ሲነሱ ያዙን ልቀቁን ትላላችሁ፥ ዛሬ ደግሞ መንግሥት እነ አቶ አባይ ጸሃዬ ፖትሪያርክ እኛ እንሁን አለበለዚያ ለኛ የሚሰሩት ባንዳዎች ብቻ ላክሆነ ግን ትግራይ ላይ እኛ የራሳችንን እንሾማለን ሲል የታላችሁ ድሮ ያዙን ልቀቁን ስትሉ የነበራችሁ ሁላ. . .ነገ ያስተዛዝበናል
7/ ድሮ የቤተክርስቲያን አስተዳደሯ ከላላ ለመናፍቃን ለከሃዲያን ያመቻል ስትሉ የነበራችሁ ቲፎዞ ስትሰበስቡ የነበራችሁ ሰባኪያን ዛሬ ኳስ እንዴት ሆነ ከምትሉ ወገን ለይታችሁ ቁጭ ከምትሉ ድሮ የቆማችሁለትን የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ይጠበቅ ዛሬም ከወያኔ መንግሥት ጋር ተባብራችሁ የምታፈርሱ ሕዝብ ይታዘባል፣ ያዝናል፣ ማንነታችሁን አውቋል እና ስለ ቅድስቲቱ ብትሰሩ ይሻላል
ዛሬ የቆመ የሚመስለው ነገ እንደሚወድቅ ሊገነዘብ ይገባል
ወያኔ የዛሬ መንግሥት ነው የነገ ተከሳሽ መሆኑን አትዘንጉ
በመጨረሻ ምዕመናን
እንደው እንደጎርፍ ውሃ ዝም ብለን አንነዳ እባካችሁ እንጽና ባለንበት እንቁም ጥቂት የጎጥ ካባ ለብሰው ከዚህ በኃላ የውጪ ሲኖዶስ ነው ትክክለኛ ሲሉን ተከትለን አንነዳ ቢያንስ ቆመን እንያቸው ትላንት በውንብድና የተባረሩ ዛሬ እዚህ የሚሾሙበት ከሆነ ልንጠነቀቅ ይገባል ማንን እንደምንከተል
በሌላ በኩል ትላንት ትጉሃን የነበሩ አባቶች ዛሬ ግብረ በላ ከሆኑ ዝም ብለን በጭፍን መከተላችንን እናቁም አቋማችን ለቤተክርስቲያን እንጂ ለሰዎች ለዚያውም ለዘረኞች እንዳይሆን እንጠንቀቅ
ስመ ክርስትናን አያጥፋብን

Anonymous said...


በመጀመሪያ ደረጃ ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ከሆንን የቤተክርስቲያን አባቶችን ማክበር የግድ ይላል:: እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ዘለፋ ተገቢ አይመስለኝም:: በእኔ እይታ የዕርቁ አፈጻጸም ከመነሻው ችግር አለበት:: ዕርቁ መሆን የነበረበት ውግዘቱን እስከ ማንሳት ብቻ ነበር:: ምክንያቱም ፓትረያርኩን ያባረራቸው ያገር ቤቱ ሲኖዶስ ነው አልተባለምና:: በዚህ ሰዓት ሲኖዶሱ ፓትርያርኩን የመመለስ አቅም አለው? አሁን ጊዜው ነው? መባረራቸውን ያኔ በግልጽ ለሲኖዶሱ ተናግረው ከነበረ ሰማይትነትን የሚጠይቀው ትግል የቀረ መጀመሪያ ነው:: በግልጽ ካልተናገሩ 'ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይደርስም' እንደሚባለው ነው የሚሆነው:: መደራደር የሚያስፈልግ እኮ ከተጣሉት ካባረረ አካል ጋር ነው :: እንደማይሆን እየታወቀ እኒህ አባቶች ምን ያድርጉ? 'አህያውን ፈርቶ ዳውላውን' የሚባለውን ተረት ነው የሚመስለው! ይልቅ በውግዘት ላይ ሌላ ውግዘት ከመደረት ውግዘቱን አንስቶ የፍቅር አባትነትን ማሳየት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው::

Anonymous said...

May God bless "Fnote Abewe"- you have spoken my heart! Keep blessed man!

Anonymous said...

የመጀመሪያው አስተያየት ሰጭ Bilata,«
ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም። መቼም ቢሆን ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ሊመራው አይችልም። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት (እንደ ሰዉነታቸው) ሊሳሳቱ ይችላሉ።» ብለው መጻፋቸው አስገርሞኝ ነው ይህንን የጻፍኩት፤ ሲኖዶስ የሚባላው እኮ የጳጳሳት ጉባኤ ነው፤ ጳጳሳቱ ከመንስ ቅዱስ የተሳጣቸውን አደራ የማይወጡ ከሆነ፣ በሥጋ ፈቃድ የሚራመዱ፣ ለመንጋቸው የማያስቡ፣ ለሥልጣን የሚስገበገቡ፣ የአምላክን ፈቃድ ሳይሆን የባለስላጣኖችን ፈቃድ የሚፈጽሙ ሲሆኑ፣ ውሳኔያቸውም በሕገ እ/ር እና በቃለ እ/ር ላይ ያልተመሠረተ የአድማ ስራ ሲሰራ የሚታይ ሲኖዶስ ተሳሳተ ይባላል። ተሳስቷልም። ሲኖዶስ ማለት እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉት ስብሰባ ነውና። መንፈስ ቅዱስ የተለየው በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ተሳሳተ አያሰኝም። በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተካሄደ ባለመሆኑ፤ «እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል» የሚለው አይነት የቅዱስሳን አባው ሲኖዶስ ግን አይሳትም እንላላን፤ ምክንያት ጉባኤው በመንፈስ ቅዱስ ስለሚመራ ነው።
ስለዚህ አባቶችን ከሲኖዶስ ሲኖዶስ ከአባቶች ለይቶ ማየት የሲኖዶስን ትርጉም ካለማወቅ ይመስለኛል።
እውነተኛ ሲኖዶስ እንዲኖር እውነተኛ አባቶች ያስፈልጋሉ፤ ሲኖዶስ እንዳይሳሳት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የሚመራቸው ሰዎች መሆን አለባቸው።
ዘአባ ኢየሱስ ሞአ ዘሐይቅ ወዘ ደሴ።

Anonymous said...

በትናንትናው እለት ሰላም ለጸሐፊው በሚል ጀምሬ ትንሽ ሀሳቤን ሰንዝሬአለሁ። የኔ አገላለጽ ያተኮረው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ላይ ነበረ ይህን ያልኩበት ምክንያት በተለይ የሀሳብ አግላለጽ ላይ ትኩረት እንድንሰጥበትና መማማሪያና መተራረሚያ መድረክ እንጅ መተቻቻ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በመስጋት ነው። ለዚህ እንደምክንያት ሊሆን የሚችለው የምንነጋገረው ስለቤተ ክርስቲያን መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ልናስገባው ስለሚያስፈልግ የቃላት አመራረጥ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ስለቤተክርስቲያን ቅንዓት ያስፈልጋል የሆኖ ሆኖ መልክታችንን ስናስተሳልፍ በተበሳጭንበት ውቅት ሳይሆን በተረጋጋንበት ጊዜ ቢሆን ከስሕተት ሊያድነን ይችላል። ከአመታት በፊት ድረ ገጾች ባልነበሩ ጊዜ እንዴት መልካም ነበረ ለማለት አንዳንዴም ያስደፍራል እርግጥ ትልቁ ቁም ነገር በአግባቡ መጠቀም ላይ ነው። ምንም አልን ምንም በኛ አቅም ሊሆን የሚችል ነገር ያለ አይመስልም ዛሬ ዘመኑን የምንዋጅበት ነው። ከቤተ መቅደስ ፍቅር ጠፍቶአል ትውልዱ ራስ ውዳድ ሽንገላን የሚያበዛ ወረተኛ ሆናል ይህ ሁሉ ትንቢቱ ይፈጽም ዘንድ ነውና አባቶችም ምእመናንም በአንድነት እንጸልይ ይህ ትልቅ መልስ አለው ይህን ነው አጥብቄ የምለው። በዚህ ድረ ገጽ እንደማነበው ማህበሩ ለምን እንዲህ አያደርግም ለምን ዝም ይላል የሚል ቃላት ተሰንዝረዋል እርግጥ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ስብስብ ነው እኔ እንደማውቀው ግዴታውንም እየተወጣ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው ይህ ማኅበር ጎልቶ ወጣ እንጅ ሌሎች መሰል ማኅበራትም እንዳሉ አውቃለሁ። እኔ የምፈራው እኛስ ምን እያደረግን ነው ለቤተ ክርስቲያንስ ምን ክርስቲናዊ አስተዋጽኦ እየከፈልን ነው? ለዚህ መልስ ካለን መልካም ነው አለበለዚያ ግን ትችት ብቻ ይሆንና ይቀራል ይህ ደግሞ ያስፈረድብናልና ጥንቃቂ ያስፈጋል ነው የምለው። በተረፈ ግን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም እንጸልይ " እስመ በጸሎተ ጻድቅ ትድኅን ወኢትማስን ሀገር"

Anonymous said...

ጳጳሳቱ ከመንስ ቅዱስ የተሳጣቸውን አደራ የማይወጡ ከሆነ፣ በሥጋ ፈቃድ የሚራመዱ፣ ለመንጋቸው የማያስቡ፣ ለሥልጣን የሚስገበገቡ፣ የአምላክን ፈቃድ ሳይሆን የባለስላጣኖችን ፈቃድ የሚፈጽሙ ሲሆኑ፣ ውሳኔያቸውም በሕገ እ/ር እና በቃለ እ/ር ላይ ያልተመሠረተ የአድማ ስራ ሲሰራ የሚታይ ሲኖዶስ ተሳሳተ ይባላል። ተሳስቷልም::

እውነተኛ ሲኖዶስ እንዲኖር እውነተኛ አባቶች ያስፈልጋሉ፤ ሲኖዶስ እንዳይሳሳት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የሚመራቸው ሰዎች መሆን አለባቸው።

ስለዚህ አባቶችን ከሲኖዶስ ሲኖዶስ ከአባቶች ለይቶ ማየት is the a b c of wisdom.

Thank you ዘአባ ኢየሱስ ሞአ ዘሐይቅ ወዘ ደሴ. We want people like you to educate the fools.

I wonder some people try to fool us even after 21 years of misery of the church. That is because they don' care about the church as long as they get what they want. 'Hodachew amlakachew teblualena!' The woreset thing is they commit these crimes in the name of God and Church and 'Synod’. We know you even if we are late. Fool yourself! You can have as many cadre papas as you wish!
Gebre Ke Etissa T/Haymanot.

Anonymous said...

ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም። መቼም ቢሆን ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ሊመራው አይችልም። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት (እንደ ሰዉነታቸው) ሊሳሳቱ ይችላሉ።» <>THANK YOU GOD bells you

Unknown said...

" Anonymous said...
የመጀመሪያው አስተያየት ሰጭ Bilata,«
ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም። መቼም ቢሆን ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ሊመራው አይችልም። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት (እንደ ሰዉነታቸው) ሊሳሳቱ ይችላሉ።» ብለው መጻፋቸው አስገርሞኝ ነው ይህንን የጻፍኩት፤ ሲኖዶስ የሚባላው እኮ የጳጳሳት ጉባኤ ነው፤ ጳጳሳቱ ከመንስ ቅዱስ የተሳጣቸውን አደራ የማይወጡ ከሆነ፣ በሥጋ ፈቃድ የሚራመዱ፣ ለመንጋቸው የማያስቡ፣ ለሥልጣን የሚስገበገቡ፣ የአምላክን ፈቃድ ሳይሆን የባለስላጣኖችን ፈቃድ የሚፈጽሙ ሲሆኑ፣ ውሳኔያቸውም በሕገ እ/ር እና በቃለ እ/ር ላይ ያልተመሠረተ የአድማ ስራ ሲሰራ የሚታይ ሲኖዶስ ተሳሳተ ይባላል። ተሳስቷልም። ሲኖዶስ ማለት እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉት ስብሰባ ነውና። መንፈስ ቅዱስ የተለየው በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ተሳሳተ አያሰኝም። በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተካሄደ ባለመሆኑ፤ «እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል» የሚለው አይነት የቅዱስሳን አባው ሲኖዶስ ግን አይሳትም እንላላን፤ ምክንያት ጉባኤው በመንፈስ ቅዱስ ስለሚመራ ነው።
ስለዚህ አባቶችን ከሲኖዶስ ሲኖዶስ ከአባቶች ለይቶ ማየት የሲኖዶስን ትርጉም ካለማወቅ ይመስለኛል።
እውነተኛ ሲኖዶስ እንዲኖር እውነተኛ አባቶች ያስፈልጋሉ፤ ሲኖዶስ እንዳይሳሳት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የሚመራቸው ሰዎች መሆን አለባቸው።
ዘአባ ኢየሱስ ሞአ ዘሐይቅ ወዘ ደሴ።

January 25, 2013 at 5:34 AM"...እኔም ከዚህ በላይ በተሰጠው መሰረተ ሃሳብ ነው ስለሲኖዶስ ምንነት የምስማማው። ይህን መልስ የሰጡትን ወግን በጣም ነው የማመሰግነው። በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚመሩ ጳጳሳት በምንም መመዘኛ ለነአቶ ዐባይ ፀሐዬ ታዛዦች ሊሆኑ አይችሉም። በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ጳጳሳት የሚሰባሰቡበት ሲኖዶስ ሃይማኖታቸው የቀና 318ቱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቁስጥንጥንያ ውስጥ በ325 ዓ.እ የደነገጉትን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይጠብቃል እንጅ አይሽርም። መንፈስ ቅዱስ በበላይነት የሚመራት ቤተ ክርስቲያን በጳጳሳቶቿ ፥ በካህናቶቿ ፥ በምዕመናኖቿ መካከል ሰላም ፥ ፍቅርና አንድነት ይኖራል እንጅ፤ እንደዚህ ጠብ፥ ርክርና ክፍፍል አይኖርም። ስለዚህ የመንግሥት ደጋፊዎች የሆናችሁ ሁሉ የሌለውን እንዳለ ፥ ያለውን እንደሌለ አድርጋችሁ ለማሳየት ብትሞክሩም፣ እኛ የችግሩ ባለቤቶች የሆነው ኢትዮጵያውያኑ ብቻም ሳንሆን ዓለም ያወቀው ገመናችን ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ለነ ዐባይ ፀሐዬ የሚታዘዘውን ሲኖዶስ ''አይሳሳትም'' ማለት በራሱ መንፈስ ቅዱስን እንደ መፈታተን መሆኑን አውቃችሁ ይህን ድፍረታችሁን ብታቆሙ መልካም ነው ብየ ወገናዊ ምክሬን ላስተላልፍላችሁ ፍቀዱልኝ። እውነተኛ አማኞች ከሆናችሁ ማለቴ ነው !

Anonymous said...

"Anonymous said...
ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም። መቼም ቢሆን ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ሊመራው አይችልም። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት (እንደ ሰዉነታቸው) ሊሳሳቱ ይችላሉ።» <>THANK YOU GOD bells you January 26, 2013 at 3:56 AM"

How about ለነ ዐባይ ፀሐዬ የሚታዘዘውን ሲኖዶስ?

Those of you ye wayae tultula ድፍረታችሁን ብታቆሙ መልካም ነው!!!

Believe it or not, our church has been under the colony of ዐባይ ፀሐዬ mafia group and ለነ ዐባይ ፀሐዬ የሚታዘዘውን ሲኖዶስ.

Anonymous said...

Amlak hoyi Betekrstian antewu tadegat . Eregnoch adrgeh yeshomkachewu yekebedachewu yimeslal.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)