January 19, 2013

አሜሪካ የሚገኙት አባቶች ሲኖዶስ መግለጫ አወጣ


(ደጀ ሰላም፤ ጥር 11/2005 ዓ.ም፤ ጃኑዋሪ 19/2013/ PDF)በትናንትናው ዕለት የአሜሪካው ሲኖዶስ  ያወጣው መግለጫ የተለያዩ ጉዳዮችን የያዘ ነበር፡፡ እነዚህም ጉዳዮች የቅዱስ ፓትርያርኩን መሰደድ በተመለከተ ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 4 ቁጥር 77 እስከሚድን ጠብቁት የሚለውን ቀኖናዊ ሕግ መሻሩን በመግለጽና ሌሎች ተጨማሪ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የተዘረዘሩ አስረጅዎችን የሚጠቅሱ፣ የሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስን በስደት መቀጠል በተመለከተ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስን፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን ስደት አብነት ያደረገ መሆኑን የሚተነትኑ እና የዕርቀ ሰላሙን ውይይት በተመለከተ ለምን? እንዴትና? በማን? እንደከሸፈ አስረጅዎችን በመጥቀስ የሚስረዱ ናቸው፡፡
በመግለጫውም የሰላም አንድነት ጉባኤ በራሱ ተነሳሽነት ለሶስት ዓመታት ያለመታከት ላደረገው ጥረት ምስጋና ተችሮታል።

ከዚህም በመነሣት መግለጫው ባለ 10 ነጥብ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ መልእክቱን ይቋጫል፡፡ በእነዚህም ነጥቦች ሲኖዶሱ፦
1ኛ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውንም የሐዋርያዊ መንበር ሽሚያ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ያወግዛል፤

2ኛ አዲስ ለሚሾሙትም ፓትርያርክ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች እስከ መጨረሻው ጸንተው በአንድነት እንዲቃወሙት፣ እውቅና እንዳይሰጡትና፣ እንዳይታዘዙት ያዛል፤ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ከፍተኛ መሥዋዕትነት በመክፈል የቆሙ እውነተኞቹም አባቶች በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊዎች ሆነው በታሪክም በእግዚአብሔርም ተወቃሽ እንዳይሆኑ ጥሪ ያደርጋል፣

3ኛ እግዚአብሔርን ሳይፈራ፣ ታሪክና ህዝብን ሳያፍር አቅዶ በመነሳትና “ዓላመችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የአማራን አከርካሪ መስበር ነው፡፡ እርሱም ተሳክቶልናል” በማለት በድፍረት የሚናገረው የኢህአዴግ መንግስት ለችግሩ ሁሉ ዋነኛ ተጠያቂ ያደርጋል፣

4ኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀገራችን የገባችበትን መከራ በመረዳት በአንድነት አጥብቀው እንዲፀልዩ ያዛል፣

5ኛ ሲኖዶሱ ከማናቸውም የዘር፣ የጎሣና፣ የፖለቲካ ኃይላት ተጽዕኖ ነጻ በመሆን የሕዝባችን እውነተኛ ድምጽ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ከሀገራችን ህልውና ተነጥሎ ስለማይታይ አገር ወዳድ የሆናችሁ ወገኖች ሁሉ ከዳር እስከ ዳር በመነሣት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጎን በጋራ እንድትቆሙ በማለት ጥሪውን አስተላልፋል፤

6ኛ በሀገር ቤት የሚደረገው ሕገ ወጡ የፓትርያርክ ምርጫ ተገትቶ ለሰላሙ ቅድሚያ በመስጠት ለሚደረግ ማንኛውም ጥረት ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶሱ በሩን ከፍቶና እጁን ዘርግቶ የሚጠባበቅ መሆኑን አሳውቋል፣

7ኛ ለዕርቀ ሰላሙ ሲባል ተገትቶ የነበረውን አዳዲስ አህጉረ ስብከቶችን የማጠናከርና ኤጲስ ቆጶሳትንም የመሾም ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳውቃል፡፡ የጠቅላይ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅና ዋና ፀሐፊ ሰይሟል፤

8ኛ ከነገ ዛሬ ሰላም ይወርዳል በማለት በገለልተኝነት የቆዩትን አብያተ ክርስቲያናትና ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ራዕይና ዕቅድ ያላችሁ ማኅበራትና የቤተ ክርስቲያኒቱ አቅጣጫ እጅግ ያሳዘናችሁ በአዲስ አበባው አስተዳደር ሥር የነበራችሁ አብያተ ክርስቲያናት “በቅዱስ ሲኖዶስ ጥላ ሥር በመሆን ለአንዲት ሀገር፣ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን፣ ለአንድ ሕዝብ በጋራ እንድናገለግል” በማለት ጥሪውን አቅርቧል፤

9ኛ በመላው ዓለም ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” (ኢሳ 40፥1) በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የስብከተ ወንጌል ስምሪት ያዘጋጀ መሆኑን አሳውቋል፣

10ኛ መግለጫው በመጨረሻም ይህን ልዩ ጉባኤ ለማስተናገድ የደከሙትን የሎስ አንጀለስ ድንግል ማርያም ካቴድራል ካህናት፣ የአስተዳደር ቦርድ አባላትና ምእመናን አመስግኗል፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ የሚመራው  ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን መግለጫ ያወጣበትን አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው በሎስ አንጀለስ ከተማ ከጥር 7-9/ 2005 ዓ.ም  ነው፡፡ 

የመግለጫውን ዝርዝር ይዘት ለመመልከት ይህንን ይጫኑ።


ቸር ወሬ ያሰማን አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)