January 12, 2013

የመጨረሻው መጀመሪያ እንዳይሆን

(መልዕክተ ተዋሕዶ -ዘ ሮኪ፤ በተለይ ደጀ ሰላም እንደጻፉት/ PDF)፦ በዚህ በውጭው ዓለም ለምንገኘው ለብዙዎቻችን፣ በተለይ ባለፉት 7 እና 8 ዓመታት ላቋቋምናቸው አጥቢያ አቢያተ ቤተ ክርስቲያናት፣ ምርጫችንን እናት ቤተ ክርስቲያናት አድርገን ስንጓዝ፣ መንገዱ እንደዚህ እንደ ዛሬው ቀላል አልነበረም፣ የተለያዩ ቅጥያ ስሞች እየተለጠፉብንና በአደባባይም ስንት ነቀፋ እየተቀበልንም ነበር። የወያኔ ቅጥረኞች እና የአባ ጳውሎስ አሽከሮች የሚሉት በተደጋጋሚ የሚዘወተሩ ሲሆኑ አጥቢያ አቢያተ ቤተ ክርስቲያናቱን ለማኅበረ ቅዱሳን አባላት ብቻ  እንደ ተቋቋመ የሚመለከቱም ቁጥራቸው ትንሽ አልነበረም።
የሆነው ሆኖ ቅዱስ ሲኖዶስ አይሰደድም (ፓትርያርክ እና ሊቃነ ጳጳሳት ሊሰደዱ ይችላሉ)፣ የቅዱስ ሲኖዶስ መንበሩ አዲስ አበባ ነው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው ወሳኝ የበላይ አካል ነው (ከፓትርያርኩም በላይ)፣ እና የቅዱስ ሲኖዶስ መሪው መንፈስ ቅዱስ ነው የሚሉትን መሰረታዊ ሃሳቦች በማንገብ ነበር፣ ቅዱስ ሲኖዶስን ለውጭው ዓለም በድጋሚ ያስተዋወቅነው። ዛሬ፣ በተደጋጋሚ እየመጡ ያስተምሩን የነበሩ መምህራን ሳይቀር፣ ይህ የሰላም ድርድር፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ለምንገኝ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ብቻ የሚደረግ፣ አገር ቤት ያሉ ቅጠል ሸጠው ያስተማሩን ወላጆቻን ከእኛ የተለየ ፍላጎት እንዳላቸው አድርገው፣ ሲናገሩና በየብሎጋቸው ሲጽፉ የተስተዋሉት። አዝነንባችኋል! አንድ  ለወደፊቱ  የምንገባላችሁ ቃል ቢኖር ውሎአችሁ ከማን ጋር እንደሆነ በስፋት እናጠናለን!! የሚል ነው። ወደ ዋናው ቁም ነገር እንገባ።

የተከበራችሁ የተዋሕዶ ልጆች ፣ የዛሬ ሃያ ዓመት፣ እንኳን እናት ቤተ ክርስቲያናችን ፣ ኢትዮጵያ ሀገራችን የወደ ፊት ዕጣዋ ምን ሊሆን መገመት በማይቻልበትና ማለቂያ ለሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ልትዳረግ ጫፍ ላይ ባለችበት ወቅት፣ የተፈጸሙ ታሪካዊ ስህተቶችን ፣ ዛሬ በሰከነ አእዕምሮ ስንመለከተው ሊያስቆጨን ጀምሮአል። ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ለምትቸገርባቸው አብዛኛዎቹ ችግሮች መነሻው ፣ ከጫካ የመጣው እንግዳው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ፣ ዛሬ በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት ያሉ አረጋውያን አባቶቻችን፣ በውጭው ዓለም የሚገኙትም አረጋውያን አባቶች፣(ሙት ወቃሽ አትበሉኝ እንጂ ከሁለቱም ወገን ፣ወደ እውነተኛው ቦታ የሄዱትን አባቶች) ጨምሮ፣ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነታቸውን ባለ መወጣታቸው ነው። አንዳንዶቹም ልክ እንደ ዛሬዎቹ ጥቂት ጳጳሳት መንበረ ፕትርክናው ቃል ስለተገባላቸው ነበር፣ በአንድ ልብ ፣ቅዱስ ፓትርያርኩ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለመንግሥት የጻፉትን ደብዳቤ ወደ ጎን ገፍተው የወደዱትን ያደረጉት። አንድ ትልቅ  ቁርጠኛ አባት ግን በይፋ ተቃውመው፣ “እኔ በዚህ ነገር አልስማማም “። ብለው በማለታቸው፣ ድምጻቸው በድምጸ ተዓቅቦ ተመዝግቦላቸው፣ ለታሪክ ትዝታ ጥለው አርፈዋል።

ከባለፈው ታሪክ “ጥሩ” ልምድ የቀሰመው የኢሕአዴግ መንግሥት እንደ ልማዱ የገዛ አባቶቻችንን አሰልጥኖ ለምርጫ አዘጋጅቶልናል። ለቤተ ክርስቲያናችንና ለብፁዓን አባቶቻችን ያላቸውን ንቀት በአደባባይ “ጳጳሳቱ አይረቡም” ሌላም ሌላም እያሉ ሲናገሩ እንኳን የማያፍሩ፣ በእውነቱ ከቤተ ክህነቱም ሆነ ከሌላ ጠያቂም የሌለባቸው “ነጻ ዜጎች ናቸው”።  መንግሥት በልዑካኑ ተጠቅሞ፣ የስድስተኛ ፓትርያርክ ማስመረጫ ደንቡንም በሚስፈልገው መልኩ ቀርጾ ፣ ለቤተ መንግሥቱ ያልተጠቀመበትን የዕድሜ ገደብ (ለፕሬዝዳንቱ ማለቴ እንደሆነ ይታወቅልኝ)፣ በመጀመሪያ አረጋውያኑን ከጨዋታ ውጪ አስወጣ። ብልጣ ብልጦቹ አባቶቻችን ደግሞ በድርብ ዜግነት ሽፋን ዋናውን የመንግሥት ዕጩ ጨምሮ፣ አንድ አራቱን አባቶች፣ ከምርጫ ውጭ አደረጉበት። ለጊዜው መንግሥትም ከእነርሱ መካከል በሁለተኛና ሶስተኛ ዕጩዎች እንዲረጋጋና፣ እንዲገፋበት ተገዷል። ባለፉት ሁለት ሶስት ድርድሮች፣ ልክ እንደ ዲፕሎማት ያዝ ለቀቅ እያደረጉ የተደራደሩት አባቶቻችንም፣ ድርድሩ ከመልካም ፍጻሜ የመድረስ ዕድሉ እየጨመረ ሲመጣ ያለ ይሉኝታና ፍርሃት፣ የሰላሙን ሂደት ለማደናቀፍ የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ምክንያታቸውን በመደርደር ላይም ይገኛሉ።

የሰላምና አንድነት ኮሜቴው የቅዱስ ሲኖዶስ አካሄድን ተመልክቶ ባወጣው መግለጫ ያልተደሰቱትና፣ የፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ ያደናገጣቸው የቤተ ክህነትና የመንግሥት ባለሥልጣናት ድርድሩ እየተካሄደ የሰጧቸው ቃለ ምልልሶች የመጀመሪያዎቹ አመላካች ማስረጃዎች ናቸው። ከዚያም በእነ ዲያቆን ኃይለጊዮርጊስና በ”ንቡረ ዕድ” ኤልያስ የሚወከለው መንግሥት በጥሩ መንፈስ የሰላም ድርድሩን ሲካፈሉ የነበሩትን የቅዱስ ሲኖዶስ ሰላም ልዑካን አስፈራርተው የሚያሳዝን መግለጫ ማውጣታቸው ሌላው ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ከዚያማ በውጭው ለም የሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያን ቁጣው ሲገነፍል፣ መንግሥት በግልጽ ርምጃ ወደ መውሰድ ገባ። የሰላም ልዑኩን ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁን አስሮ አንገላታ፣ አቋማቸውን እንዲለውጡ በግልጽ ጠየቀ። ሌላው የሰላም ልዑክም ከዚያ ያልተናነሰ ወከባ አጋጥሟቸዋል፣ ለእስርም ሊዳርጓቸው ዝግጅታቸውን ጨርሰው ሲያበቁ በእግዚአብሔር ቸርነት ወደ መጡበት ተመለሱ። ይህ ሁሉ ወከባ ለምን አስፈለገ?

እጅግ የምንወዳቸውና የምናከብራቸው አባቶቻችን ብዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ እንዲሁም ሌሎች፤ ታኅሣሥ 23 በተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ያሳያችሁት ቆራጥነት መንፈሳዊ ኩራት ሆኖናል። በርቱ!! እኛ በውጭም በሀገር ያለን ልጆቻችሁ እስከ መጨረሻው ከእናንተ ጋር አብረን እንቆማለን።

እዚህ ላይ አንድ አስተያየቴን መስጠት የምፈልግበት ጉዳይ አለ። ቅዱስ ሲኖዶስ የሰላምና አንድነት ኮሜቴው በሌላ እንዲተካና ኮሜቴው ለሌሎች አደራዳሪዎች ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ያለፈ ሚና እንዳይኖረው የተፈለገው ለምንድን ይሆን?? ለመሆኑ በእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያደጉ፣ በክፉም በደጉም ሰዓት ለቤተ ክርስቲያናቸው መስዋዕትነትን የከፈሉትን፣ ስንቱን የቤተ ክርስቲያን ገመና ሸፍነው የያዙ አባቶችን የሚያስመርጥ ሌላ አደራዳሪ ተገኝቶ ነው? ምንድን ነው፣ የሰላምና አንድነት ኮሚቴ ያጎደለባችሁ? ዕርቅ አውርዱ ስድስተኛ ፓትሪያርክ ለመምረጥ የምታደርጉትን ሩጫ አቁሙ ስለተባላችሁ ነውን? በምትካቸውስ የታሰቡት የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ይሆኑ? ወይስ የቤተ መንግሥቱ? ቤተ ክርስቲያን መዳኘት ያለባት በዓለማውያን እጅ ይሆን? ወይስ  እነ ፓስተር እከሌ ወይም ፕሮፌሰር እከሌ ወይም እነ አትሌት ወይም ራስ፣ ደጃዝማች ስላልገቡበት ይሆን ቅር ያላችሁ? ጥቂት የመንበረ ፕትርክና አላሚዎች የሰላሙን ሂደት ከመንግሥት ጋር በመሆን ሊያበላሹት ስለሆነ እባካችሁ አባቶቻችን ድካማችንንና የቤተ ክርስቲያንን ልጆች ጩኸት አሁንም አዳምጡ እላለሁ። 

ሌላው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ፣ በግልጽ ቋንቋ ለመናገር ፣ መንግሥትም ሆነ የመንበረ ፕትርክና አላሚዎች መቼም ቢሆን  ያሰቡትን ከማድረግ አይተኙም። እናንተም እኛም ልጆቻችሁ ለረጅም ጉዞ እንዘጋጅ። ብፁዓን አባቶቻችን ከመካከላችሁ ማን ምን እንደሆነ ታውቁታላችሁ። እኛ ምዕመናኑ እንኳን በሚገባን መጠን ገብቶናል። ከመሐከል ያሉትን  ጊዜና ሁኔታዎች በሚፈቅዱበት አካሄድ የሚገባውን ዕርማት ማድረግ ትችላላችሁ። ከሁሉ በፊት  ግን ከዘበኛው ጀምሮ የቤተ ክርስቲያኒቷን ጥሪት እየተመገበ ታማኝነቱ ለውጭ የሆነውን ሁሉ (የመንግሥት ቅጥረኛም ሆነ የሌሎች)፣ የሥራ ስንብት ወረቀቱን ስጡት። ቅዱስ ሲኖዶሱ ነጻ አየር እንዲተነፍስ አድርት። እነ አቶ ብርሃኔ እነ ማን ናቸው? ማን ቀጠራቸው? ከዚህ ቀደም አቡነ ጳውሎስ በሰጡት ይሁንታ ተጠቅሞ፣ መንግሥት በደንነት ክፍሉና በእነዚሁ “ዘበኞቻችን” በእናንተ ብፁዓን አባቶቻችን ላይ ያደረሰው ጉዳት ይረሳል ወይ? ለምን መንገዳችሁ ላይ እንቅፋት ተቀምጦ እያያችሁ ታልፉታላችሁ?  በአጠቃላይ ሕብረታችሁና አንድነታችሁ እንዳይሳሳ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጉ።

በውጭውም ዓለም የምትገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲሁ ለረጅሙ ጉዞ ተዘጋጁ። አቋማችሁ ግልጽ ይሁን። ስድስተኛ ፓትርያርክ ቢሾም አንቀበልም ብሎ ማለትን አትፍሩ። ከእናት ቤተ ክርስቲያን መለየት ሳይሆን እናት ቤተ ክርስቲያን በስልጣን ወዳጆችና በአር ባዮች መንገዷን እንዳትስት መርዳት ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ ሊመራ የሚገባው ከመንግሥት ምክር ቤት በሚወጣ መመሪያ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ነው። በመንፈስ ቅዱስ የማይመራ ሲኖዶስ የእናት ቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል ተብሎ ሊጠራ አይገባም። ፍርሃታችሁን አስወግዱ፣ ቢያንስ በውጭው ዓለም ያላችሁን የመናገር መብት ለበጎ ነገር ተጠቀሙበት። ከእናንተ ጋር አብሮ ተሰዶ ያለ የመንግሥት ሰላይ አያስፈራራችሁ። አጋልጣችሁ ላላችሁበት መንግሥት አሳልፋችሁ ስጡት። ሽፍንፍን ይቅር። እዚህ ላይ፣ ሀገር ቤት ንብረቴ ይወረስብኛል፣ የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ሀገሬ አያስገባኝም፣ ብለው የሚፈሩትን አይጨምርም። እነዚህ  ወገኖች መቼም ለራሳቸውም፣ ለቤተ ክርስቲያናቸው አይሆኑም። እሾሁ አንቋቸዋልና!

ትልልቆቹ እና ትንንሾቹ ማበራት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለቤተ ክርስቲያናችሁና ለአባቶቻችሁ እንደ አጥር ሁኑ። ዝምታችሁ ይብቃ።  ይህ ወቅት ለእኛ መፈተኛ ጥያቄ  አቅርቧል። መልስ ያሻዋል። አሁን!!

እስከ አሁን የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሳብ ያልሰጣችሁ አያተ ክርስቲያናት እባካችሁ ትልቅ ወንዝ የብዙ ጠብታ ውሃ ጥርቅም መሆኑን አስታውሱ። መንግሥትም ሆነ እኒህ “አባቶቻችን” በሰሙትና ባዩት ተቃውሞ ምንኛ እንደተረበሹ ከሚወስዷቸው ርምጃዎች ተረዱ። ያላችሁን ሃሳብም ይሁን ድጋፍ ግለጡ። አሁን የማይጠቅም ነገር የለም። ሲሆን ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ጠንክራ ባላት ምዕመናን ብዛትና መዋቅር ጥቅሞቿን ለማስከበር መንግሥትንና ፖሊሲዎቹ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ደረጃ ላይ ብትደርስ ምኞቴ ነበር። አሁን ግን መንግሥት አጥር አልፎ የቤተ ክህነቱን ደንብ ቁጭ ብሎ እስከ ማርቀቅ ደረሰ። ትልቅ ድፍረትና ንቀት ነው። ይህ በዚህ መቀጠል የለበትም። የኢሕአዴግ መንግሥት እኛ አልደረስንብህም እባክህ ልብ ግዛ። ሕዝበ ምዕመናኑን ወደ አልተፈለገ መንገድ አትምራው። ያለበለዚያ የመጨረሻህ መጀመሪያ መሆኑን እወቅ። የእኛ  ጥያቄ የቤተ ክርስቲያናችንን ዕጣ ፈንታ እኛ ብቻ እንድንወስን ተወን!! ምነው የራስን ጉዳይ በራስ መወሰን መብት የአንድ ወቅት መፈክር ብቻ ሆኖ ቀረ?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)