February 2, 2013

በኢ/ኦ/ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመን አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን የተማኅጽኖ ደብዳቤ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለዉ "ከሁሉም ግን ፍቅር ይበልጣል።"
(READ THIS ARTICLE IN PDF)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በውስጧ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር እንኳ ፍቅርን በማስቀደም በመፈቃቀርና በመከባበር በክርስቶስ ራስነት፣ በሐዋርያት አስተምህሮና እምነት መሠረት ላይ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ስታፋጥን ዘመናትን አስቆጥራ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እኛ ካለንበት ዘመን ደርሳለች። የቤተ ክርስቲያኗ ሐዋርያዊ ጉዞ በርግጥ ጥንትም ቀላል አልነበረም።
ሆኖም  በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟት ፈተናዎች በአመዛኙ ከዉጭ የመጡ እንደመሆናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ የእምነት አባቶች በጽናትና በሃይማኖት ተጋድሎ አልፈውት ዛሬ ታሪክ ሆኗል። የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያናችንም ከመንጋዉ እረኛ ስያሜ ጋር በተገናኘ በተለይም ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት እጅግ አሳዛኝ ሂደትን አሳልፋለች። ዛሬም የሚሰማዉ ሁሉ ፆሩ እንዳልበረደ ያመለክታል። ይህ የዉጭ ተፅዕኖ ብቻ ነዉ ለማለት እንዲከብድ የሚያደርገዉ ደግሞ አሁንም ከዚሁ የፈተና አዙሪት መዉጣት እንዳትችል የተደነቀረው ውስጣዊ መሰናክል መኖሩ ነዉ።


በፓትርያርክ ስያሜ መግባባት ጠፍቶ የሀገር ውስጥና ስደተኛ ሲኖዶስ በሚል አባቶቻችን መለያየታቸዉና ይልቁንም እስከመወጋገዝ መድረሳቸው ኅሊናችንን ሲፈታተነው ቆይቷል። ይህን የመለያየት መንፈስ ይሰብራል የተባለ የእርቅ ሰላሙ ውይይት  በዳላስ መጀመሩን ሰምተን መንፈሳችን ነቅቶ ፈጣሪያችን ፍሬዉን እንዲያሳየን ስንማፀንም ሰነበትን። የእርቀ ሰላሙ ዉይይት በይደር ተቀጥሮ ሳለ ውጤቱ ሳይታይ በሀገር ቤት ለፓትርያርክ ስያሜ እጩ መረጣ ብሎም ዝግጅት መኖሩን መስማት፤ የዚህች ቤተ ክርስቲያን ልጅ ነኝ ብሎ በጽናት ለሚቆም ኦርቶዶክሳዊ ሁሉ ምን ያህል አስደንጋጭና አንገት አስደፊ እንደሆነ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም። ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት ካህናትም ሆኑ ምእመናን የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ተጠብቆ ማየት ዋና ምኞታቸው ብሎም እፎይታ ስለሆነ ነው። ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን በቀጣይም አዳዲስ ገለልተኞች አብያተ ክርስቲያናትና መንፈሳዉያን ማኅበራት እንዳይፈጠሩም ስጋት አሳድሯል።

ዘንድሮ ሰላሳኛ ዓመቷን የምታከብረዉ፤ በዘመነ ስደት (ደርግ) በዓለም ዙሪያ ለተቋቋሙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ቀዳማዊት ፋናወጊ የሆነችው በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክስቲያን ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ትኩረቷን በኦርቶዶክሳውያን አንድነት ላይ ብቻ በማድረግ በዚህ ሀገር የሚኖሩ ምእመናንን አሰባስባ ቆይታለች፤ አሁንም በእምነት ጽናት ስለ አባቶች ኅብረትና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ትሰብካለች። ለዚህም ነው ከስድስተኛዉ ፓትርያርክ ምርጫ አስቀድሞ ሊታሰብበት የሚገባው በአባቶች መካከል የዶግማ ልዩነት ስለሌለ እርቀ ሰላም ይዉረድ፧ አንድነት ይቅደም የሚል ጥሪዋን ደግማ ደጋግማ የምታስተላልፈው።

«እርስ በእርሱ የሚቃወም መንግሥት አይጸናም» እንዳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ፍቅርና ትኅትናን ብሎም አንድነትን ለእኛ ለልጆቻቸዉ የሚሰብኩ አባቶቻችን እንደመሪያቸዉና እነሱም በሐዋርያነት እንደሚከተሉት ፈጣሪያቸዉ ቃልን በተግባር የሚገልጹ  መምህራን እንዲሆኑላትም ትሻለች። ከፍቅር የሚበልጥ አንዳች ነገር የለምና፤ ሥልጣንም ሆነ ፓርትርያርክነት። እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን በሙሉ ልብ አባት የምንለው፤ እርሱም በእኩል ዓይን ልጆቼ የሚለን የመንጋ መሪ እንፈልጋለን። በየብዙኃን መገናኛውና ማኅበራዊ መድረኮች የሚጥላላ፤ በየሄደበት በዚህችዉ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዓይንህ ላፈር እየተባለ የሚዘበትበት፣ የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ የሆነ አባት እንዲኖረንም አንመኝም። ለዚህም ነዉ በአባቶች መካከል እርቅ ወርዶ እኔ የአጵሎስ፣ እኔ የጳውሎስ፤ እኔ የኬፋ በሚል የተበታተኑት የአንዲት እናት ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ጌታችን «እረኛውም አንድ መንጋውም አንድ» እንዳለ በአንድ ጥላ ሥር አሰባስቡ የሚል ጥሪያችንን የምናስተላልፈው።

ብፁዓን አባቶቻችን፤ ዛሬ የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ውሳኔ በእናንተ እጅ ላይ ይገኛል። በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በጀኔቫው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተናገሩትን እኛም እንድገመውና ስለ እውነት ፍርድ    ካልተሰጠ « እግዚአብሔር እና ታሪክ ይፈርዳሉ። » ለውድቀቷም ሆነ ለልማቷ ከእናንተ በፊት የሚወቀስም ሆነ የሚወደስ አይኖርም። በቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ብሎም በምእመናን ኅብረት ከእናንተ በላይ የሚጠቀምና የሚከበር አይገኝም። ስለዚህም አሁንም ጥሪያችን ከእናንተ ላይ አትኩሯል። የተሸከማችሁት ኃላፊነት የምትገኙበትንም መስቀለኛ መንገድ ከእኛ ከትናንሾቹ ልጆቻችሁ በተሻለ መንፈሳዊ ዓይን እናንተ ታዩታላችሁ ብለንም እናምናለን። ቀደምት የሃይማኖት አባቶቻችሁ አባቶቻችን እንኳን የፓትርያርክነት ሥልጣን ቀርቶ የአንድ ገዳም አለያም ማኅበረ መነኮሳት አበምኔትነት ላለመቀበል ያደርጉት የነበርነዉን ሽሽት ከእኛ በላይ እናንተ ታዉቁታላችሁ። ስለ ትኅትናም ይሁን ኃላፊነቱን በመፍራት እምቢታቸዉ ጠንቶ ሲያስቸግሩም  በግንድ   እስከመታሰር እንደሚደርሱም ይዘነጋል ብለን አናስብም።     

በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት የተጀመረዉ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ዝግጅት ከፍጻሜ ሳይደርስ፤ ባለፉት ፓትርያርክ ዘመነ ፕትርክና ተጀምሮ የነበረውና አሁንም በሂደት ላይ ያለው የእርቀሰላም ጉዳይ እልባት ሳያገኝ የሚደረገውስ የፓርትርያርክ ምርጫ ጥቅሙ ለማን ነዉ? ተሰያሚዉ ፓትርያርክ እኮ በሙሉ ልቡ የሚቀበሉት ምእመናን ያስፈልጉታል። ለዚህም ነዉ ለአባቶቻችን ስጋታችንን እንድናሰማ የተገደድነዉ፤

ዘወትር የምናከብራችሁ ብፁዓን አባቶቻችን፣
ጭንቀታችን ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ጸንቶ እንዲኖር ነውና ይህንኑ ጭንቀታችንን በሚከተሉት ነጥቦች ስናጠቃልል ብፁዓን አባቶቻችንም ለዚህ ጭንቀታችን ከፍተኛ ትኩረት እንደምትሰጡት ሙሉ ተስፋ በማድረግ ነው።

ነጥቦቹም፦
1ኛ፤ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በመከፋፈል ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰዉ የጉዳት ጠባሳ እንዲሽር አባታዊ ብሎም መንፈሳዊ ኃላፊነታችሁን ለመወጣት ከሁሉም በላይ የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት እንድታስጠብቁልን እንጠይቃለን፤

2ኛ፤ ከምንም በላይ የተሰጣችሁን ሃይማኖታዊ ግዴታ በማስተዋል እርቀሰላሙ ሳይቋጭና የቤተ ክርስቲያን አንድነት ሳይመለስ ወደ ፓትርያርክ ምርጫ የሚደረገዉን ዝግጅት እንድትገቱ በትኅትና እንጠይቃለን፤

3ኛ፤ የመንፈሳዊ መሪ አባት ምርጫ ጉዳይ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሃይማኖት አባቶችና እንዲሁም የምእመናን ጉዳይ መሆኑን ከእኛ በላይ እናንተ ታዉቁታላችሁ። ስለሆነም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ውጭ የሚደረግ ጫና ካለ ይህን የመቋቋም መንፈሳዊ ጽናት እንድታሳዩ እንጠይቃለን፤

4ኛ፤ ከዓለም ዙሪያ  የሚቀርበው የካህናትና የምእመናን ተማኅፅኖ ሰሚ አጥቶ ሢመተ ፓትርያርክ የሚፈጸም ከሆነ እንደ ደንቀዙ፣ እንደ ደብረ ታቦሩና እንደ ቦሩ ሜዳ በጉባኤ ለሊቃውንቱ የመከራከሪያ ዕድል ተሰጥቶ የመጨረሻ ውሣኔ ያገኝ ዘንድ እናሳስባለን። 

5ኛ፤ ለእኛ ለልጆቻችሁ ያልታየ፥ ለእናንተ ለአባቶቻችን ብቻ የታዬ ካለ፥ ከሢመተ ፓትርያርክ አስቀድሞ በዓለም ዙሪያ ተበትና ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ሁኔታውን የሚያስረዳ ግብረ ኃይል ከመንበረ ፓትርያርክ ቢልካልን።

6ኛ፤ በተራ ቁጥር አምስት የተጠቀሰውን ለማድረግ ከወጭ አንጻር የማይቻል ሆኖ ከተገኘ በውጭ የምንገኝ ሊቃውንት፣ካህናትና ዲያቆናት በያለንበት ሀገረ ስብከት ባሉት ብፁዓን አባቶቻችን መሪነት ጉባኤ እንድናካሂድ ዕድሉ ቢሰጠን።

አንዲት ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በተመሠረተችበት የክርስቶስ ደም  ጸንታ እንደምንትኖር እናምናለን። ልዑል እግዚአብሔር አባቶችን ከፈተና፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመከፋፈልና ምእመናንንም ከመበታተን ይሰውርልን።

እረኛውም አንድ መንጋውም አንድይሁን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የጀርመን ሀገረ ስብከት ካህናት እና ምእመናን

14 comments:

Anonymous said...

"ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን በቀጣይም አዳዲስ ገለልተኞች አብያተ ክርስቲያናትና መንፈሳዉያን ማኅበራት እንዳይፈጠሩም ስጋት አሳድሯል።" የሚለው አረፍተ ነገር ጠጠረብኝ። እኔ አባታችን መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ቢመለሱ ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ነገር ግን የማንኛውም የቤተ/ክ ጉዳይ የመጨረሻው ውሳኔ የሲኖዶሱ ነው ብዬ ነው እማምነው። የሲኖዶስ ውሳኔ ብንስማማበትም ባንስማማበትም በፀጋ መቀበል ነው ያለብን። አባቶች ስለአንድነቱና እርቁ ከማናችንም ይልቅ ያስባሉ። የነዶ/ር መራዊ አካሄድ አደጋ አለው። ከመግቢያዬ ኮፒ ያደረግኩት ዐ.ነገር "ሲኖዶስ እኛ እምንለው እማያረግ ከሆነ ገለልተኛ እንሆናለን" የሚል ማስፈራርያ ያዘለ ይመስላል። እንዲህ ከተጀመረ ለወደፊቱ ሌሎች ታላላቅ አጀንዳዎች በተነሱ ቁጥር አባቶችን "እንዲህ እሚል ውሳኔ ካላሳለፋችህ... " እያልን እጅ እግራቸውን ልንይዛቸው ነው ማለት ነው። ይሄ አያስኬድም።

Anonymous said...

01/10/13
ይድረስ ለጀርመን የተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንልጆችበእግዚአብሔር ሰም ሰላምታዬን አቀርባለሁ።በወቅቱ ያለውን ችግር እንደ ማንም እንሰታችሁ መፃፋችሁ ባልከፋ ነገር ግን እርግጠኛ ባልሆናችሁት ጉዳይ በዶግማ አልተለያያችሁም የምትለዋ ጥቆማ ግን ምን ለማለት እንደሆነ ግልፅነት ይጎለዋል።ስለ እመቤታችን ስለ ቅዱሳኖች ስለ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት ያላቸው አስተምሮ ከዕውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ነው።የተሀድሶ መንፈስ አራመጆች መሆናቸውን መዘንጋት የለበትም።ታዲያ አፃፃፋችሁ ለማደባበስ ወይስ ለማተራመስ? እኛ አጠገባቸው የምንኖር ስለምናቃቸው ነው ለማያውቋቸው ግን የተሳሳተ መረጃ ማቀበለችሁን እንዳትረሱ
አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን አሜን

Unknown said...

ከላይ ስማችሁን እንጅ ግብራችሁን የሚገልጸውን ማንነታችሁን መደበቅ ያልቻላችሁት 2 አስተያየት ሰጭዎች ፤ ስለዶግማ መግለጽ የሞከርከው ፥ ለመሆኑ ዶግማ ማለት ምን ማለት እንደሆን የምታውቀው ነገር አለ ? የትኛው ነው ሥርአተ ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቀው ? በፓትርያርክ ላይ ሌላ አርትፍሻል የመንግሥት ካድሬን ፓትርያርክ ብሎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሁለት የከፈለው ነው ወስ በግፍ የተሰደዱት አባት ይሚመሩት ሲኖዶስ? ''ሲኖዶስ የሚወስነውን ሁሉ በፀጋ መቀበል ነው '' ያልከው ወገንም ተሳስተሃል። ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ ሲኖዶስ የሚወስነውን ውሳኔ እንድንቀበል የሚያዘን የቀኖና ሥርአት የለም። ለሕገ ወጥ የመንግሥት አገልጋይ ሲኖዶስ መታዘዝ በራሱ እንደ ፀረ ቤተ ክርስቲያንነት የሚያስቆጥር ነው። ስለዚህ እውነተኛ የሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ግን የወያኔ አገልጋይ ሁኖ እርቅና ሰላምን ረግጦ በጉልበት እየመራ ያለውን ሕገ ወጥ ''ሲኖዶስ'' በስሙ ብቻ እውቅና አንሠጠውም። የሚሾመውንም ''ፓትርያርክ'' አንቀበለውም። በማንና ለምን አገልግሎት እንደተሾመ ጠንቅቀን እናውቃለና !

Anonymous said...


አንተም ተው አንተም ተው: የሚል ዳኛ ጠፍቶ::
በሬውን ወሰደው: ከቀምበሩ ፈትቶ::

አለ ያገሬ ሰው!

እንዲያው ምን አለ አንዳቸው ቢሸነፉ?

Anonymous said...

አልሆነም አልሰላም: ሁለት አውራ አንድ ቤት:
አንዱ ተሸንፎ: ካላለ አቤት አቤት::

የሚባለውም እውነት ሆነ እኮ!

ለማን እንናገር ምን ብለን እንጻፈው?
ሞቶ አልነበረም ወይ ሞትን ያሸነፈው!

ኧረ ተዉ አባቶች ይሄ ደራ ይቁም:
መሸነፍ ማሸነፍ መሆኑን አታውቁም?

Forgive me said...

"be mejemeria le hegu sannegeza, endet new tiru abbat menefelegew?"

So called "Neutral/gleltegna" Churches, first follow the church cannon laws your self if you want others to follow the church's law. Our Lord taught us to teach by patience and example. I truly do not understand how those who do not follow the law try to tell others to follow the law. I do not understand. I do not understand how one can fight an enemy who is in his house from the outside? If you want the enemy to leave, go INSIDE AND FIGHT. This is what is missing today, NO ONE, wants to sacrifice (their lives, marriages, jobs, reputations, families, money, fame, education) and go IN (sereat / church admin order) AND FIGHT. This is true both spiritually (our church); socially; economically; and politically. We lack the true pride of our fathers who fought the true fight and won because they fought risking they can lose everything they have, we fight too but we want to keep the things I mentioned above (our livelihood). Our pride is NOT based on our fight to preserve the heritage of our church and country, but we have a superficial pride based on the achievements of our past, we pride on our history but seek not to make it ourselves just like our fathers... I am also guilty of this false pride, we do not realize the huge responsibility we have, and that history will judge us one day. When my 1 year old daughter grows up one day she might ask me, "Father you were alive during this terrible time in our church and country's history, what did you do?” Am I going to tell her I was a coward? Am I going to tell her I didn’t want to get involved because so and so was Patriarch and so and so was in government, will that be a good lesson for her? I do not know much, but I know that it's by sacrifice (even unto death) our church and country WAS established and CAN continue to exist, there is NO freedom of spirit and body without blood. Blood is received only on the battle field; the battle field is being within the church’s administration, this is one of the areas the devil fights us, avoiding it gives the devil SURE VICTORY…what is the use of joining the administration after there is peace if we failed this test ? Forgive me; it’s what I learned from my fathers. Lets all have faith and serve according to our grace and leave judgment at the door.

Anonymous said...

ይህ ደብዳቤ የዶር መራዊ ሣይሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በጀርመን ነው። የነ ዶር መራዊ የሚለው አባባል መሰሪነቱ ጉዳዩ የምዕመናን ወይም የህዝበ ክርስትያን አይደለም ለማለት የተፈለገ ይመስላል። ከዚህም በላይየተማጽኖ ደብዳቤውን ይዘት ሆን ብሎ ለመጠምዘዝ የተሰነዘረ ትችት ነው። ለእውነት ለንገርህ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተከርስትያን ከእናት ቤተክርስትያን መቼም አትለይም። ውሎ አድሮ እውነት በቤተክርስትያናችን መልሶ ሢነግሥ እንዳንት ያሉ የሃሰት መልክተኞች ቤተክርስትያናችንን ለቃችሁ እንደምትወጠ- እርግጠኛ ነኝ። እስከዛው ግን ለቤተክርስትያናችን አንድነትና ሰላም በጸሎት እንተጋለን።

Anonymous said...

ከቤተክርስቲያን አንድነት የሚቀድም ነገር የለም። በዚህ መሃል የሃይማኖት ልዩነት ያለ ለማስመሰል የምትጽፋ ሰዎች እባካችሁን ሁሉንም በየቦታው እንናገር። በውጭም ሆነ በሀገር ቤት የቤተክርስቲያንን ትምህርትና ሥርዓት የሚያዛቡትን ለማጥራት መፍትሔው የአባቶች አንድነት ነው። ከምንለያይበት ይልቅ አንድ የምንሆንበት ስለሚበልጥ ልዩነትን ለማጥበብ እንሲ ለማስፋት አንሞክር።በሁለቱም ወገን የየራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ወገኖች አይጠፉም። እውነታው ግን አብዛኛው ምእመን አንድነትን ፈላጊ ነው። ከየትኛውም ወገን የሚሰጠንን የመለያያ አጀንዳ ከማስተጋባት ብንንቆጠብ ቤተክርስቲያንን እንጠቅማለን እኛም በማናውቀው ጉዳይ ገብተን በመፈረድ ከመኮነን እንድናለን።

Anonymous said...

ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመረው በመንፈፍ ቅዱስ ነው የምንል የሲኖዶሱን ውሳኔ በመቀበል ለቀጣዩ በፀሎት መትጋት የቤተክርስትያንን አንድንት ያመጣል በተረፈ የመሰለንን ሁሉ የምንፅፍ ከሆነ የቤተክርስቲያን ልጆች ያደረገናል።
እግዚአብሔር ኢትዮጽያን ያስባት

Anonymous said...

I think there is simple solution for this why don't you choose Eritrean pope for the 6th Ethiopian Orthodox pope then God knows for the next.

Adam said...

እንደ ሚመስልኝ ኤርትራዊ ጳጳስ ቢመረጥ ኣይሻልም ነበር፤ ምክንያቱ ኣሁን ያለው ኣማኝ በጎሳ የተከፋፈለ ያለሱ ወይ ውገኑ ካልሆነ ሌላ ወገን መሾም ማይፈልግ ነውና ስለዚ ኣንድ ኑትራል የሆነ ወገን ኣምጥተህ ብትሾም ያንን ሁሉ ጥላቻ ያርፋል ቢየ ኣምናለው፤ ይህ ግን የኔ ሃሳብ ነው እንጂ ይእግዚኣብሔር ፍቃድ ማን ያውቀዋል፤ ሁልግዜ ይርሱ ነው የተሻለና የበለጠ፤፤

Anonymous said...

May our lord Jesus Christ bring our country & specially our church the much needed peace, reconcilliation & togetherness... It is only the Holy Trinity who can help us bring about peace & unity. Those of us who serve in the church know & are always reminded by the gospel of St. John (6:26) that we who partake in the covenent dwell in Christ & he in us. Knowing this, it is apparent that we are all one in Christ. The earthly power seem to have affected our fathers & hence our mother church that it make some of us silently sad. Let's be reminded of what our northern brothers (ofourse the Egyptians) have done and perhapse lean from them some of the strengths that Christians should have... we atually do not need to go that far..let's learn from our fallen fathers like our beloved martyr His Holiness Abune Petros!
Please, let us also stop rebuking each other and try to find ways of reconilliation of all Orthodox Christians as we are one. May the kindness of the Father, the love of the Son and the unity of the Holy Spirit be upon us all. And May God bless Ethiopia & Tewahido. Amen.

Anonymous said...

ወያኔዎችን መለማማጥ ይቁም!!!!!
ወያኔዎችን መለማማጥ ይቁም!!!!!
ወያኔዎችን መለማማጥ ይቁም!!!!!
ወያኔዎችን መለማማጥ ይቁም!!!!!
ወያኔዎችን መለማማጥ ይቁም!!!!!
ወያኔዎችን መለማማጥ ይቁም!!!!!

Anonymous said...

የዮሐንስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ 6:56
ሥጋዬን፡የሚበላ፡ደሜንም፡የሚጠጣ፡በእኔ፡ይኖራል፡እኔም፡በርሱ፡እኖራለኹ።
....
Just in case you did not understand in english what I'm driving at (forgive me for the typo s/b John 6:56 and not 6:26)
The point is made clearly but, my brother did not understand history of either the determination of the Egyptian christian brothers or the sacrifice His Holiness Abune Petros made for us all. This is not about WOYANE or any earthly entity but, about the preservation of our christianity and oneness.
Remember one fact... Haile-Silasie was there & perished, Mengistu was there & did not last... and now Woyane will go in due time! but, our heavenly Jerusalem (our mother Tewhido church) will live on forever and lets mend our differences and make a pleasant road ahead for her. Beloved brothers and sisters, do not dwell on the short lived earthly kingdoms & widen our differences but, let us help our lord dwell in us as John 6:56 instructs & become one in him and minimize or eliminate our differences.... make no mistake! this is not about woyane... woyane will pass too but, our lord & the mother Tewahido Churh won't!
kiristian maninim aylemametim... ante mogn atihun!
St. Paul affirms our ways when he talks to the Corinthians in his letter...
1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡2:14 & 15
ለፍጥረታዊ፡ሰው፡የእግዚአብሔር፡መንፈስ፡ነገር፡ሞኝነት፡ነውና፥አይቀበለውም፤በመንፈስም፡የሚመረመር፡ ስለ፡ኾነ፡ሊያውቀው፡አይችልም።
መንፈሳዊ፡ሰው፡ግን፡ዅሉን፡ይመረምራል፡ራሱ፡ግን፡በማንም፡አይመረመርም።
As for the rest,

2ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡6:24
ከማያምኑ፡ጋራ፡በማይመች፡አካኼድ፡አትጠመዱ፤ጽድቅ፡ከዐመፅ፡ጋራ፡ምን፡ተካፋይነት፡አለውና፧ብርሃንም፡ ከጨለማ፡ጋራ፡ምን፡ኅብረት፡አለው፧
let's follow our Lord and his deciples & resist the force of evil which is trying to diminish our Christian ways.

Glory be to the father and to the son and to the Holy spirit. One God. Amen.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)