January 16, 2013

ከዕርቀ ሰላም ይልቅ ለ6ኛ ፓትርያርክ ምርጫ ቅድሚያ የሰጠው የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ ተስፋዎችን አጨላሚ ሆነ

(ደጀ ሰላም፤ ጥር 8/2005፤ ጃኑዋሪ 16/2013/ PDF) በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና ከመነሻውም በውጪ ተጽዕኖ ሥር የወደቀው የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ እንደተፈራውም ዕርቀ ሰላሙን አሽቀንጥሮ ወርውሮ 6ኛ ፓትርያርክ በመፈረሙ ላይ ጸንቷል። በብፁዕ አቡነ አብርሃም በተነበበው መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው ቅ/ሲኖዶሱ ያደረገው ሙከራ ያልተሳካው በአሜሪካ የሚገኙት አባቶች ባቀረቧቸውና ከዕርቁ ጋር በማይገናኙ ሌሎች ምክንያቶች የተነሣ ነው። ይህ “ከእርቁ ጋር የማይገናኝ” የተባለው ምክንያት አሜሪካ ያሉ አባቶች የሚያነሧቸው “ፖለቲካዊ ጥያቄዎች” መሆናቸውን ደጀ ሰላም ትረዳለች። በተለይም ለብዙዎቹ የቅ/ሲኖዶስ አባላት የተነገራቸው ምክንያት “አገር አቀፍ ዕርቅ” ይውረድ ይላሉ፤ ውጪ አገር አሉት ፖለቲከኞችም አብረውን ካልገቡ ይላሉ የሚለው መልዕክት ነው።


ዛሬ በቅ/ሲኖዶሱ ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሳይሆን ከሰሞኑ በተለያዩ ዜናዎች ስማቸው ተደጋግሞ ሲጠቀስ በሰነበተው በብፁዕ አቡነ አብርሃም የተነበበው መግለጫ የብዙዎች ምእመናንና ካህናትን ተስፋ እንደሚያጨልምና ወደ ቀቢጸ ተስፋም እንደሚከታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ጥበብና አስተዋይነት በጎደለው፣ ከሃይማኖታዊነት ይልቅ ፖለቲካዊ አንድምታው ጎልቶ በሚሰማው በዚህ ውሳኔ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከ20 ዓመታት በኋላ ድጋሚ ልታገኘው ትችል የነበረውን የአንድነት መንፈስ ተኮላሽቷል። ለዚህም ከታዋቂ ሰባኪ ነን ባዮች እስከ አንዳንድ “ልጅግር” ጳጳሳት፣ ተሰሚነት አለን ከሚሉ ጦማርያን እስከ ፖለቲከኞች ያደረጉት ርብርብ በርግጥም ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ እንዳትሆን የሚሠራው አካል እስከ ደም ጠብታ እንደተዋደቀ አሳይቷል፤ የብዙዎችንም አሰላለፍ በርግጥ ተረድተንበታል። የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይፈርዳል!!

አንዳንዶቹ ጳጳሳትና ብሎገሮች እንዳሉት በርግጥ ለጳጳሳቱ ደሞዛቸውን የሚከፍላቸው አሜሪካና አውሮፓ፣ አረብ አገርና በሌሎች ዓለማት በስደት የሚገኘው ምእመን አለመሆኑ ብቻ የሚያስንቀው ከሆነ አገር ቤትም እያለ ጠቀም ያለ ገንዘብ መክፈል የማይችለው ደሃ ምእመን በእነርሱ ዘንድ ሞገስ የለውም ማለት ነው? በዚህ ደሃ ሕዝብ ገንዘብ ቤታቸውን አልሰሩምን? የሚንደላቀቁትስ በዚሁ ደሃ ምእመን ጥሪት አይደለምን? በሌላ ጊዜ ለዕረፍትም ለመዝናናትም የሚሆዱባቸው የአሜሪካና አውሮፓ አገራት ምእመናን አይሰሙ/ አይሰማቸው መስሏቸው ይሆን? ለማንኛውም በዚህ ውሳኔ አንድነምታ ዙሪያ ተከታታይ “ምልከታዎች” ማቅረባችን ይቀጥላል። ደጀ ሰላማውያንም ሐሳባችሁን እንድትሰጡ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።

የዚህን መግለጫ ሙሉ ቃል ከዚህ (PDF) ማንበብ ይቻላል።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)