· የተከሳሽ ጠበቃ እና ዐቃቤ ሕግ የክርክር ማቆሚያ ንግግር አድርገዋል::
· ውሳኔው ለየካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሯል::
· “የአርማጌዶን ቪሲዲ እውነትን
መሠረት አድርጎ ከፍ ላለ ሞራላዊ ዓላማ የተሠራ ዝግጅት እንጂ የስም ማጥፋት ተግባር አይደለም፤ አዘጋጁም ሥራውን የመሥራት ችሎታ
እና ሥልጣን አላቸው፡፡ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች የግል ተበዳይ [ከሳሽ
በጋሻው ደሳለኝ] አጉራ ዘለል መሆኑን በበቂ አላስተባበሉም፤
የማስተማር ችሎታ እና ሥልጣን እንዳለው ያቀረቡት አሳማኝ ማስረጃ የለም” (የተከሳሽ ጠበቃ)::
(ደጀ ሰላም፣ ጥር 20/2004 ዓ.ም፤ January 29/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ በአርማጌዶን ቪሲዲ የተነሣ
የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ የመከላከያ ምስክሮቹን ለፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ
ችሎት አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ተከሳሹ ከቆጠራቸው አምስት የመከላከያ ምስክሮች መካከል በችሎቱ የተሰማው የሦስቱ የምስክርነት ቃል ሲሆን
ቀሪዎቹ ሁለቱ ምስክሮች ከሦስቱ የተለየ የማያስረዱ በመሆኑ ከምስጋና ጋራ ተሰናብተዋል፡፡ የግራ ቀኙ ክርክር የተጠቃለለ ሲሆን ዐቃቤ
ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቃ የክርክር ማቆሚያ ንግግራቸውን ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡ መዝገቡን መርምሮ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት
27 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በ8፡00 ሰዓት ቀጠሮ ተይዟል፡፡









