December 27, 2012

የጉባኤ ካህናት ወምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን ሰላም ጥሪ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ግልጽ ደብዳቤ 
ታኅሳስ ፲፯ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ
ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ዋሽንግተን ዲሲ
ለብፁዕ አቡነ ናትናኤል
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ እና የአርሲ  ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ
አዲስ አበባ: ኢትዮጵያ
ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት - የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
በያላችሁበት
ጉዳዩ: የተጀመረውን የእርቀ ሰላም ከፍጻሜ ስለማድረስ: ሀገራችን ኢትዮጵያ በሶስቱ ሕግጋት ማለትም በሕገ ልቡና በሕገ ኦሪትናበሕገ ወንጌል ሀልዎተ እግዚአብሔርን በማመንና ለሥርዓቱ በመገዛት ኖራለች:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንኑና ክርስትናን በቀደምትነት ከተቀበሉት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ናት::  ቤተ ክርስቲያኒቱ በሳለፈችው ሶስት ሺህ ዘመናት ጊዜ ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ያለውን ኅብረተሰብ አስተሳስራ የፍቅርና የአንድነት ሰንሰለት ሆና ቆይታለች:: እንደዚሁም ለመላው ዓለም ይልቁንም ለአፍሪካውያን ሁሉ መኩሪያ የሆኑትን ኮኖዊ : መንፈሳዊና ማበራዊ ሀብታትን አበርክታለች::  እያበረከተችም ትገኛለች:: 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር ለ1600 ዓመታት ስትሠራ ከኖረች በኋላ ከቅዱስ ርቤ ዘመን ጀምሮ በብርቱ ሲደከምበትና ሲጸለይበት የነበረው ራስን የመቻል ጉዳይ በእግዚአብሔር ቸርነት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጸሎትና ብርቱ ጥረት በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግት ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ከራሷ ልጆች ሊቀ ጳጳሳትንና ፓትርያሪኮችን መርጣ ለመሾም በቅታለች::  

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ማርቆስ ከተቀመጡ አበው ጋር በመመካከር በመንበረ ተክለሃይማኖት  የራሷን ልጆች መሾም ከጀመረች ወደ 60 ዓመት ሊሆነው ነው:: በነዚህ ጊዜያት የቤተክህነት አስተዳደሩ እየተጠናከረና እየሰፋ የሄደውን ያህል በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ላይ ጥቁር ነጥብ የጣሉ ከፍተኛ ችግሮችም ተከስተዋል::  ከነዚህም ችግሮች መካከል በዋናነት ላለፉት ሃያ አመታት የቆየው የአባቶች በአስተዳደመለያየት ተጠቃሽ ነው። ይህም ሁኔታ ብጹዐን አባቶች: ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን : ካህናትና ምዕመናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቀጣይ የቤተክርስቲያናችን ሉዓላዊ ሥልጣን ታፍሮና ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባን አመላካች ነው::

አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ በሀገር ቤትና በውጭ ባሉት አባቶች መካከል የተጀመረውና ቅዱስ ፓትርያሪኩ ካረፉም በኋላ የቀጠለው የእርቀ ሰላም ድርድር  በቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችና እውነተኛ ተቆርቋሪዎች ልብ ዘንድ ትልቅ ተስፋ ጭሮ ነበር::  በተለይም በቅርቡ በዳር ወር መጨረሻ በሰሜን አሜሪካ ዳላስ ከተማ ለ3ኛ ጊዜ የተካሄደው ድርድር በምልተ ጉባኤ ውሳኔ ይሰጥባቸዋል የሚባሉ ፍሬዎች የተጠበቁበት ነበር ::

በዚህ መካከል በሀገር ቤት ያለው ሲኖዶስ የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት ሳይፈጸም የላካቸውን የሰላም መልዕክተኞች ሳይጠብቅና ሪፖርት ሳይሰማ ወደ ቀጣዩ  ስድስተኛ ፓትሪያርክ ምርጫ ሂደት መሄዱ ታላቅ ድንጋጤና ሀዘን ፈጥሮብናል ::

ብጹዓን አባቶቻችን ሆይ !
ከዚህ ቀደም በወርኀ ኅዳር 2005 ዓ/ም ለእናን ግልጽ የተማጽኖ ደብዳቤ እንደገለጽነው; ይህች ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፤ ከሃያ ዓመት በላይ በልጆቿ መለያየት ሠላም አጥታ ትገኛለች ብዙ ከባድ ጠንቆችም ተጋርጠውባታል።  ገባያነ ሰላም የሆናችሁ: የፍቅርና የመተሳሰብ ትምህርት አስተማሪዎች የምትባሉት አባቶች ይህንን የአስተዳደር ልዩነት ባለመፍታታችሁ ምክን የካህናት አንድነት ፣ የምእመናን ሕብረትና ሰላም ጠፍቶ ምእመና ለነጣቂ ተኩላ ተጋልጠው የጠባቂ ያለህ እያሉ ይገኛሉ።  በአባቶቻችን መለያየት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተጎድታለች፤ ምዕመናኖቿ ቀቢጸ ተስፋ ላይ ወድቀዋል::  አንተ ዐለት ነህ በዚህች ዐለት ላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እመሰርታታለሁ” የተባለላችሁ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታዮች ሊቃነ ጳጳሳት፡ለናንተ በተሰጠች ዐለት በሆነችው  ትምህርተ ወንጌል እና ሥልጣነ ክህነታችሁ ላይ የተመሠረተችውን ቤተ ክርስቲያንን ከሚያሸብሩ የሲኦል ደጆች ትጠብቋት ዘንድ፡
1.              በሀገር ውስጥና በውጭ ያላችሁ ብጹዓን አባቶች ፥ ከሁሉም በላይ፥ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ በመስጠት  ለቤተ ክርስቲያናችን ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንመጣ የመለያየቱ ዘመን እንዲያበቃና ለዘመናት የነበረው አንድነታችን እንዲመለስ እንድታደርጉ፣
2.            የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት እልባት ሳያገኝ: እንዲሁም በቀጣይ ቀጠሮ በእንጥልጥል ላይ እያለ በሀገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለመሾም አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ የእርቀ ሰላሙን ጥረት አደጋ ላይ የሚጥለው ስለሆነ ይህን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም በታላቅ ተማጽኖ እንለምናለን።
3.            በሀገር ቤትም ሆነ በውጭውም ዓለም የምትገኙ ብፁዓን አባቶች ለእርቀ ሰላሙ እንቅፋት የሆኑትን ቅድመ ሁኔታዎች ተመልሳችሁ በማጤን በአደጋ ላይ ላለችው ቤተ ክርስቲያንናእር ሰላሙን ስኬት በታላቅ ተስፋና ጉጉት እየጠበቀ ላለው ሕዝበ ክርስቲያን በመራራት የእርቀ ሰላም ሂደቱን ለማሳካት ከጸሎትና ኃዘን ጋር ጊዜያቸውን፥ ገንዘባቸውንና የሚቻላቸውን ሁሉ በመስጠት አስተዋጽኦ ያደረጉትን በጎ አድራጊዎች ም በመቁጠር እንዲሁምአንድነትና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠትና አስፈላጊውንም መስዋዕትነት በመክፈል ፥ ተሸንፎ በማሸነፍ ፥ ታሪክ እንድትሠሩ በአክብሮት እንጠይቃለን።
4.             ከሀገር ውጭ ተሰደው ያሉት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ሀገራቸው በክብር እንመለሱ እንዲደረግ
5.              በፍትሐ ነገሥት፤ አንቀጽ 9 ቁጥር 338፤ "ከተወገዘው ወይም ከተለየው ጋር የተነጋገረ ወይም ከነርሱ ጋር የጸለየ ከቤተ ክርስቲያን ይለይ።" በሚለው ድንጋጌ መሠረት በሁለቱም በኩል የተላለፈው ውግዘት ልዩነቱን እያስፋፋና በብጹዓን አባቶች ፣ በካህናትና በምዕመናን ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ስለሆነ ውግዘቱ በአስቸኳይ እንዲነሣ እንዲደረግ፤
6.            ይህ መለያየት የተከሰተው በእናንተው ዘመን እንደመሆመጠን የሰላምና አንድነት መፍትሄውም በእናንተው ዘመን : በእናንተው አማካኝነት ይፈጸማል ብለን እናምናለን::  ስለዚህ በሃይማኖትና በአስተዳደር አንድ የነበረችውን ቤተክርስቲያን እንደነበረች እንድታስረክቡን በአክብሮት እንጠይቃለን::
7.             እናንተም ሆናችሁ እኛ ከወላጆቻችን የወረስነውን በጎ ነገር ለትውልድ የማስተላለፍ የታሪክ ግደታ አለብን። በመሆኑም ቀጣዩ ትውልድ ከእናንተ ከፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም ይሁን ከእኛ ከካህናትና ምዕመናን የሚጠብቀውና መረከብ ያለበት አንት ሃይማኖት፣ አንዲት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትርያርክ፣ መሆኑ በግልጥ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በቀጣዩ  የሰላም ጉባኤ ቤተክርስቲያኒቱንና መላውን ሕዝበ ክርስቲያን ማዕከል ያደረገ መፍትሔ እንዲሰጥ፤  እንዲሁም ይህ የአስተዳደር ልዩነት አድጎ ወደ ከፋና ሃይማኖታዊ ልዩነት እንዳያመራ አሁኑኑ ዘላቂ መፍትሔ  እንዲፈለግለት ብጹዓን አባቶቻችንን እንማጠናለን
8.            በመጨረሻም ብጹዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ መርቆሬዎስም ከሁሉም በላይ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተና ያለዎትን የውሳኔ ሀሳብ ለህዝበ ክርስቲያኑ በራስዎ አንደበት እንዲያስረዱልን በታላቅ ትህትና እንለምናለን ::
የእግዚአብሔር ሰላም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን
ፍቅርና አንድነት ለመላሕዝባችን ይሁን፡፡ አሜን !

ከጉባኤ ካህናት ወምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን ሰላም
ታኅሳስ ፲፯ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

6 comments:

Anonymous said...

የተንጸባረቀው "አባ መርቆርዮስ ይመለሱ" የሚል ነው:: እባካችሁ የቤተክርስቲያን አንድነት ማለት የእኚህ አባት ወደ ስልጣን መመለስ አይደለም:: ይህ የተቃዋሚ ጎራዎች የያዙት ስትራተጂ ነው:: እውነት ለመናገር አባ መርቆርዮስን የማይፈልግ ህዝብ እጅግ ብዙ ነው:: የእርሳችው መመለስ ልዩነታችንን ያሰፋል እንጂ አንድነትን አያመጣም::ስልጣንንና አንድነትን ለይታችሁ እዩ:: አዲስ ፓትርያርክ ቢሾምም የቤተክርስቲያንን አንድነት ማምጣት የሚቻልበት ብዙ አማራጭ አለ:: ያጣነው ነገር ቢኖር መንፈሳዊነቱን ነው:: አባቶች የፓርቲና የቢዝነስ ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ ቤተክርስቲያን መምጣታቸው ነው ችግሩ::

Anonymous said...

የተከበሩ አስተያየት ሰጭ; የተቃዋሚና የደጋፊ ጎራ የሚለውን እዚህ ምን አመጣው? የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከሁለትና ከዚያም በላይ ተከፋፍላ እየታመሰች የሚትገኘው ፓትርያሪክ መርቆሪዮስ ያለአግባብ በፖለቲካ ውሳኔ እንዲለቁ በመደረጉ መሆኑን አያውቆም ይሆን ? ደግሞስ ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ወደ መንበራቸው እንዲመጡ አይፈለግም የሚሉት የትኛውን ህዝብ ነው ? ሊያወሩ የፈለጉት አማራጭስ ለምን ይሄ ብለው አይናገሩም ? በመጨረሻም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሃገሩና በሃይማኖቱ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ መጠየቅ "የተቃዋሚ ጎራ" የሚል ስያሜ መስጠት እርሶም "የተላላኪ ጎራ" የሚል ስም አያሰጠኝም ይላሉ ?
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

Anonymous said...

ጉዳዩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፓትርያርክ አይደለሁም እስካላሉ ድረስ ፓትራሪክ ናቸው የሚሾሙትም ጳጳሳት በኢትዮጵያ ባሉ አባቶች አሜን ብለው ተቀብለዋል ፕትርክናቸውን ውስጣቸው ይቀበለዋልና ፤ እና ነገሩ የርሳቸው የግል ጉዳይ ሳይሆን የቀኖና ቤተክርስቲያንና የአሚሪካው በስደት ላይ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ እና የምእመናንም ጉዳይ እንጂ። ሌላው አባ ጳውሎስ ከሞቱ በኋላ ለምን ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵ ስልክ ደውለው ያወራሉ? አያችሁ የተዋህዶ ልጆች ከዚህ ላይ ማስተዋል ያስፈልጋል ወያኔ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ ነገሩን ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ጨርሰውት ነበር ። ዋናው የቤተክርስትያናችን ጉዳይ የጳጳሳት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው በዘረኝነት የተለከፉትንም እስከመጨረሻው እንፋለማቸዋለን!!!።

Anonymous said...

የእግዚአብሔር ሰላምና ፍቅር ከሁላችን ጋር ይሁን፣ በይቅርታውና በቸርነቱ አምላካችን አይለየን፣ እንደስራችን ሳይሆን እንደምህረቱ ይሁንልን። ብዙ አስተያየቶችን፣ መግለጫዎች በየጊዜውና በየቦታው እየተሰጡ ይገኛሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን (ተገደውም ይሁን በፈቃዳቻው ከኢትዮጵያ የወጡት - እርሳቸው፣ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት አባቶች ከሁሉም በላይ ልዑል እግዚአብሔር እውነቱን ያውቃል) በፓትርያርክነት ስያሜ ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ናቸው። ትልቅ እንቆቅልሽ የሆነው ለምን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለማረጋጋት ድምጻቻውን በአደባባይ መሰማት እንዳልተቻለ ነው። መግለጫና አስተያየት ሰጪዎችም ለምን ይህን ነገር ችላ እንዳልንው ግልጽ አይደለም። ቅዱስነታቸው አባታችን ናቸው፣ እንዲህ ገራ ስንጋባ ቢያንስ ቃለ ቡራኪያቸው ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ከሁላችንም በላይ ይውቁታል። ፈጣሪያችን እኮ በማንኛውም ጊዜ “አባታችን ሆይ” ስንለው ይሰማናል ይመልስልናል፣ አይተወንም፣ የትም አይጥለንም። መንጋውን የመጠበቅ፣ የማጽናናት፣ የመምከር፣ የመባረክ ኃላፍነት በቅድሚያ የፓትርያርክ አባታዊና ክርስቲያናዊ ግዴታ መሆኑን ለቅድስነትዎ ማሳሰብ እንደ ድፍረት ሳይቆጠር፣ የክርስቶስን መንጋዎች የሆነውን በአደባባይ ወጥተው ድምጾትን በማሰማት ቢባርኩንና ቢመክሩን፣ እውነቱን ቢገልጹልን የሚሻል አይመስሎትም? መፍትሄው በይበልጥ በእጅዎ እና እርስዎ ዘንድ እንዳለ ይታመናል። አምላክ ሁላችንንም ይታረቀን። አሜን!

zerubabel ketema said...

እባካችሁ የጉዳዩንና የልዩነቱን መሰረት አቅጣጫ ለማሳት አትሞክሩ፤ አሁን ቤ/ክርስቲያን ለተከፈለችበት ምክንያት የሆነው ሳይታመሙ ታመሙ ተብለው ከመንበራቸው እንዲሰደዱ የተደረጉት የብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጉዳይ ነው መጀመሪያ ይህ ስህተት ይታረም ከዛ ሁሉም ነገር ቀላል ነው፤ሌላው አቡነ መርቆሬዎስ ይናገሩ ድምጻቸውን እንስማው የሚለው ነገር ግርም ይለኛል ምን እንዲናገሩ ነው የምንሻው ሁሉንም ነገር እኮ አወቅነው ታምራት ላይኔ (የቀድሞ ጠ/ሚኒስትሩ) ከመንበራቸው አባረሩዋቸው ይሄ የአደባባይ ምስጢር ነው ይልቅስ የሳቸው ዝምታ ትምህርት ሊሆነን ይገባል በሸላቾቹ ፊት ዝም እንዳለው አምላክ በቃ ሁሉንም ችለው ዝም አሉ ይገርማል በእውነት ይህ የሳቸው አርምሞ የሚገርምም የሚደነቅም ነው፡፡ አባቶች የሰላም አምላክ የሆነውን የክርስቶስን መስቀል ይዛችሁ የሰላምን በር አትዝጉ፤፤

zerubabel ketema said...

እባካችሁ የጉዳዩንና የልዩነቱን መሰረት አቅጣጫ ለማሳት አትሞክሩ፤ አሁን ቤ/ክርስቲያን ለተከፈለችበት ምክንያት የሆነው ሳይታመሙ ታመሙ ተብለው ከመንበራቸው እንዲሰደዱ የተደረጉት የብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጉዳይ ነው መጀመሪያ ይህ ስህተት ይታረም ከዛ ሁሉም ነገር ቀላል ነው፤ሌላው አቡነ መርቆሬዎስ ይናገሩ ድምጻቸውን እንስማው የሚለው ነገር ግርም ይለኛል ምን እንዲናገሩ ነው የምንሻው ሁሉንም ነገር እኮ አወቅነው ታምራት ላይኔ (የቀድሞ ጠ/ሚኒስትሩ) ከመንበራቸው አባረሩዋቸው ይሄ የአደባባይ ምስጢር ነው ይልቅስ የሳቸው ዝምታ ትምህርት ሊሆነን ይገባል በሸላቾቹ ፊት ዝም እንዳለው አምላክ በቃ ሁሉንም ችለው ዝም አሉ ይገርማል በእውነት ይህ የሳቸው አርምሞ የሚገርምም የሚደነቅም ነው፡፡ አባቶች የሰላም አምላክ የሆነውን የክርስቶስን መስቀል ይዛችሁ የሰላምን በር አትዝጉ፤፤

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)