December 23, 2012

"ቅድሚያ ለእርቀ ሰላም!" (የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ)


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
የተከበራችሁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችን፣ በቅድሚያ ቡራኬያችሁ ይድረሰን። ቤተ ክርስቲያናችን ለሁለት አሥርት ዓመታት በፈተና ውስጥ እንድትቆይ ያደረገውን የልዩነት ግድግዳ አፍርሶ አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትርያርክ፣ አንድ አስተዳደር እንዲኖራት ለማድረግ የተጀመረውን የእርቀ ሰላም ዓላማ በመደገፍ ልዑካንን በመሰየም የጀመራችሁት ሂደት አስደስቶናል። ነገር ግን የእርቀ ሰላሙ ሂደት ሳይጠናቀቅ ወደ ፓትርያርክ ምርጫ ጉዞ መጀመሩ በእጅጉ እንድናዝን አድርጎናል።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በሰንበት ት/ቤት ውስጥ የምንገኝ ወጣቶች አብዛኛው ዘመናችንን ያሳለፍነው ቤተክርስቲያናችን  በሁለት ሲኖዶስ ተከፍላ የልዩነት፣ የውግዘት እና የመራራቅ ባዕድ ሥርዓቶችን ስናስተናግድ ነው። ይህም በሰንበት ት/ቤት ተሳትፎ ለቤተክርስቲያናችን የሚገባውን አገልግሎት እንዳንሰጥ ትልቅ መሰናክል ሆኖ ቆይቷል። ቢሆንም ጊዜው ደርሶ የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት ትልቅ ተስፋ ሰጥቶን ነበር። ነገር ግን በተቃራኒው እየተከናወነ ያለው የፓትርያርክ ምርጫ ጉዞ የተቀረ ዘመናችንን በተስፋ እና በበለጠ መነሳሳት እንዳንጓዝ እያደረገን ይገኛል።
በተለይም እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የምንገኘው የቤተክርስቲያን ልዩነት በእጅጉ ገዝፎ በሚታይበት አኅጉር በመሆኑ የእርቀ ሰላሙ ሂደት መደናቀፍ የቤተክርስቲያናችንን ችግር ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ እንደሚጨምረው ለመገመት አያዳግተንም። በእርቀ ሰላም ጉባኤያቱ ምክንያትም የተጀመረውን ወደ አንድነት የመምጣቱን የተስፋ ጭላንጭልን አክስሞ ለሚቀጥሉት የማይታወቁ አያሌ ዘመናት የምእመናንን አንገት የሚያስደፉ ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚችልም ግልጽ ነው።
የቤተ ክርስቲያን አንድነት ወደ ተሻለ የአገልግሎት ምዕራፍ አሸጋግሮን በልዩነት ምክንያት ያልተነኩ ዘርፈ ብዙ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም እየተሰናዳን ባለንበት ወቅት ከእኛ አልፎ ለልጆቻችን የምናወርሰው የመከፋፈል እና የመለያየት ሥርዓትን በድጋሚ የምናስተናግድበት አቅም ለማግኘትም እንቸገራለን።
ስለዚህ ፍጹም በሆነ የልጅነት መንፈስ የሚከተለውን መልእክት ለማስተላለፍ እንወዳለን፦
1)   የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት ሳይጠናቀቅ ወደ ፓትርያርክ ምርጫ ጉዞ በመጀመሩ በእጅጉ አዝነናል። የቀጣይ የአገልግሎት ዘመናችንንም በተስፋ እንዳንጓዝ እንቅፋት ሆኖብናል። ስለዚህ ለተተኪ ልጆቻችሁ ስትሉ የእርቀ ሰላሙ ሂደት እንዲጠናቀቅ እንድታደርጉ በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም እንጠይቃለን።


2)  እንደ ቀደሙት አባቶቻችን ለቤተክርስቲያን እና ለመንጋችሁ ስትሉ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ከሆነ ተፅዕኖ በጸዳ ሁኔታ መክራችሁ የእርቀ ሰላሙን ሂደት ለውሳኔ እንድታበቁ እንማጸናለን።

3)  የተፈጠረው የአስተዳደር ልዩነት ተወግዶ ቤተ ክርስቲያንን ወደ አንድነት ሊያመጣ የሚችል ጥንቃቄ የተሞላበት የመፍትሄ ውሳኔ እንድትወስኑም አደራ እንላለን።

አምላካችን እግዚአብሔር የተፈጠረውን መለያየት አስወግዶ እና የቤተ ክርስቲያን አንድነትን ወደ ቀድሞ ቦታው መልሶ በአንድነት እንድናመሰግነው ያበቃን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።

ህዳር 13/2005 ዓ. ም
በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ
ሰሜን አሜሪካ

ግልባጭ:
  • ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  • ለሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት
  • ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት በያሉበት ፣
  • ለኢትዮጵያ የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት ፣
  • ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት ፣
  • በካናዳ፣ በአፍሪካና አና በአውሮፓ ለሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች ፣
  • ለሰላም እና አንድነት ጉባኤ፣
  • ለመገናኛ ብዙኃን በሙሉ።
6 comments:

Anonymous said...

The letter is timely and great. I just hope it doesn't fall into deaf ears. This is such a tough time for us. We have to stay strong in prayer, hope for the best. And no matter the outcome we have to remain calm and cool. We can't defeat evil with evil.

Anonymous said...

ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ከእግዚአብሐር የተሰጣቸውን ኃላፊነት የሚወጡበት መሠረታዊ ሀሳቦችን የያዘ ታላቅ መልእክት ነው፡፡ በፁአን አባቶች ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ለመንጋቸው ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሲሉ ተማጽኖውን እንደሚያዳምጡ እምነታችን ጽኑ ነው። እናንተም በዚህ ብቻ እንዳትቆሙ ታላቅ አደራ አለባችሁ፤ ጉዳዩ እጅግ በጣም አስጊ ነውና። ዕርቀ ሰላም እስኪ ወርድ ድረስ ብፁአን አባቶችን መጎትጎታችሁን አታቋርጡ። ኢትዮጵያ ካሉት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አውታሮች ጋር በመተባበርና ሥራችሁን በማቀነባበር ቀናውንና ሰላማዊውን መንገድ ሁሉ ግፉበት። ብፁአን አባቶች በዕርቀ ሰላም የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት መልሰው እንዲገነቡ ኢትዮጵያ ያሉትም የሰንበት ትምህርት ቤቶች ድርሻቸውን በመወጣት አባቶችን በሙሉ አጥብቀው እንደሚያሳስቡ ይጠበቃል። እናንተም አበረታቷቸው። ቸሩ አምላክ ይለመነናል።

Anonymous said...

የእርቀ ሰላሙ ሂደት መደናቀፍ የቤተክርስቲያናችንን ችግር ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ እንደሚጨምረው ለመገመት አያዳግተንም። በእርቀ ሰላም ጉባኤያቱ ምክንያትም የተጀመረውን ወደ አንድነት የመምጣቱን የተስፋ ጭላንጭልን አክስሞ ለሚቀጥሉት የማይታወቁ አያሌ ዘመናት የምእመናንን አንገት የሚያስደፉ ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚችልም ግልጽ ነው።

Anonymous said...

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካህናትና ምእመናን በሙሉ።

ባለፉት ሃያ አመታት ቤተክርስቲያን የተከፈለችው ሃገር ውስጥ ባሉና በፈረንጅ አገር ባሉ ብቻ አይደለም። ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያና የኤርትራ ተብላም ተከፍላለች። ስለዚህ አሁን በሚደረገው የእርቀሰላም ውይይት ውስጥ አሥመራ የሚገኙ ካህናትም እንዲካፈሉ በትህትና አሳስባለሁ።

ሙሉጌታ

Anonymous said...

አንድ ጓደኛዬ ደወለና ሳናስበው የኢትዮጵያ ሲኖዶስና ፓትሪያርክ ጉዳይን ተመልክተን ስንነጋገር "ውክልና" በሚለው ሃሳብ ተዋጥን። ሁለታችንም ስሜታዊ እንዳንሆን ስለተፈራራን ውጤቱን ወደ ትምህርታዊና መሆን የሚገባው ወደሚለው ድምዳሜ ደረስን፡
1- አንድ ወይም ከዚያም በላይ የሆነ ተወካይ/ዮች ተጥሪነታቸው ለምዕላተ ጉባኤው/ ሲኖዶስ/ ወይም ስብስብ ይሆናል
2-አንድ ወይም ከዚያም በላይ የሆነ ተወካይ/ዮች ውክልናው ለአንድ ለተወሰነ ጉዳይና ለተወሰነ ጊዜ ይሆናል
-አንድ ወይም ከዚያም በላይ የሆነ ተወካይ/ዮች በማንኛውም ጊዜ ለወከለው አካል ፍፁም ተገዢ ነው።
3- አንድ ወይም ከዚያም በላይ የሆነ ተወካይ/ዮች በተወከለበት ጉዳይ ላይ ለወከለው አካል የደረሰበትን ጉዳይና ስለነበረው ሁኔታ ከማስረዳት በስተቀር የግሉን አሳብ በማፍለቅም ሆነ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል አስተሳሰብ ማፍለቅ ፍጹም ተልዕኮውን እንዳልተወጣ ይቆጠራል
4- አንድ ወይም ከዚያም በላይ የሆነ ተወካይ/ዮች ከተወከለበት ጉዳይ ወጪ ሊያስወጣው የሚችል ሁኔታ እንዳይፈጠር በጥንቃቄ ውክልናውን መምራት አለበት
5- አንድ ወይም ከዚያም በላይ የሆነ ተወካይ/ዮች ከላይ እንደጠቆምኩት ለተወከለበት ጉዳይ ከመግለጽና ለሚነሱ ጥያቄዎችም መልስ ከመስጠት ባሻገር በወከለው አካል ላይ የአስተሳሰብ/ የሀሳብ ተፅዕኖ ለመፍጠር መሞከር ፍጹም ትክክል ያለ መሆን ብቻ ሳይሆን የአሰራር ብልሹነትንም ያጋጥማል።
6- አንድ ወይም ከዚያም በላይ የሆነ ተወካይ/ዮች ውክልናው በማንኛውም ጊዜ በወከለው ሀይል የሚለወጥ ወይም የሚፈርስ ነው።
ይህ ካልሆን ግን፤ ስርአት ማጣት ካልሆነም ተክለ-ሰውነተኛ መምጣት ግድ ነው።

WONDWOSSEN said...

Let us defeat our "Fear". make sure we are ready to tell our enemy(the devil) it's time to leave our church alone, this is our time to stop the devil once for all. The Devil work so hard over twenty years while we(the belivers} sleeping. This is our time to wake up do something. This my suggestion or solution let us break our silence. Every one who cares about our church must involve and be a part of the process. GOD BLESS ETHIOPIA.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)