December 21, 2012

ፖለቲካዊ ፓትርያርክነት፤ የዘመናት ጉስቁልና


(ቀሲስ ወንድምስሻ አየለ/ PDF):- ታሪክ የአስተዋዮች መሠረት ነው፡፡ ትናንትን ቸል ያለ ስለማንነቱ ካለማወቅና የሌሎች ማንነት ላይ ካለው ንቀት ወይም ጥላቻ ጋር የተያያዘ ስህተቶችን ያበዛል፡፡ ስለዚህም የፓትርያርክነትን ዳራ የመረመረ በፓትርያርክ ሹመት ዙሪያ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትን ለመድገም ሲፈልግ ከማንነት ጋር፣ ከፍትሕና ሰብአዊነት ጋር የተያያዘ ስህተቶችን ለመሥራት ወስኖ መሆን አለበት ብሎ መጠርጠር ተገቢ ነው፡፡ ሃይማኖት ሰብአዊነትን ወደ ፈጣሪ ክብር መጥራት እንጂ ሌላ ምንም አይደለምና፤ እንስሳዊም ሳይንሳዊም፣ ፈላስፋዊም አይደለም፤ ሰው ሆኖ በፈጣሪ መፈጠር ብቻ የሚበቃው መጠራት፡፡

 ታሪክ፦
1.      ዘመነ ኬልቄዶን 5 መቶ //- ከሰዎች ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝን በመምረጥ ላይ የታየ ልል ምርጫ ከመለካዊ~ ሮማ በተጨማሪ ኦርቶዶክሳውያኑን ሰማዕትነትንና ብልጣብልጥነትን ያቀላቀለ፣ ንጹሐንን በተጥባበ ነገር አሳልፎ ለመከራ የሰጠ ርጉም ዘመን ነው፡፡  ይኸው የዶግማችን ልዩነት ግልጥ ሳይሆን ከፋፍሎን ቀርቶአል፡፡
2.     ዘመነ መሳፍንት ወነገሥታት 17 -20 መቶ //- ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋ ሰማያዊ ሲሆን ምድራዊውን ተግባር መባረኩዋ ሳይፈለግ ተፈልጎ ወገን ማደራጃ፣ ጠላት መፍጃ አድርገዋት ተጠቅመውባታልና የዛሬውን የዘረኝነት ጦስ መሪ ተዋናይ ተደርጋ ለማስፈረጅ ህሊናቸውን ሸጠዋል፡፡ ያላመነውን ለማጥመቅና ሙስሊሙን ለማስተዳደር ሲባል መንፈሳዊ ወግ ይዞ መቅረባቸው የዘመኑ ፍልስፍና ቢሆንም የመሳፍንቱና የነገሥታቱ ፍርድ ሲጎድል ሐዋርያውያኑ እንዳይናገሩ በይሉኝታና በጎዶሎ ጥብዐት መታፈናቸው ለዛሬ በጉልህ የሚጠቀስ ታሪክ እንዳይነበብ ወይም እንዳይጻፍ ሆኖአል፡፡
3.     ደርግ፡- ሀገሩንና ሕዝቡን ያላወቀው ካወቀም የናቀው ‹‹ ትውልድ›› የዴሞክራሲ ስም ጣፍጦት ተግባሩን ሳያጣጥመው በደም የተጀመረው ዘመን ፓትርያርክን ገድሎ ጀምሮ ዘመኑን ሙሉ በደም ተጨማለቀ፡፡ ግን በእውነት ፍጹም መነኩሴ ለመምረጥ የበቃ ዲሞክራሲያዊ ወኔ ይዞ ቀረበ፡፡ ‹‹ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ከወዲያኛው /ከጠላቴ ጋር ነው›› በሚለው ፍልስፍና የታወረው ወታደራዊ ጁንታ ባለርዕዮተዓለም ተብሎ ሳይንስንና መንፈሳዊነትን ካልመራሁ በማለቱ ሀገርን አዋረደ፤ ወገኑን አጎሳቆለ፡፡
4.     የወያኔ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት፡- ፍትሕ ማጣትን ያመፀ/የወየነ/ የተባለለት ‹‹ ትውልድ›› ወገንተኛ ሕወሓት ሀገሪቱን በብሔርተኝነት አናቁሮ እየገላገለ፣ በሃይማኖት ስም አቀያይሞ ‹‹እያቻቸለ›› አልሆንለት ሲል ደግሞ የአንድነት ምክንያት ያላቸውን ስስ ብልቶች እየነካካ /ባንዲራ፣ የብሔረሰቦች ቀን፣…/ ለማግባባት ሲሞክር የሃይማኖት ጉዳይ ግን የማይታረቅ ፀብ ይዞበት ቀርቶአል፡፡ ይህም የሚያሳስበው ጉዳይ አይመስልም፡፡ ሌላው ሁሉ ምድራዊ ነውና አጀንዳው ሁሉ በፍልስፍናና በሳይንስ ምስክርነት ወደ ዕርቅ ይመጣል፡፡ ያልተሳካለትና የማይሳካለት ግን ምንጩም ሆነ ፍጻሜው ሰማያዊ የሆነ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ጋር ከፖለቲካው ጋር ለመደራደርና ለመቀራረብ የሚሞክሩ የእምነት ተቋማት መኖራቸው ‹‹ ሀሳባቸው ምድራዊ፣…›› የተባሉት ፖለቲካ ፈጠር ድርጅቶችን አልዘነጋም፡፡ የተሻልን ነን የሚሉት የመድብለ ፓርቲው ፍሬዎችም /ተቃዋሚዎች/ ጊዜው እስኪመቻቸው ሃይማኖትን ወያኔን የመውቀሻና የተቆረቆርንልህ ዐውዳዊ ጥሪ ቢያደርጉትም ሀሳባቸው ፍትሕን የማያመጣው ሊበራሊዝም/ ኒዮሊበራሊዝም ስለሆነ ለሃይማኖት የሚጠቅም ነገር አይጠበቅባቸውም፡፡ ይልቁንም ጥቂት ተሰሚነት ያገኙ በመሰለቻቸው ቅጽበት ራሳቸውን መግዛት ተስኑዋቸው እንደ 1997 አጋጣሚ እየፈለጉ በሕዝብ ደም ለሥልጣን የሚሽቀዳደሙ ዓይነት ናቸው፡፡ ይሄም ያም በሚያደርጉት ርብርብ ተባብሶ ቤተ ክርስቲያንንን ስደተኛና ሕጋዊ የሚባሉ ፖለቲካዊ መሠረት ያለው ግን ዶግማና ቀኖና የተጠቀሰለት ልዩነት አስከመወጋገዝ አስከተለ፡፡ ያም ሆኖ በብዙዎች ትግል ወደአንድነት ሊመጡ ሲቃረቡ ግልጥ ፖለቲካዊ ቀኖና ወጣ፤ ‹‹ 5 ብለን 6 እንጂ 4 አንልም›› የሚል፡፡ ‹‹ፍቅር ከሕግ ሁሉ በላይ ነው›› የሚለውን ጠቅሶ ለዕርቁ ቅድሚያ እንደመስጠት ‹‹ሁሉም ከሕግ በታች ነው›› በሚለው ፖለቲካዊ ሕግ ተተካ መሰለኝ፡፡ እሺ ወያኔስ /ወቅ/ አቡነ መርቆሬዎስን ጠላቸው እንበል፡፡ ታዲያ ለምን ያለፓትርያርክ አንኖርም! ወይስ ለሥልጣኑ ጎመጀን! ፓትርያርክን ለመምረጥ በድምፅ ብልጫና ከመነኩሴ ውጪ እንዲሆን ማድረግስ ከፖለቲካ ዓላማ የተለየ ምን ትርጉም አለው! ፍፁም እምነት ቢኖርማ ኖሮ በሰው የተመረጡት የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ላይ 4 ባዶ ዕጣ አስገብተን ‹‹ሦስቱንም ባይፈልጋቸውስ!›› ብሎ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ መትጋት ይቻል ነበረ፡፡ ኤድያ!

ዛሬ ፖለቲከኞቹም ለሃይማኖት የሚሰጡትን ነጻነት ሙሉ በማድረግ ቢያንስ ከደርግ ያላነሰ ተግባር ሊፈጽሙ ሲገባቸው የሚታየው ወከባውና ሸፍጡ በራሳቸው የማይተማመኑ ዝንጉዎች መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡ ሃይማኖተኞቹም በአቦይ ስብሐትና በመሰሎቻቸው ንግግሮች ‹‹የማይረቡ›› ተብለው ሃይማኖትን ለማዘለፍ የበቃን ነንና ምን መናቅ እንደቀረን አላወቅሁም እንጂ የምናሳያቸው ጥበብ ነበረን ብዬ አምናለሁ፡፡

ፖለቲካ የለሽ ሃይማኖትና ሃይማኖት የለሽ ፖለቲካ
ፖለቲካና ሃይማኖት ሁለቱ ሥልታዊ ትብብር ከማድረግ በተጨማሪ ሌላም አንድነት ሊፈጽሙ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ቢሆንም መለያየት ግን ይችላሉ፤ በጋራ ርስታቸው በሕዝብ ላይ ድርሻን በመደራደር፡፡

ሃይማኖት የለሽ ፖለቲካ- ይህ በዲሞክራሲያዊነት ስም የሚያቀነቅኑት ነው እንጂ ሃይማኖት የለሽነት /secular/ በራሱ ሃይማኖት ነው፡:  በተለይም በአብያተመንግሥቱ ምሥጢራትን ለመመርመር ቢቻል ከርኩሳት መናፍስት አምልኮ ጀምሮ ልዩልዩ የማይጨበጥ ሥርዓተእምነቶችን እንደሚያካሂዱ አዲስ ቁምነገር አይደለም፡፡ በግልጥ መንግሥታዊ ሃይማኖት ያላቸው ሀገራት ብዙ ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ብዙ የተሸለ ዲሞክራሲያዊነትም ሆነ ብልጥግና ላይ የሚገሠግሱ አሉ፤ በተቃራኒው ክፋት እየሠሩም፡፡ ሩሲያ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ግብፅ፣ ቱርክ፣ አርመን፣ ሌሎች ዐረብ ሀገራት፣ ግሪክ፣ ኦስትሪያ፣ ቫቲካን፣ ወዘተ፡፡

ፖለቲካ የለሽ ሃይማኖት-  ይኸ የግድ የሆነና በሃይማኖት ስም የሚካሄድ ፖለቲካን በግልጥ መወቀስና መገታት የነበረበት ይመስላል፡፡ እነወርልድ ቪዥንና መሰሎቹ የነጫጭባዎቹ ወረራ ከእነሱም የተኮረጀው ሀገርኛው የኢንቨስተሮቹ መሣሪያዎች ሃይማኖትን ለማስፋፋት የሕዝብን ስነልቡናና ሰብአዊ ፍላጎቶች የሚፈታተን መመሪያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መኖራቸው ዓላማቸው ከሃይማኖት ይልቅ በሃይማኖት ካባ የተሸፈነ ፖለቲካ እንዳለ ይገልጣል፡፡ ኦርቶዶክሳዊው ምእመን ‹‹ ኩሩ›› ሊባል የሚችል አስተሳሰብ ስለሚታይበት ለፖለቲከኞች ስጋት ነው፡፡ ኩሩነቱ ከክፋት ያይደለ በክርስቶስ ነጻ ከመውጣቱ የተነሣ ማንንም መቼም አለመፍራቱ፣ ከሞት ይልቅ ስህተትን ኃጢአትን ስለሚሸሽ ነው፡፡ ይህን ጠባይ ከየዋህነት ጋር ይዞ ስለሚበዛ የሃይማኖት መሪዎች ፖለቲካዊ ሀሳቦችን ሳይቀላቅሉ ሊመሩት ያስፈልጋል፡፡ ይልቁንም ከምድራዊ ክርክር/ትግል የተለየ የእልፍኙ ‹‹ አቡነ›› ጠላትን ሁሉ እንደሚያንበረክክ፣ በፍቅርም ያለዐመጽ እንደሚያሸንፍ መልሰው ከልሰው ካላስታወሱት ፈታኙ አጀንዳ እውነት ይሆናል፡፡ በሀገር ጉዳይ የመንግሥትን ትእዛዝ ተረድቶ ሕዝቡን ማስተባበር ተገቢ ሲሆን ማኅበራዊ፣ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በሃይማኖት መሪዎች በኩል እንዲታገዝ የሚፈልጉ ፖለቲከኞች ሃይማኖትን ፖለቲካዊ እያደረጉት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የዕለት ሥራዋን በራሱዋ እንዳታከናውን ማወክም ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ የሚሰማት ድሀም ሆኖ፣ ጤና አጥቶም፣ ራሱን ዝቅ አድርጎም እድናለሁ ቢል ከድህነት ወለል በላይ ወይም በታች መሆኑ፣ ዕድሜው መርዘም ማጠሩ፣ አለያም ሰብአዊ ክብሩ አለመከበሩ የራሱ ምርጫ ነው፡፡ ቤተመንግሥታቸው ኦርቶዶክሳዊ እንዳይገባ የሚታገሉ ምንደኞች ሃይማኖተኛው ላይ ለመሠልጠን /ባለሥልጣን ለመሆን/ እየፈለጉ ግን ሃይማኖቱን እየዘለፉበት እንምራህ ሲሉ በብረት ጡንቻ በመታመን ሃይማኖትን ለማስጣል ካልሆነ በቀር ሃይማኖትና መንግሥት የተለዩበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ከሆነም የራሱዋን ሃይማኖታዊ ሥራ ስትሠራ የፈቀደ ይከተላትና ከድህነትም፣ ከኃላቀርነትም ሆነ ከሙስና ጋር ማን በእውነት እንደሚታገል ያኔ ይታይ ነበረ፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ ቃል ሲናገርም እኮ ሊተጋገዙበት የሚችሉበትን ሀሳብ ጭምር በጣፋጩ ወንጌል ባለመጠቀማቸው በፖለቲካዊ ድሪቶ ቃላት ሰዉ በፖለቲካ መድረኩም ሊሰለች ይችላል፡፡

ይህ መለያየት በግልጥ እንዳይደረግ ነው እንግዲህ የፓትርያርኩ ተፈላጊነት፤ የፖለቲካው ጉዳይ አስፈጻሚ እንዲሆኑ፣ ጥዋት ማታ በልማትና ሰላም፣ ዲሞክራሲና ከድህነት መውጣት ስም ሕዝቡን ከወንጌልና ቀኖናዊነት እንዲርቅ፣ ለዘብተኛ /ሊብራል እንዲሆን፣ በሃይማኖት ዐውድ አጀንዳ ያልሆኑት ጉዳዮች የጠዋት ማታ ርእስ ማድረግና መጽናኛ ማሳጣት፣ወዮ!

ፓትርያርክነት፣ ቤተክህነታዊነት፣ ሐዋርያዊነት
ይቺ ቤተ ክርስቲያን ማለትም ምእመን የዛሬው ሠልፍ የመጣባት ግራ ገብቶት ግራ ከሚያጋባ ሥልጣን ፈላጊ ፖለቲከኛ ይመስለኛል፡፡

ቤተክህነቱ የአስተዳደር ሥራውን ምሁራዊ አድርጎ ሃይማኖትን ከፖለቲካ የለየ ሐዋርያዊ ዕቅዶችን ካላስተባበረ አደጋው ለሀገርም የሚያሰጋ ነው፡፡ በፖለቲካ ስም ከሚካሄዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓትንና ሕይወትን የማፈራረስ ተግባራት ተጽእኖአቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይበዛ ሳይንሳዊና ሃይማኖተኛ ልሂቃንን በስፋት ማካተት አለበት፡፡

ፓትርያርክ  የሁሉ አባት ነው፡፡ ቸሩ ክርስቶስም ሁሉን በአባትነት እንዲጠብቅ መላልሶ የተለማመጠው እረኛ ነው፡፡ እንዴት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደሚታዘዝ በፍርሐት የሚጠነቀቅ እንጂ ንጉሥን /መንግሥትን ተመክቶ ቤተክህነታዊ ሥራን በማጨማለቅ የሕዝብ ይሁን የቁሳቁስ አባትነቱ ግራ እንዳያጋባን ራሱን፣ ሀገርንና ቤተክርስቲያንን ከጉስቁልና በመጠበቅ ድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

ሐዋርያት የተባላችሁ/የሆናችሁ ካህናት/መምህራን ግን ፍቱን መድኃኒት ናችሁ፡፡ ምድራዊ ሥልጣን፣ ክብርና ቁስ ያስጎመጃቸው ቤተመንግሥታዊና ቤተክህነታዊ ሰዎች የተናቀውን መምረጣቸውን በቃልም በተግባርም ማሳየት ይጠበቅባችኃል፡፡ ‹‹ እኔው ራሴ እረኛ እሆናቸዋለሁ›› ያለ ጌታ ከእናንተ ጋር ነውና ‹‹ ሙታንን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዉአቸው›› ፡፡ ሕዝቡ ቃሉን ባለማወቁ ጠፍቱዋልና፡፡

4 comments:

Anonymous said...

ምድራዊ ሥልጣን፣ ክብርና ቁስ ያስጎመጃቸው ቤተመንግሥታዊና ቤተክህነታዊ ሰዎች የተናቀውን መምረጣቸውን በቃልም በተግባርም ማሳየት ይጠበቅባችኃል፡፡ ‹‹ እኔው ራሴ እረኛ እሆናቸዋለሁ›› ያለ ጌታ ከእናንተ ጋር ነውና ‹‹ ሙታንን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዉአቸው›› ፡፡ ሕዝቡ ቃሉን ባለማወቁ ጠፍቱዋልና
good thought, kalehiwot yasemalne

Anonymous said...

Sol.
Yetedebalekebish Timesyalesh...
Wey Kirstyan Honesh tenageri wey selmesh kebetachin Tifi... Min yemilut mezebarek new. You are coming to read Dejeselam and strt bleaming the writter, dejeselam and we the readers. If you are a son of church... think as son of church or go away as our Father said go away from us.

Anonymous said...

በጣም ጥሩ ትንተናና ሃሳብ ነው :: ይሁናና ቤተ ክርስቲያን ያለብችበት ሁኔታ እንድምናየው ከሆነ እጅግ ቆራጥ ሃይማኖተኝነትን የሚጠየቅበት ወቅት ነው :: እናም ከዚህ ቀውስ ለማውጣት ብሎም በትክክለኛዋ ሐዋርያዊት መንገድ ለማስገባት ምን ይደረግ ነው ጥያቄው ይሄ ደግሞ የሁሉንም የእምነቱ ተከታዮች ውሳኔና ተሳትፎን የሚመለከት ነው :: ቤተ ክርስቲያን የምድራውያንን መንግሥታት ከማገልገል ወጥታ ንጉሰ ሰማይ ወምድር የሆነውን አምላክዋን እንዴት ታገልግል ? ለምድራውያን ባለስልጣናት ከመገዛት ወጥታ ለእግዚአብሔር እንዴት ትገዛ ? የምድራውያንን ገዦች ትዕዛዝ ከማስፈጸም ወጥታ የሞተላትን የክርስቶስን ትእዛዝ እንዴት ታከናውን ? አሁን ያለው ችገር ላማንም ለማን ስውር አይደለም :: በቤቷ ውስጥ ላለነው ለእና ቀርቶ በውጭ ላሉትም ግልጽ ነው ::ምናልባት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ከሚያሰሩ ጠላቶች የገንዘብ ፍቅር ካሰጠማቸው ሃይማኖተኞች ባዮች ወይም የዘር የስልጣን የጥቅም ፖለቲካ ካዘቀታቸው የሃይማኖትና የስጋው መሪዎች በስተቀር ለሁሉም ግልጽ ነው :: ስለዚህ ምን እናድረግ ነው ጥያቄው :: ይሄ መንግስት ግለበጣ አይደለም መንግስትን መቃወምም አይደለም :: ለቤታችን ማሰብ እንጂ የምንቃወሜውም የእምነት መሪዎቻችንን ነው :; ስርዓተ ቤተክርስቲያን ይከበር ነው :: ስለዚህ ደጀ ሰላምና ደጀሰላማዉያን ምን እናድርግ ?

Anonymous said...

ኦርቶዶክሳዊው ምእመን ‹‹ ኩሩ›› ሊባል የሚችል አስተሳሰብ ስለሚታይበት ለፖለቲከኞች ስጋት ነው፡፡ ኩሩነቱ ከክፋት ያይደለ በክርስቶስ ነጻ ከመውጣቱ የተነሣ ማንንም መቼም አለመፍራቱ፣ ከሞት ይልቅ ስህተትን ኃጢአትን ስለሚሸሽ ነው፡፡ ይህን ጠባይ ከየዋህነት ጋር ይዞ ስለሚበዛ የሃይማኖት መሪዎች ፖለቲካዊ ሀሳቦችን ሳይቀላቅሉ ሊመሩት ያስፈልጋል፡፡

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)