December 28, 2012

ከማይቀበሉት ፕትርክና የሚቀበሉት ምንኩስና ይበልጣል!


(ዘሚካኤል ለደጀ ሰላም እንደ ጻፉት/ READ IN PDF)፦ 
ለጊዜው የምኖረው በሰሜን አሜሪካ በመሆኑ እና የቤተክርስቲያንን መለያየት ውጤት የግፍ ቀማሽ ምዕመን በመሆኔ ብዙ ጊዜ የቤተክርስቲያንን ነገር ባሰብኩ ጊዜ እና ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች የጠፉ በመሰለኝ ጊዜ እንደ ምዕመን ማድረግ ያለብኝን ሁሉ አድርጌ ምን አልባት መፍትሔ ያልመጣው ችግሩን በጥልቀት ካለመመልከት ይሆናል እልና የተሰማኝን ልጽፍ ብዕሬን ከወረቀት አገናኛለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ የማልጠቅም ባሪያ ሆኜ ሳለሁ ለአባቶች ጳጳሳት ይህን ማስረዳት ምጥን ለእናት እንደማስተማርም ፤ ያለ አግባብ ወደ ላይ መፍሰስም እየሆነብኝ የጻፍኩትን እቀዳለሁ፡፡ አሁን ግን የምመኘውን የቤተክርስቲያን ሰላም እና አንድነት በምንም ዋጋ ቢሆን ልንገዛ የሚገባበት ትልቅ ወቅት በመሆኑ እና ከየአቅጫው የሚሰነዘሩ ምክሮች፣ አስተያየቶች፣ ልመናዎች ወዘተ እንዳለ ሆነው የእየሩሳሌምን ጥፋት እያዩ ከመቀመጥ መጻፍን መረጥኩ፡፡


ቅድስት ቤተክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ በታሪክ ውስጥ ወሳኝ ጊዜ እንደሆነ በተለያየ ቋንቋ ብዙዎች ገልጸውታል፡፡ ለምን ወሳኝ ጊዜ ተባለ ቢሉ አጭር መልሴ ነገን በትላንት እና በዛሬ መነጽር ለክቶ ለተመለከተው መልሱ እጅግ በጣም ግልጽ ስለሆነ ነው፡፡ ባለንበት በሰለጠነው ዓለም ነገ ሊሆን የሚችለውን ለመገመት ትላንት ለአንድ ፤ ለአስር አሊያም ለሃምሳ ዓመት ሲሆን የነበረውን ክንውን መርምረው የዛሬን ደምረው ነገ እንዲህ አይነት ነገር ስለሚጠብቀን እንድህ አይነት ቅድመ ዝግጅት ያስፈልገናል ይላሉ፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት በመጀመሪያው 5፣10፣15፣20 ዓመታት በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን ጥፋት መመርመር ለሚቀጥሉ 5 ወይም 10 ዓመታት ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ቀላል ያደርገዋል፡፡

ዛሬ የቤተክርስቲያንን ሰለምና አንድነት በምንም ዋጋ ቢሆን ለመዋጀት በቤተክርስቲያን ላይ ይህንን በማጣት ላለፉት 20 ዓመታት የሆነውን እና ነገ ሊሆን የተዘጋጀውን በጥልቀት መመርመር መልካም ይመስለኛል፡፡

ባለፉ ሃያ ዓመታት በቤተ ክርስቲያን

 • ሁለት ፓትሪያሪክ በአንድ ላይ የኖረበት እና ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍሎ የኖረበት ነው፡፡
 • ቤተክርስቲያን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመኖችዋን ያጣችበት ነው (የሕዝብ ቆጠራ ውጤትን ይመልከቱ)
 • አስተዳደራዊ ድክመቶች ገዳማቱን እና የአብነት ት/ቤቶችን ደረቅ ምንጭ ማድረጉ
 • ቅጠል ሽጠው መቀነታቸውን ፈትተው ቤተክርስቲያንን ለትውልድ ለማቆየት ከሚጥሩ ምዕመናን የሚሰበሰብ ገንዘብ በጥቂት ሙሰኛ የአስተዳደር ሰዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደቀልድ የሚዘረፍበት
 • የፕሮቴስታንታዊ ተሃድሶ ወረራና ለሁለት በመከፈሉ የፈጠረው ምቹነት ሁኔታ ቤተክርስቲያንን በቁሟ የራሱ ለማድረግ የተጓዘው እረጅም ጉዞ
 • ከአክራሪ እስልምና የመጣባትን ጥቃት ዳግም እንዳይከሰት መከላከል ያልቻለችበት ሁኔታ
 • በቤተ ክርስቲን የዘር መከፋፈል የነገሰበት እና የተባባሰበት ፤ በሃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች የጥቂት ጎሳ አባላት የሆኑበት ዘመን ነው
 • ስለ መስቀል የሞቱ ሳይሆን በገንዘብ ለገንዘብ የሚሞነኩሱ ፣ እራሳቸውን የሸጡ መነኮሳት እንደ አሸን መፍላታቸው
 • የቤተክርስቲያን ካህናት፤ ሰንበት ት/ቤቶች እና ምዕመናን ወንጌልን ለማስፋፋት ከሚያጠፉት ጊዜ ይልቅ ስለ ዕርቅና ስለ ቤተ ክርስቲያን ችግር በመጨነቅ የሚያወጡት ጉልበት ፣ ገንዘብ ፣ ዕውቀት መብዛቱ
 • ከሁለት መከፈል አልፎ ገለልተኛ በሚል ሶስተኛ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎ ሀገሮች የተጀመረ ከመሆኑ በላይ በጳጳሳት ሳይባረኩ በግል የሚከፈቱ “አቢያተ ክርስቲያናት” መስማት የተለመደ ሆኗል
 • በሰሜን አሜሪካ የተጀመረው መከፋፈል ወደሌሎ አህጉሮች ተዛምቷል
 • በፕሮቴስንታንታዊ ተሃድሶ ውስጣዊ እንቅስቃሴ የቤተክርስቲያን የዶግማ ቀኖና ስርዓት ትምህርት ፣ አንድምታን ማዕከል ያደረገ ስብከት ከአውደ ምሕረቱ እየጠፋ ቅዱሳኑን፣ ዶግማን፣ሥርዓትን የሚያስረሱ ማዕበራዊ ሕይወት ነክ በሆኑ ቀልድ አዘል ትምህርት አይሉት ስብከት እየተስፋፋ በመሆኑ፡፡
 • በፕሮቴስንታንታዊ ተሃድሶ ሽምቅ ሴራ ቤተ ክርስቲያኗ ፣ የጳጳሳት ፣ የመነኮሳት፣ በአጠቃላይ የሁሉም የቤተክርስቲያን ጠንካራ አገልጋዮች ስም በብሎጎች እየጠፋ ምዕመናን ያንን በማንበብ ክብር አለመስጠትን እንዲለማመዱ እየተደረገ ነው
 • ገዳማቱ እየፈረሱ እየተቃጠሉ እየጠፉ ነው፡፡
 • ወዘተ


ይሔ ጥፋት ላለፉት 20 ዓመታት በእግዚአብሔር ቸርነት በጥቂት ቅን አገልጋይ ጳጳሳት፣ካህናትና ምዕመናን ጥረት ፤ የስብከተ ወንጌል መርሃ ግብር መስፋፋት ፣ የሰንበት ት/ቤትን አገልግሎት መጠናከር ፣  የማኀበረ ቅዱሳን እና የተለያዩ ማኀበራት የተማረውን ትውልድ ወደቤተክርስቲያን በማቅረብ፣ ወንጌልን በተለያየ ቋንቋ ማስፋፋት እና ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶችን መታደግ ወዘተ  ባይታገዝ ኖሮ ችግሩ በብዙ እጥፍ በተባባሰ ነበር፡፡ ይህ ችግር ዛሬ ለቤተክርስቲያን ሰላም እና አንድነት በማምጣት ፤ የተበላሸውን አስተዳደር በማስተካከል እርምጃ ካልተወሰደ ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ከዚህ በፊት በእጥፍ(Exponentially) እያደጉ እንዳሉ ሁሉ አሁንም በዚያው ረገድ ከመቀጠል ባሻገር ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ በእጥፍ ስል በተለመደ አማርኛ ሳይሆን በሒሳባዊ አሰራር በፊጥነት ጊዜ ሳይሰጥ በሚያድገው Exponential አካሔድ ማለቴ ነው፡፡ በየዓመቱ የችግሩ ግዝፈት በሁለት እየተባዛ የችግሩን ክብደት መፈታት ወደማይችል መከራ እየወሰደው ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ላይ ከውጪ ሃይሎች ያለው ፈተና ቀላል አይደለም፡፡ የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች የቤተ ክርስቲያንን ልጆች ፣ ድንበር ፣ ክብር ፣ ተሰሚነት እየነጠቁ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ምዕመናንን በወንጌል ለመድረስ ፣ የተዘጉ አቢያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት፣ ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶችን ለመታደግ ወዘተ ከሚያወጡት ዕውቀት፣ጉልበትና ገንዘብ ከመቶ ሃምሳው በመከላከል ላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ ደግሞ መፍትሔውን በግማሽ ሲያዘገይ ፤ በግማሽ ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ በዚህ ላይ ውስጣዊ የተሃድሶ እንቅስቃሴ የሚሰሩ መናፍቃን የአባቶችን ፣ የምዕመናንን ፣ የማኀበራትን ስም በማጥፋት ከሃምሳ በመቶ በላይ አገልጋዮችን ሽባ ያደርጋል፡፡ በዚህ ላይ በቤተ ክርስቲያን መከፋፈል ምክንያት ገለልተኛውን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ፤ በእናት ቤተ ክርስቲያን ያለውን ወደ ገለልተኛ ወዘተ ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ሃይላችን ይበታተናል፡፡ በዚህ ላይ በዘር መከፋፈል ፤ ለጥቅም የሚሰሩ ሲጨመሩበት በየዓመቱ ችግሩ እንዴት Exponentially እንደሚጨምር ማየት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ቤተ ክርስቲያኑን በጣም ስለሚጎበኛት በክርስቶስ ደምም ስለተመሰረተች እንደምንም እዚህ መድረስ ችላለች፡፡ ብዙዎች በክርስቶስ ደም ስለተመሰረተች የእኛ ስንፋና አያጠፋትም በሚሉት ግን አላስማማም፡፡ አትጠፋም ግን ሳስታ በዘመናት ፈተና ውስት ልትወድቅ ትችላለች፡፡ ለዚህም በግብጽና በሕንድ የሆነውን ከታሪክ ማዕደር መመልከት መልካም ነው፡፡ በእኛም ሃገር ቢሆን የዛሬ መቶ አመት ቤተክርስያን ያላት የምዕመናን ድርሻ ፣ በሃገሪቱ ያላት ተሰሚነት ዛሬ የለም፡፡

ዛሬ ይህ ችግር መፍትሔ ካልተሰጠው ነገ ምን ይሆናል?

 • ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉም ችግሮች ወይም ፈተናዎች በእጥፍ ማደጋቸውን ይቀጥላሉ
 • የማናከብረው ፣ የማንታዘዝለት ፣ ጸልይልን የማንለው፣ በሁሉ የተናቀ ፓትሪያሪክ ይኖረናል፡፡ ይህ ክብር ማጣት ወደ ጳጳሳት ወደ መነኮሳት ይወርዳል፡፡
 • በውጭ ያለው አስተዳደር ከሦስትዮሽ ክፍፍል ወደ እራስ ገዝ ይዘዋወራል፡፡
 • ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ቢያርፉ እንኳን በውጭ ያሉ አባቶች ሌላ ፓትሪያሪክ ሊሾሙ ይችላሉ
 • በውጭ ያለው ክፍፍል በገለልተኛ ፤ በቦርድ አስተዳደር ስም ወደ ሃገር ቤት ይዘልቃል፡፡ የመንግስት ለውጥ በመጣ በማግስቱም ሁለተኛ ሲኖዶስ ወደ ሃገር ቤት ይገባል
 • ወዘተ


የትላንቱን አይቶ ይህንን እጅግ በጫፍ ላይ ያለ ግምታዊ ትንታኔ መስጠት መጥፎ እንደመመኘት እዳይወሰድብኝ፡፡ ሊመጣ ካለው ፈተና እንድንታደግ ነብያት ሲነግሩን እንደቆዮት ገዳማዊያን አባቶችን ባሕታዊያንን ለማመን ሳይንስ አይናችንን ቢሸፍነውም ፤ ሳይንሳዊ ትንታኔም ተመሳሳይ ነገር እደሚያቀብለን ልብ እንበል፡፡

ታዲያ መፍትሔም ምንድር ነው?

መፍትሔው ከራስ መጀመር ነው፡፡ ከራስ ስል አንድም ከእያንዳንዱ ግለሰብ አንድም ከቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ቁንጮ ማለቴ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ፓትሪያሪክ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ በስሩ ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት የሚታዘዙለት ፤ የእግዚአብሔር እንደራሴ አድርገው የሚመለከቱት ከሆነ ካህናቱም ምዕመናንም ያንኑ ያረጋሉ፡፡ ተነጋግሮ መስማማት ፤ መፍትሔ ፈልጎ ማግኘት ቀላል ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሰው ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ችግር እኔ ነኝ እያለ እራሱን ለንስሐ ፤ ሰውነቱን ለአገልግሎት የተቀደሰ መስዋት አድርጎ ያዘጋጃል፡፡ ለምን ቢሉ መሪው በመለኮታዊ ሃይል ሙት የሚያስነሳ ድዊ የሚፈውስ ፤ በሃሳብ የሚስማማ ፣ በፍቅር የሚገዛ ስለሚሆን፡፡ ስለዚህ እንዴት አድርገን ይችን ቤተ ክርስቲያን ከፈተና እናውጣት ፣ ብልሹ አስተዳደሩን እናስተካክል ለሚለው ከባድ እርምጃ የሚፈልግ ጉዳይ እንኳ ቢሆንም በጋራ መወጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን እራስ የሆነው ፓትሪያሪክ በማጭበርበር የተመረጠ ፣ የሰው ምርጫ ብቻ የሆነ ፣ ሁሉንም ያልወከለ ከሆነ ከላይ የዘረዘርኳቸው የቀለሉ መፍትሔዎች እንደ ሕዝበ እስራኤል የ40 ቀን መንገድ የ40 ዘመን ይሆኑብናል፡፡

ሁሉን የሚወክል ሲል ምን ማለት ነው ?

ዕርቅን ያስቀደመ ሰላመ ቤተ ክርስቲያንን ያረጋገጠ መለያየት የጠፋበት ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነትን በምንም ዋጋ ቢሆን እንግዛ የምንለው፡፡ ከ40 ሺህ በላይ የሆነ ምዕመን ይህንን ነው በቤቱ እየተመኘ ያለው፡፡ በምንም ዋጋ ቢሆን ስንል ክርስቶስ እኛን በዋጀበት ዋጋ እንኳን ቢሆን ማለት ነው፡፡ ዛሬ ስለ ቤተ ክርስቲያን ብሎ የሚሞት ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ የእየሩሳሌምን ጥፋት ከማይ ምላሴ ከትናጋዮ ትጣበቅ የሚል ያስፈልጋል፡፡ በቃላት ብቻ ሳይሆን በምግባር፡፡ ይህንን ማለት ከተቻለ ሁሉም ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ሰላም ሳይመጣ እኔ ፓትሪያሪክ አልሆንም ፤ ፓትሪያሪክ አስመራጭ አልሆንም ፤ እኔ ፓትሪያሪክ አልመርጥም ሊሉ ይችላሉ፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስም ቢሆኑ እኔ ብዕትውናንን መርጫለሁ ከፕትርክናው ወንበር ይልቅ ሃገሬንም ሆነ ሃይማኖቴን በጸሎት ብጠብቅ ሰማያዊ ክብር ይጠብቀኛል ማለት ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች አይ ይህን ሁሉም እንዳያደርጉ የዚህ ወይም የዛ ጫና አለባቸው፡፡ ዘር ፣ ፓለቲካ ፣ መንግስት ፣ ጥቅመኞች ጫና እያደረጉ ባቸው ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን ቀድሞ አለምን ንቆ ለመነኮሰ (ለዓለም ሙት ለሆነ) መነኩሴ ያውም ከመነኮሳት ተመርጦ ጵጵስና ማዕረግ ለተቀበለ መነኩሴ ፤ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ሃገር ለሚያስተዳድር ለዚህም ሰማያዊ ዋጋ ብቻ ለሚፈልግ መነኩሴ ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ በዜሮ የተባዙ ናቸው፡፡ የትኛውም አካል ቢሆን በስጋቸው እንጂ በነፍሳቸው ስልጣን የለውምና፡፡ ስጋቸውን ደግሞ ገና ሲመነኩሱ ገድለዋታል እና፡፡ ስለዚህ ማንም የሚፈተን ቢኖር በገዛ ፈቃዱ ይፈተናል እንጂ ሌሎቹ ምክንያቶች ዋጋ የላቸውም፡፡ ሌላው ምክንያት ቀኖና ተጣሰ የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ሁሉም በድሏል፡፡ ቀኖና ደግሞ ይሻሻላል፡፡ ሁሉም ደግሞ ፍቅር ይልቃል የሚለው መልስ ይሰጣል፡፡

ስለዚህ ዕርቁን በተመለከተ ምን መንገድ አለ?

1.      ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ለቤተ ክርስቲያን ሳላም ብዕትውናን መርጠው ፣ የፖትርክናን ክብር ንቀው(ለበጎ) ቅዱሳንን ተከትለው ለበለጠ ክብር እራሳቸውን ማጨት
2.     ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን ለቤተ ክርስቲያን ሳላም ሲባል ከነሙሉ ክብራቸው ወደ መንበረ ፕትርክናው እንመልሳለ ብሎ መቀበል
3.     ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትሪያሪክ አድርጎ ሀገሩን እና ሁኔታውን የሚያውቅ ሊቀ ጳጳስ እንደራሴ መሾም
4.     ከላይ የተዘረዘሩትን የሚቀበል ቢጠፋ እንኳን ምርጫውን ለእግዚአብሔር መስጠት፡፡ በሃይማኖት ለሚኖር ሰው ሁሉ ቀላል ነው፡፡ ዕርቀ ሰላሙን አድርጎ ፤ ውግዘቱን አንስቶ ሁሉም አባቶች ወደ ሃገር ተመልሰው፤ ሲባኤ ታውጆ አቡነ መርቆሪዎስ በመንበሩ ይቀመጡ ወይስ አዲስ ይመረጥ የሚለውን በዕጣ ለመንፈስ ቅዱስ ምርጫውን መስጠት ይቻላል፡፡ አሊያም እጩ ሆነው በምርጫ ከሚያልፉ ሶስት አዲስ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አራተኛ የቅዱስነታቸው ስም አምስተኛ የእግዚአብሔር ስም ገብቶ እጣ ሊወጣ ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር ስም ቢወጣ ሁሉንም ትቶ አዲስ ሦስት እጩዎች ለማግኘት እንደ አዲስ መስራት ይቻላል፡፡
5.     ሰላም ተገኝቶ ይህ ሁሉ ማድረግ ባይቻል እንኳን 4ተኛው ፖትሪያሪክ በህይወት እያሉ ሌላ ፓትሪያሪክ አለመሾም ለምን ቢሉ የተሻለ ሰላም የሚያመጣ ከሆነ በፓትሪያሪክ ከተመራንበት ጥቂት አሥርት ዓመታት ይልቅ በመንበረ ማርቆስ ሊቀ ጳጳሳት የተመራንበት ስለሚበዛ
6.     ሌሎችም

በማጭበርበር የተመረጠ ፤ የሰው ምርጫ ብቻ የሆነ ማለት ?

የሰው ልጅ በብዙ ኃጢያት የተተበተበ ነው፡፡ ፓትሪሪክ ለመምረጥ የሚወከሉ 500 በላይ የሚሆኑ ተወካዮች ወደዱም ጠሉም በውስጥ ፍላጎታቸው ፣ በዘር ፣ በፓለቲካ ፣ በመንግስት ፣ በጥቅመኞች ጫና ውስጥ የሆኑ መሆናቸው ግድ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ሁላችን ያለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውጤቶ ች በመሆናችን፡፡ በነዚህ ሰዎች ድምር ውጤት ብቻ የተመረጠ ፓትሪያሪክ ከግማሽ በታች ምዕመናንን ቢያስደስት እንጂ የመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የማይቀበሉት ፓትሪያሪክ ከመሆን አይድንም፡፡ የማይቀበሉት ፓትሪያክ ደግሞ የማይሰሙት ሊቃነ ጳጳሳት የማይታዘዙ ካህናት አሜን የማሉለት ምዕመናን ይሆናል፡፡ ስለዚህ ፈተናው ይቀጥላል፡፡ የመጨረሸውን ውሳኔ ለመንፈስ ቅዱስ በመስጠት ሰው አጣርቶ ያመጣውን የእግዚአብሔርን ስም አራተኛ ጨምረን በጸሎት በለቅሶ መንፈስ ቅዱስ መረጠ ካልን ግን በሃይማኖት ሁሉም ያምናል፡፡ ሁሉም ይሰሙታል ሁሉም ይታዘዙለታል ሁሉም አሜን ይሉለታል፡፡

የመጨረሸውን ደረጃ በዕጣ ላለማድረግ የሚቀርቡ ምክንያቶች ለምሳሌ በግብጽ የተደረገው ጳጳሱ የልጁን እጁ መርተውታል እና ግድፈት ያመጣል ለሚሉ መፍትሔው ቀላል ነው፡፡ የእጣውን ስሞች በትልቁ ጽፎ በግልጽ እያነበቡ ሰፊ በሆነ እና እንደ መስታወት በግልጽ በሚያሳይ የእጣ ማስቀመጫ ማስቀመጥ ፤ ማስቀመጫውን ከድኖ ጥቁር ልብስ አልብሶ በማነቃነቅ መቀላቀል ፤ ማስቀመጫውን ግልጽ በሆነ ቦታ አስቀምቶ እና ክፍት አድርጎ ውዳሴ ማሪያም እያደረሱ በየተራ በሶስት ሊቃነ ጳጳሳት በመስቀል መቀላቀል ፤ በመጨረሻም ይህ ሁሉ ሲደረግ አይኑን ታስሮ የነበረ ሕጻን ልጅ አቅርቦ አይኑን ፈትቶ ያለ ማንም መሪነት እግዚአብሔር ብቻ በሚመራው እጁ እጣውን እንዲያወጣ ማድረግ ይቻላል፡፡ እጣን የመጨረሻ መለያ ማድረግ የመንግስትን ምርጫ ትክክል አይደለም እንደማለት ይሆንብናል ለሚሉ፡፡ ይህ ፓለቲካ ነው ከማለት ውጪ መልስ መስጠት አያስፈልግም ነበር፡፡ ነገር ግን መንግስት በሳይንስ ነው የሚያምነው ስለዚህ የአብላጫ ድምጽ አሰራር ይስማማዋል፡፡ ሃይማኖት ግን በእግዚአብሔር ሃይል ስለሚያምን ለእግዚአብሔር ቦታ ይሰጣል የሚለው የተሻለ መልስ ይሆናል፡፡ ሌሎችም ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ ነገር ግን ሁሉ አይረባም ስለፆም ብትከራከሩ ለፆም አድሉ ነው መጨረሻው፡፡ ምንም ምክንያት ቢቀርብ እግዚአብሔር ወዳለበት ፤ የእርሱ እጅ ወዳለችበት ማድላት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ በዚህ ወይም በዚያ መንገድ አድርገን ዕገሌን ብናስመርጥ የሚል ሃሳብ ከየአቅጣጫው እንዳለ አይዘነጋም፡፡ እነዚህ ሁሉ ሃይሎች እስከ መጨረሻው ድረስ ወሳኝ ግን መሆን የለባቸውም፡፡ እግዚአብሔርን አራተኛ በማስገባት በእጣ ሲመረጥ ግን የትም ያህል ቢሮጡ መጨረሻው የእግዚአብሔር ምርጫ ብቻ ይሆናል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በራሳችን መንገድ መርጠን የማንቀበለው ፓትሪያሪክ ከመምረጥ የምንቀበለው ጳጳስ ሆኖ መኖር ይሻላል፡፡ ስስት እና ትዕቢት የራቁለት መነኩሴ እግዚአብሔር በሚሰጠው የማይታይ ጸጋ ማንም ያከብረዋል የግድ ጳጳስ ወይም ፓትሪያሪክ መሆን የለበትም፡፡ ጵጵስና ማዕረግ ደርሶ በነዚህ ጾሮች የተፈታ ጳጳስ ደግሞ ፕትርክና ክብሩን አይመልስለትም፡፡

ከሁሉ በላይ ሰላም የተጠማውን 40 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እናስብ ፤ ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎ አውለው በዚህ ችግር ምክንያት ዘርተው ማጨድ ፣ ነግደው ማትረፍ የተሳናቸውን አገልጋዮች እናስብ፡፡

በተለይ ሰሞኑን ከየአቅረጣጫው የሚጠቆሙ የመፍትሔ ሃሳቦችን አስመልክቶ ሁሉንም በቀናነት እያዩ ፣ የተሳሳቱትን እያረሙ ፣ የደከሙትን እያበረቱ ከመሔድ ውጪ እርስ በእርስ በመካሰስ ለመፍትሔውም አንድነት እንዲጠፋ ማድረግ አግባብ አይደለም፡፡ ጥቂት ድረ ገጾች ለዕርቅ የሔዱ አባቶቻችን ዘገዩ ፤ ዕርቁ ለምን አሜሪካ ሆነ ፤ እነ እገሌ የዚህ ወገን ናቸው ፤ ይሔ ማኅበር እንዲህ ሊያደርግ ነው ፤ አስታራቂ ኮሚቴው ጥሩ አልተናገረም ወዘተ እያሉ አቅጣጫ የማስቀየር ስራ ሲሰሩ አስተውያለሁ፡፡ ወደዳችሁም ጠላችሁም ጊዜው የመረጃ ዘመን ነው፡፡ ሁሉም የሚሰራውን ታሪክ በቀላሉ መዝግቦ እየያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ለማረሳሳት ፣ አጀንዳ ለማስቀየር ፣ ወዘተ የሚደረግ ብልጣ ብልጥ ሩጫ ሁሉ ዋጋ የለውም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ እውነት የሚሞትላት ብቻ ነው የምትፈልገው የሚያጣላ ሳይሆን፡፡

የመረጃ ዘመን ማለት ምን ማለት ነው?
ቀድሞ አንድን መረጃ ሌላ ቦታ ለማድረስ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ በደብዳቤ ወይም በስልክ ብቻ መወሰን ግድ ይላል፡፡ በዚህም ምክንያት የዛሬ 21 ዓመት የሆነውን እንኳን በአግባቡ ለማወቅ እስከዛሬ ከባድ ሆኖብን ነበር፡፡ ምን አልባት ሁለተኛ ፓትሪያሪክ በስደት እንዳለ እንኳን በቅርብ የሰማ ብዙ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ባለፉት 15 ዓመታት የግል ጋዜጣ እንኳን መብዛቱ በፓትሪያሪኩ እና በአስተዳደሩ ላይ ይነሱ የነበሩ ነጥቦች ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከሰሯቸው ብዙ ጠቃሚ ስራዎች ይልቅ በዘመኑ የተፈጠሩ ችግሮች እንዲጎሉ የሆነው በብዙ ምዕመናን ዘንድ ተቀባይነት በማጣታቸው ነው፡፡ እንግዲህ መረጃዎች(የስብሰባ አጀንዳዎች ማን ምን አለ እንኳን ሳይቀር) በኢንተርኔት በደቂቃ በሚሰራጭበት የዚህ የመረጃ ዘመን ጥቂት ስተት እንኳን መስራት ትልቅ ተቀባይነት የሚያሳጣ መሆኑን ትኩረት ልንሰጥ ይገባል፡፡ ለዚህ ነው ከሰዎች ምርጫ ይልቅ እጣ የለየው በምንም አይነት መንገድ ይምጣ ፤ መንግስት የወደደውም ተብሎ ቢመረጥም ፤ የእገሌ ዘር የጠቆመው ቢባልም ፤ ጥቅመኞች ብዙ ሺህ ብር ያፈሰሱበትም ቢባል መጨረሻ እግዚአብሔር ከመረጣው ሁሉ ለበጎ ነው ብሎ መቀበል እና የቀድሞ ታሪኩን መሰረዝ ቀላል ይሆናል፡፡

የምዕመናን ድርሻ በዚህ ውስጥ ምንድር ነው?
በክርስትና ሃላፊነቱን ከላይ ለሚመሩን አባቶች መስጠት እና የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ከእግዚአብሔር እንደመጣ መቀበል አግባብ ያለው ነው፡፡ ሁል ጊዜም ልንቀጥለው የሚገባ ልምድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አባቶቻችንን ከታች ሆኖ በጸሎት ማገዝ ቀዳሚው መፍትሔ ነው፡፡ ይህን ሁሉ የምናደርገው ግን ከላይ ያሉ አባቶችን እንድንቀብል በጸሎትም እንድናግዝ ያደረገን እግዚአብሔርን ከሁሉም በላይ የመቀበል እና የነሱን ስልጣን እንድናምን ያደረገን የአምላካችን ኃይል ሲከበር ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል ወደ ጎን በመተው በሰው እና በመንግስት ብቻ የሚተማመን ምርጫ ሲደረግ ፤ የማንቀበለው ፓትሪያሪክ ሲመረጥ መመልከት ግን አግባብ አይደለም፡፡ አባቶችም ቢሆኑ ከመንገድ ስተው ሲያስቱ ፤ አስፈራርተው ሲያሳምኑ በቃ ማለት ይገባል፡፡ እነ አሪዎስም ቢሆኑ በቃችሁ ባይባሉ ኖሮ ብዙ ባጠፉ ነበር፡፡ አንድ አባት በሙስና የተዘፈቁ የአስተዳደር ሰራቶኞችን መናፍቆች ይሉ ነበር ፤  እግዚአብሔርን የማያምኑ (ስለማያምኑትም ከእርሱ የሚሰርቁ) ሲሉ፡፡

እኔም ምዕመናን ከማይቀበሉት ፕትርክና ይልቅ የከበረ ምዕመንነትን መርጫለሁ፡፡ ምን አልባት በቤተክርስቲያን ላይ የሆነውን እና ሊሆን ያለውን ጥፋት ይገልጥ ከሆነ በሚል ያጠፋሁት ካል ይቅርታ ለመጠየቅ ከአባቶቼ እግር በመውድቅ የተጻፈ፡፡


7 comments:

Anonymous said...

wooooooow excellent view

ዛሬ ይህ ችግር መፍትሔ ካልተሰጠው ነገ ምን ይሆናል?

ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉም ችግሮች ወይም ፈተናዎች በእጥፍ ማደጋቸውን ይቀጥላሉ
የማናከብረው ፣ የማንታዘዝለት ፣ ጸልይልን የማንለው፣ በሁሉ የተናቀ ፓትሪያሪክ ይኖረናል፡፡ ይህ ክብር ማጣት ወደ ጳጳሳት ወደ መነኮሳት ይወርዳል፡፡
በውጭ ያለው አስተዳደር ከሦስትዮሽ ክፍፍል ወደ እራስ ገዝ ይዘዋወራል፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ቢያርፉ እንኳን በውጭ ያሉ አባቶች ሌላ ፓትሪያሪክ ሊሾሙ ይችላሉ
በውጭ ያለው ክፍፍል በገለልተኛ ፤ በቦርድ አስተዳደር ስም ወደ ሃገር ቤት ይዘልቃል፡፡ የመንግስት ለውጥ በመጣ በማግስቱም ሁለተኛ ሲኖዶስ ወደ ሃገር ቤት ይገባል
ወዘተ

Anonymous said...

እግዚአብሔር ለሁላችንም መካሪ፣ ተቆጭ፣ መፍትሔ ሰጭ፣ ማስተዋል የበዛበት ሀሳብ፣ ተህትና የለበሰ ስጋ እንደ ወንድማችን ያድለን። ገና ከመጀመሪያው አነሳስህ አሸንፈኸኛል። እራስህን ዝቅ አድርገህ ብፁዓን አባቶች እያሉ እነዴት እኔ እፅፋለሁ በማለት የጻፍኩትን እቀዳለሁ ማለትህ ብቻ ምን ያህል ነገሩን በመንፈሳዊ አይን ስታይ እንደነበርክ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ግን ከአቅምህ በላይ እነዳስጨነቀህ እረዳለሁ። ሁሉን ማድረግ የሚችለወ አምላክ ስለ እናቱ ድንግል ማርያም ብሎ ለሀይማኖታችን ብንችል መፍትሄ ፈላጊዎች፣ እውቀቱ ከሌለን ደግሞ የንስሐ ለቀሶን ወደ አምላካችን በማድረስ ከወሬ ተቆጥበን እውነተኛ የመንፈስ ልጆች እንድንሆን ይርዳን። በእውነት ይህንን ማሰብ ለብዙዎች ተሰውሮ ይሆን? ለዚህም ቁም ነገር አዘል ጽሑፍ ቅሪታ ይኖረን ይሆን? አይመስለኝም ነገር ግን ለስጋ ለባሽ የማይመች እና የቤተክርስቲያንን ሰላም ለማይፈልግ እጅግ የሚቃጥል እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። እግዚአብሔር መፍትሔ ካልተሰጠው ነገ ምን ይሆናል የሚለው ተከስቶ እውነት እገሌ እንዲህ ብሎ ፅፎ ነበር ከማለት ሰላምና ፍቅሩን አልብሶ እንድነታችን እንዲያቀርብልን የዘወትር ፀሎቴ ነው። የቅዱሳን አምላክ ይጠብቅህ ይጠብቀን።

Anonymous said...

ግሮእግዚአብሔር እድሜ ይስጥህ ወንድሜ.... እንድዚህ በትህትና የሚጽፋ አይሳጣን አሜን

Anonymous said...

የእግዚአብሔርን ኃይል ወደ ጎን በመተው በሰው እና በመንግስት ብቻ የሚተማመን ምርጫ ሲደረግ ፤ የማንቀበለው ፓትሪያሪክ ሲመረጥ መመልከት ግን አግባብ አይደለም፡፡ አባቶችም ቢሆኑ ከመንገድ ስተው ሲያስቱ ፤ አስፈራርተው ሲያሳምኑ በቃ ማለት ይገባል፡

Holy said...

I love the way you wrote it much much better than other people's post. I love the politeness also. EgziAbHer Yibarkih. Amlak le betekiristianachin selamun yaweredilin. Amen.

Hailu said...

Wud Zemichael,

Ejig melkam neger bilewal!

May God bless you.

Kekedemechiw tifat yilk limeta yalew tifat ejig kebdo yitayegnal.

Bekifilu betekirstian lalefut 20 ametat betam tegoditalech. Ahunm selamina ena andinet yemayameta agul yepatriarch mircha betekirstianin lekefa gudat yitlatal.

Alemin nikenal le Egziabher motenal bilew yeteshomu papasat lemin yebetekirstian neger endemayangebgibachew aygebagnim.

May God save our Chruch.

Anonymous said...

አበው ተመከሩ፦
በተቻለ መጠን ከሁሉ በፊት ለሰላም ፍጠኑ የሰላምን ሸማ ተጎናጸፉ የጸብን ግድግዳ ሌላ ማንም መጥቶ ሊያፈርስ አይችልም እናንተው ናችሁ የሁሉም ነገር ጊዜው አሁን ነው ይህን ወቅት በማስተዋል እና በትዕግስት ካለፋችሁ ለትውልድ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ታስተላልፋላችሁ በተቃራኒው ደግሞ የሚሆነውን ልባችሁ ያውቀዋል ትውልድ እና ታሪክ ኅሊናችሁም ሁሌ እስታልፉ ደረስ እየወቀሳችሁ ለዘለዓለም ይኖራልይህ ከመሆኑ በፊት አባቶቻችን ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- አንዳችሁ ተሸነፉና አሸንፉ፥ ወይም ሁለታችሁም ተሸነፉና አሸናፊዎች ሁኑ። ከመንፈስ ልጀችሁ ቀሲስ ነኝ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)