December 24, 2012

የዴንቨር መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን “ከፓትርያርክ ምርጫ ዕርቅ ይቅደም” ሲል ፋና ወጊ መግለጫ አወጣ

  •    ሌሎች አብያተ ክርስቲያንም መግለጫ እንዲያወጡ ጥሪ አድርጓል፤
(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 15/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 24/2012/ READ THIS IN PDF)፦ በአባቶች መካከል የተጀመረውን ዕርቅ በሚያደናቅፍ መልኩ በአገር ቤት አባቶች መካከል የተጀመረውን የ6ኛ ፓትርያርክ ምርጫ የመቃወሙ እንቅስቃሴ ሥር እየሰደደ በመሔድ ላይ ነው። በአሜሪካን አገር ታዋቂና ታላላቅ ከሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት አንዱ የሆነው የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለምም መግለጫውን በማውጣት ድምፁን አሰምቷል።በሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ ተፈርሞ የወጣው ይኸው መግለጫ እንደሚያመለክተው ቅዱስ ሲኖዶሱ “ከማንኛቸውም ጉዳዮች በላይ፥ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ በመስጠት፥ በሙሉ ልብና ለቤተ ክርስቲያናችን ችግር መፍትሄን ሊያስገኝ በሚያስችል መልኩ፥ እንዲሰራ፤ ሳይስማሙ፥ ስድስተኛ ፓትሪያርክ ለመሾም፥ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቆም፤ በተለይ በውጭው ዓለም በእናት ቤተክርስቲያን ሥር የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን ካህናትና ምዕመናን፥ በጥር 16/ 2005 ዓ. ም ሊደረግ ከታሰበው የዕርቀ ሰላምና አንድነት ጉባዔ በፊት፥ ተመሳሳይ የአቋም መግለጫ እንዲያወጡ፤” እንዲሁም “መንግስትም ባለበት ሕዝባዊና ታሪካዊ  ኃላፊነት፥ የቤተክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ፥ ለሀገራችን  ልማትና ዕድገት የሚሰጠውን ጥቅም ግንዛቤ ውስጥ በመክተት፥ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ብፁዓን የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች በጋራ ተስማምተው ለሚደርሱበት አቋም ሁሉ፥ ያለውን ድጋፍ በይፋ እንዲገልጥና ፥ ለሰላምና አንድነት ኮሚቴ  ተፈላጊውን እገዛ እንዲሰጥ” ጥሪ አድርጓል። የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ (PDF) ሰፍሯል።

በርግጥም ሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ዝምታቸውን ሰብረው ቢያንስ ስለ አንድነት ያላቸውን ኅብረት እንዲያሰሙ ይጠበቃሉ።

ቸር ወሬ፡ያሰማን፣ አሜን።
ቀን ታህሣሥ 14, 2005 ዓ. ም.
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ - አዲስ አበባ                            
ለሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብጹአን አባቶች - አሜሪካ
ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራዲያዊ ሪፖብሊክ  መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ - አዲስ አበባ
          ጥንታዊት ፥ ሐዋርያዊትና ታሪካዊት የሆነችው ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ሃያ ዓመታት ፥ ሢመተ ፓትሪያርክን ተከትሎ ባጋጠማት የአስተዳደር ክፍፍልና መለያይት ምክንያት፥ እስከ አሁን በታሪኳ አጋጥሟት የማታውቀው ትልቅ ችግር ውስጥ ትገኛለች።  በዚህም ምክንያት፥ ቀኖና ቤተክርስቲያን ፈርሶ ፥ በሃገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙት ብፁዓን አባቶቻችንም ፥ ተወጋግዘው  በመለያየት ፥ የቤተክርስቲያናችን ካህናትና ምዕመናንም ፥ ከሦስትና ከዚያ በላይ ተከፋፍለው ፥ መንፈሳዊና ማሕበራዊ ህይወታቸው ተቃውሶ ይገኛል።
          በረከታቸው ይድረሰንና ፥ በብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ዕረፍት ምክንያት ፥ የተሰባሰቡ ካህናት አባቶቻችን፥ ለቤተክርስቲያናቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ፥ በብጹአን አባቶቻችን መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት ፥ በቅድሚያ የሰላምና አንድነት ኮሚቴን  መሠረቱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፥ መላውን ሕዝበ ክርስቲያን በማስተባበርና ፥ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ፥ በግልም ሆነ በጋራ ፥ ታላቅ ታሪካዊ መስዋዕትነትን ፥ ለቤተክርስቲያናቸው በመክፈል ላይ ይገኛሉ።
          እስከ አሁን ድረስ ከተደረጉት ፥ የዕርቀ ሰላም ድርድር ጉባኤዎች ሁሉ ፥ በተለይ ከህዳር 26 እስከ ህዳር 30, 2005 ዓ. ም. በዳላስ ቴክሳስ የተደረገው ሦስተኛው ጉባኤ ፥ የተሻለ ተስፋ የሚሰጥ ፥ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ሀሳቦች የተሰነዘሩበትና ግልጽ ውይይት የተደረገበት ቢሆንም ፥ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ለምንገኝ የቤተክርስቲያናችን ልጆች፥ ልንሰማው የናፈቅነውን የምሥራች ባለማሰማቱ ፥ ቀጣዩን ጉባኤ በሥጋት  እንድንጠብቀው አስገድዶናል።
          ስለዚህ እኛ ፥ በዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የምንገኝ ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን ፥ ታህሳስ 14, 2005 ዓ. ም. ባደረግነው ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ፥ የዕርቀ ሰላሙ ሒደት ያለበትን ሁኔታ በጥልቀት በማገናዘብ ፥ የሚከተለውን አቋም መግለጫ አውጥተናል።
1.              በሀገር ቤት የሚገኘው ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶሳችን ፥ ከማንኛቸውም ጉዳዮች በላይ ፥ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ በመስጠት ፥ በሙሉ ልብና ለቤተክርስቲያናችን ችግር መፍትሄን ሊያስገኝ  በሚያስችል መልኩ ፥ እንዲሰራ ፥ በአክብሮት እንጠይቃለን። ይህ ጥያቄ፥ የኛ ብቻ ሣይሆን ፥ በመላው ዓለም ያሉ ካህናት እና ምዕመናን ጭምር በመሆኑ፥ ብጹአን አባቶቻችን ፥ የእኛ ልጆቻችሁን ልመናና ተማጽንዖ እንድትቀበሉ፥ በድጋሚ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

2.             በአሁኑ ወቅት ሰላምና አንድነት ሳይመለስ ፥ በውጭ ሀገርና በሃገር ውስጥ የሚገኙ ብጹአን አባቶቻችን  ሳይስማሙ፥ ስድስተኛ ፓትሪያርክ  ለመሾም፥ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያደረገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
          ይህ ሳይሆን ቀርቶ ፥ ሰላምና አንድነት ሣይገኝ ፥ ስድስተኛ ፓትሪያርክ ቢሾም ፥ የችግሩ ግንባር ቀደም ሰለባ የምንሆነው  እኛ  በውጭው ዓለም የምንገኘው ሕዝበ ክርስቲያን  ስለሆንና ወደ አልተፈለገ መንገድ  ከመሄድ እንድንድን ከሁሉም በፊት ሰላምና አንድነት እንዲቀድምልን አጥብቀን እንጠይቃለን።
          ከዚህ በተጨማሪም፥ በተለይ በውጭው ዓለም በእናት ቤተክርስቲያን ሥር የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን ካህናትና ምዕመናን፥ በጥር 16, 2005 ዓ. ም. ሊደረግ ከታሰበው የዕርቀ ሰላምና አንድነት ጉባዔ በፊት ፥ ይህ ጉዳይ ከሚመለታቸው ክፍሎች ጋር ሁሉ በመነጋገር ፥ ተመሳሳይ የአቋም መግለጫ ታወጡ ዘንድ ፥ በእናት ቤተክርስቲያን ስም ፥ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። 

3.             በውጭው ዓለም የምትገኙ ብጹአን አባቶቻችንም ፥ ከሁሉም በላይ ለቤተክርስቲያናችሁ አንድነትና ሰላም ቅድሚያ በመስጠትና የሚፈለገውን መስዋዕትነት በመክፈል ፥ ታሪክ እንድትሰሩና ፥ ቤተክርስቲያናችንን  ከመከፋፈል አደጋ ትታደጉ ዘንድ ፥እኛ ልጆቻችሁ በአክብሮት እንጠይቃለን።

4.             የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራዲያዊ ሪፖብሊክ  መንግስትም ባለበት ሕዝባዊና ታሪካዊ  ኃላፊነት፥ የቤተክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ፥ ለሀገራችን  ልማትና ዕድገት የሚሰጠውን ጥቅም ግንዛቤ ውስጥ በመክተት፥ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ብጹአን የቤተክርስቲያናችን አባቶች በጋራ ተስማምተው ለሚደርሱበት አቋም ሁሉ፥ ያለውን ድጋፍ በይፋ እንዲገልጥና ፥ ለሰላምና አንድነት ኮሚቴ  ተፈላጊውን እገዛ እንዲሰጥ ፥ በአክብሮት እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር የሀገራችንንና የቤተክርስቲያናችንን፥ ሰላምና አንድነት ፥ ይጠብቅልን።

ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ
የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ዋና አስተዳዳሪ ግልባጭ

ለሰላምና አንድነት ኮሚቴቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
  

6 comments:

Anonymous said...

ይድረስ ለከበደ ቦጋለ:- በመጀመሪያ በደጀሰላም ላይ ዘወትር አስተያየት መስጠትዎን አደንቃለሁ:: ነገር ግን ይህ ብሎግ የእርሶን አመለካከት የሚቃወሙ ሀሳቦችንም የማስተናገድ ሃላፊነት እንዳለበት የዘነጉትና ለምን እኔ የምደግፈው ሀሳብ ብቻ አይንፀባረቅም የሚል ዝንባሌ ያለዎት ይመስለኛል:: የእርስዎን ሐሳብ የማንቀበል እኛም ልክ እንደ እርስዎ ሙሉ ሰው መሆናችንንና ሓሳባችንንም ያላንዳች ገደብ መግለፅ የምንችል ነንና እባክዎን ይህንን ዘመን ያለፈበት ግትርነት ያስተካክሉ::

hailu said...

I totally agree with the Denver Medhanealem's position letter.

All other Ethiopian Orthodox Church's must follow suit.

Please realize that a divided church will be an easy prey to its challengers and will eventually destroy itslef.

Peace and Reconcilliation FIRST. We don't need a "6th patriarch".

WE NEED UNITY IN OUR CHURCH.

Anonymous said...

አንድ በዕድሜ የገፉ አባት ናቸው አሉ ካህኑ ሲናገሩ፦ " እባክህን ልጄ ለሁለት አሥርት ዓመታት ለሁለት ተከፍላ፤ ከአንድ ማዕፀን የወጡ የአንድ እናት ልጆች እንደበላንጣ ሲተያዩ፣ የአገር አለኝታ የነበረች ቤተክርስቲያን ዛሬ የሁሉም መዘባባቻ ሆና ልጆቿ አንገታቸውን ሲደፉ. . . እንዲህ ሆና እናዳትቀር እባክህን አደራህን አሉኝ እጄን ጭብጥ አድርገው እንባቸውን እያፈሰሱ" አንጀት የሚበላ አነጋገር! ምነው አባቶቻቸችን ለአፍታ መለስ ብላችሁ የልጆቻችሁን ድምጽ ሰምታችሁ እንባችንን ብታብሱ። የቤተክርስቲያን አምላክ ማስተዋሉን ይስጣችሁ

Anonymous said...

የዴንቭር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ዕርቀ ሰላም እንዲቀድም ያወጡት መግለጫ በእርግጥ ለሌሎች በኢትዮጵያም ሆነ በውጭው ዓለም ላሉት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች ሁሉ ፈር ቀዳጅ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መከፋፈል በውጭው ዓለም የሚኖሩትንና በኢትዮጵያም ፍቅርና ሰላም ተሰውሮባቸው በታላቅ ስቃይ ላይ ያሉትን ከአርባ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ምእመናን በጋራ እንደሚጎዳ እሙን ነው።
ስለዚህ ለብፁዓን አባቶች የሚተላለፈው መልእክት በኢትዮጵያም በውጭም ያሉትን የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች ሁሉ ይመለከታል። እርሱም “እኛን ምእመናንን ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላም፣ ስለ ዕርቅና ስለ አንድነት የምታስተምሩንን ሁሉ እናንተም በተግባር እየፈጸማችሁ መልካም አርአያ እንድትሆኑን እንማጸናለን” የሚል አደራ ነው። ዴንቭር የወሰደውን እርምጃ ውጭ ያሉት ሌሎች አጥቢያዎች ስልክ እየተደዋወሉና በየድረ ገጹ (ለምሳሌ ደጀ ሰላም) ስለሚያገኙት እነርሱም የየራሳቸውን መልእክት ለብፁዓን አባቶች በመላክ ግዴታቸውን ፈጥነው እንደሚወጡ ይጠበቃል።
ከባድ የሚሆንባቸው ኢትዮጵያ በተለይም በየገጠሩ ያሉትን ከመገናኛ ብዙሐን ተቋርጠው የሚኖሩትን ገዳማት፣ አድባራትና አያሌ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች ነው። እነርሱም በዓለም ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው የዕርቅ፣ የሰላምና የአንድነት እንቅስቃሴ ሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ዜናውን የሚያበሥራቸውና የሚያስተባብራቸው አካል እጅግ ያስፈልጋል። ለዚህም ተቀዳሚው አደራ ያረፈው በነፃው የብዙሐን መገናኛ አውታርና ማኅበረ ቅዱሳንን በመሳሰሉ መንፈሳዊ ድርጅቶች ላይ ነው።

Anonymous said...

ዴንቨር እሰይ ብያለሁ

ብፁአን አባቶች አንድ ነገር መርሳት ያለባችሁ አይመስለኝም።እናንተ በፍቅር በሰላም ሳትኖሩ እኛ ምዕመናን ሰላም ሁኑ በፍቅር ኑሩ ብላችሁ ልታስተምሩን አትችሉም ዱላ ሁሉ እንደሚጠብቃችሁ አስተውላችሁት ይሆን ?ዱላ ትዕግስት ሲሟጠጥ ተስፋ ሲቆረጥ የሚወሰድ እርምጃ ነው። እንደ እኔ አመለካከት ግን የቤተ ክርስቲያኔ ሰላም ሊመለስ ያ በጥባጭ የሆነውን ደፍቼ ቤተ ክርስቲያኔ ሰላም ብታገኝ እኔ ብኮነን ደስ ይለኛል።
ይህ ያልኩበት ምክንያት በዚህ ጉዳይ ስንቱ መናፍቅ ይሆናል ስንቱስ የእምነቱ ጥንካሬ ይጠፋል ከሚል ነው።በእርግጥ እማመልከው ጳጳሳቱን ወይም ካህናቱን ወይም ዲያቆናቱን አይደለም ግን እነዚህ ከላይ ያሉት ከሥር ሀ ብሎ ለሚመጣ ሰው እንቅፋት ይሆናሉ።

ሰላም ሁናችሁ ሰላም ስበኩን።ተፈቃቀሩና ፍቅር አሳዩንና እኛም ብፍቅር እንኖራለን።
እምቢ ብትሉ ግን የቤተ ክርስቲያን ሰላም ለመመለስ አስፈላጊውን ሁሉ ብሎም ሰማዕትነት ለመቀበል በማያወላውል በማያጠራጥር ሁኔታ ዝግጁ ነኝ።

Anonymous said...

ሰላም ለሁላችሁም


ዴንቨርን ደግፈው አስተያየት የሰጡትን የእኔም ሃሳብ ስለሆነ እውነት ነው እኔም ከእርስዎ ጋር እሰለፋለሁ::
እነሱን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን በምትበድሉ ሁሉ ላይ ባትመለሱ እርምጃችን ሊሆን እንደሚችል አትጠራጠሩ::

ክቡራን ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን ሰላም መቼ ነው ሆ ብለን የምንነሳው?

I think we have to get up! we have to stop Over sleeping on the situation!
Break silence!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)