December 28, 2012

ለእርቁ እንቅፋት እየሆነ ያለው ማን ነው?

ይድረስ ለደጀ ሰላም፤ መልእክት በእንተ  አቡነ ማትያስ
(ቶላ ገመቺሳ ለደጀ ሰላም እንደጻፉት/ READ IN PDF)፦ የደጀ ሰላምን ድረ ገጽ ከሚከታተሉ አንዱ ነኝ፡፡ ጥሩ የመረጃ ምንጭ እየሆነች  በማገልገል ላይ  ስለምትገኝ ሥራዋን አደንቃለሁ፡፡ መረጃ ቁልፍ መሆኑን እንድንረዳ በተግባር አሳይታናለች፡፡ ስለቤተ ክርስቲያናችን  አጠቃላይ ጉዞ  ጥቂት የማይባሉ መረጃዎችን አቀብላናለች፡፡ በዘወትር አንባቢነቴ እድሜ ይስጥልኝ እላለሁ፡፡ ደጀ ሰላም ባትኖር እነ አባ ሰላማ ብቻቸውን ይፈነጩብን ነበር፡፡ ጉዳዩ ሳይደግስ አይጣላ ሆነና  በመናፍቃን “ብሎግ” ተብዮች አንጻር የእውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆችንም ድረ ገጽ  እግዚአብሔር  አዘጋጀ፡፡


ታዲያ በአንድ በኩል ደጀ ሰላም  ይህን የመሰለ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች የማንቃት ሥራ እየሰራች ብታስደስተንም አንዳንዴ ግን የአመረጃ ፍልሰት ይሁን ወይም ሌላ  የማይጠበቅ ስህተት ትሳሳታለች፡፡ ከእነዚህም ስህተቶች አንዱን ለማሳያ እነሆ ብያለሁ፡፡ ሰሞኑን  አንድ አውሮፓ ውስጥ የሚዘጋጅ ፓል ቶክ /የፍቅርና የሰላም ቤት/ግልጽ ደብዳቤ ለብፁዕ  አቡነ  ማትያስ በሚል  በዩት ዩብ  አቅርቦ ሰምተነዋል፡፡ ይህ ዝግጅት ብፁዕ  አባታችን  ፓትርያርክ እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ጥያቄ እንዳይቀበሉ  የሚመክር ነው፡፡ ወጣቶቹ  ከታማኝ ምንጭ  እንዳገኙት በመጥቀስ/ደጀ ሰላምን ማለት ነው፡፡ መቼም አባ ሰላማን እንደማይጠቅሱ  ተስፋ አደርጋለሁ/ብፁዕነታቸውን ሹመታቸውን እንዳይቀበሉ ይማፀናሉ፡፡ ደጀ ሰላም የፈጠረችው  የመረጃ  መዛባት  ጉልህ  ሆኖ የታየኝ  ይህን ዝግጅት ባደመጥኩ  ጊዜ  ነው፡፡ እውነትም ብፁዕ አቡነ  ማትያስ  በቀረበባቸው መረጃ ምክንያት  ለፈተና መዳረጋቸውን ተረዳሁ፡፡ እናም ይህችን መጣጥፍ ለመላክ ተነሣሁ፡፡

በመጀመሪያ ግን የብፁዕ አቡነ ማትያስን ነገር ትንሽ ያዝ አድርገን በእኔ እይታ የሰሞኑን ነውጥ በቤተክህነት ያስነሣውን አካል ጠቆም ላድርግ፡፡ የሰሞኑ አሳፋሪ  ድርጊት  እየተፈፀመ ያለው እራሱን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሥልጣን በማስጠጋት ላይ ባለ አንድ ቡድን አማካይነት ነው፡፡ ይህ  ወጣቶች ጳጳሳትን የያዘ  ቡድን  አስቀድሞ ለፕትርክና ይበቃሉ  ያላቸውን ታላላቅ አባቶች በተለያየ ሁኔታ ከጫወታ ውጭ ሲያደርግ  ቆይል፡፡ የሚፈልገውን ለመሥራት  የትኛውንም  አካል  እየቀረበ፣ፍላጎቱ  ሲጠናቀቅ ደግሞ ከየትኛውም አካል ለመለየት የሚፈጥን  ይህ ቡድን ማንን በማን ማጥቃት እንዳለበት  ጠንቅቆ  ያውቃል፡፡ ፍላጎቱን ለማሳካትም እነማንን መያዝ እንዳለበትም ያውቃል፡፡ በዚህም የተነሳ መጣላትም አብሮ መሥራትም ሲፈልግ ያለ ይሉኝታ  ያደርገዋል፡፡ ይህ ቡድን ወደ ሥልጣን ይመጣሉ ብሎ  ከሚፈራቸው አካላት አንዱ ብፁዕ አቡነ  ማትያስ  ናቸው፡፡ ስለዚህም ሰሞኑን እርሳቸውን  ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ   የተለያየ  ዘዴ በመጠቀም የብልጠት ሥራ ሲሠራ ቆይል፡፡ ይህም፡- 

1-የምርጫ መስፈርቱን እሳቸውን እንዳያካትት ማድረግ፡፡
የምርጫ  መስፈርትን  የያዘው ረቂቅ ሲቀርብ የታየው  ሁኔታ የዚህን ቡድን  ፍላጎት ግልፅ   ያደረገ  ነው፡፡ በዚህ ረቂቅ ላይ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለምርጫ  እንዳይቀርቡ ለማድረግ  ሁለት ነገሮች ሆን ተብለው ቀርበዋል፡፡ ዜግነት እና እድሜ፡፡ ዜግነት  ሲቀርብ  አቡነ ማትያስን  ጥሎ በቡድኑ  የተዘጋጁ እነ አቡነ እገሌን ለማሳለፍ ጥሩ መስፈርት ይሆናል ተብሎ ታምኖበት ነው፡፡ እድሜም በፍትሐ ነገሥታችን ከተቀመጠው  ውጭ  ከሰባ  ማለፍ የለበትም  የሚል  ሕግ  ረቂቅ የቀረበው ብፁዕነታቸውን ከምርጫ ውጭ ለማድረግ  ይመስላል፡፡

2-ለፕትርክና እንደተጠየቁ አድርጎ ሥማቸውን ማጉደፍ፤
ከላይ  የጠቀስነው  እንዳለ  ሆኖ  ምን አልባት የምርጫ ረቂቁ በታሰበው መልኩ ካልሄደልን  ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሳባችንን ከጣለብን ሌላ መንገድ ያስፈልገናል  በሚል  ሌላኛው መንገድ  ተቀየሰ፡፡ ሁለተኛው መንገድ  የብፁዕነታቸውን  ስም  ከመንግሥት ጋር አገናኝቶ  ማጥፋት ነው፡፡ የትግራይ ተወላጅነታቸውን  ግምት  ውስጥ አስገብቶ ሕዝቡ ከመንግሥት ሊገናኙ ይችላሉ ብንለው ያምነናል፣ ይቀበናል በሚል ለፕትርክና እንደተጠየቁ  ወሬ ማናፈስ ተጀመረ፡፡ ደጀ ሰላም  ይህንን  ዘገባ ታገኝበታለች  ወደሚባልበትም  አቅጣጫ  የወሬው  ንፋስ  ነፈሰ፡፡ ከዚያ  በቃ ያሰቡት ተሳክቶላቸው  የብፁዕነታቸው ስም  ጎደፈ ባልዋሉበት ተጠረጠሩ፣ መጪው ፓትርያሪክ ተብለው ሳይመረጡ መንበሩን ተረከቡ፡፡ ብዙ የዋሃን በዚህ የተሳሳተ መረጃ  ተሰናከሉ፡፡ እኔ ይህን ዜና የተሳሳተ ስል ከኢየሩሳሌም እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስለ ጉዳዩ  በቂ የሆነ የመረጃ ቁፋሮ አድርጌ ነው፡፡ እነ አቡነ ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም የሄዱት እርሳቸውን ለማነጋገር አለመሆኑን ከበቂ በላይ መረጃዎች አሉኝ፡፡

ይልቅስ አሁን ትኩረታችን ኢየሩሳሌም ባሉት አቡነ ማትያስ ላይ ከሚሆን እርሳቸውን የማያካትት የምርጫ መስፈርት አውጥቶ ምርጫውን እያጣደፈ ያለው የአዲስ አበባው ቡድን ላይ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ለሰላም የተላኩ መልእክተኞች ሳይመለሱ አስመራጭ ኮሚቴ ሠይመው ለምርጫ እየተቻኮሉ ያሉት እኮ  አቡነ ማትያስ አይደሉም፡፡ እርሳቸው የጎደፈ ሥማቸውን ይዘው ኢየሩሳሌም  ተቀምጠዋል፡፡ የአዲስ አበባው ቡድን ግን  ወደ መንበሩ ይጣደፋል፡፡ ይህ ቡድን ለራሱ እንደሚሠራ አሁን አሁን ግልፅ እየሆነ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ራሱን ያገለለው ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ደጀ ሰላምም ሰሞኑን ስለዚህ ቡድን ጥቆማ ሰጥታለች፡፡ ትናንት አመስግነናል ዛሬ ደግሞ ተሳስተው ካገኘናቸው መጻፋችን አይቀርም ዓይነት ስሜት አሳይታለች፡፡ መልካም ጅማሬ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በመንፈሳዊ ቤት ውስጥ እንዲህ ያለ ድራማ መሥራት ያሳዝናል፡፡ እግዚአብሔር ሳያስቀምጥ ይህንን  የቅዱሳን አባቶች መንበር እና ሥልጣን  በእጅ ለማድረግ መቸኮል በእጅጉ ይገርማል፡፡

ቀጥለን ወደ ብፁዕ አቡነ ማትያስ እንመለስ፡፡ ብፁዕነታቸው በተለይ በሰሜን አሜሪካ ያለውን የእናት ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ያስጀመሩ የጀመሩ አሁን ካለበት ደረጃም  እንዲደርስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ታላቅ አባት ናቸው፡፡በየፍርድ ቤቱ ብቻቸውን በመንከራተት  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን  መብት ለማስከበር የደከሙ አባት ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ ተጠናክሮ በየሥፍራው ተስፋፍቶ የምናየው የሀገረ ስብከት እንቅስቃሴ እዚህ እንዲደርስ የደከሙትን ድካም የሚያስታውሱት ሁሉ ሊናገሩት ይችላሉ፡፡ ሰሜን አሜሪካ በተለያየ አህጉረ ስብከት ከመከፋፈሉ በፊት ብቻቸውን ይህን ሁሉ ስቴት አዳርሰዋል፡፡ ከአንድ አባት የሚጠበቀውን መንፈሳዊ ተግባር ዘመኑ በፈቀደላቸው መጠን በሚገባ አከናውነዋል፡፡ ከወጣቱ ወጣት ከአረጋውያን  አረጋው  ሆነው የሚገለግሉ እኝህ አባት ንጽሕናን ከመጠበቅ አንጻር፣ በፍቅረ ነዋይ፣ በዘረኝነት የሚታሙም አይደሉም፡፡ ከእውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጋር ሁሉ የሚተባበሩ መሆናቸውንም በቅርበት የሚያውቃቸው ሁሉ ያውቁታል፡፡ የጸሎት አባት፣ በመንፈሳዊውም በሥጋዊውም እውቀት የበለጸጉ አባት ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው  ባለፈው ዘመን ቤተ ክህነት ውስጥ የነበረውን የተበላሸ እንቅስቃሴ በመቃወምም ረገድ የሠሩትን ሥራ የቤተ ክህነቱ ሰዎችም ይመሰክሩታል፡፡ ሰው ይውደደኝ ቡድን ለአደራጅበት ብለው ሳይሆን ስለ እውነት የቆሙ በመሆናቸው ብቻ መቃወም የሚገባቸውን ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡

ምን አልባት በተሐድሶ አራማጆች ዘንድ  ይጠሉ ይሆናል፡፡አንዳንድ የተሐድሶ አራማጆች በብሎጋቸው  የእርሳቸውን ነገር እያነሱ ሲጥሉ የምናየው ለዚህ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን  ለኚህ ትልቅ አባት ፍቅር እና አክብሮት አለን፡፡ ያልሆነ  ሥም ሲለጠፍባቸውም ዝም አንልም፡፡ ምርጫው በትክክል ይፈፀም መንግሥት ጣልቃ አይግባ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እርሳቸውን ባልዋሉበት ማማት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ እኚህ አባት በትክክለኛ መንገድ ተመርጠው ቦታው ላይ መቀመጥ እንዳይችሉ የመመረጥ መብታቸው  እንደተገፈፈ  አስተውሉ፡፡ ግን ለምን? ባልዋሉበት ውለዋል ብሎ ይህንን ሥም ለብፁዕነታቸው መስጠት ተገቢ ነው ብላችሁ ታስባላችሁ? ደጀ  ሰላሞችም  እባካችሁ ብፁዕ አቡነ ማትያስን ለቀቅ የአዲስ አበባውን ቡድን ጠበቅ አድርጉ፡፡ መንግሥትም  ገብቶበት ከሆነ ለምን  ብለን እንድንጠይቅ  መረጃውን  በቶሎ አድርሱን፡፡ ከምርጫ በፊት እርቀ ሰላም  እንዲቀድም ድምጻችንን ከየሥፍራው እንድናሰማ ዘዴውን ጠቁሙን፡፡
                                                                             ለሁሉም ቸር ያሰንብተን፡፡
      

            
            
          

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)