December 31, 2012

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት መግለጫ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“በትሕትና ዅሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችኹ በፍቅር ታገሡ፤
በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” ኤፌ 4:2-3
ታሕሳሥ ፲፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.
ቁጥር: ኢ/ኦ/ተ/ቤ/እ/ተ/00182005/
ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ
ዋሽንግተን ዲሲ
ለብጹዕ አቡነ ናትናኤል
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ እና የአርሲ  ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ብጹዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ መርቆሬዎስ  እና ብጹዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል
ቡራኬያችሁ ይድረሰን !
ጉዳዩ:-  እርቀ ሰላምን፣ የቤተክርስቲያንን አንድነትና የምዕመናንን መንፈሳዊ ደህንነትን ከስልጣንና ከሹመት ማስበለጥን ይመለከታል ፦


የአክብሮት ሰላምታችንን በታላቅ ትህትና እያቀረብን ቅድስት ቤተክርስቲያን በታሪኳ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመጀመሪያ የመንጋው ጠባቂ በሆናችሁ በእናንተ በአባቶቻችን መካከል መለያየት እና ውግዘት ገባ፤ በመቀጠል ደግሞ በወረርሽኝ መልክ ወደ ምዕመናን ተዛመተ።  ይህንንም መሠረት አድርጎ የአገር ቤት ሲኖዶስን የሚከተሉ፣ የውጪ አገር ሲኖዶስን የሚከተሉና ገለልተኛ የተባሉ ቤተ ክርስቲ ያናት ተቋቋሙ፡፡  ይህ የተማከለ ክፉ ግብራችን ደግሞ እንኳን ንፁሕ ባህሪይ በሆነው በልዑል እግዚአብሔር ፊት ይቅርና ንፁህ አእምሮ ባለው ሰው ፊት ሳይቀር  አስቀያሚም አሳፋሪም ነው። በፈጣሪና በታሪክ ፊት የሚያስወቅስ መጥፎ ተግባር ነው። አበው እንደሚሉት ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለምና እናንተ አባቶቻችንና የእኛም ትውልድ ግድፈት ቢፈፅም ተዓምር የሚባል አይደለም ምክንያቱም ሃጢያት፣ መለያየት፣ ከሰው ልጅ የሥጋ ባህሪያት አንዱ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን በክርስቶስ ስም ክርስትያን ተብለን እንደ መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት ወይንም እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ከግድፈታችን በእውነተኛ ንሰሃ መመለስ ካልቻልን የእነ ቅዱስ ጴጥሮስ እና የእነ ቅዱስ ማርቆስ ልጆች መሆናችን ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን ግን ይህን እንዳንናገር ከሕዳር 26 - 30, 2005 ዓ.ም. በዳላስ ቴክሳስ ከተማ በአባቶቻችን መካከል የተደረገው ቀና ውይይትና ምዕመኑም ያሳየው ክርስቲያናዊ ተሳትፎ ይከለክለናል።
         
   በዚህ የውይይት ወቅት ከተከናወኑና ማራኪ ከሆኑ  ተግባራት መካከል
1.  ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ምዕመናን እኔ የአጵሎስ ወይንም እኔ የኬፋ ነኝ ሳይሉ አባቶችን በአንድነት ወጥተው ተቀብለው የዋዜማ ፀሎት አድርሰው ጉባኤው በቀና መንፈስ እንዲጀመር ማድረጋቸው፣
2.  በጉባኤው ወቅትና በኋላ ያለአግባብ መግለጫዎች በተናጥል እየተሰጡ ምዕመኑ እንዲታወክ አለመደረጉ፣
3.  በዕለተ ሰንበት አባቶች በአንድነት ሆነው ሥርዓተ ቅዳሴ ማድረጋቸው፣
4. በብፁእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዮዎስ ወደ አገር ቤት መመለስ ላይ ስምምነት መደረሱ፣
5.  ቀሪ ተግባራትን ከፍፃሜ ለማድረስ ቀንና ቦታ ወስነው መለያየት መቻላቸው አበይት የሚባሉ ናቸው፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት አምስት (5) ነጥቦች ውስጥ እጅግ አንኳር የሆነው ደግሞ የአባቶቻቸን በአንድነት ሆነው ስርዓተ ቅዳሴን መፈፀማቸው ነው፡፡  ይህ ደግሞ "ተግባር ከቃላት በላይ ይናገራል" እንደሚባለው በሁለት ወገን ተላልፎ የነበረው የውግዘት ቃል በተግባር መሻሩን አሳይቷል፡፡  በዚህም ተግባር ነፍሳችን ሀሴት አድርጋለች፡፡  የብፁዕ ፖትርያሪኩም ወደ አገር ቤት መመለስ ላይ ስምምነት መደረሱ ትልቅ እመርታ ነው። በቀጣዩ ጉባኤ ወቅት ወጥ እና እንከን ወደሌለበት የአባቶቻችን አንድነትና ሰላም የሚወሰድ ውሳኔ ላይ ሊደረስ እንደሚችል አመልካች ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ጉባኤው በመካሄድ ላይ እያለና በምዕመናን ህሊና ውስጥ የአንድነትና የሰላም መንፈስ እያቆጠቆጠ በነበረበት ወቅት ከአገር ቤት በአሜሪካን ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ የተላለፉ መልዕክቶች አዋኪ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡

1.   በድፍረት ሳይሆን በትህትናና በልጅነት ፍቅር አቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ያስተላለፉት ወቅታዊ ያልሆነ መልዕክት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ ሆኖ አግንተነዋል፡፡  በአንዳንዶች እይታ የሰላሙ ጉባኤ ከመጠናቀቁ በፊት ተጠናቋል ብለው እንዲያስቡና እንዲያዝኑ አድርጓል። ለዚህ ደግሞ ዋንኛው ምክንያት ምዕመኑ የሰላምና የአንድነቱን ጉዳይ በተመለከተ በአባታችን በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ላይ የነበረና አሁንም ያለው ትልቅ አመኔታ ነው፡፡ ይህ የሰላምና አንድነት ጉባኤ ተሳክቶ አባቶች እና ቤተክርስቲያን አንድ እንድትሆን የሁሉም አባቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው። በእግዚአብሔር ፈቃድ በተቀበሉት ኃላፊነታቸው ምክንያት  ምዕመናን ከአባታችን ከብፁዕ አቡነ ናትናኤል የሚጠብቁት በቃለ መጠይቁ ላይ ከተላለፈው መልዕክት አስር፣ሰላሳና ስድሳ ጊዜ እጥፍ የሆነ ነው፡፡

2.   የፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አማካሪ የሆኑ አቶ አሰፋ ከሲቶ በዚሁ የሬድዮ ጣቢያ ያስተላለፉት መልዕክት እንዴት ነው ነገሩ ብለን እንድናስብ አድርጐናል፡፡ በቃለመጠይቁ ላይ የተናገሩት የግል ሀሳባቸውን ከሆነ በቤተ ክርስቲ ያናችን ላይ ምንም ስልጣን የሌላቸው ሰው ስለሆኑ ሀሳባቸው ላያሰጋ ይችላል፡፡  ነገር ግን የሳቸው ሃሳብ በውቅያኖስ ውሀ ውስጥ አብዛኛውን አካሉን ደብቆ ጫፉ ብቻ እንደሚታይና መርከቦችን አደጋ ላይ ለመጣል አድፍጦ እንደሚጠበቅ ግግር በረዶ (tip of the iceberg) ከሆነ የዚህች በክርስቶስ ደም የተመሰረተች ቤተክርስቲያን መከራዋ ወደማባራት አለመቃረቡን ያመለክታል። ይህ ሀሳብ ሲጠቃለል በብፁዕ አባታችን በአቡነ ገብርኤል በዚሁ የሬድዮ ጣቢያ ላይ የተገለጸው እውነት ሆኖ የቤተክርስቲያናችንን ቁስል በመርፌ የሚጨቀጭቅና ቅዱስ ሲኖዶሱን የሚሾፍር ስውር እጅ ከሌለ የዚህ  ዘመን አባቶች ታድላችኋል። ስለሆነም በርቱና የቤተክርስቲያንን ሰላምና አንድነት አሳዩን እንላለን። እንደ ሰዶምና ጎመራ ሰዎች ኃጢአት እስከ ጭንቅላታችን አስጥሞን የፈላ ውኃ እስኪበላን ልንጠብቅ አይገባም።

የቤተክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት በተመለከት እየተሰጡ ያሉ ሐሳቦች
ለዚህ ሀሳብ መነሻ ይሆን ዘንድ እንደእኛ እናት ቤተክርስቲያን ሁሉ የቅዱስ ማርቆስ መንበር የሆነችውን የግብፅ ቤተክርስቲያን ሰሞነኛ ውሎን መመልከት ጠቃሚ ነው። እግዚአብሔር አምላክ የግብፅና የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች እጣ ፋንታችን ተመሳሳይና በአንዲት የተዋሕዶ ሃይማኖት መጽናት መሆኑን የሚያመለክት በሚመስል ሁኔታ በአንድ ወቅት ሁለታችንም ስለ ፓትሪያርክ ምርጫ እንድናስብ አድርጐናል። ግብፃውያን የቤት ስራቸውን በአኩሪ ሁኔታ ፈጽመዋል። የቀናውንም ጉዞ ጀምረዋል።  በሂደቱም ግብፃውያኑ የመልካም ተግባር መመዘኛውን ቀመር በተለይ በአባቶች ዙሪያ ያለው በእጅጉ ከፍ አድርገውታል። እናንተ አባቶቻችን ደግሞ ከእኛ ይልቅ በቦታው ተገኝታችሁ የተመለከታችሁትና የተሳተፋችሁበት ስለሆነ ምስክሮች ናችሁ። መፋረጃ እንዳየሆንባችሁ ከግብፃውያኑ የተማራችሁትን ለመልካም ተግባር ተጠቀሙበት። በክርስቶስ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሆኑ የግብፃውያን ጉዞ ይህንን ከመሰለ፥ የኛስ ምን ሊመስል ይገባዋል የሚል ጥያቄ ይፈጠራል። የእኛም የቅዱስ ማርቆስ መንበር የሆነችው እናት ቤተክርስቲያናችን ጉዳይ የችኮላና የይድረስ ይድረስ፣ የሽፍንፍንና የድንግዝግዝ ጉዞ ሊሆን አይገባውም።

እስካሁን በተዘዋዋሪ እየሰማናቸው ያሉ የመፍትሄ ሀሳቦች፤
1.   አዲስ ስድስተኛ ፓትሪያርክ መሾም
2.   ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ማድረግ
3.   ቤተክርስቲያናችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሕይወት እስካሉ ድረስ በአቃበ መንበር ፓትሪያርክ እንድትመራ መደረግ ናቸው።

እናንተ አባቶቻችን ልዩነትን አስወግዳችሁ፤ አንድ ሆናችሁና ከወስጥም ሆነ ከውጪ ያለባቸሁን ተፅዕኖ ተቋቁማችሁ በስምምነት የምትወስኑት ውሳኔ ከማርና ከወለላ በላይ የጣፈጠ ይሆናል። ተልዕኳችሁ አንድ ሆኖ ሳለ ሁለት ሆናችሁ፣ የሰላም ሐዋሪያ ሆናችሁ ሳለ ተቃረናችሁ፣ የአንድነት ተምሳሌት ሆናችሁ ሳለ ተለያይታችሁ የምትወስኑት ማንኛውም ውሳኔ ግን በምዕመናን ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። እንደምን ቢሉ፦

1. ስድስተኛ ፓትሪያሪክን መሾም በተመለከተ፦
በአገር ቤት አዲስ ስድስተኛ ፓትርያርክ በተናጠል ቢሾም በውጭ አገር ያሉ አባቶች ደግሞ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ በማይኖሩበት ወቅት የነሱን አምስተኛ ፓትርያርክ የሚሾሙ መሆኑን  ለመተንበይ ጠቢብ መሆን የማያሻው ጉዳይ ነው።
ይህ ደግሞ ርትዕት ሃይማኖታችንንና መንጋውን ለዲያብሎስ መሳለቂያነት አሳልፎ ይሰጣል። ይህ ይሆን ዘንድ ፈቃዳችሁ ነው? በእንዲህ ዓይነት የሚሾሙ ስድስተኛውም ሆነ አምስተኛው ፓትሪያርክ እውነት ፓትሪያርክ ነው የሚባሉት ወይንስ የታሪክ ጠባሳዎች? ሹመት ሰጪውስ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ወይንስ ሌላ አፍራሽ ግብረሃይል ነው የሚባለው? ከእናንተ መሐከል ምን ዓይነት ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌለው አባት ነው ይህን ኃላፊነት በድፍረት የሚወስደው? እኛስ እንደምዕመን

እንደምን ብለን ነው ለታይታ ሳይሆን በሃይማኖት ከልባችን ሆነን ከስድስተኛውና ከአምስተኛው አዳዲስ ፓትሪያርኮቻችን ወይንም የታሪክ ጠባሳዎቻችን ቡራኬን ተቀብለን አሜን (ይሁንልን) የምንለው? መፍትሄው አንድ ነው መጀመሪያ እርቀ ሰላም ማውረድ ፣ ቀጥሎም ቅድስት ቤተክርስቲያን አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትርያርክና አንድ ምዕመን እንዲኖራት ማድረግ ነው። ከሕይወት ይልቅ፥ የሞት መንገድን እንደማትመርጡ እስከ አሁን ድረስም ተስፋችን አልተሟጠጠም፤  ለእናንተም የእግዚአብሔር እንደራሴነታችሁን የምታስመሰክሩበት፥ ብሎም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች 21 ዓመታት የናፈቅነውንና የራበንን ሰላም የምታመጡበት ወሳኝ እና ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆናችሁን መዘንጋት የለባችሁም። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አለቀለት፣ አበቃለት፣ አፈር ገባ የተባለለትን አልዓዛርን ከሞት አስነስቶ ሕይወትን እንደዘራበት ሁሉ ዛሬም የሰላሙ መንገድ ሕይወት ዘርቶ ቅድስት ቤተክርስቲያን አንድ ሆና፣ አባቶቻችንን በአንድነት ሲያገለግሉ ማየት፣ ምዕመናን ምዕመናት ልዩነትን አጥፍተው የቤተክርስቲያንን ትምህርት ለዓለም ለማዳረስ ሲተጉ የምናይበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን።

2. የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው መመለስ በተመለከተ፦
ይህ ጉዳይ በዋናነት በውጪ በስደት ያሉ አባቶቻችንንና በተለይ ደግሞ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ይመለከታል። በዚህ ጉዳይ ላይ በአገር ቤትም በውጪም ያላችሁ አባቶች ተስማምታችሁ ይህን ማስፈፀም ብትችሉና የምዕመናንንና ምዕመናትን ነፍስ ወደ ማዳኑ ሥራ ፊታችሁን ብታዞሩ ምንኛ መታደል ነው። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያፈራቻቸው ብፁዓን አባቶቻችንን የወጪ ሃገር አፈር በላቸው፥ አፈሩን ያቅልላቸው እና ዛሬም ሌሎች የቤተክርስቲያኒቱን ብርቅ እና ንዑዳን የሆኑ አባቶቻችን ለውጪ ሃገር አፈር ልናበረክት ተዘጋጅተናል? ብፁዓን አባቶቻችን “ለሃገራችን አፈር ሁላችንም ያብቃን” በባዕድ ሃገር አፈር መቀበር ምንኛ አለመታደል ነው? ይህ በሚሆንበት ወቅት በስደት ያላችሁ አባቶች የምትወስዱት እርምጃ በእውነት ዛሬ ቤተክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ የማያስገባና መፍትሄ የማያመጣ ከሆነ እግዚአብሔር ያዝንባችኋል። በታሪክም ሁልጊዜ ስትወቀሱ ትኖራላችሁ።

ቀኖና ቤተክርስቲያን ተጥሶ ስለ አንድነት ማሰብ በፍጹም አይሆንም በማለት፤ ከዚህ አቋማችንም ፍንክች አንልም፤ በማለት ለቤተክርስቲያን አንዳች ዘለቄታ ያለው ጉዳይ ልታከናውኑላት አትችሉም። ህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ብላችሁ እራሳችሁን በመጥራትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ በማውጣት ቤተክርስቲያናችንን ጠላት ዲያቢሎስ ከሰነዘረባት ፍላጻ ልትታደጓት አትችሉም። እለት በእለት እየተማረረ ከቤተክርስቲያን እየጠፋና ከሕይወት መንገድ እየወጣ ያለው ምዕመን ጉዳይ በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ዋጋ ያስከፍላችኋል። ክርስቶስ እንደተናገረው « በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር » እንዳለው የቅዱስ ማርቆስ ወንጌል 9፥ 42 ። በመከፋፈሉና በመለያየቱ ምክንያት እየጠፋን ስለሆነ ሊገዳችሁ ይገባል። “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደሆነ ተነስተህ አምላክህን ጥራ” ትንቢተ ዮናስ 1 ፥ 6 ብፁዕ አባታችን አቡነ መርቆሬዎስ! መርከቢቱ ልትሰጥም ስትቃረብ ስለምን ዝም ይላሉ? ምነው እድሜ ዘመንዎን ለደከሙላት ቤተክርስቲያን እና ሕዝበ ክርስቲያን ግድ አይልዎትም?
  
ከሁሉም በላይ ቀኖና ተጣሰ ከሚለው በበለጠ እልፍ ብላችሁ የቤተክርስቲያን አንድነት እንዴት ይጠበቅ፣ በምድራዊቷ ቤተክርስቲያን አምሳያ መንጋው ሰማያዊቷን እየሩሳሌም እንዴት ይመልከት ወደሚለው ትልቅ ቁም ነገር ልታተኩሩ ይገባል
ብለን እናምናለን። ለዓለም ብርሃንና እውነት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም ህዝብ ሁሉ ወደ ማስተማርና መግለጥ ፊታችሁን ልትመልሱ ይገባል ።ይህንን ለማድረግ ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ማዋቅር መስተካከልና አንድነትን በአስቸኳይ ማምጣት አለባችሁ። ለዚህ ደግሞ ቅድመ ሁኔታዎችን ልታሰቀምጡ አይገባም የቤተክርስቲያን ጉዳይ እና የምዕመናን አንድነት ቅድሚያ ተሰጥቶት ከታሰበ ፓትርያርክ ማን ይሁን የሚለው ጥያቄ እንኳን ለእናንተ ለአባቶቻችን ለክርስቶስ እንደራሴዎች ይቅርና ለእኛም ለምዕመናን ግልጥ እና ቀላል ሆኖ ይታየናል።

3. በአቃቤ መንበር ፓትርያሪክ መመራትን በተመለከተ፦
በሰፈሩት ቁና መሰፈር አለና አገር ቤት ያላችሁ አባቶች ያለስምምነት ይህን ካደረጋችሁ ነገ ደግሞ በስደት ያሉት አባቶች አቡነ መርቆሬዎስ በማይኖሩበት ወቅት ያንኑ ላለመድገማቸው ማረጋገጫ የለም። ይህ ማለት ደግሞ የጥፋቱ ጅረት ይቀጥል ማለት ነው። ስለዚህ የአባቶች ብሂል እንደሚለው "አለባብሶ ቢያርሱ በአረም ይመለሱ" እንዳይሆንብን ችግሩ ከየት እንደጀመረ ምንጩን ጠንቅቃችሁ የምታውቁ እናንተ አባቶቻችን ይህን ችግር በማያዳግም ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዛሬ ፈትታችሁ ታሳዩን ዘንድ ተማፅኖአችንን እናሰማለን። በዚህ ዘመን የእኛ የምዕመናን ሕይወትና ጉዞ መስዋዕተ ቃየል፣ የአስቆሮቱ የይሁዳ ንስሃ ፣ የሐናንያና ሰጲራ ጥሪ እንዳይሆንብን ዛሬ ትታደጉን ዘንድ ድምፃችንን እናሰማለን።

ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች ብሎ ነብየ እግዚአብሔር ኢሳያስ የተናገረውን የትንቢት ቃል ባለማመኑ ሞት እረስቶት ክርስቶስ ተወልዶ አይቶትና አቅፎት አስከሚያምን ድረስ አረጋዊው ስሞዖን በህይወት ቆይቷል። እኛም ዛሬ የአባቶቻችን እድሜያችሁ ምንኛ ቢገፋና አቅማችሁ ቢደክም ቤተ ክርስቲ ያናችንንና ህዝባችንን አንድ ሳታደርጉ እግዚአብሔር እንዳያሰናብታችሁ እንማፀነዋለን።

ይህች የምንኖርባት ዓለም ከፍተኛ በሆነ መንፈሳዊ ረሀብና ጥማት ውስጥ ትገኛለች። ቅድስት ቤተክርስቲያን በአላት ታላቅ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ስፍራ ምክንያት ይህን መንፈሳዊ ረሀብና ጥማት ለማስታገስ ግንባር ቀደም ሚና  ሊኖሯቸው ከሚገባቸው ተቋማት ውስጥ ዋነኛዋ ናት ። ይህን አደራዋን ግን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በሙሉ አቅም እየተወጣች አለመሆኗ መንፈሳዊ ቁጭትና ሐዘን ፈጥሮብናል። ይህን ሐዘናችንንና ቁጭታችንን በተግባር ለመግለፅ ከአሁን በፊት ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋምና ገዳማውያኑን አቅማችን በፈቀደ መጠን በሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ለመርዳት በመሞከር ላይ እንገኛለን። ይህንንም በተመለከተ በተለይ በአገር ቤት ላላችሁ ብፁዓን አባቶች የዋልድባ ገዳምንና ገዳማውያኑን ትታደጉ ዘንድ እንደ ልጅነታችን ማሳሰባችንን እና ማስታወሳችንን እንቀጥላለን። አሁን ደግሞ በአግዚአብሔር ቸርነት “ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስቲያን እምነት ተከታዮች አነድነት” ን በማቋቋም መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችንን ለማጎልበትና ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን።

ከጥረቶቻችንም ውስጥ አንዱና ዋነኛው የቤተክርስቲያንና የአባቶች አንድነት ስለሆነ ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ መነሳታችንን በትህትና እንገልጻለን። ስለዚህም ከጥር 16 ቀን እስከ ጥር 18 ቀን 2005 ዓ.ም. በሎሳንጀለስ ካሊፎርኒያ በሚደረገው ጉባኤያችሁ ላይ የናፈቅነውን የብስራት ዜና ታሰሙን ዘንድ በታላቅ ተስፋ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። በጥረታችሁ እና በድካማችሁ ሁሉ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዲራዳችሁ እና በዚሁ አጋጣሚ ስለናፈቅነው የቤተክርስቲያናችን ሰላም፣ የአባቶች እና የምዕመናን አንድነት በጋራ ወደ ፈጣሪ የምናመለክትበት ዓለም አቀፍ የጸሎት እና የምሕላ ሳምንት ታውጁልን ዘንት በታላቅ ትህትና በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ስም በአክብሮት እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን በረደኤት ይጠብቅልን።

                                                ቡራኬያችሁ ይድረሰን በፀሎታችሁ አስቡን።           
                        ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት
                                               ስልክ ቁጥር፦ 703-307-9478 አሜሪካ
                                                                    905-531-3277 ካናዳ                        
ግልባጭ:-
        ለመንበረ ፖትርያሪክ
        ለብፁዓን አባቶች በሀገር ውስጥም በውጪም ለሚገኙ በየግላቸው
        ለእርቀ ሰላም እና አንድነት ጉባኤ
        ለጉባኤ ካህናት ወምዕመናን ለቤተክርስቲያን11 comments:

Anonymous said...

ጸልዩ !!!

"ወደ፡ፈተና፡አንዳትገቡ"

ቸሩ፡አግዚዓብሄር፡ይርዳን፡፡

Anonymous said...

የመፍትሄ ሃሳቦቹ ላይ የተሰጠው ማብራሪያ ከወገንተኝነት የጸዳ ባለመሆኑ አዚኛለሁ። አስተሳሰባችን ወደ አንድ ጎራ ባጋደለ ቁትር ችግሩ እኛ ባሰብነው መልኩ ብቻ እንድፈታ መፈለግን ያስከትላል። ይህም አባቶች አንድ ሆነው መፍትሄ ሚሆን ውሳኔ ቢወስኑ እንኳ እንዳሰብነው ካልሆነ ላለመቀበል ሊያበቃ ይችላል። የቅ/ሲኖዶስን ውሳኔ አለመቀበል ደግሞ ሃይማኖታዊ አይሆንም/...ወደ ክህደት ይመራልና። ስለዚህ መፍትሄ እያልን የየራሳችንን የአቋም መግለጫ ከምንነዛ... አባቶች ተገናኝተው መምከር እንድችሉ፤ መግባባት እንድችሉ ብንጸልይ እና በምንችለው ብናግዝ የተሻለ ይሆናል ብየ አስባለው። ይህ ሲሆን እግዚአብሔር በአባቶች መካከል ይገኛል፤ ትክክለኛ መፍትሄም ይመጣል።
አምላካችን እግዚአብሔር እንደኛ ዝርክርክነት ሳይሆን እንደቸርነቱ መፍትሄ ይስጠን፤ አሜን!

Anonymous said...

I found a youtube video showing the late Abune Zena Markos leading a prayer service in 1990.
at
http://www.youtube.com/watch?v=NMtb7zPMZcA

Anonymous said...

ለቤተ ክርስቲያናችን ስላምና አንድነት ቁልፉ አንድ ብቻነው፤
አቡነ መርቆሬወስ ወደ ኢትዮጵያው መንበራቸው ይመለሱ።

Anonymous said...

God be with you

Anonymous said...

Let God bless you guys . Hope God is got plan always he is with us .

Anonymous said...

"Kewegentengnet yetseda ayidelem" yalkew asiteyayet sechi, minalbat ante yeweyane akenkagn timeslengaleh.20 amet mulu yetamesechiw BETEKIRISTIYAN,zarem leante ayinetu michu yemitihonew: GEDAMATIN yemiyasikofru, MENEKOSATIN ende-dkula yemiyasedidu, lemengaw denta yelelachew.... abatoch silalu bicha new.And ken gizew siders Ende ARIYOS yemiwegezubet ken ruk ayihonm.EGZIABHER ke kinoch gar le-zelealem yinoral.

Unknown said...

''የቅ/ሲኖዶስን ውሳኔ አለመቀበል ደግሞ ሃይማኖታዊ አይሆንም/...ወደ ክህደት ይመራልና።'' ይህን ከላይ ያሉት ወገን ምን ማለታቸው እንደሆን ቢያብራሩት ጥሩ ነበር። ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት እኮ በስም ብቻ አይደለም በተግባር ቅዱስነቱን ሲያሳይ ነው እንጅ። ሲኖዶስን ሲኖዶስ የሚል ስም ያሰጠውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚሺር ሲኖዶስ እንዴት ብለን ነው ሲኖዶስ ብለን እንድንቀበለው የምንገደደው ? የዓለማዊ መንግሥትን ፈቃድ ለመፈፀምና ለማስፈፀም ብሎ የቅዱሱን ተቋም ሕግ የማያከብርን ስብስብ ስሙን እንደ ንግድ ፈቃድ ምልክት ስለተጠቀመበት ብቻ ውሳኔው የመንፈስ ቅዱስ ነው ብለን ልንታዘዝለትና ልንገዛለት ቀኖናዊ ግዴታ የለብንም። እንዲያውም ሲኖዶስ የሚል ስም እስከያዘ ድረስ አይሳሳትም ወደሚለው የክህደት መንገድ የሚወስደውስ የርስዎው አመለካከት ነው። ካቶሊኮቹ ''ፓፓው አይሳሳትም'' ማለት ፍፁም ነው ወደሚለው አይነት መንገድ ነው የሚያመራው። እኛም ሲኖዶስ የጳጳሳት ጉባኤ እንደመሆኑ ፥ ጳጳሳት ደግሞ ብፁአን ሲሆኑ ነው ሲኖዶሳቸው ''ቅዱስ'' የሚለውን ለእግዚአብሔር የሚቀጸለውን ቅጽል ሠጥተን የምንጠራው። ለምን ? ቅዱስ የሆነ ስም ይዞ የራሱን ሕግ/ቀኖና የማያከበር ከሆነ ሲኖዶስ የሚለውን መስፈርት አያሟላምና እኛም አንቀበለውም። የሚወስነው ውሳኔ ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን ፈቃድ ሳይሆን እምነተ እግዚአብሔር የሌላቸው የመንግሥት መሪዎች የሚመሩትን ቤተ መንግሥት ፈቃድ እየፈፀመ ያለን ሲኖዶስ እንዴት በስሙ ብቻ አክብረን እንታዘዘው? እውነተኛው ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ ነው የሚመራው። መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አያስጥስም። ምዕመናንን በጎጥና በቋንቋ ወይም በክፍለ ሀገር አይከፋፍልም። በእርቅ እንጅ በጥል አይመራም። በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሲኖዶስ ይህን ሁሉ አያደርግም፤ ተቃራኒውን እንጅ !በስም እማ ከሆነ የተጠመቀው ሁሉ እኮ ክርስቲያን ነው ። ግን መጠመቁ ብቻ አመንዝራውን ፥ ነብሰ ገዳዩን ፥ ቀመኛውን ፥ ሌባ ወንበዴውን፥ ሀሰት መስካሪውን ወደ መንግሥተ ሰማያት አያገባውም። ስምና ግብር ሲጣመሩ ብቻ ነው አንድን ነገር እውነት ነው ብለን የምንቀበለው እንጅ እውነተኞቹ የተጠሩበትን ስም ብቻ ስለያዘ ነው ብለን እውቅና በመሥጠት ለጥፋት ሥራው አንተባበረውም። ''አኀዊነ ለኩሉ መንፈስ ኢትእመኑ ፤ አላ አመክርዋ ለመንፈስ ለእመ እምኀበ እግዚአብሔር ይእቲ ፣ እስመ ብዙኃን ሐሳውያነ ነቢያት መጽኡ ውስተ ዓለም። =ወዳጆች ሆይ !መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዜብሔር ሁነው እንደሆነ መርምሩ።ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋልና !'' 1ኛ ዮሐ. 3 ፤ 1-2። ይህን ቃል ተጠቅመን ነው ስሙና ግብሩ መጣጣሙንና መቃረኑን መርምረን መቀበልና አለመቀበል ከሚለው ውሳኔ ላይ የምንደርሰው። ይህ ነው ትክክለኛው መንገድ !

Anonymous said...

መንፈሳዊነት ማለት በህይወት ሲኖሩ መልካም ነገር ሰርቶ ማለፍ ነው፡፡አሁን በዘመናችን አሳፋሪ መንፈሳዊ ሳይሆን ስጋዊ ጥማት እያየን በመሆናችን በጣም አዝነናል፡፡እባካችሁ በእግዚአብሄር ስም ሰላምን አብስሩን የመከፋፈልን ጥል አስወግዱና አንድነትን በዘመናችሁ ሰርታችሁ እለፉ! እውነት በትዕቢት ያለ ፈሪሀ እግዚአብሄር የሆነ ስልጣን ዘመን አያሻግርምና ፣አንዳችሁ ተሸነፉና የእግዚአብሄርን መንጋ በእውነት ጠብቁ! በመሸነፍ ውስጥ ያለውን የአሸናፊነት ፀጋ ተቀበሉ…… .. . . . .

Anonymous said...

Ato Kebede Bogale:
" ሲኖዶስን ሲኖዶስ የሚል ስም ያሰጠውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚሺር ሲኖዶስ እንዴት ብለን ነው ሲኖዶስ ብለን እንድንቀበለው የምንገደደው ? " Why did it takes you 21 years to ask this? Why didn't you demand Abune Merqorewos to return to Addis rathere than establishing another Synodos in America? Please defend your faith not your Patriarch, remember, Abune Merqorewos should not leave Ethiopia, he should have go to geddam or die on his soil. We Miemenan forgive him but it looks like Papasat are not forgiving him.

Anonymous said...

ውሃ ቢወቅጡት መልሶ እንቦጭ እንዲሉ ይሄንን የዚህ ክፉ እና ዘረኛ አገዛዝ መንግስት ካድሬዎች አባባል ዛሬም አለማቆሙ ከመገረም አልፎ ያስቃል። „ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መሰደዳቸው እራሱ የእግዚአብሄር ጥበብ እንጂ እኔ እንደምገምተው በእሳቸው የተደረገ አይመስለኝም“። ለምን እዛው ቀርተው የመጣውን አልተቀበሉም የሚባለው ተራ ወሬ አልፎበታል። ክርስቶስም ሀዋርያትም ተሰደዋል ብዙ መከራ አይተዋል። አዲስ አበባ የተሰበሰበውን ሲኖዶስ ሲኖዶስ ሳይሆን እኔ የማየው እምነት የሌለውን መንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ አድርጌ ነው።

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)