December 28, 2012

“በፓትርያርክ ምርጫ ሂደት መንግስት ጣልቃ አልገባም፤ አይገባምም” (መንግስትና ቤተክርስቲያኗ)


(አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2005, Fana Radio/ PDF) የቀደሞው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን እረፍት ተከትሎ ፥ የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀጣዩን ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለመሾም የሚያስችል ደንብ አዘጋጅቶ ሲመክርበት ቆይቷል።


የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለፋና  ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ፥  ፓትርያርክ የሚሆን አባት ለመምረጥ የሚያስችል እጩዎችን እንዲመረጥ ኮሚቴ ተሰይሟል። ይሁንና ሰሞኑን አንዳንድ የግል የህትመት ውጤቶችና ድረ ገጾች በምርጫው የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለ የሚሉ መረጃዎችን ይዘው ሲወጡ ተስተውሏል።

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር  ለጣቢያችን  መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ፥ ይህን ለማድረግም ህገመንግስቱ እንደማይፈቅድ ገልጿል። የሚኒስቴሩ  የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቄ እንደገለፁት ፥ ወሬዎቹ በፍጹም ከእውነት የራቁ ናቸው። በሃገሪቱ ባሉ በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ የመከባበር፣ የመቻቻልና ሰላማዊ የአምልኮ ስራ እንዲያካሂዱ ሚኒስቴር መስሪያቤታችን ይሰራል ይህም በአዋጅ የተሰጠው መብት ነው የሚሉት አቶ አበበ፤ ከዚህ ባለፈ ግን መንግስት በየትኛውም ሃይማኖታዊ ስርዓት ውስጥ በሚካሄዱ ማናቸውም ተግባራት ጣልቃ እንዲገባ የተሰጠው ስልጣን የለም።

አንዳንድ አካላት መንግስት የሃገር ልማትን በተመለከተ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደ ጣልቃ ገብነት እንደሚመለከቱና ይህም ከግንዛቤ እጦት የመጣ  መሆኑን  አስረድተዋል። በፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ውስጥም መንግስት ጣልቃ አልገባም ፤ አይገባምም ነው ያሉት ሃላፊው ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ይህንኑ አረጋግጣለች። ከፓትርያርክ ምርጫው ጋር ተያይዞ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለ መባሉ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው ነው የተናገረችው። ቅዱስ ሲኖዶሱ ለምርጫው የሚያስፈልጉ በቤተክርስቲያኗ ህግና ስርዓት ላይ የተመረኮዘ ደንብና መመሪያ አዘጋጅቶ ውይይት ከማድረግ ባለፈ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርጫው ባልገባበት ሁኔታ ስለጣልቃ ገብነት ማውራት ትክክል ነው ብለን አናምንም ብለዋል ዋና ጸሐፊው ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል። በደንብና መመሪያው መሰረትም እጩዎችን የሚያቀርቡ አካላት መመረጣቸውንም ነው ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል የነገሩን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምንጊዜም ቢሆን ሰላምን ትሻለችና ፤ በውጪ ሃገርም ካለው ሲኖዶስ ጋር ሰላም ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም ዋና ጸሐፊው አቡነ ሕዝቅኤል መናገራቸውን ባሃሩ ይድነቃቸው ዘግቧል።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)