December 24, 2012

“ከፓትርያርክ ምርጫ ዕርቅና ሰላም ይቅደም” ማለት የጀመርንበት የመጀመሪያው እሑድ

 •      አገር ውስጥ እና በውጪ አገር የሚገኙ ሚዲያዎቻችን አንጸባርቀውታል፤
 •     ቅ/ሲኖዶስ በዚህ ሣምንት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል፤ ስሕተቱን ያስተካክል ይሆን?
 •      ለምትፈጽሙት ስሕተት ሕዝቡም ታሪክም ይቅር አይላችሁም!!!
(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 15/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 24/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በአባቶች መካከል ላለፉት ሁለት አሠርት ዘለቀውን መለያየት ለማጥፋት እና በግራም በቀኝም ያለውን ለማዋሐድ በተጀመረው ዕርቀ ሰላም ላይ የገጠመውን ጋሬጣ ለማንዋት ኦርቶዶክሳውያን የጀመሩት ሥር ነቀል እንቅስቃሴ መልክ እየያዘ ነው። ሚዲያዎች ሐሳቡን ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን በማዳረሱ በኩል የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እያደረጉ ሲሆን አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በውጪው ዓለም የሚገኙ ሬዲዮኖች “ዕርቁ ይሳካ” ሲሉ ሰንብተዋል። በተለይም የአካባቢ ሬዲዮኖች በሚበዙበት በአሜሪካ መንግሥትን የሚቃሙትም፣ የሚደግፉትም፣ አማካይ ነን የሚሉትም በአንድ ድምጽ ዕርቁ እንዳይሳካ የሚያደርጉትን አካላት ተችተዋል።


እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ልዩነቱ ሊፈታ የሚችልበት ጭላንጭል ታይቶ ነበር። ነገር ግን ይህንን የተስፋ ጭላንጭል በሚያዳፍን መልኩ በጥቂት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ግፊት 6ኛ ፓትርያርክ ለመሾም “አስመራጭ ኮሚቴ” በመቋቋሙ “የቤተ ክርስቲያኔ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ምእመናን በሙሉ ውሳኔውን በጽኑዕ ለመቃወም ከትናንት እሑድ፣ ቅዳሴ ካለቀ በኋላ በየአጥቢያችን በመሰባሰብ ይህንን ሐዘናችንንና መከፋታችንን እንዲሁም በውሳኔው ማዘናችንን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለመግለጽ የመሰባሰቡ ሒደት ተጀምሯል። የፍርሃቱ መጋረጃ መገለጥ ጀምሯል።

ደጀ ሰላም “ሰንበት ት/ቤቶች፣ ማኅበራት፣ ሰንበቴዎች እና ምእመናን በሙሉ ከሚያውቋቸው ሰዎች በመጀመር ለእሑዱ ቀጠሮ መያዝ እና የመሰባሰቡን ሁናቴ መልክ መስጠት መጀመር ይኖርባቸዋል። ዓላማችን አንድ ነው። እርሱም “ሃይማኖታችንን እና ሃይማኖታችንን ብቻ የተመለከተ ነው”። ስብስባችንን የሚጠሉ ሰዎች በፖለቲካ በማሳበብ በመንግሥት ዱላ ለማስደብደብ የሚያደርጉት ሙከራ እንደሚኖር ስለምናውቅ ከወዲሁ ለሚመለከተው ሁሉ ዓላማችንን መግለጽ እንፈልጋለን። መነጋገር የምንፈልገው ከቅ/ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አባቶች ጋር ነው።” ባለችው መሠረት ምእመናን ጉዳዩን አንሥተው መነጋገር ጀምረዋል።

በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ ኦርቶዶክሳውያን ማኅበራት እና ስብስቦች በሙሉ በአንድ ላይ በመገናኘት “እኛም የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ያገባናል” ለማለት አንድና ወጥ የሆነ አካል አቋቁመዋል። ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ለማሳሰብ፣ አንድና ወት ሆነ መረጃ ለየሚዲያው ለማቅረብ፣ ለሕዝበ ክርስቲያኑም ጠሪ ለማድረግ ወስነዋል። በውጪው ኣለም የሚገኘው ምእመን ወደ ቤተሰቦቹ በመደወል ጉዳዩን እንዲያሳውቅ ጥሪ ተደርጓል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የመረጃ እትረት ክፈተት ለመሙላት እያንዳንዱ ምእመን “ሬዲዮና ቴሌቪዥን” እንዲሆንና “የቤተ ክርስቲአኔ ጉዳይ ያገባኛል” የሚለውን ሐሳብ እንዲያስተጋባ ተጠይቋል። የዚህን እንቅስቃሴ ዝርዝር ሐሳብ በሌላ ዘገባ እንመለስበታለን።


ይሁን እንጂ እንደገመትነውም ይህንን ፍፁም ሃይማኖታዊ ጥያቄ ሌላ መልክ ለመስጠት፣ ኢሕአዴግ ላይ የተነሣ ሰላማዊ ሰልፍ ለማስመሰል የሚሞክሩት አካላት በሶሺያል ሚዲያዎችና በብሎጎች የማዳከም ጥረታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። አልተሳካላቸውም። አሁንም የጀመርነው እንቅስቃሴ ይቀጥላል። “እኔም ለቤተ ክርስቲያኔ ያገባኛል” ማለታችን ይቀጥላል።

አሁንም ይህንን ለማድረግ እንሞክር፦
 •     መረጃውን ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እናድርስ፣ (በስልክ የኤስ.ኤም.ኤስ መልእክቶች፣ በፌስቡክ፣ በትዊተር)፣
 •      ዜናውን ለመገናኛ ብዙኃን እናድርስ፣
 •      ብፁዓን አባቶችን በስልክም በአካልም በመቅረብ ስለ ጉዳዩ ማነጋገር፣ በውሳኔው እንደማንስማማ እናሳውቅ፣
 •      ጉዳያችን እና ዓላማችን “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ” ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን አባት የመምረጥ ጉዳይ መሆኑን ለሚመለከታቸው አካላት አለ ፍርሃትና ያለ ሥጋት እንግለጽ፣
 •      ከመንግሥት አካላት የተደበቀ የመሥራት ፍላጎት እንደሌለን ከወዲሁ በተደጋጋሚ እንግለጽ፣
 •     በአገር ውስጥ ያሉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ለጉዳዩ ሽፋን እንዲሰጡት እናበረታታ፣
 •      የውጪ አገር ኢትዮጵያውያን ሚዲያዎችም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ በሚል በዚሁ ሰበብ ኢሕአዴግን ለመተቸት ሳይሆን ጉዳዩን ለክርስቲያኑ ሕዝብ በማይጎረብት መልክ እንዲያቀርቡት እናግዝ፣
 •      ኦርቶዶክሳውያን ጡመራ መድረኮችም ዜናዎችን በትብብርና በኅብረት ለምእመኑ እናድርስ።
  
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
  
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)