December 23, 2012

ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ መነሻ በማድረግ በዋሸንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠ መግለጫ


የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ እና ማስጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታችን ነው። 
(ታኅሳስ 13  2005 ዓ. ም/ PDF):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ መንበረ ፕትርክና ከማግኘቷ በፊት ለ 1600 ዓመታት ከግብጽ በሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት በመንበረ ማርቆስ ሥር ስትተዳደር መቆየቷ ይታወሳል ። በእነዚህ ባሳለፈቻችው ዘመናት የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲጠበቅ በነበራት ጽኑ አቋም ብዙ መስዋዕትነት ከፍላለች። ችግር በገጠማትም ጊዜ ከግብጽ የሚመጡ አባቶች ሲቀሩባት እንኳን  ስለ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ምስክርነቷን እየሰጠች ፤ በርካታ ሊቃውንትን ፤ በቅድስና የከበሩ አባቶችን  ይዛ ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ስትል ግን ከመንበረ ማርቆስ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲላኩላት ስትማጸን ኖራለች።
በተለይም “ ወሰብአ ኢትዮጵያ ኢይሢሙ ላዕሌሆሙ  ሊቀ ጳጳሳት እማእምራኒሆሙ ወኢበሥምረተ ርእሶሙ” ኒቅያ   ፵፪፡ ፶  የሚለውን  ምንባብ በማንሳት  ፤ በሥርዋጽ የገባ መሆኑን ለማስረዳት አድካሚና ተደጋጋሚ ጉዞ ወደ ግብጽ በማድረግ  ፤ መጽሐፋዊና ታሪካዊ ማስረጃን በማቅረብ በመንበረ ማርቆስ ለሚገኙ አባቶች ችግሩን በማስረዳት በውይይት ለብዙ ዘመናት እንደ ተራራ ገዝፎ የተቀመጠውን ችግር በማቅለል  የቤ ክርስቲያን አንድነት እንደተጠበቀ የራሷ መንበረ ፕትርክና እንዲኖራት አድርገዋል ። የቀደሙት አባቶችቻን በተግባር ያስተማሩን ትምህርት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ ሲባል የማይከፈል መስዋዕትነት አለመኖሩን ነው። ዛሬም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚፈታተኑ፤ መዋቅራዊ አንድነቷን የሚያናጉ፤ አለመግባባትና መለያየትን የሚፈጥሩ ችግሮች  በተለይም  በሰሜን አሜሪካ  እየታዩ መምጣታቸው  ፤ ትክክለኛ ፍርድ እና ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች መብዛታቸውን ስንመለከት፤ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ እና ሃይማኖታዊ አመራር መዋቅራዊ ተዋረዱን ጠብቆ መጠናከር እንዳለበት ያስገነዝበናል። እኛም በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምንገኝ አብያተ ክርስቲያናት የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ይጠበቅ በማለት በተደጋጋሚ ለቅዱስ ሲኖዶስ በማሰማት ላይ የምንገኘው ይህንኑ ችግር ለማቃለል እገዛ እንዲያደርግ ነውበሰሜን አሜሪካ ያለው የቤተ ክርስቲያን አንድነት ጉዳይ መፍትሔ ተሰጥቶት ካህናትና ምእመናን በአንድነት ለአንዲቷ፤ ቤተ ክርስቲያን ማገልጋል ባለመቻላቸው፤ በርካታ ችግሮችን አስከትሏል። የምእመናን እና ካህናት ህሊና በብዙ ጉዳይ ተፈትኗል፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለገዳማትና አድባራት መርዳት ሲቻል አንድነቱ በመጥፋቱ ብዙ ልጆች ያላት እናት ቤተ ክርስቲያን ለችግሯ መድረስ ሳይቻል ቀርቷል። የቤተ ክርስቲያን አንድነት መፈጠሩ በመላው ዓለም ለምንኖር  ኦርቶዶክሳውያን  በሙሉ ትልቅ የህሊና እረፍት የሚሰጥና  በአንድ ልብ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ትልቅ በር የሚከፍት ነው:: ለዚህም  በአባቶች መካከል የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት ይህንን ተስፋ እውን ያደርጋል የሚል ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል።  ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ቀጣይ ፓትርያርክ በመንበር ላይ ለማስቀመት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ኃላፊነት ውስጥ ትገኛለች። የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመጨረሻ ወሳኝ አካል መሆኑን ሙሉ ለሙሉ የምንቀበል መሆኑን በማስገንዘብ፤ እንደ ቤተ ክርስቲያን አባልነታችን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ካለን ጽኑ አቋም እንዲሁም በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችን ያሉ ካህናትና ምእመናን  ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እያሳዩት ያለውን መጨነቅ በመገንዘብ  ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  የሚከተሉትን ጥያቄዎችን  ስናቀርብ  በታላቅ መንፈሳዊ አክብሮት ነው፦

1.              የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና በወቅቱ የነበረውን ታሪካዊ እውነት መሰረት ባደረገ መልኩ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲያገኝ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል  በእመናንና በካህናት የሚታየው ግራ መጋባት እንዲቃለል  ግልጽ የሆነ መግለጫ በየደረጃው እንዲሰጥ፦

2.             በመንበረ ፓትርክና አባት ከማስቀመጥ በፊት ቤተ ክርስቲያናችን የገጠሟትን  የተወሳሰቡ ዘርፈ ብዙ አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲፈቱ  በቂ ጊዜ መስጠቱ ትውልዱን ከታሪክ ተወቃሽነት ስለሚያድን እና  እስካሁን የታዩት አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲፈቱ  የሚያደርግ፤ አሰራር በተጠናከረ መልኩ ማስቀመጥ ተገቢ ስለሆነ  ለዚህ ጉዳይ በቂ ጊዜ እንዲሰጠው፦
  
3.             በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ይህንንን የተወሳሰቡ ዘርፈ ብዙ  የቤተ ክርስቲያን  አስተዳደራዊ ችግር ለመፍታት  እንዲያግዝ  በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ካህናት ምእመናን፤ የአስተዳደርና የሕግ ባለሙያዎች   የሚገኙበት  የምክክር ጉባኤ ቢዘጋጅ፦

በማለት በታላቅ ትህትና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ስናቀርብ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር የምትገኙ አብያተ ክርስቲያናትም  ወቅታዊ  የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በጸሎትና በምህላ በማሰብ  በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመሆን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ  ከብፁዓን አባቶቻችን ጋር በቅርበት በመወያየት ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ  ጥሪ በማስተላለፍ ነው።

እግዚአብሔር አንድነታችንን ይባርክ
ግልባጭ
·                     ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
·                     ለመንበረ ፓትርያርክ ቅዱስ ጽ/ቤት
·                     ለብፁዓን አባቶች በያሉበት 

1 comment:

Anonymous said...

ይበል ብለናል!
እግዚአብሔር ይጨመርብት።

ዳላስ/ ቴክሳስ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)