December 20, 2012

“ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ስኬት የአባቶቻችን ስምምነት ወሳኝ ነው” (ማኅበረ ቅዱሳን)

(ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም./ READ THIS IN PDF)፦ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሥጋ ሕይወት በነበሩበት ባለፉት ዓመታት “ስደተኛ ሲኖዶስ” ተብሎ ከተጠራው በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አባቶች ጋር ዕርቅ ለመፈጸም ጥረት ይደረግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገብ ሳይችል በእንጥልጥል እንዳለ ቅዱስነታቸው ዐረፉ፡፡ የእርሳቸው ዕረፍት ቀጣዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ከመመረጣቸው በፊት በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ተለይተው ከሚኖሩ አባቶች ጋር ውይይት ለመጀመር አስገዳጅ ሁኔታ አምጥቷል፡፡
ይህ እንዲታሰብ ግድ የሚያደርገውም ቀጣዩ ፓትርያርክ የሚሰየሙበት መንገድ ሁሉን የማያስማማ ከሆነ የነበረውን ልዩነት የሚያሰፋ ውዝግብ በዚህች ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ስለሚቻል ነው፡፡ ይህንን ከግምት አስገብቶ የወቅቱን አንገብጋቢነት ተረድቶ ወደ ዕርቅ የሚያደርስ ውይይት ማድረግ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን ወሳኝ አገልግሎቶች በብቃትና በስፋት ለመስጠት፣ ጠንካራ መሠረትም ለመገንባት ስለሚያስችል ነው፡፡


በመሠረቱ ሲኖዶስ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በጉልህ የተገለጠ ተግባሩ መለያየቶችን መፍታት ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መትከል ነው፡፡ ስለዚህ ሲኖዶስ ሲታሰብ ሰላምና አንድነት ይታሰባሉ፡፡ ትሕትናና ፍቅር ይነግሣሉ፡፡ ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን የሐዋርያዊ አገልግሎት አደራ መንጋውን የመጠበቅ ሓላፊነት ከመወጣት ሌላ ለሚሰበሰበው መንጋ አርአያነት ያለው ሕይወት አባቶቻችን እንዲኖራቸው፣ ብርሃናቸውም በዓለም እንዲያበራ ስለታዘዙም ነው፡፡

እነዚህ የክርስትና ዐበይት ተግባራት በአባቶቻችን ደግሞ ጎልተው እንዲገለጹ ይፈለጋል፡፡ አባቶች የክርስቶስን መልክ /እርሱን መምሰልን/ እንደያዙ በሚያስበው የእግዚአብሔር መንጋ፣ እንዲሁም የምድር ጨው ሆነን ሕይወታቸውን ለማጣፈጥ እንድንበቃ አደራ በተሰጡን የምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ በጎ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ብፁዓን አባቶች መልካሙን ጎዳና ሁሉ ሲከተሉ መገኘታቸው ታላቅ ሚና አለው፡፡

ከዚህ ጎዳና ወጥተን ፍቅርን በማጣት፣ በጠብ በክርክር ጸንተን ብንገኝ ፍቅር ከሆነ እግዚአብሔር ጋር ለመኖር ባለመፍቀዳችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከእርሱ ጋር እንዳይኖሩ ማሰናከያ በመሆናችንም ጭምር ያዝናል፤ ይፈርዳል፡፡ ስለዚህ ለብፁዐን አባቶች ብቻ ሳይሆን በክርስቲያኖች ሕይወትም በፍቅር ጸንቶ መኖር፣ ከበደልንም በይቅርታና በዕርቅ ሕይወት ውስጥ ማለፍ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ የዚህ ሕይወት መሠረቱ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያደረገው ዕርቅ ነው፡፡ ጠላቶቹ ከሆነው ከእኛ ጋር እግዚአብሔር ታረቀ መባሉ የሕይወታችን መሠረት ፍቅር መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ስለ ዕርቅ ሕይወት በብዙ ምሳሌና በብዙ ኃይለ ቃል ራሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንም በመሆኑ በጉልሕ በሕይወታችን መንጸባረቅ የሚገባው የጽድቅ ሥራ ነው፡፡

ለእግዚአብሔር ከምናቀርበው ከየትኛውም ዓይነት መባዕ አገልግሎታችን በፊት ከወንድሞቻችን መታረቅ እንደሚገባ ጌታችን አበክሮ ያስተማረው የሕይወት ቃል ነው፡፡ “አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ” ያለው የጌታ ቃል ይልቁንም በቤተ መቅደሱ ዕለት ዕለት መሥዋዕት ለሚያቀርቡ፣ ብዙዎችን በጸጋ እግዚአብሔር ባዕለ ጸጋ ለሚያደርጉ፣ ምስጢራትንም ሁሉ ለሚፈጽሙ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ምልክት ለሆኑ ከሁለቱም ወገን ላሉ ብፁዐን አባቶች የሚያስተምሩት ብቻ ሳይሆን ዘወትር እንዲኖሩት የሚጠበቅ ክርስቲያናዊ ሕይወት ነው፡፡

ይህ በመሆኑም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል “ክርክርና መለያየት አለ” መባሉ ሳይሆን ክርክሩን መፍታት፣ ልዩነትን ወደ አንድነት ስምምነት ማምጣት አለመቻል ከላይ የጠቀስነውን ወሳኝ የሕይወት ቃል የሚፈታተን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራት ባለን አቅምና በጎ ፈቃድ ላይ ጥያቄ የሚያሥነሣ ይሆናል፡፡ በዚህ የማይደሰተው እግዚአብሔርም ብቻ አይደለም፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ ያሉ የክርስቶስ ቤተሰቦችም ናቸው፡፡

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ አንድነት የሚያመጣ ዕርቀ ሰላም መፈጸም ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር አንጻር፣ ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ከማሰብ አንጻር፣ መንጋውን ከማነጽና ሐዋርያዊ አገልግሎትን ከማቅናት አንጻር ለአባቶቻችን ግዴታ ይሆንባቸዋል፡፡ የሚፈለገው ዕርቀ ሰላም እውን እንዲሆንም ለእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ለእውነት፣ ለኅሊና ምስክርነት መገዛት አግባብ ይሆናል፡፡

ከዚህ በፊትም ማኅበረ ቅዱሳን እንዳስገነዘበው አባቶች ሰላሙን ለማምጣት የሚያስችሉ ቀኖናዊ ጉዳዮችም ላይ ለመወሰን ለማጽናትም መንፈሳዊ ሥልጣንን የተጎናጸፉ በመሆናቸው ዕንቅፋትን ማራቅ ይችላሉ፡፡ የዕርቅ ሒደቱ ሲፈጸምም ሃይማኖታዊ መልክ ያጡ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና ምእመናንን የማያሳምኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመደርደር መታቀበ ከተቻለ በተስፋ የተሞላ ሒደት እንደሚሆን ይታመናል፡፡

ከማንምና ከምንም በላይ የቤተ ክርስቲያናችንን ቤተሰብ ማሳመን የማያስችሉ እርምጃዎች ውስጥ መግባት ተአማኒነትን ሊያሳጡ ይችላሉ፡፡ ለዓመታት የዘለቀውን መለያየት /ውዝግብ/ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥም የካህናቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ማኅበራትና በአጠቃላይ የሕዝበ ክርስቲያኑ ሐሳብና አስተያየቶች ከግምት የሚገቡበት አካሔድ ሊኖር ይገባል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ካልተሰማ በቀጣዩ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር አካላት ላይ የሚኖረው አመኔታ ይላላል፡፡ በመሆኑም በዚህ በዕርቁ ሒደት ክርስቲያኖች ያላቸው ሐሳብ ሊመረመር ይገባል፡፡ ስለዚህ ሁሉም የሃይማኖት ቤተሰብ ደስ የሚሰኝበት ምዕራፍ ላይ ለመድረስ መትጋት ከአባቶቻችን ይጠበቃል፡፡

ስለዚህም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ለሰላሙ መስፈን አስፈላጊ የሆነ ዋጋ እንዲከፈል ግፊት በማድረግ ሊረባረቡ ይገባል፡፡ ምእመናንም ከካህናት አባቶች ጋር በጸሎት በመትጋት ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እግዚአብሔር እንዲሰጠን መማጸን ይገባናል፡፡ የተጀመሩትን ሒደቶች ሁሉ በእውነተኛነት በሚዛናዊነት እየተከታተሉ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችው ያለፉት ዓመታት ኣሳዘኝ ሁኔታዎች እንዳይቀጥሉ ዛሬ ላይ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባን ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ለዚህም ይሠራል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


4 comments:

Anonymous said...

“ሰማይ ይስማ” እንላለን፤ የተጀመረው ዕርቅ ይፈጸም፣ ሰላም ይውረድ፣ አባቶች አንድ ይሁኑ፣ በዚህ ግርግርግር መካከል ፕትርክናዋን “ለቀም ላድርጋት” ብላችሁ የቋመጣችሁ ስለ ቤተ ክርስቲያን ብላችሁ ልብ ግዙ!!!

ሀ: አቡነ መርቆሬዎስ በህይዎት አሉ፤
ለ: ስልጣናቸው መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸው ስልጣን ነው፤
ሐ: ከሃገር የወጡት ተገፍተው ነው፤
መ: ሕዝባቸውን በሙያቸው እያገለገሉ ናቸው፤
ሠ: እምነትን ያጎደሉበት ህጸጽ ካለባቸው ለምእመናን ግልጽ ይደረግ።

ምእመናን የምናውቀው፥ የምናየውና የምንሰማው ሀቅ ሕዝባቸውን በሙያቸው እያገለገሉ መሆናቸውን ነው፤ ይህ ሆኖ እያል፤ ታድያ አቡነ መርቆሬዎስ ተርማቸውን ሳይጨርሱ ለምን ሌላ ፓትርያርክ መምረጥ አስፈለገ? ውድ ወገኖቸ፤ ከኰሚዩኒዝም ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ እግዚአብሔር በሀገራችን ላይ ያደረገው ለሁላችንም ግልጽ ሳይሆንልን ቀርቶ አይደለም፤ እግዚአብሔር ያረመውን እኛ ፍጡሮቹ እንዳናበላሽ እናስተውል እንጂ፤ በማቴ ፮፥፲፬ -፲፭ ያዘዘው አባቶቻችን አይመለከታቸውምን?
ሁሉም ለማለት ብቸገርም፤ አብዛኛው ምእመናን ዛሬ ይቅር ለእግዚአብሔር እያል ይገኛል። ከአባቶቻችንም ይህንኑ ይጠበቃል። በጐች ተቅበዘበዙ፥ በጐች ጥሩ እረኛ ፈለጉ፥ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ሰግስገው ገብተው በጐችን እያመሱ ናቸው፤ የተኩላው መንጋ ራቅ ብሎ በጐች እስኪበተኑ ይጠብቃል። አባቶቻችን ሆይ ልጆቻችሁ ተኩላውን እናሸንፍ፤ እርዱን? ለቤተ ክርቲያኗና ለምእመናን አንድነት ስትሉ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን አድርጉልን?

አቡነ መርቆሬዎስ በቀራቸው የእድሜ ዘመን መንጋውን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ከሆኑ:-
፩ ወደ ኢትዮጵያ ይግቡ፣
፪ ማእረጋቸው ፬ኛው ፓትርያርክ እንደሆነ ይጠበቅ፣
፫ አሜሪካ ከ፬ ባላነሰ አህጉረ ስብከት ትከለል፣
፬ ቃለ አዋዲ በመላው የውጭ አገር ላሉ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ባስቸኳይ ይሰራጭ፣
፭ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ከሙስናና ከዘረኝነት ባስቸኳይ ትንጻ፣
፮ የአባቶቻችን ስራ ሁሉ የክርስቶስን ይምሰል፤ ጻድቃንና ሰማእታት ትተውልን እንዳለፉ ጠብቀን እናስተላልፍ።

የቅዱሳን አምላክ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፤ አሜን።

Anonymous said...

Mahibere Kidusan,

I would like to ask you a forgivness as an organization. It's true that my hatered and so negative view of the organization came from my true love to my church and also some of the things that went on around the organizations(name calling, spying, personal character assasination, and the cult like culture that memebers have to the organization)

I always thought MK is and will be at the top of the list in the all rounding problems our church has. And I always htought MK is the only major obstacle for peace and reconsiliation, in my opinion the MAKE or BREAK of the Ethiopian Orthodox Tewahido Church. Let's not kid ourselves, if this is not done now, the church is is not church of God. It cant be. It wont be

I would like to thank MK for being such a positive force in this trying times. I would like to thank MK setting aside EVERYTHING and realizing THIS IS IT.

This is our time to take our church back.

God help us

Unknown said...

"...ይሠራል፡፡" እናንተን "አይሠሩም" ብሎ የሚገምት ሞኝ ነው። የምትሠሩት "ለዝህም" ስለመኾን አለመኾኑ የሚጠራጠር ቢኖር ግን ምክንያት አለው። ቃላችኹን ጠብቃችኍ ከጥርጥር አውጡንና ቤተ ክርስቲያናችንን ከክፍፍል ለመታደግ ዐብረን ተባብረን እንሥራ። እንዲያ የኾነ እንደኾነ እግዜሩም ይረዳናል።

Hailu said...

AMEN. Thank you MK.

If the fathers don't work to arrive at a solution to the most pressing issue of our church, what is it in there to be called holy fathers?

If they don't make peace among themselves and unite our church, what is holy about them?

If whatever they decide is going to leave our beloved church and its followers divided and weakened, what are they going to profit in spiritual sense?

Oh GOD, don't forsake us. Please unite us. Amen.


Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)