December 11, 2012

ከጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምእመናን ኅብረት የተላከ


(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 2/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 11/2012/ READ THIS IN PDF)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት አስመልክቶ ብዙ አንባብያን ሐሳባችሁን ስትሰጡ መቆየታችሁ ይታወሳል። በተለይም ከአበው ሊቃውንት መካከል በጀርመን የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ያስነበቡት ጽሑፍ አንዱና ዋነኛው ነው። ጽሑፉ ስለ ዕርቁ ያነሣቸው መሠረታዊ ጉዳዮች እንደተጠበቁ በጀርመን ከሚገኙ ደጀ ሰላማውያን ደግሞ ስለ ጽሑፉ ባለቤት አስተያየቶች ሲላኩ ቆይተዋል።
ደጀ ሰላምም ጊዜው ስለ አካባቢያችን ችግር የምንነጋገርበት ሳይሆን ዋነኛውን አጀንዳ ማለትም ዕርቁን የተመለከተ ቢሆን ይመረጣል በሚል ሐሳብ አስተያየታችሁን ሳናስተናግድ ቆይተናል። ቃል በገባነው መሠረት እነሆ አሁን በጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምእመናን ኅብረት የተባለ ክፍል የላከውን አስተያየት የምናቀርብ ሲሆን ሊቀ ካህናትም በበኩላቸው የሚሰጡት መልስም ሆነ አስተያየት ቢኖር ለማስተናገድ የምንችል መሆናችንን ከወዲሁ እናስታውቃለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ይህን ጽሑፍ እንድናዘጋጅ ምክንያት የሆነን በጀርመን ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊያችን ከሆኑት ከሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በዲሴምበር 1 ፥ 2012 በኢሜይል አድራሻችን የተላከለን ግልጽ ደብዳቤ ሲሆን ይኸውም ግልጽ ደብዳቤ በደጀ ሰላም የመጦመሪያ ገጽ ላይ ከመውጣቱም በተጨማሪ መልእክቱን በስፋት ለማስተላለፍ ይረዳ ዘንድ እኛም በፌስቡክ ገጻችን ለምትከታተሉን ምእመናን መለጠፋችን ይታወቃል። 

የምእመናን ኅብረቱ ሊቀ ካህናት በደብዳቤያቸው ያነሷቸውን አሳቦች በሚገባ ይገነዘባል፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም አንድነቷ እንዲመለስ ጊዜው አሁን መሆኑን አጥብቆ ያምናል። በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ አባቶቻችንም የጀመሩት እርቀ ሰላም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እስኪመለስ ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳስባል። ይህንንም ከግምት በማስገባት የሊቀ ካህናትን መልእክቅት በፌስ ቡክ ገጻችን ላይ አውጥተነዋል።

ሆኖም ግን በተለይ በደጀ ሰላም የወጣውን የሊቀ ካህናትን ግልጽ ደብዳቤ ተከትሎ የተሰጡ አንዳንድ አስተያየቶች እዚህ በጀርመን ያሉ ሊቀ ካህናት በበላይነት በሚመሯቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉትን ችግሮች ተፍነው እንዲያልፉ ያደርጋሉ የሚል ስጋት ስለያዘን በጉዳዩ ላይ አንዳንድ የግንዛቤ ነጥቦች ለማንሳት አስገድዶናል። በተለይ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ሊቀ ካህናት በደብዳቤያቸው ላይ ያነሷቸው አሳቦች አሉና በዚያው ላይ እናተኩራለን።

በዚህ ባለንበት በጀርመን ሀገር ያለችው ቤተ ክርስቲያናችን ያለፉትን 30 ዓመታት ስታሳልፍ ያለ ችግር እንዳልሆነ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። የአስተዳደሩን እንኳን ለጊዜው ወደ ጎን ብናስቀምጠው ለበርካታ ዓመታት በምእመናኑ አቤቱታ ሲቀርብበት የከረመው እና የቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጣስን የሚመለከተውን መጥቀስ እንችላለን።

ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ ሊቀ ካህናት በደብዳቤያቸው ብዙ ብለዋል፤ ያነሷቸው ነጥቦች ተገቢ መሆናቸውም አያጠራጥርም። ሆኖም ግን ይህን እንደሚያነሳ ሰው ደግሞ ባሉበት አካባቢ ሥርዓት መጠበቁን ቢያረጋግጡ መልካም በሆነ ነበር። ዳሩ ግን እርሳቸው ራሳቸው ቀኖናን አስመልክቶ በዚሁ በጀርመን ሀገር የፈጸሙትን ከባድ ስህተት የዘነጉት ይመስላል። መናፍቅ ሆነው አሁንም በዛው ሥራቸው የቀጠሉበትን ግለሰብ ክህነት መልሶ አለቃ አድርጎ መሾም ምን ማለት ይሆን? ደብዳቤያቸው ላይ ለማጣቀሻነት የተጠቀሙት የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መጽሐፍ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 6 ከንዑስ አንቀጽ 224 ጀምሮ ያለውን፤ አንድ ካህን ከክህነቱ የሚሻርበትን ምክንያት፤ አስመልክቶ በስፋት የተጻፈውን ምነው ችላ አሉት? ሊቀ ጳጳሱ ናቸው ክህነቱን የመለሱለት፤ እኔ ምን ላድርግ?” ሲሉ የቆዩት ሊቀ ካህናት አቡነ ዮሴፍ ክህነት አለመመለሳቸውን በደብዳቤ ገልጠው መጻፋቸው ሲታወቅ ምነው ዝምታን መረጡ? እውን ማን ሆነና ነው እኚህን ግለሰብ ቀኖና ሽሮ አለቃ ብሎ የሾመው? ይሄስ በታወቀ ጊዜ ግለሰቡን ካስቀመጧቸው ቦታ ላይ ለማንሳት ምን ጊዜ መውሰድ አስፈለገ፤ ሊያውም ግለሰቡ አሁንም ኑፋቄያቸውን በአደባባይ እየረጩ ባሉበት ሁኔታ።

እንደው የቀኖና ነገር መነሳቱ ካልቀረ ደግሞስ መች ይህ ብቻ ሆነና፤ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2007 ማግደቡርግ ከተማ ላይ ከአስር የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት፣ የአንግሊካን እና መሰል አብያተ ክርስቲያናት ጋር አንዱ ቤተ እምነት የሌላውን ጥምቀት እንዲቀበል በሚያዝ ሰነድ ላይ ሊቀ ካህናት ማንንም ሳያነጋግሩ፤ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ውሳኔ ሊሰጥ ከሚችለው ብቸኛው የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል ከቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ለማስፈጸም ኃላፊነቱ ሳይሰጣቸው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ስም ፊርማቸውን ሲያኖሩ (http://de.wikipedia.org/wiki/Magdeburger_Erkl%C3%A4rung) ምነው ሃይማኖት መጣሱን፣ ሥርዓት መፍረሱን ወደ ጎን አሉት? በፍትሐ ነገሥቱስ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 24 ላይ ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም የሚለው ትእዛዝ ተሰርዞ ይሆን? ይህንን በሚመለከት ለስም ጽድቅ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በመፈረሜ ይቅርታ አልጠይቅም፤ አልጸጸትም፤ የምፀፀተው ስፈራረም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ባለመጠየቄ ነው፤ እንዲህ ሰዎችን የሚያሳዝን መሆኑን አላወኩም በማለት ለሠሩት ከባድ ስህተት አጥፍቻለሁ፤ ቀኖና ብቻ ሳይሆን ዶግማም አፍርሻለሁ ሳይሉ ይቅርታ አልጠይቅም፤ አልጸጸትም ብለውናል። ይቅርታውስ ቀርቶ ቢያንስ ከቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል ፍቃድ ሳያገኙ መፈጸማቸውን ካመኑ እስካሁን ድረስ ምነው ፊርማቸው እንዲነሳ አላደረጉ? ይህ የቀኖና ችግር አይደል ይሆን? ዶግማንስ አይመለከት ይሆን?

ከላይ ከጠቀስናቸው በተጨማሪም ምእመናኑን እያስነቡ ያሉ ሌሎች በዚህ ጽሑፍ ያላካተትናቸው የአስተዳደር ችግሮች ባለመፈታታቸው ቢያንስ በዚህ በጀርመን ሀገር ላለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መከፋፈል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ምክንያት እየሆኑ ነው።

እስከ ጥቂት ዓመታት ድረስ ፍራንክፈርት ከሚገኘው የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ውጪ በስደተኛው ሲኖዶስ የሚመራ ቤተ ክርስቲያን ጀርመን ውስጥ አልነበረም። በቪዝባደን፣ በሙኒክ፣ በሽቱትጋርት ከተሞች ከነበሩበት ወጥተው በነኚሁ ከተሞች በውጪው ሲኖዶስ ሥር የሚመራ ቤተ ክርስቲያን ያቋቋሙት ምእመናን እኮ ሊቀ ካህናት በአካባቢያቸው ለተነሱ፣ ከሃይማኖት አንስቶ እስከ ገንዘብ ምዝበራ ድረስ ለተፈጸሙ በደሎች ምላሽ ሊሰጧቸው ስላልቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ ለበዳዮቹ ጥብቅና በመቆማቸውም ጭምር ነው። እነኚህ ተገንጥለው የወጡ አብያተ ክርስቲያናት ከነኚህ ችግሮች በፊት እኮ አልነበሩም። እና ይሄስ የቤተ ክርስቲያን አንድነትን የሚመለከት አይደለም? በሲኖዶስ አንድነት ብቻ የሚፈታ ጉዳይ ነው?

ፈጣሪ መልካም ፍላጎታችንን የሚያሟላው በንጽሕና ሆነን ከእኛ ዘንድ በቅድሚያ መወጣት ያለብንን ሠርተን የመጣን ጊዜ ነው። ሁላችንም ለሠራናቸው ስህተቶች በቅድሚያ ይቅርታ ጠይቀን በውጪም በውስጥም ያለውን የቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት ከችግር በማጽዳት አንድነቷን እንመልስ፤ ሩቅ ሳንሄድ ቅርብ ካሉብን ችግሮች መጀመር ከቻልን የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ሳይውል ሳያድር የሚፈጸም ይሆናል። የፈረሰውን ለመመለስ፣ ለማቃናት አሁንም አልዘገየም። አብረን ለቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች መፍትሔ እንፈልግ እንላለን። እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ለምትሆን ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምን፣ ፍቅርን እና አንድነትን ይስጥልን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።
በጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምእመናን ኅብረት።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)