December 1, 2012

“አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ፅኑዕ መዝጊያ አኑር”


(በተለይ ለ“ደጀ ሰላም” የተሰጠ ምላሽ)
አብዩ በለው (abiyuye@gmail.com)
ኮሎምቦስ/ኦሃዮ  ኖቨምበር 29, 2012

ምክንያተ ጦማር
ከላይ በርዕሱ እንደተቀመጠው አዘውትሬ የምጎበኛት የቀደመችይቱ ደጀ-ሰላማችን “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ የት ነዎት?” በሚል ርዕስ በድጋሚ “እንደገና እንጠይቅ” በሚል ባስነበበችን አነስተኛ መጣጥፍ (የአፍልጉኝ ማስታወቂያ አይነት ነገር) ላይ የእኛን የአንባቢዎቿን “አስተያየት” እንድናካፍላት በተማፀነችው መሰረት ፣
እንዲሁም በደጀ ሰላም በኩል የተነሳው መጠይቅ በሌሎችም የዜና አውታሮችና የጡምራ መድረኮች በተደጋጋሚ ሲቀርብ በማየቴ እግረ መንገዴን ጉዳዩን እየተከታተሉ ለሚገኙ ወገኖቼ በሙሉ የእኔን የግል እይታ፣ ሃሳብና፣ እምነት ለማካፈል ወደድኩና ነው፡፡
መልካም ንባብ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ  እና ....
 ፩ ፡- “….የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፍን አልከፈተም”
ፈጣሪያችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ማድረግ ሲችል አስቀድሞ በነብዩ በኢሳያስ  “እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፍን አልከፈተም ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤  የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፍን አልከፈተም” ኢሳ. ፶፫፥፯-፰ ተብሎ እንደ ተነገረለት ዘመኑ ሲደርስ እርሱ ፍፁም ንፁህ ሳለ እንደ ክፉ ወንጀለኛና እንደ በዳይ በአለማዊው ዳኛ ፊት  በፍርድ አደባባይ ቀርቦ “የሚከሱህን አትሰማም?” እየተባለ እርሱ ግን በከሳሾቹ ፊት አንዳች ቃል ሳይናገር መከራውንና አሳሩን ሁሉ ታግሶ በደሙና በሞቱ ነፃ እንዳወጣንና ቅድስት ቤተክርስቲያኑንም እንደ ዋጃት በተረዳ ነገር እናውቃለን፡፡
ዛሬም በዘመናችን ይህቺው አማናዊት ቅድስት ቤተክርስቲያ አስቀድሞ ከ37 ዓመታት በፊት በህወሃት/ኢህአዴግ በኩል “ሞት” እንደተፈረደባትና በዚህ የእኩዮች ውሳኔ ጦስ የቤተክርስቲያኒቱ መሪ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ከመንበራቸው በፖለቲካዊ ውሳኔና በሃይል መወገድና ለስደት መዳረግ እንዲሁም በምትካቸው ሟቹ አባት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ(ነብስ ይማር) እንዲሁ በተመሳሳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ “በመንበረ ተክለሃይማኖት” መቀመጣቸው ዛሬ ላይ ሁነን ስንመዝነው “እውነትና ንጋት”ን በከንቱ ማነብነብ ይሆንብኛል፡፡ ምክንያቱስ ቢሉ አንጋፋዎቹ የፓርቲው መስራቾችና መሪዎች እነ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ ክንፈ ገ/መድህን(ነብስ ይማር)፣ ታምራት ላይኔና፣ እንዲሁም በቅርቡ ስብሃት ነጋ (አቦይ) በቃልም በመጣፍም በልበ ሙሉነት ገልጠውታልና ነው፡፡
ይልቁንም በማያውቁት በደልና ጥላቻ አስቀድሞ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር በአንድነት የተፈረደባቸው እኒህ አረጋዊ አባት ለማያውቁትና ለአስጨናቂው ክፉው ስደት ሲዳረጉና በዚያ ሁሉ ግፍና መከራ ሲያልፉ እርሳቸውም እንደ ፈጣሪያቸው በኢህአዴጋዊያን ሸላቾች ፊት እንዲሁ “ዝም” ማለትን እንደመረጡ እናስተውላለን፡፡ ይህ “ዝምታ” እንደምንስ ያለ ክርስቶስን የመምሰል ድንቅ ህይወት? እንደምንስ ያለ መታደል ይሆን?
፪፡- ጲላጦስም “ይህን ያህል ሲከሱህ አንዳች አትመልስምን?”
ዛሬ እንዲህ እውነቱ ሊገለጥ በአለፍት 20 ዓመታት የብፁዕ አባታችን ስደት በተመልከተ ብዙዎች እጅግ ብዙ ብለንበታል፡፡ አንዳንዶቻችን ትንትናኔዎችን በመስጠት፣ ጥቂት የማንባልም አቋም በመያዝ እረጅም እርቀት ስንጓዝ ከርመናል፡፡ በዚህም ምክንያት የአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች ከሦስት ተከፍለን ግማሾቻችን ከአሳዳጆቹ ፣ ግማሾቻችን ከተሳዳጁ አባት፣ ቀሪዎቻችንም በቤተክርስቲያናችን የመከራ ዘመን ገለልተኞች ነን (ገለልተኝነቱ ምኑ ላይ እንደሆነ ባይከሰትልኝም) ከሚሉቱ ወገኖች ጎን ተሰልፈን በከንቱ ስንቅበዘበዝ መኖራችን ዛሬም መቋጫ ያላገኘ የክርስትናችንና የኢትዮጵያዊ አንድነታችን ፈተና መሆኑ በእጅጉ ይገርመኛል፡፡
ይለቁንም ይህ ኢህአዴጋዊ ድል ዛሬም ድረስ ተሻግሮ እነ አቦይ ስብሃትን በየመድረኩ በድል አድራጊነት ዳንኪራ ቢያስረግጣቸውም እኛ የአደራ ልጆቻቸው ሳንቀር ከከሳሾቻቸው ጀርባ አሸምቀን ብዙ እጅግም ብዙ ዘላብደናል፡፡ ጭራሽ ወደ ዓለም አደባባይ ወጥተው የየዜና ማሰራጫዎቻችን ግብዓት እንዲሆኑ ብዙ ለፍፈናል፡፡ ምን አልባትም ከሳሾቻቸውና አህዛብም ከሚወተውቱት በላይ እኛ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች በቁንፅል ዘመናዊነታችን “እውነቱን ለአህዛብ ይናገሩ” እያልን ዘብዝበናቸዋል፡፡ እርሳቸው ግን መሪያቸው እርሱ እውነተኛው መንፈስ ቅዱስ ነበርና የመረጣቸው እርሱ ክርስቶስ በጲላጦስ አንደበት “ይህን ያህል ሲከሱህ አንዳች አትመልስምን?” ብሎ እንደገና ጠየቀው ጌታችን ኢየሱስ ግን ጲላጦስ እስኪደንቀው ድረስ አንዳች አልመልሰም” ማር. ፲፭፥፬-፮   እንደተባለለት         እንዲሁ ዛሬ ዓለም ይልቁንም የተገላቢጦሽ እኛ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች እስኪደንቀን ድረስ አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ለ21 ዓመታት በከሳሾቻቸውና በእኛ በልጆቻቸው ፊት ለዓለሙ የወሬ መሸቀጪያ መድረክ አንዳች ሳይሉ ሁላችንም እዚህ ደርሰናል፡፡
፫፡- አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ፅኑዕ መዝጊያ አኑር
ልበ ዐምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ፅኑዕ መዝጊያ አኑር  መዝ ፵፥፫ እያለ እንደፀለየው ሁሉ በዚህ ሁሉ መተራመስና ውዥንብር መካከል የቅዱስ አባታችን አቋምና ምላሽ ግን ፍንትው ያለ፤ ለአለፍት ረዥም የመከራ ዓመታት በብቸኝነትና በፅናት የዘለቀ አንድና አንድ ነበር፡፡ይኃውም በሰው ዘንድ የማይቻል የሚመስል ቅዱስ ዳዊት እንዳለው ለከነፈሮቹ ጠባቂ መላዕክት ለተኖሩለት ግን እንደሚቻል ያረጋገጠ ፍፁም ዝምታ፡፡ ዝም! ጭጭ!
ይህ  አባታዊ “ዝምታ” ደግሞ እጅግ የሚገርም ነው፡፡ አብዛኞቻችን የቤተክርስቲያናችንና የሃገራችን ጉዳይና የወደፊት እጣ ፋንታ የሚገደን ወገኖች በቅርበት እንደምንከታተለው ከሆነ ቅዱስ አባታችን እንኳንስ በአለማዊው የመካሰሻ መድረክና የዜና አውታሮች ይቅርና በእርሳቸው ስም በስደት የተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርጋቸው ጉባኤዎች ላይ እንኳ በእጅጉ ዝምታን የሚያበዙና በተለይም አሳዳጆቻቸውን በተመለከተ በሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት የከሳሽነት ቃል ተናግረው እንደማያውቁ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡
ይሁንና ይህ አስቀድሞ ጲላጦስን እንደ አስደነቀ ያለ የ“ደጀ ሰላም”ንም ሰላም የነሳ ፍፁም ዝምታ! ከቶ ከወዴት ይገኛል? እንደ ቅዱሱ ንጉስ ዳዊት አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ፅኑዕ መዝጊያ አኑር እያለ አብዝቶ ለተማፀነና ከላይ “እኔንም ምሰሉኝ” ካለው ከዝምታ ባለቤት ከእርሱ ከክርስቶስ ዘንደ ለተሰጠው እንጂ ለሌላ ከቶ ለማን ይቻለዋል?
“ደጀ ሰላም”ና ጥያቄዋ
ደጀ ሰላም ማን ናት? በሚለው ክፍሏ ላይ ባሰፈረችው መነሻነት መድረኳ በቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ላይ የሚነሱትን የህዝበ-ክርስቲያኑን የተለያዩ ጥያቄዎች ይዛ መውጣቷና ለነዚህም ምላሽ ማፈላለጓ የተሰለፈችለት አላማዋ በመሆኑ የሚመሰገን ተግባር እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ በዚህም መነሻነት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን አባታዊ ቃል ለማስተናገድ መንቃሳቀሷ በተለይም መድረኳ“የምትሰራውን እስካወቀች ድረስ” ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ነገርግን ሁኔታዎች ሁሉ ከ“እንቁላል”ም በላይ “እንቁላል” በሆኑበት በአሁኑ ሰአት ይህን “ጥያቄ” “እንደገና እንጠይቅ” በሚል በድተደጋጋሚ መወትወቷ ምነው ይህ ነገር አለበዛም? መካሪስ የለንም?( ኃሳብ መጠየቁ እንዳለ ሆኖ) እንድል አስገድዶኛል፡፡ ለምን ቢሉ ነገርዬው፡-
፩ኛ.  የተቀደሰውን ሁሉ ለ“ዕርያዎች” ቢሆንብኝ
ለእኔ እንደ አንድ ክርስቲያን እጅግ እያሳቅቀኝና ዘወትር ከሚያሳስቡኝ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ነገር ቢኖር የቤተክርስቲያናችንን ችግሮች ለመፍታት የምንከተለው መንገድ ነው፡፡ ይልቁንም ዓለማዊውን የፍትህ ተቋማትና የዜና አውታሮች የሙጥኝ የማለታችን ነገር፡፡
ፈጣሪያችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በህያው ቃሉ “ዓለምን አትውደዷት” በማለት እንድንለያትና ለክርስትናችን የሚበጅ አንዳች መልካም ነገር እንደማናገኝባት፤ ይባስ ብላ ቅዱሳኑን እንደምታሳድድና በስሙም ለተጠራነው ሁሉ ሰይፍና ሾተልን እንደምታዘጋጅ እንደ ተመሰከረላት፤ ይልቁንም በነገሯ ሁሉ እንዳንተባበራት እንደ ታዘዝንባት እናውቃለን፡፡
ነገር ግን እኛ በተለይም የዛሬዎቹ ከዚች እኩይ ዓለም ዘንድ ለሃይማኖታዊ ችግሮቻችን  “መፍትሔ” ፍለጋ ወደ መፍረጃ አደባባዮቿ እየወጣን እርስ በእርሳችን የምንካሰሰውና የሙግት ስይጥንናችን በአህዛብ ሁሉ መንደር እንዲናኝ ብሎም “ክርስትናችን” በእነርሱ ዘንድ “እንዲመሰከርልን” ለዚህም የዓለምን ወሬ-ነጋሪዎችን ቀልብ ለመሳብ የምናደርገው ፍትጊያ እንዲሁም በዚህ ሁሉ ጥቃቅን መስመሮች መካከል ዘወትር ለእርያዎች የምናዝረከርከው የቤታችን ገመና የትየለሌ ነው፡፡ ይህንም ስጋቴን አብዛኛው ህዝበ ክርስቲያን እንደሚካፈለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ደጀ ሰላምንም ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ በዚህም ላይ መድረኳንም የሚያዘገጁ ወንድሞች ብዙ ተመራምረው በግሩም ሁኔታ ለእኛም እያስተማሩን እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ታዲያ የቀደመችይቱ ውዷ ደጀ ሰላም ምነው ይህን ከንቱ መንገድ የሙጥኝ አለች?  ሁሉም ነገር ወደ … ሆነሳ?፪ኛ.  ጲላጦስ ጲላጦስን ቢሸተኝ
ቅዱስ አባታችን የደረሰባቸውን ግፍና መከራ ይልቁንም በእርጅና ዘመናቸው የሚጎነጩትን መራራውን የስደት ኑሮ ታግሰው በከሳሾቻቸው ፊት እንደ አምላካቸው ፍፁም ዝምታን በመረጡና በተለይ ይህን ለሰሚው እንኳ ግራ የሚያጋባ የቤታችንን ጉድ ለዓለምና የዜና አውታሮቿ ባለመሸቀጣቸው በእኛዋ “ደጀ ሰላም” ዘንድ እንደ “መደበቅ”ና “መጥፋት” ተቆጥሮ  “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ የት ነዎት?” “ለምን ድምፅዎትን አንሰማም?” “ሀሳብዎን ለምን አይገልፁም?” “ከምዕመኖችዎ ጋር በትርጁማን፣ በስማ በለው፣ በተላላኪ፣ በሦስተኛ ወገን መነጋገር መቼ ነው የሚያበቃው?ለማለት እንወዳለን”… ወዘተ እየተባለ መዘብዘቡ እጅግ አሳፍሮኛል፡፡ ገርሞኛልም፡፡ ኢ-ክርስቲያናዊም እንደሆነም ይሰማኛል፡፡
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነውና መድረኳን ትዝብት ላይ የሚጥለው ጭብጥ ደግሞ ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ ለዘመተባቸው ለዓለማዊው የዜና አውታርና ጋዜጠኞች ያላሰለሰ ውትወታና ወከባ ሳይበገሩ በመንፈስ ቅዱስ ጥበቃና መሪነት (በግሌ እንዲህ አይነት ማስተዋልና ፅናት ከመንፈስ ቅዱስ ብቻ የሚገኝ እንደሆነ ስለማምን) ቤተክርስቲያናችን የምትጠብቅባቸውን ወቅታዊ አባታዊ ምላሻቸውንና አቋማቸውን ማግኘት ለሚገባቸው የቤተክርስቲያኒቱ አካላት በተለይም ሃገር ቤት ለሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስና ለዐቃቤ መንበሩ ለብፁዕ አቡነ ናትናኤል በትክክለኛው ወቅትና ጊዜ ግልፅ ደብዳቤ እንደፃፉና በስልክም ተገናኝተው መወያየታቸው እየታወቀ ይህንንም ዜና እራሷ ደጀ ሰላም፡-
፩ኛ.  በጥቅምት 5/2005 ዓ.ም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን ምስል በማስደገፍ “ዐቃቤ መንበሩ ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር የስልክ ውይይት አደረጉ” (ሰረዝ የተጨመረ) እንዲሁም፣
፪ኛ.  በድጋሚ ጥቅምት 15/2005 ዓ.ም “የዕርቀ ሰላሙ ውይይት በመጪው ህዳር ወር ይቀጥላል” በሚለው ርዕስ 2ኛ አንቀፅ፣ 5ኛ  መስመር ላይ “ እርቀ ሰላሙ ከተፈፀመ ዘንድ አራተኛው ፓትርያሪክ ወደ መንበረ ፕትርክናው ተመልሰው እንዲቀመጡ የመሻት አቋም በደብዳቤ ጭምር በተገለፀበት አኳኃን” (ሰረዝ የተጨመረ) በማለት መዘገቧ እርግጥ ነው፡፡
ከዚህም እውነታ በመነሳት ደጀ ሰላማችን ቅዱስ አባታችን እየተጓዙበት ያለውን ድንቅ ክርስቲያናዊ አካሄድ እንደ ማበረታታትና እርሷ አብዝታ ከምታውቀው ከዓለማዊው የሚዲያ ወከባ ለመታደግ እንደመትጋት የባስ ብሎ ከባዕታቸው ለማስወጣት በሚመስልና ወደ አደባባይ ጎትቶ ለጥንተ ጠላታችንና ለታወቀው ከሳሻችን የመክሰሻና የመዘባበቻ አጀንዳ ለማቀበል እንዲህ በጲላጦሳዊ ግብር አብዝቶ መዘብዘብና መነትረክ ምን ይሉታል? ምንኛስ መውረድ እንዴትስ ያለ አለማስተዋል ይሆን?
ማጠቃለያ
እንግዲህ የህይዎታችን እራስ የሆነውን ጌታችንና መድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በቀራኒዮ አደባባይ አሻግረን እያየን፤ ለእኛ ሲል የሆነውን ሁሉ ዘወትር እያሰብን፤ በመዋለ ስብከቱ ያስተላለፈልንን የህይወት ቃል ጠብቀን በሥርዓትና በአግባቡ የቅድስት አማናዊት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮትና ሥርዓት አክብረን በመከተል ይህቺን አጭሯን ምድራዊ ዘመናችንን መልካም ፍሬ በማፍራት ሁላችንም በድል አድራጊነት እንድንወጣት እመኛለሁ፡፡ ለዚህም ይረዳን ዘንድ
፩ኛ. መልካም ለሆነው ክርስቲያናዊ ተጋድሎ አጋዥ ይሆኑ ዘንድ በቅንና ደጋግ ወገኖች መልካም ፈቃድ የተዘጋጁት “ደጀ ሰላም”ና መሰል መድረኮች፣
፪ኛ. የቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ “ከምር” ያገባናል በማለት “በእውነት” የአቅማችሁን በጎ ድርሻ ለማበርከት በየፊናችሁ በቡርቱ እየደከማችሁ የምትገኙ ግለሰቦችም ሆናችሁ ተቋማት፣
፫ኛ. በአጠቃላይ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ሁሉ ፣
ታላቋ የኢ/ኦ/ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በዚህ በእኛ ዘመን የገጠማትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች እንደ ቀደሙት ትውልዶች ሁሉ በአሸናፊነትና ዳግም በድል አድራጊነት እንድትወጣና ብሎም ዘመኑ የሚጠይቀውን ሐዋርያዊ አገልግሎቷን በላቀ ትጋትና ጥራት እንድታከናውን ይረዳት ዘንድ ፡-


-        ውስጣዊ ችግሮቿን ሁሉ በአግባቡና በሥርዓት የምትፈታበት ብቃትና ጥራት ያለው የዘመናዊ ተቃማዊ አሰራር ባለቤት እንድትሆን በማሰቻል፣

-       ከውጭ የከበቧትን፣ በውስጥ የገጠሟትን፣ ወደፊትም  በቋፍ የሚጠብቋትን ውጫዊወቹን እንደ ዘመናዊው የሉላዊነትና የሉላዊነት ውልድ የሆኑትን እነ “ሊበራል-ክርስትና”ን የመሳሰሉትን ባላንጣዎች መመከት የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ “ጦርና ጋሻ” በማስታጠቅ፣

-       ከሁሉም በላይ ለመጪው ትውልድ የምትመጥንና የተሰጣትን አምላካዊ አደራዋን በአግባቡ እንድትወጣ ሊያግዛት ወደሚያስችል ዘመን ተሻጋሪ አቅጣጫና ምዕራፍ በመምራት፣


-       እንዲሁም በሁሉም መስክ ሁላችንም በአለን አቅም ሁሉ ቤተክርስቲያናችንን ለመደገፍና የየድርሻችንን ለመወጣት እንድንችል በሚያስችል መልኩ በማደራጀት ፣

በአጠቃላይ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ወደ አንድና ወጥ አቅጣጫ ለመጓዝ የሚያስችል እቅድና እስትራቴጂ በአፋጣኝ “ይወለድ” ዘንድ ሁላችሁም በተሰጣችሁ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ተደግፋችሁ ታምጡ  ዘንድ እማፀናለሁ፡፡ በተለይም ለዚህና ለተመሳሳይ አላማ አስቀድማችሁ የተሰለፋችሁ የተደራጃችሁ የቤተክርስቲያኒቱ ባለድርሻዎች ሁሉ ቅድሚያውን ትወስዱ ዘንድ የከበረ ጥሪዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡
በመጨረሻ
በመጨረሻም ውድ ደጀ ሰላሞች! ከዚህ ቀደም ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል ክብረት “ማህበረ ቅዱሳን”ና “አመራሩን” በሚመለከት ያቀረበውን ዝርዝር መጣጥፍ “ለቤተክርስቲያናችን አንድነትና ለማህበሩ እድገት አይበጅም” በሚል ከመድረካቹሁ እንዳነሳችሁት ሁሉ ይህን ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ያወጣችሁትን ጲላጦሳዊ ተንኳሽ /Provocative/ የአፍልጉኝ ማስታወቂያ ከመድረካችሁ ታወርዱ ዘንድ እንዲሁም ለዚህ ግድፈት የእርምት እርምጃ መውሰዳችሁን በክርስቲያናዊ አግባብ ለአንባቢዎቻችሁ ታሳውቁን ዘንድ በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፡፡
ለብፁዕ አባታችን ትዕግስቱንና ፅናቱን የሰጠ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእኛ ለደካማዎቹ በየጎዳናው በመካሰስና በመወነጃጀል ለምንባዝነው ሁሉ ማስተዋሉን ያድለን ዘንድ ፀልዩ፡፡

ወስብሃት ለእግዚአብሔር
5 comments:

Anonymous said...

ውድ ወንድማችን:- እንደ አንባቢ ሆኜ የጻፍከውን አስተያየት ሳየው የመጽሀፍ ቅዱስን ቃል በመጥቀስ አንድ ግለሰብ (አባ መርቆርዮስን) የምታመልክ መሰለኝ:: ስለ ቤተክርስቲያን እንጂ ስለ ግለሰብ ጉዳይ የሚያገባኝ ነገር ስለሌለ አስተያየቴን በዚሁ አበቃለሁ:: ደጀ ሰላም ግን ለቤተክርስቲያን ብቻ ወግና የጻፈችው መነሳት የለበትም እላለሁ::

Anonymous said...

በጣም:የሚገርም:ነው:አቡነ: መርቆሪዎስ :ወደ :ሀገራቸው:ብቻ :እንዲገቡና:በፈለጉበት :ቦታ: በጸሎት: ተወስነው :እንዲቀመጡ: ነበር ::የመጀመሪያው: ጥያቄ :አሁን ደግሞ: ይግቡ እና: በፈለጉበት: ቦታ: ይቀመጡ: ሲባል: አይ: ከገቡ: ደግሞ: ፓትርያርክ: መሆን :አለባቸው:አሉ:: ይገርማል! የሚያሳዝነው: ነገር:ቅዱስነታቸው :ይህንን: አይመኙም:: መጠቀሚያ: ሲያደርጓቸው:ግን: ያሳዝናል:: በቅርብ:ካናዳ:በተደረገ:የቤተክርስቲያን: ምርቃት: ላይ: ስናያቸው: ከማርጀታቸው: የተነሳ :ወደ :ህጻንነት: ተመልሰዋል:: *ጃጅተዋል* ማለት: ፈልጌ: ነው:: ታዲያ: እዛ :ያያቸው :ሰው: እንኳን: ለዚህ: ስልጣን :ቀርቶ: ቅዳሴ :መቀደስ :አቅቷቸዋል:: ስለዚህ :እባካችሁ: ከጐናቸው: ያላችሁት: ሰዎች :ለጥቅማችሁ :ስትሉ: እሳቸውን: አትጉዷቸው: እንደ: ፍላጐታቸው: ለሀገራቸው :አብቋቸው::

Anonymous said...

Anonymous,

What part of this article makes you think that the writer is worshipping His Holiness? All the writer is saying is that His Holiness has chosen "to keep quiet" instead of politicizing his situation. He has the venue and the rational to do so but rather chose the spiritual path. The writer's assertion to the bible quote is simply to support His Holiness's reason to do so. Isn't that what we all as Christians supposed to do? Live our lives as Christ did? Why you (Anonymous) do is quick to such a negative assertion? Isn't that what the protestant world accuses us or worshiping saints and angles; just because we celebrate their biblical life?

You know it very well that how many out there (if they were in His Holiness situation) would have loved to stay in the media and use public relations to make the case ? How many amongst his peers would have loved to stay visible in the media?

His Holiness choice to stay quiet and live in fasting and prayers is something any Christian can only attest and learn from. If only the majority of our "fathers" live their life as such.

To make a point to Deje Selam in why they asked and re-asked the question is I believe from a positive motive. So, all of Faithfull's will get to hear from His Holiness. I understand that and I will not fault DS for asking the question. However, as the writer eloquently put it, His Holiness is using a proper and not-self advertising path to get himself heard. So, His Holiness is not just keeping quit but doing everything as any Christian father and leader I would like to do.

So, I wouldn’t necessarily agree with the writer's assertion that the post needs to be removed. As long as Deje Selam gets the point the writer is trying to make, the post removal or not is not that much important.

May God Bring unity to our church,

Isac20012002

Anonymous said...

በጣም ደስ የሚያሰኝ መልእክት ነው የጻፉልን!
ጆሮ ያለው ይስማ! ልብ ያለው ልብ ይበል!

EgzioMeharene said...

Anonymous[December 1, 2012 1:19 PM]

በየትኛው አይንህ ነው ቅዱስነታቸውን ያየሃቸው ?
የቀኝ አይንህን (የቀኝ አይንህ ካለ) ጨፍነህ በግራው ብቻ ነው ያየሃቸው ?

እነ አቡነ ጳውሎስም እንዲህ እያሉ ነበር ቀድመው ላይመለሱ የሄዱት!

እስኪ ቪዲዮው ላይ በደንብ ተመልከታቸው ? http://www.youtube.com/watch?v=Smz4ojb90SM&list=UUsvgHr4A1iPePj0PPbFtf-Q

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)