December 25, 2012

የ6ኛ ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴው “የተመረጠ” ሳይሆን “የተሰየመ” ነው


(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 16/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 25/2012/ READ THIS IN PDF)፦ 6ኛውን ፓትርያርክ ለማስመረጥ ተቋቁሟል የተባለው አስመራጭ ኮሚቴ በጥቆማ ስም ዝርዝራቸው የተበተነ እንጂ ብዙዎቹ ይስማሙበት ወይም አይስማሙበት እንዳልተጠየቁ ምንጮቻችን ገልጸዋልይህንን ተከትሎ ማኅበረ ቅዱሳን ምርጫው እንዲካሄድ በሾርኔ እንደተስማማ ተደርጎ በድረ ገጾች መዘገቡ አጀንዳው ከምርጫው ወደ ማኅበሩ እንዲዞር ለሚሹ ጥሩ አጋጣሚ ከመፍጠሩም በላይ ማኅበሩ ከቅ/ሲኖዶሱ ጋር ያለውን መልካም የሥራ ግንኙነት ለማጠልሸት ለሚፈልጉ ሰዎች አስደሳች አጋጣሚ እንደፈጠረ እየተነገረ ነው።


ዝርዝሩ እንደሚያመለክተው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስና ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እንዲሁም ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያ ኃላፊዎች መካከል ደግሞ የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ እና የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊው መጋቤ ምስጢር ዓምደ ብርሃን ስማቸው ተጠቅሷል። ታላላቅ ገዳማት እና አድባራትን እንዲወክሉ የተደረጉት ፀባቴ አባ ኀይለ መስቀል ውቤ (የደብረ ሊባኖስ ገዳም አበምኔት) እና ንቡረ እድ አባ ዕዝራ (የአኵስም ጽዮን ንቡረ እድ) ሲሆኑ ዲያቆን ኄኖክ አሥራት - ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፤ አቶ ባያብል ሙላቴ ደግሞ ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰየሙ ናቸው። አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ  (ከኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት)፣ ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ እና አቶ ታቦር ገረሱ ደግሞ ምእመናንን ወክለው የተቀመጡ ናቸው፡፡

ማኅበሩን ወክለው በአስመራጭነት እንዲገቡ የተጠቆሙት አቶ ባያብል ሙላቴ በማኅበሩ እንዳልተወከሉ፣ እርሳቸውም ስለመመረጣቸው ማንም እንዳልጠየቃቸው ታውቋል። ማኅበሩ በአስመራችነት እንዲያገለግል አንድ ተወካዩን እንዲወክል ባልተጠየቀበት ሁኔታ አባሉ ስም ይፋ መሆኑ ከውጪ ለሚመለከቱ ሰዎች የተለየ አንድምታ መስጠቱ እየታየ ነው። ማኅበሩ ‘ጥቆማውን ለመቀበልም ላለመቀበልም አስቸጋሪና አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ምንጮች ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ማኅበሩም ሆነ በኪሚቴው ውስጥ የገቡት ግለሰቡ ባላወቁበት ሁኔታ ለተደረገው ነገር ማኅበሩን ተጠያቂ ማድረግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው።    

ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ የኮሚቴው አባላት መካከል ብፁዕ አቡነ ቄርሎስና አቡነ እስጢፋኖስ በምርጫው አለመስማማታቸውን ተከትሎ ኮሚቴው ተሰይሞ ይፋ ከመደረጉ ውጪ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር የሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ ምንጮቻችን አብራርተዋል።

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
  

5 comments:

Anonymous said...

በ VOA ራዲዮ
"በስም መጠቀስ ያልፈለጉ አባቶች ለቪኦኤ እንዳረጋገጡት ከሆነ ይኸው አስመራጭ ኰሚቴ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን እስከ ጥር ሰላሣ እንዲያሣውቅ በሲኖዶሱ ተወስኗል።

የኢትዮጵያው ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በተጀመረው የዕርቅና የሠላም ድርድር ላይ እንዲገኙ ሦስት አንጋፋ ሊቃነ-ጳጳሣትንና አንድ ካህን የተካተቱበትን ባለ አራት አባላት የልዑካን ቡድን ወደ አሜሪካ መላኩ ይታወሣል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ አቡነ ሕዝቅኤል በወቅቱ ተጠይቀው «አሁን ስብሰባ ላይ ነኝ» በማለት መልስ መስጠት አልፈለጉም።
ይሁንና አንዳንድ የቤተ-ክርስቲያኒቱ አባቶችና ሊቃውንት በተለይም ካዲሳባ ከመጡት የሠላም ልዑካን መካከል ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ሲኖዶሳቸው የወሰደውን አቋም ተቃውመዋል። ለቪኦኤ በሰጡት ቃልም፣ «ይህ ነገር ይሆናል ብለን አናምንም፣ ከሆነ ግን ትክክል አይደለም፣ እንቃወማለን» ነው ያሉት።

ይህንኑ አቋም ይበልጥ ያስተናገዱት፣ የዋሽንግተን ዲ.ሲ.፣ የቨርጂንያና የሜሪንድ እንዲሁም የካሊፎርኒያ አህጉረ-ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ናቸው።"VOA NEWS
ይሄ ሁሉ እየተባለ ለሽምግልናው በሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ህጋዊ እውቅና ያለው የሰማምና የአንድነት ጉባኤ በሰጠው መግለጫ ተቃውሞ ማቅረብ ትክክል አይደለም። ይህ ደብዳቤ ለሽምግልና ተመድበው ከመጡት አባቶች የመጣም አይመስለኝም ምክንያቱም እነሱ ባሀገር ቤት ያሉትን አባቶች የተቃወሙትን በመስማት ያተፈጠረውን ሁኔታ ለማርገብ የሽምግልና ስራ እንጂ ድፍረት የሚባል ነገር የለበትም ።በጣም ስርአት ያላቸው የተከበሩ ሰወች ስለሆኑ እንኴን የራሳቸውን ቤተክርስቲያን እና አባቶችን ያሚያዋርድና የሚያሳዝን ስራ ሊሰሩ ቤተክርስቲያንን አንድ ለማድረግ የሚደክሙ የዘመናችን ታሪክ ሰሪወች ናቸው እርቁ ሆነም አልሆነም::ቅዱስ ሲኖዶስም የመላው የተዋህዶ እምነት ተከታዮች እንጂ የተወሰኑ የሰወች ስብስብ የግል ድርጂት አይደለም በመሆኑም ሰው ራስህን ደፈርክ አይባልም ሁላችንም አንድ ነንና። እባካችሁ ነገር አብርዱ

Anonymous said...

ምንድን ነው የተመረጠ ሳይሆን የተሰየመ ማለት ያው ነው ሁሉም ወደ ስድስተኛው ፓትርያሪክ ነው የሚያመራው አሁንም አባቶች የመንግስት ትዛዝ አለበት ብላችሁ በሚስጥር ለአስታራቂዋቹ ንገሯቸውና ወደ 6ኛ ፓትርያሪክ ምርጫ ግቡ መንግስት ሲወድቅ ሁሉም ይስተካከላል። ከቻላችሁ መወጋገዙን አንሱት ጥላቻ ይነሳ ይህም ከባድ ከሆነ ለፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለምና እግዚአብሄር ይፍታው ብለን ዝም ማለቱ መልካም ነው። መቸስ ባገራችን ላይ ያለውን ሁሉንም እናውቀዋለን ቀን ይፍታው።

Unknown said...

አዎ ይህ 'መንግሥት' በመንበረ መንግሥቱ እስካለ ድረስ ከመንበረ ፓትርያርኩም ላይ ከዚህ መንግሥት ፈቃድ ውጭ ሌላ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና ሕጋዊ አባት እንዲቀመጥበት አይፈቅድም። ለዚህ መንግሥት እኮ በአባ ጳውሎስ ስትመራ የቆየችው ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሆነ በሁሉም በኩል የተዋጣለት ሥራ ሠርታለታለች። ታድያ እንዴት አድርጎ ነው ከቁጥጥሩ ውጭ ሁና ምዕመናኖቿን ባንድነትና በፍቅር እንድትመራ ይፈቅድላታል ብለን የምንጠብቀው ? ለዚህም ተልእኮ ደግሞ በቂ የሆኑ ''ጳጳሳትና ካህናት እንዲሁም ምዕመናን'' አሉት። ከራሱ መሠረታዊ እምነት ውጭ የሆነን አንድነት፥ ፍቅርና ሰላም በኢትዮጵያውያን መካከል እንዲመጣ ይህ መንግሥት አይፈቅድም። ምክንያቱም ኪሳራ ነው እንጅ ትርፍ ከኢትዮጵያውያን አንድነት፥ ሰላምና ፍቅር አገኛለሁ ብሎ የሚያምን መንግሥት አይደለምና !...ስለዚህ ያው እንደነበርነው ሁነን ከላይ ኣንዱ ወገን እንዳሉት በያለንበት መቆየት ነው። ከሆነም እንደኔ በግፍ ከተሰደዱት አባት ስር ሁነን መመራት፤ በስደት ካሉት አባት የሚገኝ ምንም ሥጋዊ ጥቅም ስለሌለ ''እናት '' ከምትሏት ተጠግታችሁ ቆዩ። ...አስመራጭ ኮሚቴውን በሚመለከት ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የቀረበው ማብራሪያ ግን እጅግ በጣም ጠቃሚና ወቅታዊ ስለነበር ለጊዜውም ቢሆን ብዙዎቻችንን ከፈተና የሚያድን ሁኖ አግኝቸዋለሁ። ቢያንስ ይህ ማኅበር ጠንካራ ተከላካይ ሁኖ እንዲቀጥል ከሚመኙት ምዕመናን አንዱ እየሆንኩ በመምጣት ላይ ያለሁ ስለሆንኩ ተሰናክሎ እንዲወድቅ አልመኝም። ንቁም በበህላዌነ እስከ ነአምር.................

Unknown said...

ምንድን ነው የተመረጠ ሳይሆን የተሰየመ ማለት ያው ነው ከላይ ይህን እንደጥያቂ ያቀረቡት ወገን...መመረጥና መሰየም አንድ አይደለም። ተሰይመ=ተሾመ ማለት ሲሆን መመረጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር ለምርጫ ቀርቦ የመራጩን የብዙኃን ድምጽ ያገኘው አሽናፊ ሁኖ ሲወጣ ነው። መሰየም/መሾም ግን በአንድ ባለሥልጣን ለአንድ በስሩ ላለ ያገልግሎት ተግባር መሾም ነው። በግዕዝ 'ሽ' ስለሌለ በዐማረኛ 'ሽ' ይሆናል። ስዩም=ሹም። ስዩመ እግዚአብሔር=በእግዚአብሔር የተሾመ።

Anonymous said...

In the name of the Father ,the Son and the Holy spirit Amen.

Dear church fathers,brothers,sisters and all children of our mother orthodox church...
The era is an era of many temptaions where people live in unpeaceful manner.Every day we hear things very bad for our ears,see things unbleavable...the world is close to an end.Judgement Day is coming..we need to repent and get a peacful place in times of trouble.Our church is our refugee place from this chaotic world.
My respected church Fathers, Please be strong in bringing peace for our church.Where can we go if there is no peace where it is supposed to be?
May the God of Abrham,Isaac and Jacob help us in bringing peace.
Again...My dear church fathers..God has given you the power to unite us and keep us in his place...May God help you in all your efforts.

God bless Ethiopia.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)