December 20, 2012

6ኛ ፓትርያርክ የመሾሙ ነገር እርግጥ እየሆነ ነው፤ አሁንም ዝምእንበል?

  •     አስመራጭ ኮሚቴ መቋቋሙ ብዙዎችን አሳዝኗል፤
  •     ሕዝበ ክርስቲያኑ ሹመቱን ባይደግፈውም ለመቃወም የሚያስችል የተቀናጀ ዝግጅት እስካሁን አልፈጠረም፤
  •     ስለ ዕርቁ ጉዳይ ድምጻቸውን ከሰጡ ምእመናን መካከል 80% የሚሆኑት ከሹመቱ በፊት እርቁ እንዲቀድም ይፈልጋሉ፤
 (ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 11/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 20/2012/ READ THIS IN PDF)፦ ሰሞኑን በአዲሱ የፓትርያርክ ምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ ሲነጋገር የሰነበተው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እጅግ ጠቃሚ ግብዓቶችን እና ማሻሻያዎችን ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ከባለሙያዎች ሲያገኝ ሰንብቶ ነበር። ይህም ሊያስመሰግነው ይገባል። “እህ” ብሎ መስማት መጀመሩ ትልቅ እመርታ ነው። ነገር ግን ቁም ነገሩ የተሰበሰበው ሐሳብ፣ በጎ ኅሊና ያላቸው አባቶች ሁሉ ልፋት በምን መልኩ ተጠናቀቀ ነው። አሁን በሚታየው እና ምንጮቻችን እንዳመለከቱት ከሆነ የቅዱስ ሲኖዶሱ ታሪካዊ ጉባዔ ታሪካዊ ውሳኔዎች የሚቀለበሱበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ይህ ከኋላ ሆኖ “የነበረውን እንዳልነበረ” የሚያደርገው ረዥም፣ ፈርጣማ ክንድ እንዲሰበሰብ ማድረግ ባለመቻሉ የቅ/ሲኖዶሱና አባቶች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ፍላጎት ሳይሆን ከዚያ ተቃራኒው በመፈጸም ላይ ነው። ነገሩን ጠቅለል ብናደርገው፦
·         የምርጫው ሕግ በታሰበው መሠረት ፓትርያርኩ በዕጣ ሳይሆን በምርጫ ካርድ ብቻ እንዲሆን መደረጉ፣
·         የዕርቀ ሰላሙ ሁኔታ መልክ ሳይዝና አንድ ደረጃ ሳይደርስ ፓትርያርክ ለማስመረጥ የሚደረገው ሽር ጉድ፣
·         እንደ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የመረጠውን አባት ለመሾም ከመፈለግ ይልቅ በአመለካከት፣ በፖለቲካ አቋም አሁን ካለው መንግሥት ጋር ግብብነት ያለው ሹም ለማስቀመጥ መወሰኑ፣
·         የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ምንም ዓይነት ክብር በማይሰጥ መልኩ የመንግሥት ኃላፊዎች “የሃይማኖት መቻቻል ሀ-ሁ እናስተምራችሁ” በሚል አቋም ጓዳ ጎድጓዳውን በእግራቸው እየጠቀጠቁ መግባት መውጣታቸው፣
·         የምእመናን ድምጽ ከምንም ሳይቆጠር እንደሌሉ በመቁጠር የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳይ በመንግሥት እና በጣት በሚቆጠሩ የፖለቲካ ቀራቢዎቻቸው (አፋሽ አጎንባሾቻቸው) ብቻ ነገሩን ሁሉ ማስኬድ፤
·         ለይስሙላ አስመራጭ ኮሚቴ በመሰየም እንደ ሕጻናት ጨዋታ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር በማይመጥን መልኩ መዳፈር፣

ደጀ ሰላም በዋናው ድረገጿ፣ በፌስቡክና በኢ-ሜይል ባደረገችው የሕዝብ ድምጽ ማሰባሰቢያ ሥርዓት ድምጻቸውን ከሰጡ 2000 ደጀ-ሰላማውያን መካከል 80% የሚሆነው ዕርቀ ሰላም እንዲፈጸም፣ 4ኛው ፓትርያርክ በሕይወት እስካሉ ድረስ አዲስ ፓትርያርክ መሾሙ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላም እንደማይጠቅም ያምናል። ድምጻቸውን ከሰጡት መካከል 13% የሚሆኑት 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሾሙ ሲፈልግ የተቀረው ፐርሰንት ሌሎች ሐሳቦችን አቅርቧል። የክርስቲያኑ ፍላጎት ይህ ቢሆንም አሁን እየተጫነበት ያለው አዲስ ፓትርያርክ የመሰየሙ ጉዳይ ተቀባይነት የለውም። ይህንን በማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመለያየት ገደል ከማጥበብና ስብራቷ እንዲጠገን ከማድረግ ይልቅ “ለእኔ ይበጀኛል” የሚሉትን አባት ለመሰየም በመጣደፍ ላይ ያሉትን በሙሉ ታሪክም ምእመኑም ይቅር እንደማይላቸው ማወቅ አለባቸው። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ከነስማቸው ልንመለስባቸው እንችላለን። ጥሩ ሲሠሩ እንደግፋቸዋለን፣ ታሪክ ሲያበላሹ ደግሞ ባለፈው “ክሬዲት” በዝምታ አናልፋቸውም። የምናውቃቸውና የምንደግፋቸው በቤተ ክርስቲያን እንጂ በአምቻ ጋብቻ፣ በሰፈር ልጅነትና በፖለቲካ አመለካከት አይደለም።

ስለዚህ አሁን ይመረጣል የሚባለው ፓትርያርክ ሌላ የመለያየት ምልክት መሆኑ እሙን እየሆነ ነው። ልዩነቱ በውጪ አገር ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም ከባድ የመለያየት ቀውስ እንደሚፈጥር አያጠራጥርም። ቤተ ክርስቲያን ለስብከተ ወንጌል አገልግሎቷ፣ ለዕድገቷ፣ ለልማቷ ልታውል የምትችለውን ኃይል በመለያየት ሰበብ እየበታተነች መሔዷ ለወደፊቱ ህልውና አስቸጋሪ እንደሚሆን የታወቀ ነው።

ስለዚህ አሁንም እንናገራለን። የማይሰማን ባይኖር “ሰማይ ይስማ” እንላለን፤ የተጀመረው ዕርቅ ይፈጸም፣ ሰላም ይውረድ፣ አባቶች አንድ ይሁኑ፣ ሌላው ነገር በሙሉ ይደረስበታል። በዚህ ግርግር መካከል ፕትርክናዋን “ለቀም ላድርጋት” ብላችሁ የቋመጣችሁ እንደ እንቶኔም ስለ ቤተ ክርስቲያን ብላችሁ ልብ ግዙ!!!

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን። 
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)