October 9, 2012

“መሰናዘሪያ” የተባለ ጋዜጣ “አቡነ መርቆሬዎስ ኤርትራን ጎበኙ” ሲል መዘገቡ ለዕርቁ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል ተባለ

“አቡነ መቃርዮስ”

(ደጀ ሰላም መስከረም 28/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 8/2012; READ THIS NEWS IN PDF)፦ በሜላቢን ፕሮሞሽን ሓላ/የተ/የግ ማኅበር የሚታተመው “መሰናዘሪያ” የተሰኘ ሳምንታዊ ጋዜጣ መስከረም 22 ቀን 2005 ዓ.ም “አቡነ መርቆሬዎስ ኤርትራን ጎበኙ” ሲል በዜና ገጹ ላይ የተሣሣተ ዘገባ ማውጣቱ ለተጀመረው ዕርቅ እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ጋዜጣው በስደት ላይ የሚገኙት አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ኤርትራ አምርተው ለቀናት ጉብኝት እንዳደረጉ፣ ከግንቦት ሰባት አመራሮች ጋራ አብረው እንደሚሠሩና ጉብኝታቸው ከዚሁ ጋራ የተያያዘ መኾኑን በመጥቀስ ያቀረበው ዘገባ “ትግራይ ኦንላይን” የተባለውን ድረ ገጽ በምንጭነት በመጥቀስ ነው። ድረ ገጹ “Why was Abune Mekariossent to Eritrea by Ginbot-7 after Prime Minister Meles died? በሚል ርእስ ሴምቴፐር 27/ 2012 ባወጣው ዘገባው ኤርትራን ጎበኙ ሲል የጠቀሳቸው “አቡነ መቃርዮስ”ን ነው፡፡ 

ጋዜጣው “አቡነ መቃርዮስ” የሚለውን “አቡነ መርቆርዮስ” በሚል ተራ እና አማተር የፈጸመው ስሕተት በመልካም ጎዳና ላይ መራመድ ለጀመረው የአባቶች ዕርቀ ሰላም ሒደት እንቅፋት እንዳይፈጥር የሰጉ ወገኖች ሥጋታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። ጉብኝቱን ማሰናከያ ለማኖር የሚሹ ወገኖች እንደ ማስረጃ መጠቃቀስ ከመጀመራቸው አንጻር ለዕርቀ ሰላም በሚሠራው የሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት ዘንድም ስጋት ማሳደሩንም ምንጮች አስረድተዋል፡፡

“መሰናዘሪያ” ጋዜጣ በምንጭነት የጠቀሰው “ትግራይ ኦንላይን” ድረ ገጽም ቢሆን “አቡነ መቃርዮስ” እንጂ “አቡነ መርቆርዮስ” አላለም፡፡ ጋዜጣው ታዲያ ከየት አመጣው ለሚለው የተለያየ መላምት እየተሰነዘረ ቢሆንም አማተር ጋዜጠኝነት የተፈጸመ ስሕተት ከሆነ እርማት በማድረግ ያስተካክለዋል። ስሕተቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ከሆነም ውሎ አድሮ የሚለይ ይሆናል። በዚህ በኩል የሚዲያ ተቋማት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሚዘግቡት ነገር ዙሪያ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ሌላ ማሳያ ይሆናል። ደጀ ሰላም ከዚህ በፊት ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ባወጣችው መልእክት ሥር የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች (መርቆርዮስ እና መቃርዮስ የሚለውን በማምታታት) ተመሳሳይ ስሕተት ሲፈጽሙ ተመልክተናል። አቡነ መቃርዮስ በውጪ አገር ያለው ሲኖዶስ በ1999 ዓ.ም ከሾማቸውአዳዲስ ጳጳሳት (Link) መካከል አንዱ መሆናቸው ይታወቃል።

አቡነ መርቆርዮስ
በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከምንገኝባቸው ወሳኝ መድረኮች አንዱ÷ የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም ንግግር ከፍጻሜ በማድረስ የአራተኛውን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዕጣ ፈንታ መወሰን መኾኑን የሚገልጹት እነዚሁ ወገኖች እንዲህ ዐይነቱ ዘገባዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ መንግሥትና በመንግሥቱ ይደገፋሉ ከሚባሉት ተቃዋሚ ኀይሎች ጋራ ያለውን ተቃርኖ በመጠቀም በመልካም ሂደት ላይ የሚገኘውን የዕርቀ ሰላም ንግግር ለማሰናከል የሚሹ ወገኖች ኾነ ብለው ብዥታ ለመፍጠር የሚያደርጉት ሙከራ አካል ሊኾን እንደሚችል ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ እነዚሁ ወገኖች አክለው እንደሚያስረዱት÷ የዕርቀ ሰላም ንግግሩን በተመለከተ በብዙኀኑ በተለይም በሢመት ቅድምና ባላቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና አበው ካህናት፣ በመንፈሳውያን ማኅበራት፣ በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና በርካታ ምእመናን ዘንድ አዎንታዊ ግንዛቤና ግፊት እየተፈጠረ ከመኾኑም ባሻገር የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ከመፈጸሙ በፊት የቀጣዩ ፓትርያርክ ሹመት መከናወን እንደሌለበት የጋራ መግባባት እየተደረሰበት ነው፡፡

እንደ አቡነ መቃርዮስ ጉብኝት ያሉ አካሄዶች የውጭ አካላትን (መንግሥትን ጨምሮ) ጣልቃ ገብነት በመጋበዝ የዕርቀ ሰላም ንግግሩን በማዝግየት አልያም ጨርሶ በማሰናከል ያልተፈለገ ውጤት ለማምጣት የመቻሉን ስጋት በመጥቀስ የጉዳዩን ሥሡነት ያስረዱት ምንጮቻችች÷ በወዲያም ይኹን በወዲህ የሚገኙ በዕርቀ ሰላሙ ዙሪያ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የሚንቀሳቀሱ አካላት ሳይቀሩ የተቻላቸውን ጥንቃቄ በማድረግ ከቀጣዩ ፓትርያርክ ሹመት አስቀድሞ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚካሄደውን ጥረት እንዲያግዙ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በውግዘት የተለያዩት አባቶች ያለአንዳች ቅድመ ኹኔታ ዕርቀ ሰላም ፈጽመው የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እንዲያረጋግጡ ድምፃቸውን የሚያሰሙ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል÷ ዕርቀ ሰላሙ ለሁለት ዐሥርት ዓመታት በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ የቀኖና ጥሰቶችንና መወጋገዙ ያስከተላቸውን ችግሮች በድምር የሚመለከት መኾን እንደሚገባው የሚወተውቱ አካላትም እንዳሉ ተዘግቧል፡፡ መንግሥታዊ ምንጮችን የሚጠቅሱ አካላት ደግሞ መንግሥት “በሂደቱ ጨርሶ ጣልቃ እንደማይገባ” ከመግለጽ ጀምሮ የቀጣዩ ፓትርያርክ ሹመት በፍጥነት ከተከናወነ በኋላ የዕርቀ ሰላሙ ሂደት እንዲቀጥል የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለና ይህም የሢመተ ፓትርያርኩ ጊዜ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ውስጥና ዙሪያ ጎጠኝነትንና ቡድናዊ ጥቅምን ማእከል በማድረግ የየራሳቸውን ‹ፓትርያርክ› ለማስቀመጥ በኅቡእና በገሃድ የሚርመሰመሱ ቡድኖች የሚፈጥሩትን የፍላጎት ግጭት “ለመግታት ያስችላል” በሚል ነው ተብሏል፡፡

ደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ ዕርቀ ሰላሙንና ተጓዳኝ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በተስተናገዱት ዘገባዎች ላይ ደጀ ሰላማውያን ያሰፈሯቸው አስተያየቶች በአመዛኙ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ከመጠየቅ ጀምሮ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ የሚጠይቁ ሲኾኑ÷ ፓትርያርኩ ከሚገኙበት የጤናና የዕርግና ኹኔታዎች አኳያ ወደ አገር ቤት ተመልሰው በመረጡት ገዳም እንዲቀመጡና እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ መንበሩ ተጠብቆ ቤተ ክርስቲያናችን ቅ/ሲኖዶስ በሚሾመው እንደራሴ እንድትወከል የሚጠቁሙም ነበሩበት፡፡ ከዚህ ሁሉ አማራጭ ይልቅ የዕርቀ ሰላም ሂደቱም ይኹን የቀድሞው ፓትርያርክ ወደ መንበር መመለስ አስፈላጊ እንዳልኾነ በመስበክ በአስቸኳይ የቀጣዩ ፓትርያርክ ሹመት እንዲከናወን የመሻት ጠርዘኝነትም መታየቱ አልቀረም፡፡

ደጀ ሰላም በቀደሙት ዘገባዎቿ ስታስነብብ እንደ ቆየችው የዕርቀ ሰላም ሂደቱን አጥብቃ ትደግፋለች፤ ውጤቱም ብፁዓን አባቶች እንደተናገሩት አንድም ብዙም ሊኾን ይችላል፡፡ በሂደቱም ይኹን በውጤቱ ደረጃ በእጅጉ የምንፈልገው ግን ከኻያ ዓመት በኋላ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደሯ በአገር ቤት፣ በገለልተኛ፣ በስደተኛ መከፋፈሏ ቆሞ በአንድ መንበርና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሚሾመው አንድ ደገኛና ቅን አባት ስትመራ፣ ይህም በዓለም መድረክ ሐዋርያዊ ተልእኳዋን፣ ተቋማዊ ነጻነቷንና ብሔራዊ ክብሯን የሚመልስላትንና የሚያስፋፋላትን የተጠናከረ አስተዳደራዊ መዋቅር በቦታው ተመሥርቶ ማየት ነው፡፡ ይህም የቀናዒ ኦርቶዶክሳዊ አገልጋይና ምእመን ሁሉ ፍላጎት ነውና ሂደቱ ለሚጠይቀው ጥንቁቅነት፣ መንፈሳዊነት እና ብስለት የተገባን ኾነን እንድንገኝ የተላለፈውን ጥሪ ከልብ የምንደግፈው ነው፡፡

ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)