October 7, 2012

አቡነ ገሪማ ከሥራ አስኪያጃቸው ጋር እንዲቀርቡ ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ አዘዘ

  • በጠ/ቤ/ክህነቱ ኦዲት የተረጋገጠውን የ1.8 ሚሊዮን ብር ጉድለት ሲያጣጥሉ የቆዩት ሥ/አስኪያጁ ጉድለቱን አምነዋል፤
  • ሥራ አስኪያጁ ሙሰኝነትን በተቃወሙ ሰባት የደብር አለቆች ላይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፈዋል፤
  • ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ የነበረው ደብሩ በቋቱ የቀረው ከብር 70,000 አይበልጥም፤
(ደጀ ሰላም፤ መስከረም 25/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 6/2012/ READ IN PDF):- የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ በስምንት ተጨማሪ ብፁዓን አባቶች እንዲጠናከር የተደረገውና ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩን ጨምሮ ዐሥራ አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በአባልነት የያዘው ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ትናንት፣ መስከረም 25 ቀን 2005 ዓ.ም ባካሄደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው÷ የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን ተወካዮች በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ጉዳይ በደብሩ አስተዳዳሪ፣ በሕንጻ አሠሪው ኮሚቴ ሊቀ መንበር፣ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ላይ በየደረጃው ስለቀረቡት አቤቱታዎች እንዲያስረዱ ከጠራቸው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጋር መወያየቱ ተሰምቷል፡፡

በዚሁ ውይይት የሕንጻ ሥራው ሒሳብና የግንባታ ጥራቱ የደብሩ የሰበካ ጉባኤ አባላት በምእመኑ ተሳትፎ ባስመረጧቸው ባለሞያዎች እንዲመረመርና በተገኘው ጉድለት ላይ ሓላፊነት የሚወስዱት ተለይተው ርምጃ እንዲወሰድባቸው፤ በ1998 ዓ.ም ተጀምሮ በሁለት ዓመት እንዲጠናቀቅ የታቀደው ሕንጻ ስምንት ዓመት የመጓተቱን ምክንያትና በአስቸኳይ ስለሚፈጸምበት ኹኔታ፤ የደብሩ አስተዳዳሪና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በምእመናኑ የተመረጠውን ሰበካ ጉባኤ በተደጋጋሚ ስለማገዳቸውና ያልተገቡ አሠራሮች እንዲታረሙ ጥያቄ በሚያቀርቡ የደብሩ አገልጋዮችና ምእመናን እንዲጉላሉ ስለማድረጋቸው በተወካዮቹ ለቀረቡት ጥያቄዎች ብፁዕነታቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል፡፡

ይኹንና ብፁዕነታቸው ለቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ በሰጡት ምላሽ “እኔ ብቻዬን ለማስረዳት አልችልም” በሚል የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ አባ አረጋዊ ነሞምሳን ይዘው ለመቅረብ ፈቃድ መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱም ብፁዕነታቸው ሥራ አስኪያጁን ይዘው በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ በሚካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ “የብፁዕነታቸው ምላሽ የሚጠበቅ ነው” የሚሉት የጉዳዩ ተከታታዮች ብቻቸውን የተጠሩት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አባ አረጋዊ ነሞምሳ የሀገረ ስብከቱን ጸሐፊና የቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊ አበል ከፍለው ይዘው ለመሄድ እያግባቧቸው ቢኾንም በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ ግን አንድ ራሳቸው ብቻ እንጂ አጀብ እንደማይፈቀድላቸው ከወዲሁ እየተገለጸ ይገኛል፡፡ በሊቃውንት የተጠናከረውን የሀ/ስብከቱን አስተዳደር ጉባኤ ሲያዳክሙ የቆዩት ሥራ አስኪያጁ አብረዋቸው እንዲቀርቡ የሚያግባቧቸው ሁለቱ ሓላፊዎች ሥራ አስኪያጁ በብቸኝነት ከወሰዷቸው ርምጃዎች የተለየ አቋም እንደነበራቸው ተመልክቷል፡፡
 
ለአብነት ያህል ሥራ አስኪያጁ ከሳባ ደ/ኀ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ጋራ በማበር ከአንድም ሁለት ጊዜ በምእመናን የተመረጡትን ሰበካ ጉባኤ አባላት ያገዱበትን ደብዳቤ ሲጽፉ የጸሐፊው አቋም (ፓራፍ አለማድረግን ጨምሮ) የተለየ ነበር፡፡ ሥራ አስኪያጁ የግዳጅ ጡረታ እንዲወጡ በተደረጉት የቀድሞው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊ በኵረ ትጉሃን ዓለም አታላይ በተመራው የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሒሳብ የማጣራት ሥራ የብር 1.8 ሚልዮን ጉድለት ያረጋገጠውን የኦዲት ግኝት “ትክክል አይደሉም፤ ገንዘብ አልጎደለም፤ ጎደለ የሚል ወሬኛ ነው፤ ለቤተ ክርስቲያን የማያስብ ነው” እያሉ በዐውደ ምሕረት ሳይቀር ሲያጥላሉ የሀ/ስብከቱ ቁጥጥር ግን ጉድለቱን አምነው የፈረሙ መሆናቸው ተገልጧል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊ የኦዲት ሪፖርቱን ማቅረባቸውን ተከትሎ ይቅርታ እንዲጠይቁ በቀድሞው ፓትርያርክ መጋቤ ሥርዐት በእነ ሙሉጌታ በቀለ እና በተቆጣጣሪው መሐንዲስ ሰሎሞን ካሳዬ መገደዳቸውን የሚያውቁት ሥራ አስኪያጁ÷ የፕሮጀክት አማካሪ መሐንዲሶች ፈቃድና ይኹንታ ሳይገኝና ተቋራጩ ምንም ዐይነት የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና ሳያቀርብ በሚሰጠው ብድርና በሚፈጸመው ክፍያና ይህም እንዲከናወን ለሚተባበሩት የሕንጻ አሠሪው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሕገ ወጥ ድርጊት ሽፋን በመስጠታቸው ከምሥረታው ጀምሮ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የተሰበሰበ ብር 11,388,096.23 ተቀማጭ የነበረው ደብሩ ዛሬ በቋቱ ውስጥ የሚገኘው ገንዘብ ከብር 70,000 እንደማይበልጥ ነው የስፍራው ምንጮች የሚናገሩት፡፡

በሌላ በኩል በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ስብሰባ አጣሪ እንዳይመደብባቸውና በውጤቱም ከሓላፊነታቸው እንዳይነሡ ስጋት የገባቸው የሚመስሉት ሥራ አስኪያጁ “ለቦታው የሚመጥኑ ናቸውና አይነሡብን” የሚል የፊርማ ድጋፍ ከጥቂት የዋህ ምእመናንና ከአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀር እያሰባሰቡ መኾኑን ምንጮቻችን ያደረሱት መረጃ ይጠቁማል፤ የድጋፍ አሰባሰቡም ጎሰኝነትንና የቡድን ጥቅምን (ከሕገ ወጥና መናፍቃን ሰባክያን ጋራ) መነሻ ያደረገ መኾኑ ተመልክቷል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በንጽሕናቸው ካመኑ የፊርማው ጋጋታና የባለሥልጣናት ሽምግልና አስፈላጊ አልነበረም፡፡ የምእመናንና የአገልጋዮች ተወካዮች ካቀረቡባቸው ማስረጃ በላይ ፊርማውና ሽምግልናው የተሻለ ሊገልጻቸውም አይችልም፡፡ መፍትሔው ያለባቸውን ጉድለት ተቀብለው ለመታረም መዘጋጀት ኾኖ ሳለ ከቤተ ክህነቱ ወቅታዊ ኹኔታ ጋራ ተያይዞ እየገነገነ የሚታየው ጎሰኝነትንና ቡድነኝነትን ማእከል አድርጎ የዋሁን ምእመንና ሹመኛውን መቀስቀስ የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ ነጻነትና ውስጣዊ ሰላም የሚያውክ ሓላፊነት ከማይሰማው ጥቅመኝነት የሚመነጭ የጠላትነት ተግባር ነው፡፡
አባ አረጋዊ ነሞምሳ

በተያያዘ ዜና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አባ አረጋዊ ነሞምሳ በትናንትናው ዕለት እንዳደረጉት በሙስና የተበላሸ አስተዳደራቸውን በሚቃወሙ ሰባት የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አለቆች ላይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለመጻፍ አላገዳቸውም፡፡ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው መነሻ ሁሉም የድሬዳዋ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የሽኒሌ መካነ መቃብር ይዞታን በጋራ አስከብረውና አጥር አሳጥረው፣ ከሁሉም አድባራት ተውጣጥቶ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ቤተ ጸሎት ሠርተው እያጠኑ የሚጠቀሙበትና በአንድነት የሚያስተዳድሩበት የጋራ ኮሚቴ ከሚያውቀው የባንክ አካውንት ውጭ ሌላ አካውንት መከፈቱንና የሠራተኛ ቅጥር መፈጸሙን በመቃወም ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በቁጥር 2/ደ/ም/ቅ/ሚ/ካቴ/667/2004 በቀን 29/12/2004 ዓ.ም የጻፉት ደብዳቤ ነው፡፡ የአድባራቱ አስተዳዳሪዎች ጥያቄ ባለቤትም ባለይዞታም የኾኑበትን መካነ መቃብር በአንድነት ማስተዳደራቸውን እንዲቀጥሉ ቢኾንም ብፁዕ አቡነ ገሪማ በበላይነት በሚመሩት ልዩ ጽ/ቤት ውስጥ ልዩ ጸሐፊ ከኾኑት መጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም ጋራ የቁሳዊ ጥቅም ትስስር ያላቸው ሥራ አስኪያጁና ሌሎች የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ተባባሪዎቻቸው የአድባራቱን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ማስጠንቀቂያውን መጻፋቸው በመካነ መቃብር አገልግሎት ዙሪያ በሚፈጸመው ሙስና ለመጠቀም እንዲያመቻቸው ይኾን?

ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ኅልፈት በኋላ ቀድሞም ቢኾን ከውጭ ጉዞዎች ጋራ በተያያዘ በርካታ ሙስናዎችና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጣሱ ተግባራት እንደሚፈጸሙበት የሚነገረውን የልዩ ጽ/ቤቱን የውጭ ግንኙነት በበላይ ሓላፊነት ከመምራት ባሻገር የዓለም አብያተ ክርስቲያን ፕሬዝዳንት እና የዓለም አብያተ ክርስቲያን የክብር ፕሬዝዳንት ቢሮ ዋና ጸሐፊ የኾኑት ብፁዕነታቸው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኾኑበት ባለፉት ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ የተገኙት በዓመት ሁለት ጊዜ በቁሉቢ ለሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ነው፡፡ የዜናው ምንጮች እንደሚሉት ለሀ/ስብከቱ ሠራተኞች ደመወዝ ለመክፈል እንኳ የሒሳብና በጀት ክፍሉ በየወሩ ወደ አዲስ አበባ ለፊርማ መምጣት ስላለበት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለመጓጓዣ እና አበል ከብር 24,000 ያላነሰ ወጪ ተደርጓል፡፡

ይህም ኾኖ የከተማው ነዋሪዎች፣ የአጥቢያው ምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ካህናት በሀገረ ስብከቱና በሳባ ደ/ኀ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንዳለው ዐይነት አስከፊ የሙስና ወንጀሎችንና የአስተዳደር በደሎችን የተመለከቱ አቤቱታዎችን በሚያቀርብቡት ወቅት የቅርብ መረጃ የሌላቸው ብፁዕነታቸው የሚሰሙት ምእመኑን “ወሬኞችና አድመኞች፤ የዲያብሎስ ቡችሎች” እያሉ በዐውደ ምሕረት የሚሳደቡትን፣ ሲያሻቸውም በጥቅም ከተቆራኟቸው አንዳንድ የፍትሕ አካላት እና የጸጥታ ኀይሎች ጋራ በመመሳጠር ምእመኑን የሚያጉላሉትን፣ በሌሎች የቢዝነስ ሥራዎቻቸው በገንዘብ እያጨበረበሩ መከሰስን የለመዱትን (ብርሃኔ መሐሪ ሰሞኑን በአንድ የጭነት ማመላሻ ማኅበር የብር 90,000 የማጭበርበር ክስ እንደተመሠረተባቸው)፣ እነአእመረ አሸብር እንዳሻቸው ደብዳቤ እየለቀለቁ የሚልኳቸውን እንደ አሰግድ ሣህሉ ያሉ የለየላቸው መናፍቃን የሚያስተናግዱ “ሌቦችና ነውረኞች” ነው፡፡

በዚህም ያዘነውና የተቆጣው አገልጋይና ምእመን ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር መጨረሻ በአድራሻ ለብፁዕነታቸው በጻፈው ደብዳቤ በደሉ ሊታገሠው ከሚችለው በላይ እያለፈ በመኾኑ አስፈላጊው ማስተካከያ ካልተደረገ ለሚፈጠረው ችግር ሓላፊነቱን እንደማይወስድ ብፁዕነታቸውን አሳስቧል፡፡ ከዚያም ወዲህ የባሰበት እንጂ የተሻለ ነገር ባለማየቱ በሰሞኑ ጥያቄው ሙሰኛ ሓላፊዎች እንዲወገዱ፣ ሀገረ ስብከቱን በቅርበት እየከታተለ አባታዊ ቡራኬ የሚሰጠው ብፁዕ አባት እንዲሰጠው ለቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በመጨረሻ÷ የቫቲካን ፍርድ ቤት የካቶሊኩን ፓፓ ቤኔዲክት 16የግል ሰንዱቅ በመመዝበር በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን የሥልጣን ሽኩቻዎች፣ የሙስና ቅሌቶች የሚያሳዩ በርካታ ሰነዶች ከፓፓው ዕውቅና ውጭ ለምርመራ ጋዜጠኞች በማሾለክ ከፍተኛ የስርቆት ተግባር በፈጸመው የፓፓው ዋና አሽከር (Papal - butler) ፓውሎ ጋብርኤሌ ላይ የ18 ወራት (የአንድ ዓመት ከስድስት ወራት) እስር ቅጣት አስተላልፏል፡፡ ላለፉት ሰባት ዓመታት ፓፓውን በማዕድ ከማገልገል እና ከማልበስ ጀምሮ በማንኛውም አገልግሎታቸው ዋና ረዳታቸው የነበረው ፓውሎ ጋብርኤሌ ለፓፓው አለመታመኑ ቢጸጽተው እንጂ ውስጣዊ ብልሽቶችን በማጋለጡ አለማጥፋቱን ለችሎቱ ተናግሯል፡፡ ከአራት ተከታታይ የችሎት ስሚዎች በኋላ የቅጣት ውሳኔውን የሰጠው ፍ/ቤቱ የፓውሎን ጸጸትና ከዚህ በፊት በወንጀል አድራጎት ተከስሶ ያልተፈረደበት መኾኑን በማየት በቀላል እስራት ቢቀጣውም ብዙዎች ተስፋ የሚያደርጉት የፓፓው ይቅርታ ግን እየተጠበቀ ነው፡፡

ከፓፓው መዝገብ የተወሰዱ ኅትመታቸው የማይገኙ መጻሕፍት፣ ቼኮች፣ አነስተኛ ወርቅና ሌሎችም ሰነዶች በፍተሻ ወቅት ከቤቱ የተገኘበት የካቶሊኩ ፓፓ ዋና አሽከር  [የቀድሞው ዘመን አነጋጋር ነው] ፓውሎ ጋብርኤሌ በዚህ የእጅ አመሉ የፓፓውን አመኔታ በማጣቱ ተጽጽቷል፡፡ በአንጻሩ ሙስናንና ዘርፈ ብዙ ብልሽቶችን በማጋለጡ ትክክለኛ ተግባር መፈጸሙንና ቤተ ክርስቲያኑንና ፓፓውን እንደሚወድ ቢናገርም ደግሞ ፍርዱ አልቀረለትም፡፡ በዚሁ ተመሳስሎ ወደ ቤታችን ስንመለስ በብፁዕ አቡነ ገሪማ ልዩ ጽ/ቤት ተቀምጠው ከሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች ጋራ የጥቅም ቁርኝት በመፍጠር ሀ/ስብከታቸውን በዘነጉት ሊቀ ጳጳስ ምትክ የአገልጋዩንና የምእመኑን አቤቱታ የሚያፍኑት የቀድሞው ፓትርያርክ መጋቤ ሥርዐት እነሙሉጌታ በቀለ፣ መጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም ከተባባሪዎቻቸው እነአባ አረጋዊ ነሞምሳ ጋራ የሚሰጣቸውን ውሳኔ በተስፋ እንጠብቃለን፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡ 

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)