October 27, 2012

የፓትርያርክ ምርጫ ሕግን በሚመለከት ቅዱስ ሲኖዶሱ በኅዳር ወር መጨረሻ ልዩ ስብሰባ ይጠራል


አርእስተ ጉዳይ፡- 
  • READ THIS ARTICLE IN PDF
  • የግብጹ ፓትርያርክ ምርጫ ልኡክ ዛሬ ማምሻውን ወደ ካይሮ ያመራል፤ በምርጫው ይሳተፋል፤
  • የጠ/ቤ/ክህነቱ ‹የጨለማ ቡድን› የተቋማዊ ለውጡን አመራር ለመቀልበስ ያደረገው ሙከራ ከሸፈ፤
  • በወኅኒ ቤት የሚገኙ መነኰሳት ቁጥር መጨመር አሳሳቢ ኾኗል፤ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ብቻ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው የተፈረደባቸው ከ70 ያላነሱ ‹መነኰሳት› ይገኛሉ፤
  • ገዳማት የመነኮሳታቸውን ቁጥር ጨምሮ ዝርዝር መረጃዎቻቸውን ለአህጉረ ስብከት ያሳውቃሉ፤ መነኰሳት መታወቂያ እንዲኖራቸውና ከቦታ ወደ ቦታም ያለደብዳቤ እንዳይንቀሳቀሱ ይደረጋል፤
  • ከአብነት ት/ቤቶች ጋራ የተያያዘው የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ በልዩ ትኩረት ክትትል ይካሄድበታል፤ የአብነት ትምህርት መለኪያ ተበጅቶለትና በየቋንቋው መምህራን ተመድበው መምህራን በየጊዜው የሚስመርቋቸው ደቀ መዛሙርት በምደባ በየአህጉረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እንዲመደቡ ይደረጋል፤
  • ምልአተ ጉባኤው በድሬዳዋ ሀ/ስብከትና በድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር የሚያጣራው ልኡክ በአስቸኳይ ወደ ስፍራው እንዲያመራ አዘዘ፤ የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አባ አረጋዊ ነሞምሳ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ስም በማጥፋት የኮሚቴውን ተልእኮ የሚያደናቅፉ ሕገ ወጥ ቡድኖችን እያደራጁ ነው፤
  • የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፤

 (ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 17/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶ. 27/2012)፦ ከተጀመረ ስድስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ከቀትር በኋላ እንደሚጠናቀቅ እየተጠበቀ ነው፡፡ ምልአተ ጉባኤው በትናንት፣ ጥቅምት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ውሎው በፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ዝግጅት ዙሪያ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በውሳኔው መሠረት ቀደም ሲል የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ማሻሻያ እንዲሠራ የተሠየመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ምሁራን ኮሚቴ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ረቂቅንም አዘጋጅቶ በኅዳር ወር መጨረሻ ያቀርባል፡፡ የስብሰባው ምንጮች እንደገለጹት ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በተሻሻለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ እና በፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ሰነዶች ላይ ተወያይቶ ሕግጋቱን የሚያጸድቅ ልዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ የሚጠራ ይኾናል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ዛሬ ከቀትር በኋላ እንደተጠናቀቀ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 118 ፖፕ ምርጫ ላይ ተገኝቶ በምርጫው በድምፅ እንዲሳተፍ የተሠየመው አምስት አባላት የሚገኙበት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ልኡክ ማምሻውን ወደ ካይሮ እንደሚያመራ ተነግሯል፡፡ የልኡካን ቡድኑ አባላት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስን፣ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በመንበረ ፕትርክና ራሷን በምትችልበት ዋዜማ የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን የኤጲስ ቆጶስነት (ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ.ም) እና የሊቀ ጵጵስና (ጥር 6 ቀን 1943 ዓ.ም) ማዕርጋት በሰጧቸው 115ው የግብጽ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ በኋላም ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም ወደ ፓትርያርክነት ማዕርግ ከፍ ባደረጓቸው በ116ው የግብጽ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ 6 ሹመት ላይ ኢትዮጵያውያን አባቶች በካይሮው ቅዱስ ሲኖዶስ በመራጭነት ተወክለው መገኘታቸው ይታወቃል፡፡

ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)