October 25, 2012

የዕርቀ ሰላሙ ውይይት በመጪው ኅዳር ወር ይቀጥላል


  • ቅዱስ ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአራት አህጉረ ስብከት እንዲከፈል ወሰነ
  • እስከ መጪው ግንቦት ወር የአራቱን አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች የማጠናከር ሥራ እየተሠራ ይቆያል
  • የአራት ኪሎውን መንትዮች ሕንጻ ጨምሮ 283 ቤቶችንና ሕንጻዎችን ማስመለስ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ከከተማው ከንቲባ ጋራ ውይይት ተካሄደ

(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 15/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶ. 25/2012/ READ NEWS IN PDF)፦ አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙት አባቶች ጋራ የተመጀረው የዕርቀ ሰላም ውይይት በመጪው ኅዳር ወር መጨረሻ እንዲቀጥል ወሰነ፡፡ ከኅዳር 26 - 30 ቀን 2005 ዓ.ም በአሜሪካ ለሚቀጥለው ውይይት ምልአተ ጉባኤው ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን፣ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስን፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማን በልኡክነት የሠየመ ሲኾን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በልኡካን ቡድኑ ጸሐፊነት ብቻ እንዲያገለግሉ ተወስኗል፡፡

“ሰላምን በተመለከተ” በሚለው የምልአተ ጉባኤው ቁጥር አንድ አጀንዳ ለሁለት ቀናት ክርክር ሲካሄድበት የቆየው የዕርቀ ሰላም ጉዳይ÷ በመሠረቱ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘና አዎንታዊ አቋም የተያዘበት ቢኾንም የአራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ዕጣ ፈንታ በመወሰን በኩል የተለያዩ አስተያየቶች ተንጸባርቀዋል፡፡ በአንድ በኩል÷ ዕርቀ ሰላሙ ከተፈጸመ ዘንድ አራተኛው ፓትርያርክ ወደ መንበረ ፕትርክናው ተመልሰው እንዲቀመጡ የመሻት አቋም በደብዳቤ ጭምር በተገለጸበት አኳኋን የተንጸባረቀ ሲኾን በሌላ በኩል ደግሞ÷ አንዱ በሌላው ላይ ያስተላለፈው ውግዘት መነሣቱንና ዕርቀ ሰላም መፈጸሙን ዋነኛ/በቂ ጉዳይ በማድረግ ይህን ተከትሎ አራተኛው ፓትርያርክ ስማቸውን በቅዳሴ ከመጥራት ጀምሮ አስፈላጊው ሁሉ ተሟልቶላቸው በመረጡት ስፍራ እንዲቀመጡና ወደ ቀጣዩ ፓትርያርክ ሹመት የመቀጠል አቋም ታይቷል፡፡

በኅዳር ወር መጨረሻ በሚቀጥለው ውይይት እኒህና ቀደም ሲል በቀረቡ ሰባት ጥያቄዎች ላይ የተሰጡት ምላሾች የሚተኰርባቸው ሲኾኑ ለዕርቀ ሰላም ውይይቱም የመጨረሻ እልባት እንደሚሰጥበት ተስፋ ይደረጋል፡፡

በዕርቀ ሰላሙ ዙሪያ የሚሠራው “የሰላምና አንድነት ጉባኤ” በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎችና ለቅዱስ ሲኖዶሱ በጻፋቸው ደብዳቤዎች “አግላይ/አድሏዊ” እና “ቅዱስ ሲኖዶሱን ለማዘዝ ሞክሯል” የተባለበት ኹኔታም ሌላው አወያይ ጉዳይ እንደነበርና ሁሉም ወገኖች ዕርቀ ሰላሙን ከሚያደናቅፉ ተግባራት እንዲቆጠቡ ማስታገሥና ለሁሉም ወገኖች በማእከላዊነት ማገልገል ይጠበቅበታል መባሉም ተዘግቧል፡፡ ከሰላምና አንድነት ጉባኤው አባላት መካከል ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ እና ዲያቆን አንዱዓለም ዳግማዊ የምልአተ ጉባኤው አቋም የተገለጸበትን ውሳኔ ለመቀበል በዚያው በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ምልአተ ጉባኤው በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በጎሰኝነት ላይ ባተኮረ የቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር አፈጻጸም ሲታመስ የቆየው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአራት አህጉረ ስብከት ተከፍሎ እንዲተዳደር መወሰኑ ተነግሯል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ትናንት ከቀትር በኋላ በነበረው ውሎ ባስተላለፈውና አከራካሪ በነበረው በዚሁ ውሳኔው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ ተብሎ በአራቱ ዐበይት ማእዝናት ይከፈላል፡፡ በውሳኔው መሠረት አራቱ አህጉረ ስብከት ከጠቅላላው 160 አድባራትና ገዳማት አርባ-አርባ አጥቢያ ክርስቲያን በመያዝ የየሀገረ ስብከታቸውንና የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶቻቸውን ያቋቁማሉ፡፡ አሁን በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የሚገኙት ሠራተኞች በአራቱ አህጉረ ስብከት ተከፋፍለው የሚመደቡ ሲኾን በሚሾሙላቸው ሥራ አስኪያጆች እና በሚቋቋሙት የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ጽ/ቤቶቻቸውን እያጠናከሩ እስከ መጪው ግንቦት ወር ከቆዩ በኋላ የየራሳቸው ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚሾሙላቸው የስብሰባው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ለ31ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቀረበው የሀ/ስብከቱ የበጀት ዓመት ሪፖርት ላይ በወጣው የአቋም መግለጫ ከሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ጀምሮ በአድባራትና ገዳማት ሁሉ በተደጋጋሚ የሚታየውን የሥራ አለመቀላጠፍና ከሙስና ጋራ የተያያዘ ልዩ ልዩ ችግር በቋሚነት ለመፍታት ይቻል ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ “የማያዳግምና ሥር ነቀል ውሳኔ” እንዲሰጥበት አጽንዖት የተመላበት ማሳሰቢያ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ከቀረበው የሀ/ስብከቱ ሪፖርት የሚታየው የገቢ ዕድገት የሚበረታታ እንደ ኾነ ያመለከተው የአቋም መግለጫው÷ እንደ አዲስ አበባ ተጨባጭ ኹኔታ ሲታይ ገዳማቱና አድባራቱ ከፍተኛ የሀብት ክምችት ያለባቸው፣ የብዙ ባለሀብትና ንብረት ባለቤቶች ከመኾናቸው የተነሣ በቃለ ዐዋዲው ሕግና መመሪያ ተደግፎ በታማኝነት ከልብ ከተሠራ በሀ/ስብከቱ በሁሉም የሥራ ዘርፍ ተኣምር ለመፍጠር እንደሚቻል አጠቃላይ ጉባኤው ያለውን እምነት ገልጧል፡፡

በአቋም መግለጫው ላይ ከተዘረዘሩትና አጠቃላይ ጉባኤው ከሀ/ስብከቱ ሪፖርት ከወሰዳቸው ግንዛቤዎች መካከል÷ የመልካም አስተዳደር ዕጦት (ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ በማስቀመጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት መንፈስ ሥራን አለማቀላጠፍ)፤ በጎሳ ላይ ያተኰረ የቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር አፈጻጸም ችግር፤ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት አለመደራጀትና የአባላት አስተዋፅኦ በትክክል አለመክፈል፣ የሒሳብ ምርመራን በጊዜውና በትክክል አለማድረግ፣ የፐርሰንት ገቢውም በየደረጃው በቅጽ ተሞልቶ በጊዜው አለመቅረብ፣ “ቅድሚያ ለመነኰሳት” በሚል የመጠቃቀሚያ ፈሊጥ ምንኵስናቸው በሚገባ ላልተረጋገጠ ያለበቂ ዕውቀት መነኰሳት ነን ባዮች በልብስ ብቻ ቅድሚያ ቦታ እየተሰጠ ገዳማት እየተዘጉ መኾኑና በሰበካ ጉባኤ ማ/መምሪያው መረጃና በሀ/ስብከቱ የሒሳብ ሪፖርት መካከል የታየው የብር 6,753,717.25 ልዩነት (ጉድለት) ይገኙበታል፡፡

ከዚሁ ጋራ በተያያዘ የኖረውን የሀ/ስብከቱን ችግር ወደ ከፋ ደረጃ በማድረስ ጉብኝት በሚል መርሐ ግብር በየሄዱበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በትንሹ እስከ ዐሥር ሺሕ ብርና ከዚያም በላይ (በተሣልቆ የኮቴ ብለው ይጠሩታል) ይቀበላሉ የሚባሉት የወቅቱ ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከሓላፊነታቸው እንደሚወገዱ ተነግሯል፡፡ ይኹንና ባደራጁት የደላሎች ሰንሰለት ንቡረ እዱ ርምጃ እንዳይወሰድባቸው ለመከላከል የሚደረግ የአንዳንድ ጥቅመኛ አለቆችና ጸሐፊዎች እንቅስቃሴ እንዳለ የተሰማ ቢኾንም ንቡረ እዱ ግዘፍ ነስቶ መልክ አውጥቶ የሚታየው ሙሰኝነታቸውና ከወቅቱ የመንበረ ፕትርክናው ጉዳይ ጋራ የተያያዘው የአድመኝነት ተግባራቸው ከሚያስከትልባቸው ተጠያቂነት ሊታደጓቸው የሚችሉ ግን አይመስሉም፡፡

በተያያዘ ዜና በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ የተመራ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት ቡድን ትናንት፣ ጥቅምት 14 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ጋራ መወያየቱ ተሰምቷል፡፡ ውይይቱ በመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በሚተዳደሩትና ቤተ ክርስቲያናችን ለተለያዩ ተግባራት የሠራቻቸው ቁጠባ እና ቪላ ቤቶች፣ አፓርትመንቶች፣ ሕንጻዎችና መጋዘኖች እንዲመለሱላት ቀደም ሲል በቤቶች አስመላሽ ኮሚቴ ለተጀመረው ጥረት እልባት መስጠት በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ያተኰረ እንደነበር ተዘግቧል፡፡

የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በተያዘው በጀት ዓመት ራሱን በሰው ኀይል በማጠናከርና ከብፁዓን አባቶች ጋራ በመኾን ጉዳዩን ለመቋጨት የያዘው ዕቅድ አካል መኾኑ በተነገረው በዚሁ ውይይት÷ በአራት ኪሎ መንበረ ፓትርያርክ አጠገብ የሚገኙት መንትያ ሕንጻዎች፣ የተወካዮች ም/ቤት፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት፣ የኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ ፊኒፊኔ /ዱክ/ ሆቴል እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኤጄንሲ የሚተዳደሩ የቁጠባ ቤቶች ብዛታቸው 283 ማስረጃዎቻቸው ተጠናክረው በቅርብ እንዲመለሱ ወይም መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ኪራይ እንዲከፍል፤ መንግሥት መልሶ ማልማት በሚያካሂድባቸው አካባቢዎች ለሚነሡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶች ካሳ እንዲከፍል ወይም ቤተ ክርስቲያኒቱ በቦታው ላይ ሕንጻዎችን ለመገንባትና የጋራ መኖርያ ቤቶችን ለመሥራት የምትችልባቸው ኹኔታዎች እንዲመቻቹላት ጥያቄ መቅረቡ ተገልጧል፡፡ ጥያቄዎቹ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አስተዳደር ወቅት ቀርበው የነበሩ መኾናቸው ያስታወሰው ምንጩ ከሌሎችም የፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጋራ ቀጣይ ውይይት እንደሚካሄድበት አመልክቷል፡፡

የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ለ31ው ሰበካ መንፈሳዊ አጠቃላይ ጉባኤ ባቀረበው ሪፖርትና ባሰራጨው  መረጃ÷ ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያን በስሟ የገነባቻቸውን ቤቶችና ሕንጻዎች የሃይማኖት ልዩነት ሳታደርግ የሁሉንም ኅብረተሰብ አቅም ባገናዘበና የወቅቱን ገበያ ባማከለ መልኩ የኪራይ አገልግሎት የመስጠት፤ ሕንጻዎቹ የመድን ዋስትና እንዲገባላቸው፣ ቀጣይ የዕድሳትና ጥገና ሥራ እንዲሠራላቸው ማድረግ፤ ከቤት ኪራይ ገቢ 30 በመቶ የፈንድ ሪዘርቪንግ ሥርዐት እንዲኖር ማስቻል በአጭር ጊዜ የያዛቸው ዕቅዶቹ እንደኾኑ አስታውቋል፡፡ ከረጅም ጊዜ ዕቅዶቹ መካከልም በሪልስቴት ግንባታ ዘርፍ ጥሩ ተፎካካሪ በመኾን በአገራችን የሚታየውን የቤት ችግር በመቅረፍ ከልማቱ ከሚገኘው ገቢ መንፈሳዊ አገልግሎት ፍጹም ተዳራሽ የሚኾንበትን አሠራር በመፍጠር፣ የቤተ ክርስቲያንን የኢኮኖሚ አቅም በማጠናከር ለአገልጋይ ካህናትና ምእመናን ምቹ የኑሮ ኹኔታ መፍጠር፣ ቤተ ክርስቲያናችንም ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በብቃት እንድትወጣ ማስቻል እንደኾነ አመልክቷል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

8 comments:

Anonymous said...

eleleleleleleleleelelelele

Anonymous said...

የቤተ ክርስቲያንን የኢኮኖሚ አቅም በማጠናከር ለአገልጋይ ካህናትና ... ምቹ የኑሮ ኹኔታን ለመፍጠር፣ የሚሮጥ ... የከተማ ቤት ለማስመለስ የተመደቡት ሰወች ለበረከት ሲሉ ስለዋልድባ ገዳምና በእስር ስለሚንገላቱት አበው ጥያቄ ለሚመለከተው ከፍል ቢያቀርቡ ለማሳሰብ ነው ሌላ ኮሚቴ ከማቋቋም እኛም እውነቱን ለመናገር ሁሉንም እያየን እየታዘብንም ስለሆነ ነገሩ ሁለ አለማዊነቱ ያየለበት ሁኔታ ይስተዋላል:: ሌላው ፓትሪያሪክ ለመሾም የሚፈልጉት ሰወች በውነቱ ምክኒያታቸው ምን ይሆን??? ውሻ በቀደደው ጂብ ይገባል አይደል እንደነዚህ አይነት ሰወች ስለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሳይሆን የዘረኝነትና የፖለቲካ ንክኪ ያላቸው ስለሆኑ መከፋፈሉን አጥብቀው ይፈልጉታል በዚህ ወቅት አይኖቻችን እያዩ ጆሮወቻችን እየሰሙ በጠራራ ጸሀይ ምንም ልታደርጉ አትችሉም ሊባሉ ይገባል:: በአሁኑ ሰአት ይህች ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስና የቤተ ክህነት ብቻ ሳትሆን የምእምናንም መሆንዋን ሊያስተውሉ ይገባል:: አንድነታችንን እንፈልጋለን:: የተረከባችሁት አንዲት ቤተ ክርስቲያን ነች ለዚህ ትውልድም ልታስረክቡ የሚገባችሁ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ነው:: ሁለት ፖትሪያሪክ አንፈልግም:: ከፋፍሎ መጋዛት ይቁም!!! ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ያስፈልጋታል !!!

Anonymous said...

በ እውነት አባቶቻችን አሁን እንዲህ ሁሉም ለ እርቀ ሰላም ተዘጋጅቶ በጉጉት እየጠበቀ ባለበት ሰአት ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ እያሉ ሌላ ሁለተኛ ፓትርያሪክ ለመምረጥ ካሰቡ በጣም የሚያሳዝን እና የሚያሳፍር ነው::
አስተዳደሩን የሚያስተዳድር እንደራሴ ተመርጦ ፓትርያሪኩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በፈለጉበት ቦታ ሆነው ቡራኬያቸውን እየሰጡን ሊቀመጡ ይገባል ባይ ነኝ:: ይህ ሁሉን የሚያስማማ ነውና:: የአሁኑ መንግስት ለ2ኛ ጊዜ እጁን አስገብቶ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ ባሰ ችግር ሲከታት አባቶቻችን እያዩ ዝም ማለት የለባቸውም እኛም ከአባቶቻችን ጎን ሆነን አለንላችሁ ልናላቸው ያስፈልጋል::

Anonymous said...

wow excellent news ,Deje selam
May GOD bless our church.

በሪልስቴት ግንባታ ዘርፍ ጥሩ ተፎካካሪ በመኾን በአገራችን የሚታየውን የቤት ችግር በመቅረፍ

Aregawit said...

E/r fetsamewone yasamerowe.
Amen.

orthodoxawe said...

ንቡረእድ ኤልያስ ከዚህ ኮሚቴ ውስጥ መውጣት አለባቸው! ለምን ጸሐፊ እንዲሆኑ ተፈለገ? ጸሐፊ ጠፍቶ ነውን? ወይስ የመንግስትን ፍላጎት ለማስፈጸም? የአወግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን።

Anonymous said...

What is that mean? Are they not going select the 6th Patriarc? The church is going to continue with out Patriarc till Genbot? You know that will give power for enemy.

Anonymous said...

If ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ en:
1. He must return to Ethiopia
2. The name should stay as the 4th Patriarc.
3. America shulld have four Hagere sbket like Addis Ababa.
4. Abune Fanuel shold return to Ethiopia.
5. Kale'Awade (ቃለ አዋዲ) should be printed and given to all E.O.T. Churchs. Specially E.O.T.C living outside of Ethiopia.
6. All E.O.T.C must be clean from ሙስና.
7. There should not be another Patriarc elected before እርቀ ሰላም ሳይወርድ ወይም ውግዘት ሳይነሳ::

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)