October 16, 2012

የየራሳቸውን “ፓትርያርክ ለመሾም” ሙከራ የሚያደርጉ …


(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 6/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 16/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድነት አስፈላጊነት ከምንም በላይ በሁሉም ዘንድ ትልቅ ትኩረት እየተሰጠው ነው። በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም “አንድነት፣ እርቅ” የሚሉት ቃላት ተደጋግመው በመሰማት ላይ ናቸው። የቀጣዩ ፓትርያርኩ ጉዳይ ከእርቅ እና ከአንድነት በኋላ እንጂ በችኮላ አሁን መሆን እንደሌለበት አጽንዖት እየተሰጠው ባለው በአሁኑ ወቅት የየራሳቸውን ወገን “ፓትርያርክ” አድርገው ለማስሾም ፍላጎት አላቸው የተለያዩ አካላት፣ ቡድኖች፣ ግለሰቦች እና ስብስቦች በይፋ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ከመንግሥት እንጀምር።

አቡነ ጎርጎርዮስ

መንግሥት
መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ ያለውን የቆየ እና መሠረት የያዘ አቋም በተመለከተ ከዚህ ቀድሞ ሰፊ ሐተታ ማቅረባችን ይታወሳል። ያላነበበ ካለ ከዚህ (LINK) ያገኘዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የመንግሥትን አቋም አስመልክቶ ወይም በመንግሥት ስም ስለ ዕርቀ ሰላሙ ሂደትና በቀጣዩ ፓትርያርክ መመረጥ ዙሪያ የሚሰማው መረጃ የተቀላቀለ ነው። (የሚባለውን በርግጥ የሚያደርገው ከሆነ ከሕገ መንግሥቱ ጋራ የሚጋጭ ነው፡፡) የአራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ አገር ቤት የመመለስ ፍላጎት “በራሱ መንገድ አረጋግጧል” የተባለው መንግሥት÷ ቅዱስነታቸው ወደ አገር ቤት ለመመለስ ያላቸውን ፍላጎት በአዎንታዊነት ተቀብሎ ሲያበቃ የቅዱስነታቸው ፍላጎት ምንም ይኹን በአባትነታቸው በመንበሩ ተቀምጠው ማየት እንደማይሻና ዕርቀ ሰላሙ ይህን ሳይጨምር ሊፈጸም እንደሚችል አቋም ይዟል መባሉ ግን አሳሳቢ ኾኗል፡፡ ከዚህ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ቀጣዩን ወይም ስድስተኛውን የፓትርያርክ ምርጫ እንድታከናወን፣ እንድታከናወን ብቻ ሳይሆን በዚሁ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅት ቀን ቆርጣ በፍጥነት እንድታከናወን እንደሚሻ ነው የሚነገረው፡፡

1.    ምርጫ አንድ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
ከዚህም አልፎ የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለአንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደ እንደራሴያቸውም እንደተተኪያቸውም አስተዋውቀዋቸው ነበር የተባሉትን የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን ስድስተኛው ፓትርያርክ ይኾኑ ዘንድ ወስኖ መግፋት መጀመሩ ነው የተሰማው፡፡ እንደ ምንጮች ማብራሪያ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ወደ ፕትርክናው መንበር መገፋታቸው÷ “የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አቋም እና አሠራር (እነርሱ ራእይ ይሉታል) ያስቀጥላሉ፤ ለመንግሥት ለመታዘዝና ፍላጎቱን ለማስፈጸም ይመቻሉ” በሚል ሐሳብ ነው ተብሏል፡፡

2.   ምርጫ ሁለት - ብፁዕ አቡነ ማቲያስ

የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልተሳካ ሁለተኛ አማራጭ ኾነው የተዘጋጁት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው ለበርካታ ዓመታት በውጭ የነበራቸው ቆይታ፣ ከቤተ ክህነቱ ችግር ጋራ ብዙ ንኪኪና ትውውቅ የሌላቸው መኾኑና ከመንግሥት ጋራ አብሮ በመሥራት ረገድ አላቸው የሚባለው አቋም በጉዳዩ እጃቸውን ካስገቡት የመንግሥት ሓላፊዎች እና እነርሱን እየተባበሯቸው በሚገኙት የቤተ ክህነቱ ሰዎች በዕጩነት እንዲያዙ እንዳደረጋቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ በአንድ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን የሚመራ ነው በተባለው በዚህ የ“ቀራቤ-መንግሥት” ፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ድጋፍ እየሰጡ ናቸው የተባሉት የቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች በዋናነት÷ በሦስት የአድባራት አለቆች የሚመራ አደገኛ የደላሎች ሰንሰለት በመዘርጋት ሙስናን በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አነገሱ የሚባሉት ሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን የሚጠቅስ ሲኾን ከእርሳቸውም ጋራ ዶ/ር ጸጋዬ በርሄ፣ መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ በቀለ፣ አቶ ተፈሪ የማነ፣ ዲያቆን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ዐማኑኤል የተባሉ እና ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ከነግብር አበሮቻቸው በቡድን አባልነት እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ

ቡድን ስምንት
በሌላ መሥመር ብፁዕ አቡነ ማቲያስን ቀዳሚ የፕትርክና ዕጩው በማድረግ በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) እየተገናኘ የሚመክረው ቡድን ስምንት የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አለቆችንና ጸሐፊዎችን በአባልነት የያዘ ሲኾን አንድ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣንን በበላይነት መያዙ ይነገራል፡፡ ቡድኑን በቢሾፍቱ እና በአዲስ አበባም በታላላቅ ሆቴሎች እንደሚሰበስቡት የተመለከተው ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ በእልቅና በተሾሙባቸው አድባራት ሁሉ በሙስናና ዘረፋ ቅሌቶች በካህናትና ምእመናን አቤቱታ በውርደት የመባረር ታሪክ አላቸው። ቡድኑን ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ አፍራሽ ዓላማቸው የተጋለጠው የ”ጉባኤ አርድእት” ነን ባይ ግለሰቦች፣ ከአንድም ሦስት የቤተ ክህነቱን ኪራይ ቤቶች በእርሷ እና በልጇ ስም ከመያዟ በተጨማሪ “ቀራንዮ በኢየሩሳሌም” በተሰኘውና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሚካሄድበት የጉዟ ወኪሏ በኩል የምታገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ የምትሠራው እጅጋየሁ በየነ (ብዙዎች ኤልዛቤል በሚለው ያውቋታል)፣ ጉዳዩ ለጥቅምቱ ቅ/ሲኖዶስ በይደር የሚታይበት በጋሻው ደሳለኝና መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ በአባሪ ተባባሪነት እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡

የቀሲስ በላይ መኰንን ቡድን?
ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናትን ስሞች መጠለያ ያደረገው ሌላው ቡድን በአሁኑ ወቅት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ዲን በኾነው ቀሲስ በላይ መኰንን ይመራል የተባለው ቡድን ነው፡፡ ቀሲስ በላይ መኰንን ለቦታው ብቁና ተገቢ (fit and proper) ሳይሆን በኮሌጁ ዲንነት እንደተቀመጠ ይነገራል። በኦህዴድ/ኢሕአዴግ አባልነቱ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተመራጭና የፓርቲ ፖሊቲከኝነት የሚጫነው ካህን ነው፡፡

አስገራሚው ጉዳይ ቡድኑ ኅቡእ እንቅስቃሴውን የጀመረው የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዜና ዕረፍት በተሰማበት ጥቂት ቀናት ውስጥ ግብአተ መሬታቸው ሳይፈጸም መኾኑ ነው፡፡ የቡድኑ ዋና ዓላማ “ኦሮሞ ጳጳስ በፓትርያርክነት ማስመረጥ” መኾኑ ተነግሯል፡፡ ለዚህም አንዳንድ የአድባራትና ገዳማት ሰበካ ጉባኤያት ክፍሎች ሓላፊዎችን፣ በመንበረ ፓትርያርኩ ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ጥቂት የሥራ መሪዎችን፣ በጣት የሚቆጠሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ተማሪዎችንና ጎሰኝነትን ሽፋን ባደረገ ጥቅመኝነት የናወዙ ጋዜጠኞችን በአሳታፊነት መያዙ ተጠቁሟል፤ ከአዲስ አበባ አስተዳደር እና ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተወሰኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናትንም እንደ ማስፈራሪያ እንደሚጠቀምባቸው ይወራለታል፡፡ ወደ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት ሳይቀር ስልክ እያስደወለ “ኦሮሞ ፓትርያርክ ካልተመረጠ የኦሮሞ ሕዝብ ይኹንታ የሌለበት ምርጫ ነው ብለን መግለጫ እናወጣለን” ብሎ እስከመዛት የደረሰው ይኸው ስብስብ ብፁዕ አቡነ ያሬድን አልያም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን ወደ መንበረ ፕትርክናው ለመግፋት እየሞከረ እንደኾነ ይነገርለታል፡፡

“ፕትርክና ለወሎ” የሚለው ቡድን
“የኦሮሞ ፓትርያርክ አስመርጣለኹ” ከሚለው ቡድን ጋራ በትይዩ የሚሻኮተው ሌላው ኅቡእ ቡድን ጉዳዩን በቅርበት በሚከታተሉት አካላት ዘንድ ‘w-group’ /ወሎ ግሩፕ/ ይባላል፡፡ ይኸው ቡድን “ጊዜው/ተራው የወሎ ነው፤ ፓትርያርኩም ከወሎ መኾን ይገባዋል” በሚል ይንቀሳቀሳል፡፡ እንቅስቃሴውን በዋናነት የሚያስተባብሩት የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል ናቸው፡፡ በጡመራ መድረኩ የመረጃ ምንጮች መሠረት ቡድኑ እንደምቹ ኹኔታ የወሰደው ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤትና አህጉረ ስብከት ጀምሮ እስከ መምሪያ ሓላፊነት ድረስ ከፍተኛ ቦታ የያዙትንና በቁጥርም አንጻራዊ ብዛት ያላቸውን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመምሪያና የጽ/ቤት ሓላፊዎች መኾኑ ተመልክቷል፡፡ በዋናነት የደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስን ይህም ካልተሳካ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘካናዳን፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን አልያም ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን ወደ መንበረ ፕትርክናው የማቅረቡን ሥራ በመግፋት ላይ መኾኑ ይነገርለታል፡፡

ሌላውስ ምን ይላል?
ጎልተው ከወጡትና በስም ከታወቁት ቡድኖች ውጭ በማኅበራት ስም የተደራጁና የየራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን በየፊናቸው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እንዳሉ የሚያስረዱት የመረጃ ምንጮቹ÷ ጥቅመኝነታቸውንና የፖሊቲካ ፍላጎታቸውን በጎሰኝነት መሳሳብ ለማስጠበቅ፣ ሲፈጽሟቸው በቆዩት ወንጀሎች ራሳቸውን ከተጠያቂነት የሚያድኑበትን ቀጣይ ኹኔታዎች ለመፍጠር የሚራወጡት ቡድኖች ይኹኑ ግለሰቦች ወደ ፕትርክናው መንበር ለመግፋት የሚያስቧቸውን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና አጠቃላይ ሕዝቡን እንደማይወክሉ፣ ሊወክሉም እንደማይችሉ ይከራከራሉ፡፡

ሰሞኑን አገልጋዩና ምእመኑ አባ እገሌን ከአቡነ እገሌ በትውልድ ማንነታቸው ሳይለይ ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት እንዲጠብቅ፣ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ዶግማና ቀኖና መጽናትና መስፋፋት የሚቆም፣ ለመንጋው የሚራራ ቅንና ደገኛ አባት እንዲሰጥ በግልና በጋራ የያዘውን ጾምና ጸሎተ ምሕላ፤ ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንኑ ለማስፈጸም እንዲተጋ በየአደረጃጀቱ ተፈራርሞ የሚያስገባቸው ማመልከቻዎች (ፔቲሽኖች) በአስረጅነት ይጠቅሳሉ፡፡ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት 131 ሰንበት ት/ቤቶችን በአንድነት የሚመራው ኅብረት፣ የፀረ ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት፣ ማኅበረ ቅዱሳን (ቴሌ ኮንፈረንስ በማዘጋጀት ጭምር) እና ሌሎችም ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቧቸው እና ለማቅረብ ያዘጋጇቸው ፔቲሽኖች ለዕርቀ ሰላም ንግግሩ፣ ለፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ዝግጅቱ፣ ለተቋማዊ ማሻሻያ ጥረቱ ስኬት ጥንቃቄ የተመላበት አካሄድ እንዲኖር የሚያሳስቡ ናቸው፡፡

ከመስከረም 16 - 24 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ከአራቱም ማእዝናት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ለተመመው በመቶ ሺሕዎች ለሚቆጠር ኦርቶዶክሳዊ ምእመን የፀረ - ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት አባላት እና መንፈሳውያን ማኅበራት (የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ተምሮ ማስተማር፣ የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምክሐ ደናግል፣ ማኅበረ ሰላም፣ ኢያቄም ወሐና፣ ማኅበረ ጽዮን፣ ማኅበረ ሐመረ ኖኅ፣ ማኅበረ አሮን፣ ማኅበረ ፋኑኤል፣ የሰዓሊተ ምሕረት. . .ወዘተ) በየማረፊያ ድንኳናቸው፣ ምእመኑ በተጓጓዘባቸው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ውስጥ ሳይቀር የወቅቱን ኹኔታ አስመልክቶ የዘረጓቸው የትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች፣ መዝሙሩ እና ስብከቱ ሳይቀር የጎሰኞችን፣ የጥቅመኞችንና የፖሊቲከኞችን ፍላጎት በምኞትነቱ የሚያስቀር፤ ምእመኑን ከባይተዋርነት አውጥቶ በአንድ ቃልና መንፈስ ባለቤትና ንቁ ተሳታፊ እንደሚያደርገው ምንጮቹ ይመሰክራሉ፡፡ በትምህርቶቹ እና ስብከቶቹ ላይ ተመሥርቶ በተካሄዱ የሐሳብ ልውውጦችም ምእመኑ በቀጣይ በሚደረጉ ጥረቶች ከሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካል ብቻ የሚተላለፍለትን መልእክት እንደሚከታተልና የተጠየቀውን ድጋፍ እንደሚሰጥ አቋሙን መግለጹ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት መጠበቅና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መርጦ ከሚሾመው በቀር የማንንም ጫና ላለመቀበል መወሰኑን እንደሚያሳይ ምንጮቹ በሙሉ ልብ ይናገራሉ፡፡

ይኸው የአገልጋዩና ምእመኑ አስተሳሰብና አቋም በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ዘንድም የሚታይ ነው፡፡ አንድ ብፁዕ አባት እንደተናገሩት በሞተ ዕረፍት ከመለየታቸው በፊት በቤተ ክርስቲያናችን ሁለት ነገሮች ተፈጽመው ማየት ይፈልጋሉ፡፡ አንደኛው÷ ባለፉት ኻያ ዓመታት በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ላይ የተፈጠረው ሥብራት እንዲጠገን ነው፤ ሁለተኛው÷ ደግሞ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱና እስከ አጥቢያ ለሚገኙት መዋቅሮቹ መንፈሳዊ፣ ብቁና ተገቢ የለውጥ መሠረት ተጥሎ ማየት ነው፡፡ በመኾኑም የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው ቅ/ሲኖዶስ ከአኀት አብያተ ክርስቲያን ልምዶች በመማር፣ የአገራችንን ሕጎችና የቤተ ክርስቲያናችንን የግማሽ ምእት ዓመት የመንበረ ፕትርክና ተሞክሮ በመቀመር አዳብሮ አዘጋጅቶታል በተባለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ለአራተኛ ጊዜ ተሻሽሎ ለውይይት በሚቀርበው የቃለ ዐዋዲ ደንብ እና ቋሚ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ መሠረት ከሚወሰነው ውጭ የማንኛውንም አካል ጫና ለመመከት፣ ለዚህም መሥዋዕት ለመኾን የተዘጋጁ ብፁዓን አባቶችን ማየት በርግጥም የሚያኮራ ነው፡፡ የውጭ ተጽዕኖ መግቢያው የብፁዓን አባቶች አንድነት መላላት ነውና በተለያዩ መደለያዎችና ማስፈራሪያዎች ሳይበገሩ ተስፋችንን ለቤተ ክርስቲያናችን ሉዓላዊ የመወሰን ሥልጣንን በሚያጎናጽፏት ሕጎች፣ አሠራሮችና ውሳኔዎች ላይ ብቻ ማድረግ በእውነትም የመሥዕትነት ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ117ው የኮፕቱ ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ዕረፍት በኋላ ወራትን በወሰደው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የሽግግር ጊዜ እያየነው እንዳለነው÷ ቤተ ክርስቲያናችንም ዐበይት የሽግግር ወቅት ሥራዎቻችን እንዴት፣ በማንና በምን ያህል ፍጥነት ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ መርሐ ድርጊት (Road Map) ቢያዘጋጅ የሥራውን ርምጃ ለመለካት ያስችለዋል፡፡ ከመርሐ ድርጊቱም ጋራ በአንድ ብፁዕ አባት የሚመራ የቃል አቀባይ ጽ/ቤት አቋቁሞ እንደ አስፈላጊነቱ ለብዙኀን መገናኛ፣ ለአገልጋዩ፣ ምእመኑና ለሚመለከታቸው ሁሉ በየጊዜው ርምጃዎቹን ቢያሳውቅ ከላይ የተገለጹትን ዐይነት የግብረ በላዎች ቡድን የሚራባበት ማኅበራዊ መሠረት እንደሚደርቅ፣ አውዳሚ ድርጊቱንና የሚነዛውን አሉባልታም ለመግታት አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ምንጮቹ ይመክራሉ፡፡

እንግዲህ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ዘላቂ ሰላም ጉዳይ በዚህ ደረጃ ይገኛል። የቤተ ክርስቲያናችንን የአንድነት እና የመጠናከር ተስፋ በጎሰኛ፣ ጥቅመኛ እና ፖሊቲካዊ ፍላጎታቸው ለማምከን እየሠሩ የሚገኙትንና የቤተ ክርስቲያናችንን ተስፋ ለማጨለም የሚጥሩትን ወገኖች ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ከድርጊታቸው ሊያስቆሟቸው ይገባል። ለዚህም ደጀ ሰላም አቤት ትላለች፤ በአቤቱታዋም ትቀጥላለች ! ! !

ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅልን፤ ቅን ደገኛ አባት ይስጥልን፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
14 comments:

Anonymous said...

Shame on the Ethiopian Government! This group no more be our Government. The influences of all others like ጎሰኞች፣ ጥቅመኞችና ፖሊቲከኞች ፍላጎት should have been controlled by the Gonvernment. But the Government it self is one of the most influencing groups to create violences in the country. Shame shame shame on the Government!

Anonymous said...

“በአሁኑ ወቅት በውግዘት የተለያዩት አባቶች ያለአንዳች ቅድመ ኹኔታ ዕርቀ ሰላም ፈጽመው የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እንዲያረጋግጡ … ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ … ፓትርያርኩ ከሚገኙበት የጤናና የዕርግና ኹኔታዎች አኳያ ወደ አገር ቤት ተመልሰው በመረጡት ገዳም እንዲቀመጡና እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ መንበሩ ተጠብቆ ቤተ ክርስቲያናችን ቅ/ሲኖዶስ በሚሾመው እንደራሴ እንድትወከል…”
አዲስ ፓትርያርክ እንዲመረጥ የሚፈልጉ ሰዎች አላማቸው ምን እንደሆነ ቢያስረዱን መልካም ነው:: አዲስ ፓትርያርክ መምረጥ የሚያስፈልግበት ምንም ምክንያት የለም ምንም:: አዲስ ፓትርያርክ መምረጥ የቤተክርስቲያንን መከፋፈል ያጠናክር እንደሆን እንጂ ሌላ ምንም ጥቅም የለውም:: የአዲስ ፓትርያርክ ምርጫ ቢያንስ የሚከተሉት አደጋዎች አሉት:-
1. የቤተክርስቲያንን መከፋፈል ያጠናክራል
2. ድሮ የተጣሰውን ቀኖና-ቤተክርስቲያን እንደገና ጊዜ መጣስ ይሆናል

ስለዚህ ቢያንስ ባለማወቅና በየዋህነት የአዲስ ፓትርያርክ ምርጫን የምትፈልጉ ሰዎች ቆም ብላችሁ አስቡ:: ፓትርያርክ ባይመረጥ ለቤተክርስቲያን ምንም ችግር የለውም:: የቤተክርስቲያንን ጉዳይ የሚወስነው ፓትርያርኩ አይደለም ቅዱስ ሲኖዶስ ነው:: አንዱን አባት በእንደራሴነት አስቀምጦ የአስተዳደር ጉዳዮችን ከዋና ስራ አስኪያጁ ጋ በመሆን እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል:: የአዲስ ፓትርያርክ ምርጫ ግን ለብዙዎች ግልጽ ያልሆነ አደገኛ ፈተና አለበት:: የአዲስ ፓትርያርክ ምርጫን የሚፈልጉት ወገኖች ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም በቤተክርስቲያን ጉዳይ ግን መስማማት የማንችልበት ምክንያት መኖር የለበትምና ሁሉም ክርስቲያን የአዲስ ፓትርያርክ ምርጫ ምንም ጥቅም እንደሌለው ተረድቶ አሁን እርቀ ሰላሙን ብቻ ለማፋጠን ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ ቢያደርግ መልካም ነው::
የጎሰኞችን፣ የጥቅመኞችንና የፖሊቲከኞችን ፍላጎት: እግዚአብሔር በቸርነቱ ያምክነው::

በጣም የሚያሳዝነው ግን እንደመንግስት ሆኖ የተቀመጠው አካል ብዙ ነገር እየተጠበቀበት እሱ እራሱ ዋናው ሀገር እንዲበጠበጥ ምክንያት እየሆነ መሆኑ ነው:: ከዚህ በላይ አሸባሪነት ምን አለ? አሸባሪነት ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በቀር መንግስትን ጨምሮ በቡድን ተደራጅተው እምነታችንን በነጻነት እንዳናከናውን ከሚረብሹን ከነኚህ ቡድኖች በላይ ኢትትዮጵያ ውስጥ አሸባሪነት ያለ አይመስለኝም::

Mekonen

Anonymous said...

abet ante Medahinialem! sinte gud ale. Atitewon Geta Hoyi. Ante meftihewun amitalin.

Anonymous said...

ደጀ ሰላም በርቺ አንቺ ብቅ ባትይ ይሄንስ መረጃ የት አናገኘው ነበር ? ነገሩ በጣም የሚያሳዝን ነው :: ይሄ አንደሚመጣ ደግሞ ሳይታለም የተፈታ ነው ::የ፳ ዓመት ክፍፍል ገና ከዚህ በላይ ፈተና በቤተ ክርስቲያን ላይ አንደሚያመጣ ምንም ጥርጥር የለውም ::እንደ አዲስ ነገርን አንቆጥረውም ዘረኝነት ጥቅመኝነት በቤተ ክህነት ከነገሰ ዘመናት ተቆጠሩ ::ምናልባት አሁን ጽዋው ሞልቶ ሊገነፍል ነው :እኔ ከማየውና ከማውቀው ነገር ተነስቼ አንድ ነገር ለማለት እደፍራለሁ :: አሁንም ወደፊትም ከቤተ ክህነት ሰዎች ማለትም ከድቁና እሰከ ጵጵስና ድረስ ባሉት አገልጋዮች በጎ ለውጥ ይመጣል ብዬ አልጠብቅም :: ሌላ ተአምር ካልተፈጠረ በስተቀር :: ነገር ግን ይችን ቤተ ክርስቲያን አሁን ካለችበት ቀውስ ለመታደግ የስንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምእመናን አንድ ነገር ምናልባትም አስከ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ተጋድሎን ለመፈጸም ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል ::አለበለዚያ ምናገባን እያልን የምንቅመጥ ከሆነ አስቸጋሪ ነው ::ደጀ ሰላም ይሁንም ማህበረ ቅዱሳንም ሌሎችም የቤተ ክርስቲያን ተቆርቅዋርዎች ጳጳሳትም ጭምር አውነትኞች አገልጋዮች ህብረት ፈጥራችሁ የደፈረሰው ጠርቶ አዲስ ታርክ መጀመር አለበት በምንም ይሁን በምን የተሰደዱት ፓትርያርክ ይመለሱና ምንበሩን የያዙ ዘመናቸው ለአስተዳደር ስለሚከብድ የአስተዳደር ስራው በንደራሴ ይያዝ :: አለበለዚያ ለቤተ ክርስቲያናችን መጪው ጊዜ ምናልባትም ከነበረው የከፋ አንዳይሆን እ ሰጋለሁ ::ደጀሰላም የእለት እለቱን ወሬ አንዲህ ማቀርብሸን ቀጥይ :: የቅዱሳን አምላክ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን ::

Unknown said...

Egziabher ye bete kerstianchenen yetebkelen Amen.

Unknown said...

Egziabher ye bete kerstianchenen yetebkelen Amen.

Anonymous said...

Abune Gorgorios bihonu des ylegnal. Sayachew abune mMelketsedikin silemimeslugn libe ydenegital. Bezalay endesmachew lihonu ychilalu. Mechem Egzer sewn simert sewn tetekimo new. Man yakal yhe hamet mimeslew hulu yeEgzer eji binorbetis! Zim bilo endakim menor yawatal. Lebotaw yemihonewn esu sewn tetekimo yhun dingayn maskemetu aykerm. Aynachinin kesew enansa. Egna tiru kehonin hulum tiru new. Tiru lalhone sew demo tiru neger keto yelem.

Anonymous said...

የኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን የአማራ ነው፤ "አማራን የምናጠቃው ከኦ/ተ/ቤ/ክ ውስጥ ነው።" እያለ የመጣው የትግራይ ጎሰኞች ኮሚኒስት ሰራዊት ይህን ሃይማኖት በፖለቲካ እንደከፈለው ከ ኤርትራ ጳጳስ ምርጫ አይተናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በቋንቋ፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በጋብቻ፣ በሃይማኖት፣በከርሰ ብድርና በፖለቲካ ሲከፋፈል በጎሳ ፓትርያርክም እንዲከፋፈል የፖለቲካ አጀንዳ ነበር። ይሁን እንጂ አቡነ ጳውሎስ በመመረጣቸው ምክንያት አጀንዳው ተዳፍኖ እንዲቆይ በፓርቲው ውሳኔ ተደርጎበታል። በምትኩ ብዙ ዘራቸው ከትግራይ የሆነና በሃይማኖቱ የተካኑ ሰዎች ስልጠና ተስጥቷቸው የፓትርያርኩንና የመንግስቱን ፍላጎት ለማስጠበቅ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንዲሸገሸጉ ተድርጓል። በመንግስትና በእነዚህ ሃይማኖተ ካድሬዎች መካከል ያለው ትምምን እንዲጠነክር ሲባለ "በእንተ ስለማረያም ለእመ አምላክ ብለው" ብሎ ማደር ቀርቶ ከዲቁና እስከ ጵጵስና በደሞዝ እንዲተዳደር የሚል ህግ ወጣ።
አሁን በተለያዩ ክፍለ ጎሳወችና አብያተ ክርስቲያናት ብቅ ብቅ ያሉት እነዚያ ሃይማኖተ ካድሬዎች ናቸው። ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊያውቀው ይገባል፤ እግዚአብሔር አውቆባቸዋል፤ ምስጋናና ክብር ለእርሱ ይሁን።

Anonymous said...

Whatever the case, I feel it will be better if the goverment can assign somebody for the patriarchal post. I say this because, the church (synod) lacks both capacity and experience, and there are many rival groups within the church, as stated in this news. Egziabher yirdan.

Solomon Berhe said...

ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅልን፤ ቅን ደገኛ አባት ይስጥልን፡፡

Anonymous said...

The government of Ethiopia wants to be God . It is up to God to select the right persons who deserves for the position. But this is not going to happen. Let us enumerate some of the things they did against us :
1. when they were guerilla fighters
as we all know they used to pretend as if they hide in churches and inform derg (intellegence) and derg used to bombard churches.( so that they will recruit more fighters from the angry Orthodox)
2. After they took power the first institution they want to control and destroy is Orthodox church. They were saying in public as the church is ye nefitegnas washa.
3. After controlling the church ( destroying the long standing canonical of the church ) they looted the church and the whole of the church offices are sized and manipulated by one ethnic group.
4. They send their cadres and supporters to Ethiopian Orthodox church in foreign country so that people should disagree and fight each other . Because of them we hate each other.
5. As we all know systematically they are burning ancient monasteries forests.
6. For their long standing goal of weakening and killing the national feeling of Ethiopian. The key place they should do alot of work is in Ethiopian Orthodox children.Because Ethiopia and Ethiopian orthodox church are two sides of a coin.
7.They are destroying Waldeba monastery , rounding monks and .....
Now we are talking about peace b/n church fathers, is the problem really b/n church fathers? We all want to see peace with out paying any price for it. But we can't have it. Our generation is not for peace whether we like it or not we all need to pay some price; no free lunch brothers and sisters not at all. If you do have the eye you can see , hear what is happening with Ethiopian muslims. Today for them when they are done with them they will bring some other religion and will force us to convert. I know everybody wants to see peace in the church but we can't have it unless in some way this peoples are gone. Now comes again.

Anonymous said...

በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከላይ እስከ ታች ስር የሰደደው ዘረኛነት፣ ሙስና፣ አድላዊነትና የግብረ ገብነት ንቅዘት ወደ ቤተ ክርስቲያኗም ሰርጎ መግባቱ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሰጋ ጉዳይ ነው። አባቶች በዘረኛነት፣ በአድላዊነትና በሥልጣን ሽሚያ መንፈሳቸው ተጠምዶ ለፍትሕ፣ ለሚዛናዊነት፣ ለታማኝነትና ለአገልግሎት ቅድሚያ ካልሰጡ የቤተ ክርስቲያኗን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ሥርዓትና አንድነት እንዴት ሊጠብቁና ሕዝበ ክርስቲያኑን ሊመሩ ይችላሉ? ምእመናንስ የቱን የአባቶች አርአያነት ዓይተውና አምነዋቸው ነው ጠባቂ እረኛችን ብለው የሚከተሏቸው?
ሃያ ዓመት ሙሉ ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሰቃየው ከፋፋይነት በፍጥነት መገታት አለበት። ለዚህም ዘዴው ግልጽ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አባቶች ራሳቸው ክብርና ገበናቸውን ጥብቀው በጽሞና እየጸለዩና እየተወያዩ ጊዜው ሳይመሽ አቋማቸውን ሊያስተካክሉና የቤተ ክርስቲያኗን ደኅንነት ተግተው በጋራ ሊጠብቁ ይገባል። በዘርና በጎጥ ላይ የተመሠረተ የሥልጣን ሽሚያ አያዋጣም። በእግዚአብሔርና በምእመናን ዘንድም ተቀባይነት አይኖረውም።
እንደ ዘመነ አቡነ ጳውሎስ ዛሬም አባቶች በስሕተት ጎዳና እንዳይራመዱ ለመርዳትና ቤተ ክርስቲያኗን ለመጠበቅ እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም የምእመናን ሚና ወሳኝ ነው። ስለዚህ ምእመናን በድጋሚ ሊደርስ የሚችለውን አደጋና ትክክሉን ወቅታዊ ሁኔታ ተረድተው ግዴታቸውን እንዲወጡና ተገቢውን ግፊት እንዲያደርጉ ሰፊ ቅስቀሳና ማደራጀት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የምእመናኑን ዕውቀት ለማዳበርና ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ማኅበረ ቅዱሳንና ብዙ የቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ድርጅቶች እንዲሁም አንዳንድ የመገናኛ ብዙሐን በማበርከት ላይ ያሉት አስተዋጽ የሚደነቅና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው።
ይህም የማስተማሩና ሐቁን ለሕዝበ ክርስቲያኑ የማስጨበጡ በጎ ተግባር ከኢትዮጵያም ውጪ ሊዳረስ ይገባል። በሰደቱ ዓለም የሚኖሩ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ምእመናን ችሎታው፣ ሀብቱና ፍላጎቱ እያላቸው በደረሰባቸው የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ ምክንያት ላለፉት ሃያ ዓመታት ለእናት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ጥንካሬ የሚገባቸውን ያህል ለማበርከት ሳይታደሉ ቆይተዋል። ዛሬ እነዚህ ብቃት ያላቸው ምእመናን እየተውያዩ ኅብረታቸውን በማጠንከር ኢትዮጵያ ካሉት በብዙ ሚሊዮን ከሚቆጠሩት ወገኖቻቸው ጋር የሚያገናነውን ድልድይ በማጠናከር የቤተ ክርስቲያኗን ሕግጋት፣ ሥርዓትና አንድነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ከምን ጊዜውም ይበልጥ መሥራት አለባቸው። ለዚህም በሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶሶች መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ዕርቀ ሰላም በአስቸኳይ መቋጨት አማራጭ እንደሌለው እሙን ነው።

Anonymous said...

ሰው የሚያደርገውን አውቆ የማይሰራበት ጊዜ፡፡ አይደልም በመንፈሳዊ በየትኛውም አለማዊ መስፈርት ከዚ ግባ የማይባል አሳፋሪ፣አዋራጅ፣እጂግ በጣም የወረዳ አስተሳሰብ እንዴት የሃይማኖት አባት ለመምረጥ መስፈቱ ጎጥ፣ጎሳ እና የፓለቲካ ዝምድና ይሆናል፡፡ለዚያውም የኛ ቤተክርስትያን በስንት ፈተና ተከባና ውስጥ ድህነቱ፣የአክራሪቹ ፣ ሙስናው፣ተሀድሶ፣ጎጠኝነቱ፣ዜጎች በየአገሩ ተበትነው ቁም ስቅል እያዩ ሴትን ያህል ልጅ ወንዝ፣በረሃ፣ድንበር፣ባህር ወቁያኖስ ተሻግረው አቆረጠው ቤበት ግርድና የመከራ ኑሮ እየገፉ እየተደበደቡ እየተገደሉ እየሰማን እያየን ምነው ይህ ውርደታችን አልሰማን፣ አለንገበግበን አለ? ምነው የክብራችን መነካት አልሰማን አለ? ምን ጉዱ ነው! እንዴት ነው ሰው የሚያስበው ከሁሉም ብሄር የእመነቱ ተከታይ ባለበት አገር፣ክርስቲያኖችን ሁሉ እኩል ናቸው ብላ በምታስተምር ቤተክርስትያን፤ ህዝቡ (ኦሮሞው፣አማራው፣ ትግሬው፣ ደቡቡ (ጋሞ፣ወላይታ፣ጉራጌ፣ሲዳማ፣ሀድያ ወዘተ…)፣ጋምቤላው፣ቤንሻጉሉ) እኮ በስለት፣በእርዳታ፣በአስራት፣በኩራት፣በመዋጮ በልዩ ልዩ ገቢ ለቤተክርስትያን አገልግሎት ገንዘብ የሚለግሰው ትክክለኛ አገልግሎት በማግኘት ነፍስ እና ስጋውን ለማዳን እንጂ በጎጠኝነት ተደራጅታችሁ እንደፈለገ ልትሁኑበት አይደለም፡፡ ጎጠኝነትን ጎሳን ማዕከል አድርጎ ጳጳስ ለመምረጥ መታገል እስኪምን የሚሎት ስሌት ነው፡፡አሁንስ ለብዙ ጌዜ እቃወመው የነበረው የኢትዮጲያውያን IQ ትንሽ ነው የሚለው እወነት መሆን አለበት፡፡መቼ ይሆን አሳፈሪ፣እራየ ቢስ፣ እና የአስተሳሰብ ድህነት ከአለባቸው ሰዎች ቤተክርስትያን ነፃ የምትወጣው? አቅም ችሎታ የለው መሪ አጠን በድህነት፣በስደት ከአለም መዘባበቻ ሆነናል፡፡ እስኪምን እስክንሆን ይሆን አሁን ለሹመቱ እንደመስፈት እውቀት፣በሳል የአመራር ቾሎታን፣ መንፈሳዊነት እና ጎሰኛ/ጎጠኛ አለመሆን መስፈርት የማናደርገው፡፡ ከቤተመንግስቱ በባሰ ሆኔታ ቤተክህነቱ የጎጥና ጎሳ በሽታ የተመታ ሆኖአል አጅግ አሳፋሪ፡፡እወነተኛ አባቶች የሰንበት ተማሪዎች ምእመኖች ከምንም በላይ ራሳችን ስለእወነት ለመጋዳል የምናአዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ነገር ግን እግዚአብሔር ቀድሞ እንዲያስተካክልልን አብዝተን ልንፀልይ ይገባናል፡፡ደጀ ሰላሞች እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ

Anonymous said...

Oh getahoy bekachihu belen yekir belen please lets pray people. But God knows what to do we don't .he has a reason for everything that's why he took the other patrialic tomorrow gonna be a better day lets be one lets love he is with us lets pray.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)