October 5, 2012

የድሬዳዋ ሳባ ደ/ኀ/ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ


  • የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀ/ስብከታቸውን እንቅስቃሴ በቅርበት ተገኝተው ለመከታተል ባለመቻላቸው ምእመናኑ መራራ አቤቱታ አቀረቡባቸው፣ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ብፁዕነታቸውን ለጥያቄ ጠርቷል፤
  • አስተዳዳሪውና የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ከሓላፊነታቸው እንዲወገዱ ተጠይቋል፤
  • ቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ እንደሚያሳልፍበት ይጠበቃል፤

(ደጀ ሰላም፤ መስከረም 24/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 5/2012/ READ IN PDF):- የድሬዳዋ ሳባ ደ/ኃ/ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ያለውን ውዝግብ በዝርዝር ከማቅረባችን በፊት በዚህ ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ የሚነሣውንና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና ለበርካታ ዓመታት የፓትርያርኩ መጋቤ ሥርዐት (የፕሮቶኮል ሹም) ኾነው የሠሩትን መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ በቀለን እናስተዋውቃችሁ።


መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ በቀለ ከአቡነ ጳውሎስ ቤተ ዘመዶች አንዱና በኅልፈታቸው ወቅትም በአጠገባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ በፓትርያርኩ ዕለታዊ የሥራ መርሐ ግብር ቀጠሮዎችን መያዝ፣ እንግዶቻቸውን መቀበልና የጉብኝት ፕሮግራሞቻቸውን ማመቻቸት ዋነኛ ተግባሮቻቸው ነበሩ፡፡ መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታን የሚቀርቧቸው ሰዎች የፕሮቶኮል ሹሙ ለሰዎች ያላቸውን ሐዘኔታና አክብሮት በአዎንታዊነት ይጠቅሱላቸዋል፤ ሌሎች ብዙዎችም ከአህጉረ ስብከትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ጀምሮ እስከ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት ድረስ ተዘርግቶ በነበረው የጥቅም ሰንሰለት ውስጥ እጅ መንሻን በማቀባበል በአያሌው መጠቀማቸውን፣ ከቤተ ክህነቱ የኪራይ ቤቶች የንግድም የመኖሪያ ቤቶችንም በባለቤትነት መያዛቸውን ይዘረዝራሉ፡፡ መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ የአቡነ ጳውሎስን ዘመነ ፕትርክና በተሻገረው በዚሁ ተግባራቸው ሙስናንና ሙሰኞችን በማጋለጥ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ከዘረፋና ብኵንነት ለማዳን በሚደረጉ የቀናዒ አገልጋዮች እና ምእመናን ጥረቶች ላይ አፍራሽ ሚና ለመጫወትና ያልተገባ ተጽዕኖ ለመፍጠር እየተሯሯጡ መኾኑ ተዘግቧል፡፡

የቀድሞው ፓትርያርክ መጋቤ ሥርዐት የነበሩት ሙሉጌታ በቀለ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በኋላ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በበላይ ሓላፊነት የሚመሩት የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት ምክትል ሓላፊ ኾነዋል፡፡ በዚህ ሓላፊነታቸው የድሬዳዋ ሀገረ ስብከትንም በሊቀ ጵጵስና ከሚመሩት ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጋራ÷ በተለይም ከድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ ጋራ በተያያዘ÷ ቀድሞም የነበራቸውን ግንኙነት ለማጥበቅ አስችሏቸዋል፡፡ ሪል ከተባለ የሕንጻ ሥራ ተቋራጭ ጋራ በ2,984,562.51 የውለታ ገንዘብ መጠን በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ዕቅድ የተያዘለት የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ በ1998 ዓ.ም ወርኀ ጥቅምት የተጀመረ ቢኾንም ከውጥኑ አንሥቶ ከውለታው ውጭ የይገባኛል ጥያቄዎችን በማንሣት፣ ከሥራ ተቋራጭ የሚጠበቀው የውል ግዴታ ሳይፈጸም ግንባታው በመጓተቱ ቤተ ክርስቲያንን ለከፍተኛ የሀብት ብክነትና ዘረፋ አጋልጧት ይገኛል፡፡

ከነሐሴ ወር 2002 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞው ፓትርያርክ ትእዛዝ በጉዳዩ እጃቸውን ያስገቡት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ‹ተቆጣጣሪ› መሐንዲስ አቶ ሰሎሞን ካሳዬ÷ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴውን በብቸኝነት ከሚመሩት ከአቶ ብርሃኔ መሐሪና የኮሚቴው ጸሐፊከ አቶ ሲሳይ ጸጋዬ፤ ያለ ሰበካ ጉባኤው ይኹንታ በብቸኝነት እየወሰኑ ክፍያ ከሚያጸድቁት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ኀይል አባ ገብረ ሥላሴ ቸኮል ጋራ በጥቅም በመተቃቀፍ በሚሰጡት ሽፋን ከውለታ ጊዜው ውጭ ከአምስት ዓመታት በላይ ያለበቂ ምክንያት ለዘገየ ሥራ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለሪል የሕንጻ ሥራ ተቋራጭ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ እንዲከፈል ተደርጓል፡፡ የሥራው መጓተት በግንባታ ዕቃዎች ዋጋ አተካከል ላይ የሚፈጥረውን ከፍተኛ ልዩነት ምቹ አጋጣሚ ያደረጉት የሕንጻ ሥራ ኮሚቴውና ተቋራጩ÷ የዋጋ ግሽበት የሚመለከታቸውን ዋና ዋና ግብዓቶች /ሲሚንቶ፣ ብረትና ነዳጅ/ ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ ነጠላ ዋጋ ማሻሻያ ጥያቄ በማቅረብ ጠቅላላ ወጪው ቀደም ሲል በውለታ ጊዜው ከተጠቀሰው ብር 2,984,562.51 ወደ ብር 8,566,899.25 እንዲያሻቅብ ምክንያት ኾኗል፡፡

ይህም ኾኖ ዲዛየኑ በሐዋሳ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አምሳል እንዲሠራ የታቀደው የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አሁን የሚገኝበት የአጨራረስ ጥራት ተገቢው የምሕንድስና ቁጥጥርና እርምት እንዳልተደረገለት ባለሞያዎች እየተናገሩ ነው፡፡ የሕንጻ ሥራው ለሚታይበት የአጨራረስ ጥራት ጉድለት ስፋቱና ቁመቱ ተካክሎና ተመጣጥኖ ካለመሠራቱ የተነሣ ገጽታው የተቀበረ መስሎ የሚታየው የሕንጻው ጉልላት እንዲሁም የዝናም ውኃ የሚወገድበት የፍሳሽ መዋቅሩ ችግር እንዳለበት በክረምቱ የተረጋገጠ መኾኑን በአስረጅነት አቅርበዋል፡፡ ለዚህም በቀዳሚነት ተጠያቂ የተደረጉት በሁሉም የምሕንድስና ዘርፎች ራሳቸውን ብቸኛ አረጋጋጭ ያደረጉት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ ሰሎሞን ካሳዬ፣ ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ አንቀጽ 29 በተፃራሪ ለሰበካ ጉባኤው ባለመታዘዝ ራሳቸውን ለፓትርያርኩ መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ በቀለ ተጠሪ ያደረጉት ሙሰኛው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኔ መሐሪ፣ ከአንድም ሁለት ጊዜ በካህናትና ምእመናን አንድነት የተመረጠውን ሰበካ ጉባኤ የሃይማኖታቸው ርቱዕነት ከሚያጠራጥረው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አባ አረጋዊ ነሞምሳ ጋራ በመመሳጠር ያገዱት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አባ ገብረ ሥላሴ ቸኮል ናቸው፡፡

የደብሩ አስተዳዳሪና የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በዐውደ ምሕረት ምእመኑን “ደንቆሮና አድመኛ” ብለው በግልጽ መሳዳቸባቸው ሳይበቃ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ስም የሚፈጸመውን የገንዘብና ንብረት ዘረፋና ብኵንነት የተቃወሙ የደብሩን አገልጋዮች ከደረጃቸው ዝቅ በማድረግ ወደ ሌላ ደብር አዘዋውረዋል፤ ከደመወዝና ሥራ ታግደው የተቀመጡ የደብሩ የመጽሐፍ መምህርም አሉ፡፡ በዚህም ራሳቸውን በመንግሥት ተወካይነት ያስቀመጡት የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኔ መሐሪ ተባባሪ ሲኾኑ እርሳቸው በሚስቡላቸው ሙክት ሕዝባዊ አደራቸውን የዘነጉ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ለምእመናኑ አቤቱታ ምላሽ ለመስጠት አለመቻላቸው ተዘግቧል፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ሙስናውንና ሙሰኞቹን የተቃወሙ ሁለት የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴውና ሦስት የደብሩ ሰንበት ት/ቤት አባላት በተለያዩ ጊዜዎች ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት እየታሰሩ መፈታታቸው ነው፤ ለመታሰራቸው በሽፋንነት የቀረበውም “በመለስና በፓትርያርኩ ሞት ተደስተዋል” የሚል አሉባልታ እንደነበረም ተገልጧል፡፡

በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤትና በከተማው አስተዳደር ደረጃ መፍትሔ ያጡት የአጥቢያው ምእመናን መስከረም 21 ቀን 2005 ዓ.ም ስድስት ተወካዮቻቸውን ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ልከዋል፡፡ ተወካዮቹ ከነማስረጃው በ40 ገጽ የተጠናቀረ አቤቱታቸውን በአድራሻ ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ሲያቀርቡ ግልባጭ ከተደረገላቸው አንዱ ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ መኾናቸው የጉዳዩን ተከታታዮች እምብዛም ያስገረመ አይመስልም፡፡ ብፁዕነታቸው የቀድሞውን ፓትርያርክ ተከትለው በዓመት ሁለት ጊዜ ለቁሉቢ ክብረ በዓል ሲወርዱ ካልኾነ በቀር በሀገረ ስብከታቸው እንደማይገኙና እንቅስቃሴውንም በቅርበት የማይከታተሉ ከመኾኑም በላይ÷ የሕንፃው አሠራርና የግንባታ ወጪው ምእመኑ በመረጣቸው ባለሞያዎች እንዲጣራ፣ የደብሩ አስተዳዳሪና ጸሐፊ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡና በየመድረኩ ምእመኑን ከመሳደብ እንዲቆጠቡ፣ የሕንጻ አሠሪው ኮሚቴ ሕዝቡ በመረጣቸው ሌሎች አባላት በአስቸኳይ ተተክቶ የሕንጻ ሥራው እንዲጠናቀቅ መመሪያ እንዲሰጡ ከአንድ ዓመት በፊት (በ22/03/2004 ዓ.ም) በሕዝቡ የአቤቱታ ፊርማ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ አልነበረም፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቁጥጥር አገልግሎት ባለፈው ዓመት በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ላይ ያካሄደውን ኦዲትና ያገኘው የ 1.8 ሚልዮን ብር ወጪ ጉድለት ተከትሎ ሊቀ ጳጳሱ የደብሩ አስተዳዳሪ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ ደብዳቤ ጽፈው ነበር ቢባልም መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ ከእነብርሃኔ መሐሪ ጋራ በፈጠሩት ግንኙነት ታፍኖ ሳይላክና ሳይፈጸም መቅረቱ ነው የተነገረው፡፡

በስምንት ብፁዓን አባቶች እንዲጠናከር የተደረገው ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ትናንት ባካሄደው መደበኛ ሳምንታዊ ስብሰባው በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ተወካዮች የቀረበውንና በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ የተመራለትን ጥያቄ እንደተወያየበት ተዘግቧል፡፡ ምእመናኑ በጥያቄያቸው ካካተቷቸው ነጥቦች ውስጥ÷ የደብሩ አስተዳዳሪና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፣ የሕንጻ ሥራው ሒሳብ ተመርምሮ በተገኘው ጉድለት ላይ ሓላፊነት የሚወስዱት ተለይተው ርምጃ እንዲወድባቸው፣ የሕንጻ ግንባታው ምእመኑ በመረጣቸው ባለሞያዎች ተገምግሞ ሪፖርት እንዲቀርብላቸው፣ የሕንጻ ሥራው በአስቸኳይ እንዲቋጭ ትእዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ በሀገረ ስብከቱ ተገኝቶ በቅርበት የሚከታተላቸው አባት እንዲሾምላቸው የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡ ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በሀ/ስብከታቸው አዘውትረው ስለማይገኙበት ኹኔታና የተባባሰው ችግር እልባት ያላገኘበትን ምክንያት በተመለከተ እንዲሁም የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቁጥጥር አገልግሎቱ በደብሩ የሕንጻ ግንባታ ላይ አቅርቦት በነበረው ሪፖርት መሠረት ምን ርምጃ እንደወሰደ በዛሬው ዕለት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ መጥራቱ ተዘግቧል፡፡

እነ መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታና የብፁዕ አቡነ ገሪማ ቢሮ ሠራተኞች በፈንታቸው ለብፁዕነታቸው በግልባጭ የደረሳቸውን የምእመናን አቤቱታ ጥያቄ ለቀረበባቸው የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢና ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ፋክስ አድርገውላቸዋል፡፡ ከዜናው ጋራ ተያይዞ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ሥራ አስኪያጁ የደብሩን ካህናት “መኖር የምትችሉት እኛ ስንኖር ነው” እያሉ ከንስሐ ልጆቻቸው “ወደ አዲስ አበባ የሄዱት ተወካዮች አይወክሉንም” የሚል የአቤቱታ ፊርማ እንዲያሰባስቡ በማስገደድ ከቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ በፊት ለመላክ በመሯሯጥ ላይ እንደነበሩ ተሰምቷል፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታ የሕንጻ አሠሪው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኔ መሐሪ የሰንበት ት/ቤቱን አመራር በመሰብሰብ “ተሳስተናል፤ መፍትሔ የሚያፈላልግ ኮሚቴ እናቋቁም” ቢሉም ተቀባይነት አለማግኘታቸው ታውቋል፡፡ አቶ ብርሃኔ ግን ካልተሳካው ሙከራቸው በኋላ ከአዳራሽ እንደወጡ ለመጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ ስልክ በመደወል ሲሉ የተሰሙት ነገር ቢኖር “እርሱ ጋራ ያሉት ሕዝብ ያልወከላቸው ስድስት ሰዎች ናቸው” የሚል እንደ ነበር ተነግሯል፤ መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታም ወደ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ቢሮ ገባ ወጣ ማለቱን፣ በር ዘግቶ መምከሩን አብዝተዋል፡፡

ታሪክን ታሪክ ያነሳዋልና ፓውሎ ጋብርኤሌ የተባለ የካቶሊኩ ፓፓ ረዳት ታሪክ እንትመለከቱ እንጋብዛችሁ። ሰሞኑን ከወደ ቫቲካን እንደተሰማው የካቶሊኩ ፖፕ ሊቀ ረዳእያን (butler) ፓውሎ ጋብርኤሌ በከፍተኛ የስርቆት ወንጀል ተከስሶ ፍ/ቤት ቀርቧል፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት የፖፕ ቤኔዲክት ዋና አሳላፊና ረድእ የነበረው ፓውሎ ጋብርኤሌ የተከሰሰው የፖፑን የግል የመልእክት ልውውጦችና ሌሎች ምስጢራዊ ሰነዶች ለአንድ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ አሳልፎ ሰጥቷል በሚል ነው፡፡

ሊቀ ረዳእያን ፓውሎ በምርመራ ወቅት ለቫቲካን ፖሊስ በሰጠው የተከሳሽነት ቃል÷ ድርጊቱን የፈጸመው “በመንፈስ ቅዱስ ተነሣስቶ” መኾኑንና ፍላጎቱም “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሰፈነውን ክፋትና ሙስና በማጋለጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ ትክክለኛ መንገዷ እንድትመለስ” በመሻት መኾኑ ጉዳዩን በያዙት ዐቃብያነ ሕግ በኩል ተገልጧል፡፡ የራስዋ የክብር ዘብ፣ የጸጥታ ኀይል፣ የፍትሕ ሥርዐት ያላትና በዓለም ትንሽዋና ልዑላዊት አገር ቫቲካን÷ መንግሥት(City State) ካቆመችበት እ.አ.አ ከ1929 ወዲህ በጥብቅ ምስጢራዊነት የሚታወቀውን የፖፑን እልፍኝ ውስጣዊ አሠራሮች በመከሠት በኩል ፍንጭ እንደሚሰጥ የተመለከተውን ይህንኑ ክስ ሊቀ ረዳእያኑ ማስተባበል ካልቻለ እስከ አራት ዓመት እስር እንደሚጠብቀው ተዘግቧል፡፡

ከፓውሎ ጋብርኤሌ ጋራ በፖፑ ቢሮ የሚሠራ ሌላ የኮምፒዩተር ባለሞያ በወንጀል ድርጊት ተባባሪነት እንደሚጠየቅ የተነገረ ቢኾንም ፖፕ ቤኔዲክት 16 ለክሱ ይቅርታ እንደሚያደርጉ እየተጠበቀ ነው፡፡ ፖፑ እስከ አሁን ለይቅርታው መዘግየታቸውና ጉዳዩም ባልተለመደ ኹኔታ በግልጽ ችሎት እንዲታይ መፈቀዱ በጥብቅ ምስጢራዊነቱ የሚታወቀው የፖፑ መንበር በቅርቡ የፋይናንስ ተቋሞቹን ለውጭ አካላት ምርመራ ክፍት በማድረግ በጀመረው ግልጽነትን የማስፈን አሠራር ለመቀጠል መበረታታቱን እንደሚያሳይ የቫቲካኑ አፈ ፖፕ ለዜና ሰዎች ተናግረዋል፡፡

ሊቀ ረዳእያን (butler) ፓውሎ ጋብርኤሌ ለጣሊያናዊ ጋዜጠኛ ያሾለካቸውና የብዙዎችን ቀልብ የሳቡት ምስጢራዊ ሰነዶች ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር “His Holiness: The secret papers of Pope Benedict XVI” በሚል ርእስ መጽሐፍ ተጽፎባቸው ለገበያ ውለዋል፡፡ የ46 ዓመት ጎልማሳ፣ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የኾነው የፖፑ ቀራቢና ቤተሰብ ፓውሎ ጋብርኤሌ ድርጊት የደኅንነት ተግባሩን የዘነጋና የደኅንነት ግዴታዎችን የጣሰ (security breach) መኾኑ ቢገለጽም በውስጥ ሽኩቻዎችና ሐሜቶች ላይ ያተኮሩት መረጃዎች ይፋ መውጣታቸው እርሱ እንደተናገረው ቤተ ክርስቲያኒቱን “በትክክለኛው መንገድ ላይ” መልሶ ያቆማት እንደኾን ወደፊት እናየዋለን፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡  

8 comments:

Anonymous said...

በነካ እጃችሁ ቀጥሉበት በሙሉጌታና በብጽዕ አቡነ ገሪማ በቤተ ክርስቲያኗ የተፈጸመውና እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲህ በቀላሉ አያልቅም።እባካችሁ ደጀ ሰላሞች ፈልፍላችሁ አውጡት።ያኔ ሰላሞች መሆናችሁ ይረጋገጣል።ቤተ ክህነቱን ሰላም ያሳጡት በዋናነት ከፓትርያርኩ ጋር እኒህ ሁለት ሰዎች ናቸውና በርቱ

Anonymous said...

በነካ እጃችሁ ቀጥሉበት በሙሉጌታና በብጽዕ አቡነ ገሪማ በቤተ ክርስቲያኗ የተፈጸመውና እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲህ በቀላሉ አያልቅም።እባካችሁ ደጀ ሰላሞች ፈልፍላችሁ አውጡት።ያኔ ሰላሞች መሆናችሁ ይረጋገጣል።ቤተ ክህነቱን ሰላም ያሳጡት በዋናነት ከፓትርያርኩ ጋር እኒህ ሁለት ሰዎች ናቸውና በርቱ

Anonymous said...

Dear almighty God, please continue to clean the mess in our church! Please never stop to reveal Your miracles. There are many money lovers pops, priests, deacons and others in our church, sadly in Your name. Even if some pops who claim they are shepherds of the meamenan they built buildings, collected cash for themselves; ignoring the innocent servants of God. They never satisfy. Please clean them. They are the real obstacles of our unity and peace. Please continue to clean anti-peace, power lovers, money lovers, and all of the evil doers who mask themselves as popes, priests, deacons and others. Please God, how long we cry, suffer to get your justice once and forever???????????????????????????? Please remember all of Your saints and martyrs who gave their life for Your almighty’s name sake. Please remember them and do us favor to cleanse Your church for once and all. I believe you do it! Please do it soon!

Gebre from Etisa T/Haymanot

Anonymous said...

በዚህ መንገድ የማጣራት ሥራ ከተሠራ ነፃ የሆኑ አበውን ማግኘት የምንችል አይመስለኝም:: በዚወቅት እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች ማንሳት ልብን ለማክፋት ካልሆነ ለምንም አይጠቅምም:: ቤተ ክርስቲያን አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ በምትሰራበት ወቅት ብጹእነታቸው የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው አንዘንጋ ለምርጫም ቀበው የማይሆኑበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም:: እንደዚህ አይነት ሥራዎች የሉም ማለት ባያስደፍርም ባስፈላጊ ወቅት ሆን ተብለው የሚገኑ ይመስላሉ:: ከዚህ በኋላም ጥንቃቄ እንደምታደርጉ እገምታለሁ:: ግለሰቡም ቢሆን ይህን ዓይነት ዘመቻን እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል መገመት ነበረባችሁ:: ድሬዎች እስካሁን ያስታመሙትን ጉዳይ ለአንዲት ቤተክርስቲያን ሰላም ሲሉ /ለምጣዱ ሲባል/ እንደሚታገሱ እገምታለሁ:: ጊዜው አይደለም::

Unknown said...

ከላይ እውነት እንዳይገለጥ ተቃውሞ ያቀረብከው/ሺው ወገን ታዲያ መቸ ነው እውነት መነገር ያለበት ? እውነት በመነገሩ ፥ እውነት በመመስከሩ የማይደሰቱ አበው ካሉ አበው ሊባሉ የሚችሉት በምን መመዘኛ ነው ? ወንጌሉ እውነት እንዲደበቅ ይፍቅዳል ወይስ " ኢትፍርህዎሙኬ እንከ፥ እስመ አልቦ ክዱን ዘኢይትከሠት ወኅቡዕ ዘኢይታዐወቅ። ዘነገርኩክሙ በጽልመት ንግርዎ በብርሃን ! ወዘኒ ውስተ እዝንክሙ ነገርኩክሙ ስብክዎ በዲበ አንሕስት ! ወኢትፍርሕዎሙ ለእል ይቀትሉ ሥጋክሙ ፥ ወንብስክሙሰ ኢይክሉ ቀቲለ ። ወባሕቱ ፍርህዎ ለዘይክል ነብሰ ወሥጋ ኅቡረ አሕጉሎ በውስተ ገሃነም።" (ማቴ.10፣26-29)ይላል ? የአማርኛው ትርጉምም ይህን ይመስላል=እንግዲህ ሰዎችን አትፍሩ ፣ ምክንያቱም የተሸፈነ መገለጡ ፥ የተሰወረም መታወቁ አይቀርም። ስለዚህ እኔ በጨለማ የምነግራችሁን እናንተ በብርሃን ተናገሩት ፣ በሹክሹክታ የሰማችሁትንም በሰገነት ላይ ከፍ ብላችሁ ተናገሩ፥ በይፋ አስተምሩ ። ሥጋን ከመግደል አልፈው ነብስን መግደል የማይችሉትን ወይም የማይቻላቸውን ሰዎች አትፍሩ !ይልቁንስ ነብስንና ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን አምላክ ፍሩ። ነው የሚለው። ጥያቄው መሆን ያለብት ነገሩ እውነት ነው ወይ? ነው እንጅ እውነትን አትንገሩ ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ ''ከተሠራ ነፃ የሆኑ አበውን ማግኘት ''ስለማንችል የሚለው አምክንዮ ትልቅ ስህተት ነው። ሰማዕተ ሐሰትን እንጅ ሰማዕተ ጽድቅንማ ማበረታታት ነው ያለብን ። ምክንያቱም በዚህ ዘመን ያጣነው ሰማዕተ ጽድቅን (የእውነት መስካሪዎችን) ስለሆነ ነው ችግሮቻችን ሁሉ በውሸት ጨለማ ውስጥ ሁነው በእውነት መነፀር ማየት አቅቶን እውር ድንብሳችንን እየተጓዝን ያለነው። አስተያየት ሰጩ እውነቱ እንዳይነገር ያቀርቡት ምክንያት ደግሞ እጅግ የሚያስደንቅ ነው ፣ "ቤተ ክርስቲያን አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ በምትሰራበት ወቅት በጹነታቸው የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው አንዘንጋ ለምርጫም ቀርበው የማይሆኑበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም።" ይላሉ። ለእውነት ሳይሆን ለግለሰቡ ነው የወገኑት እንጅ ፍሬ ነገሩ እውነት አይደለም ከሚል አይደለም ። የቀረበው ዘገባ በእውነት ላይ የተመሠረተ አይደለም ከሚል ቢሆን ኑሮ ተቃውሞው ፥ የውሸት ተቃራኒ የሆነውን እውነቱን በማስረጃ ቢቀርብ ኑሮ ልንቀበለው እንችል ነበር። ግን በዚህ ፋንታ እውነትን ለግለሰቡ ስንል እንድንሰዋው ነው እመከሩን ያሉት። በአለፉት 20 ዓመታት አቡነ ገሪማ በቤተ ክርስቲያናችን ክፍፍል የተጫወቱትን ሚና ሁላችንም እናውቃለን። ስለዚህ እኔ የምለው ወንጌሉ የሚፈቅደውን እውነቱን እንመስክር ባይ ነኝ ።

Anonymous said...

Anonymous said...
በዚህ መንገድ የማጣራት ሥራ ከተሠራ ነፃ የሆኑ አበውን ማግኘት የምንችል አይመስለኝም:: በዚወቅት እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች ማንሳት ልብን ለማክፋት ካልሆነ ለምንም አይጠቅምም:: ቤተ ክርስቲያን አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ በምትሰራበት ወቅት ብጹእነታቸው የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው አንዘንጋ ለምርጫም ቀበው የማይሆኑበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም:: እንደዚህ አይነት ሥራዎች የሉም ማለት ባያስደፍርም ባስፈላጊ ወቅት ሆን ተብለው የሚገኑ ይመስላሉ:: ከዚህ በኋላም ጥንቃቄ እንደምታደርጉ እገምታለሁ:: ግለሰቡም ቢሆን ይህን ዓይነት ዘመቻን እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል መገመት ነበረባችሁ:: ድሬዎች እስካሁን ያስታመሙትን ጉዳይ ለአንዲት ቤተክርስቲያን ሰላም ሲሉ /ለምጣዱ ሲባል/ እንደሚታገሱ እገምታለሁ:: ጊዜው አይደለም::

October 6, 2012 12:43 AM
yehenene yetenagerekewe yema menafeqe nehe manewe yelakehe ezawe adarashe headehe chefere leba

Anonymous said...

I like Gebre's comment.Deje Selam, why don't you post lists of pops who abuse thier power to buy or construct villa houses in Addis and eleswhere in the country before the wrong pops jumps in the unity and election of the new patrirarh process. yabetewen afendut.Eske meche negerochen eyastamemen lezelalem sinazenena sinrebesh enenoralen? Yedefresena yitra.

Aregawit said...

Egizabehren yemtasazenu sowche ebakacheu kome belachu asebu hulume negere yalfale menale yemayelefe seraa sertachehu Egziabeherenme sewonme erasachunme betasdesetu. Yekerstiane menoryawoe besmaye enji bemdre aydelem zelalemawewne mengeste lemgante zare nowe kenu.Lehulacheneme yemastwele lebona yestene. Amen

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)