October 24, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባጸደቃቸው በ20 አጀንዳዎች ላይ እየተወያየ ነው


  • ዕርቀ ሰላሙ የምልአተ ጉባኤው ግንባር ቀደም አጀንዳ ነው::
  • በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ማሻሻያ ላይ የሚሠራ ኮሚቴ ተቋቁሟል::
  • ንቡረእድ ኤልያስ ኣብርሃ ከሓላፊነታቸው ሊነሡ ይችላሉ::
  • በአቡነ ጳውሎስ ዕረፍት የታሸገው መንበረ ፓትርያርክ ጉዳይ ውሳኔ ያገኛል::

(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 14/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 24/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ጠዋት የተጀመረው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ 20 የመወያያ አጀንዳዎችን በማጽደቅ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ነው፡፡


መግባባት በተመላበት መንፈስ እየተካሄደ የሚገኘውና በአጭር ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው ይኸው የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በሁለቱ ቀናት ውሎው ከአምስት በላይ አጀንዳዎች የተመለከተ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡ የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት “ሰላምን በተመለከተ” እና “ሕገጋትን በተመለከተ” በሚል የዕርቀ ሰላሙን ሂደት፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ማሻሻልና የቃለ ዐዋዲው የማሻሻያ ሂደት የሚገመግምበት ኹኔታ በመነጋገሪያነት ከተቀረጹት አጀንዳዎች ዋነኞቹ ሲኾኑ “የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ማውጣት” በሚል ቀጣዩን ፓትርያርክ ስለመምረጥ የተመለከተው አጀንዳ ደግሞ በመጨረሻው ተራ ቁጥር ገደማ ከተያዙት ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል፡፡ ከእኒህም ጋራ “የዐቃቤ መንበሩን መተዳደርያ ሕግ ማውጣት” በሚል የተያዘ አጀንዳ መኖሩን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ÷ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን በዕቅድ ከመምራት፤ ለዕቅዱ አፈጻጸም ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዐትን ከመዘርጋት፣ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን፣ ከሀብትና ንብረት አጠቃቀምና የቀጣይ ፓትርያርክ ምርጫ ጥያቄዎች አንጻር መሻሻል እንደሚያስፈልገው ከጋራ መግባባት ላይ የደረሰው ምልአተ ጉባኤው÷ “የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደርን በተመለከተ”፤ “ዓመታዊ በጀትን በተመለከተ”፤ “የወደፊት ዕቅድን በተመለከተ”፤ “የሀብትና ንብረት አጠባበቅን በተመለከተ”፤ “ቁልቢ ገብርኤልን በተመለከተ” የተሰኙ ዝርዝሮችን በመነጋገሪያ አጀንዳነት መያዙ ተዘግቧል፡፡

ፕ/ር ጥላሁን
ለሕገ ቤተ ክርስቲያን መሻሻልና ከሌሎች ደንቦችና አሠራሮች ጋራ ተጣጥሞ መዘጋጀት ዐሥር አባላት የሚገኙበት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ምሁራን ኮሚቴ በምልአተ ጉባኤው ተሠይሟል፡፡ ለዚህም አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሁለት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ሦስት የሕግ ምሁራን መመረጣቸው የተነገረ ሲሆን ኮሚቴው ቀደም ሲል በቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱ በተመረጡ ሦስት ብፁዓን አባቶች ተለይተው የታወቁ የመነሻ ሐሳቦችን እንደ ግብአት ሊጠቀም እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ ይኸው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ በቋሚነት ለሚዘጋጀው የፓትርያርክ አመራረጥና ሥልጣኑን በዝርዝር ለሚያመለክተው ቋሚ ሕግ መሰናዶ መሠረት እንደሚኾን ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡

ለሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያው ዝግጅት የተመረጡት አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ናቸው፡፡ ከሊቃውንት ጉባኤ መምሪያም መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን በአባልነት የሚገኙበት ሲኾን ከሕግ ምሁራኑም መካከል ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ እና ዶ/ር መሐሪ ታደለ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ ፕ/ር ጥላሁን ተሾመ በ31ው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ “የመንፈሳዊ ፍ/ቤቶች አስፈላጊነትና ሕገ መንግሥት” በሚል ርእስ የጥናት ጽሑፍ በማቅረብ÷ ቤተ ክርስቲያን በሕገ መንግሥት ከተሰጣት መብት አንጻር ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የምትዳኝበት፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱና የመንግሥት ሚና ተለይቶ የታወቀበት በባለሞያ የተጠናከረ የፍትሕ ሥርዐት እና መንፈሳዊ ፍ/ቤት (Institutional and Legal Infrastructures) በየደረጃው ማቋቋም እንደሚያስፈልጋት መክረዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ግዘፍ ነስቶ የሚታየው የሙስና፣ የጎሰኝነትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሌላው የምልአተ ጉባኤው የመነጋገሪያ አጀንዳ የነበረ ሲኾን ከዚሁ ጋራ በተያያዘ የአብዛኞቹ አድባራትና ገዳማት ተቃውሞ የጠነከረባቸው ሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከሓላፊነታቸው ሊነሡ እንደሚችሉ እየተጠቆመ ይገኛል፡፡ ለ31ው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቀረበው የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ ሪፖርት ብር 6,753,717.25 ጉድለት የተገኘባቸው ንቡረ እዱ አስተዳደራቸው “የመልካም አስተዳደር ኣርአያና ምሳሌ” እንደኾነ በብልጣብልጥ አንደበታቸው ለመሸፋፈን ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቶ በመላው ጉባኤተኛ ተቃውሞ ነበር ከመድረኩ እንዲወርዱ የተደረጉት፡፡ 

የሀገረ ስብከቱን ገዳማትና አድባራት አቤቱታ ሁለት ገጽ ከዚህም ባሻገር በቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር ሥርዐቱ “ቅድሚያ ለመነኵሴ” በሚል የተደራጀ የደላሎች (የቡድን) ሙስናና ምዝበራ የሚታወቀው የንቡረ እዱ አስተዳደር በመሀል አራት ኪሎ በርክተው ለሚታዩት ሕገ ወጥ መነኰሳት መብዛት፣ ለገዳማትም መዘጋት ተጠያቂ የኾነበት መረጃም ቀርቦበታል፡፡ በመኾኑም የንቡረእዱ ከሓላፊነታቸው መነሣት ቀድሞ ያከተመለት ጉዳይ ሲኾን የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ የሚጠባበቀው ቀሪው ጉዳይ÷ “የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በአራት አህጉረ ስብከት በመከፋፈል ራሳቸውን በቻሉ ሥራ አስኪያጆችና ሊቃነ ጳጳሳት እንዲመራ በማድረግ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ጥያቄውን መመለስ አልያም ባለበት አቆይቶ በተሻለ አደረጃጀትና የሰው ኀይል መምራት ነው፤” ይላሉ ምንጮቹ፡፡ ከዚሁ ጋራ በተያያዘ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ላይ የሚነሣው የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ጥያቄ ሌላው የምልአተ ጉባኤ አጀንዳ እንደ ነበር ተወስቷል፡፡

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት አባቶች ጋራ የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም ውይይት ቀዳሚ የመነጋገሪያ ነጥብ አድርጎ ያስቀመጠው ምልአተ ጉባኤው÷ ሂደቱ በመልካም ኹኔታ ላይ እንደሚገኝ በመገምገም ለውይይቱ አስፈላጊ የኾኑ ተጨማሪ መረጃዎች እስኪቀርቡለት ድረስ በይደር እንዲቆይ መወሰኑ ተሰምቷል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ከሰኞ ማክሰኞ በይደር ከተዋቸው አጀንዳዎች ጋራ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የቦርድ ሰብሳቢነትና በአቶ ተስፋዬ ውብሸት ሥራ አስኪያጅነት የሚመራውን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሪፖርት በመስማት ሳይመለሱ በመንግሥት ይዞታ ሥር በሚገኙት በቁጥር ከ230 በማያንሱት ቤቶችና ሕንጻዎች ጉዳይ እንዲሁም በተለያየ መንገድ ሕገ ወጥ ኪራይ ስለተፈጸመባቸው የመኖርያና ንግድ ቤቶች ይዞታ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ገዳማት፣ አዳሪ የአብነት ት/ቤቶች እና ማሠልጠኛዎች፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት ወዲህ የታሸገው ማረፊያ ቤታቸው እና መንበረ ፓትርያርኩ፣ የቀጣይ ስድስት ወራት የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ምርጫ ከሌሎች የምልአተ ጉባኤው መነጋገሪያ አጀንዳዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

ከላይ በዝርዝር ከተመለከቱት የምልአተ ጉባኤው የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ውስጥ÷ ሰላምን፣ ሕጋትን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደርን፣ የሀብት ንብረት አጠባበቅን (የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ንብረት ውርስን ወይም ባለቤትነትን ሊመለከት ይችላል) የፓትርያርክ ምርጫ ሕግን በተመለከተ የተቀመጡት ነጥቦች ከቀጣዩ ፓትርያርክ ሹመት አስቀድሞ መከናወን ለሚገባቸው የቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ የተቋማዊ ለውጥ ተግባራት የቅድመ ዝግጅት ምዕራፎች አድርገው እንደሚያዩዋቸው የቅዱስ ሲኖዶሱን ስብሰባ የሚከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ በዐቃቤ መንበሩ ርእሰ መንበርነት የሚመራው ምልአተ ጉባኤው መግባባት በሰፈነበት ውይይት መደበኛ ስብሰባውን ማካሄዱና ምክንያታዊ በኾነ የጊዜ ገደብ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ መኾኑም ሌላው አዎንታዊ ገጽታው ነው፡፡


ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
  

3 comments:

Anonymous said...

ለዚህ ለተፋጠነ ስራ ለአባቶቻችንን እግዚአብሄር ፀጋውን ያብዛላቸው::

Aregawit said...

E/r lebetekristyanachene ena lehzbochwa selamene yemewerdete gubaye yehunelen.

Anonymous said...

Amlak hoy le'abatochachin rejim edimenina tibebin yadililin. Yihin mayet le'egna endet melkam new. Awo ahunim cher were yaseman. Fitsamewin yasamirilin, temesgen.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)