September 24, 2012

በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ቤተ ክርስቲያን ሰፊ የብዙኀን መገናኛ ሽፋን እንደምታገኝ ይጠበቃል

  • በሰንበት ት/ቤቶች ዐውደ ትርኢት የዕርቀ ሰላምና አንድነት ጥያቄው ትኩረት ተሰጥቶታል::
  • ግማደ መስቀለ ክርስቶስ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት የተቀጸል ጽጌ በዓል ተከብሯል::
  • ተቀጸል ጽጌ ናትናኤል ሊቀ ጳጳሳት” (የአዲስ ዓለም ጽዮን ማርያም ገዳም ሊቃውንት)::
  • የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አርባኛ ቀን መታሰቢያ ዛሬ መስከረም 14 ቀን ይዘከራል::
DEMERA (Courtesy of Teddy Haile)
(ደጀ ሰላም፤ መስከረም 14/2004 ዓ.ም፤ ምቴፕር 24/2012/ READ IN PDF):- ሃይማኖታዊ መሠረትና ብሔራዊ ገጽታ ካላቸው በዓላት አንዱና ዋነኛው የመስቀል በዓል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በዓለ መስቀልን ከጌታችን ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት አስገብታ በመወሰን ታከብራለች፡፡ ሊቁ ማሕሌታይ ቅዱስ ያሬድ “መስቀል መልዕልተ ኵሉ ነገር ያድኅነነ እምፀር” በማለት መስቀል ከሁሉም ነገር በላይ እንደኾነና ከሥጋዊ (ዓለማዊ) ጠላትም ኾነ ከመንፈስ ጠላታችን ዲያብሎስ እንደሚያድነን እንዳስተማረን÷ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት ቅዱስ መስቀል ጽንዓታችን፣ ቤዛችን፣ መድኃኒታችን ነውና እናከብረዋለን፤ እናገነዋለን፤ በመባረክና በማማተብ ረቂቃን አጋንንትን እናርቅበታለን፤ በመታሸት ከደዌ ሥጋ፣ ከደዌ ነፍስ እንፈወስበታለን፤ በሰውነታችን በመነቀስና በተለያየ ኪነ ቅርጽ ማዕተብ አድርገን ክርስትናችንና በመስቀሉ ማመናችንን እንገልጽበታለን፡፡

የመስቀል በዓል በመስከረም ወር ብቻ በአራት የተለያዩ ቀናት ይከበራል፡፡ የመጀመሪያው ግማደ መስቀለ ክርስቶስ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት የተቀጸል ጽጌ በዓል የሚከበርበት መስከረም 10 ቀን ነው፡፡ የተቀጸል ጽጌ መሠረቱ ሰኔ 26 ቀን የሚገባው ወርኀ ክረምት መስከረም 25 ቀን የሚወጣበት የአበባ በዓል ነው፡፡ መኃ.2÷11፡፡ ወርኀ ክረምቱ አልፎ ምድር ልብሰ ልምላሜ ተጎናጽፋ፣ በአበባ አጊጣ ሰማዩ በከዋክብት ሲያሸበርቅ የሚታሰበውን የአበባ በዓል (ተቀጸል ጽጌ) ለማክበር ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ወርቅና ብር የተሣለባቸውን አልባሳተ መንግሥት እየለበሱ እንደ አበቦቹ ደምቀውና አሸብርቀው ለሕዝቡ ይታያሉ፤ ካህናቱም ባማረ ልብሰ ተክህኖ ተሸልመው በነገሥታቱ ፊት በመኳንንቱና በሕዝቡ መካከል በማሸብሸብ ይዘምራሉ፡፡

የቀድሞውን አከባበር የሚያወሱ የጽሑፍ ምንጮች እንደሚጠቁሙት÷ በዚህ ቀን በካህናቱ ላይ የሚታየው ጥንግ ድርብ፣ ኩታና ነጭ ልብስ፣ የዝማሬው ጣዕምና የንባቡ ስልት የትርጉሙ ምስጢር፣ የሽብሸባው ትርኢት የተመልካችን መንፈስ የሚመስጥና ተወዳጅ ባህላችንን እንደ ዕንቍ አብርቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐጼ ገብረ መስቀል የቀይ ነጭ የጥቁር ዕንቍ አበባ ፈርጅ ያለበት ዘውድ ደፍቶ ይህን የአበባ በዓል እጅግ ከፍ ባለ አኳኋን ያከብረው እንደነበር ተጽፏል፡፡ በዘመነ መንግሥቱ የተነሣው ቅዱስ ያሬድ “ተቀጸል ጽጌ ገብረ መስቀል ዓፄጌ” ብሎ ግራና ቀኝ ከካህናቱ ጋራ በማሸብሸብ ጣዕም ባለው ዜማ ልቡናውን ደስ እንዳሰኘው፣ ጳጳሱ አቡነ ዮሐንስም በዘውዱ ላይ አበባ መበተኑም ይነገራል፡፡

ከእርሱ በኋላ እስከ አጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ደርሶ በእርሳቸው ጊዜ መስከረም 10 ቀን እንዲከበር ተወስኗል፡፡ ይኸውም የጌታችን ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀለ ክርስቶስ ከሌሎች ንዋያተ ቅድሳት (አክሊለ ሦክ፣ ቅዱስ ሉቃስ የሣላት ምስለ ፍቁር ወልዳ) ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ከእግዚአብሔር በተገለጸለት ራእይ መሠረት “አብርሂ አብርሂ ማርያም አብርሂ፤ መስቀሉ ለወልድ እንዘ ትትሞጥሒ፤ ጽዮን ዮም ተፈሥሒ” በማለት በመስከረም 10 ድጓው ላይ ተሠርቶ የምናገኘው ዕዝል በትንቢት መነጽር እንደሚያስረዳ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡

አጼ ዘርዐ ያዕቆብ አባታቸው አጼ ዳዊት ከግብጽ ሡልጣኖች ጋራ ሰላም በመፍጠርና ለኮፕት ክርስቲያኖች ዕረፍት በማስገኘት ስለነበራቸው ውለታ ከኢየሩሳሌሙ ፓትርያርክ ተልኮላቸው ስናር ድረስ ተጉዘው የክብር አቀባበል ያደረጉለትን ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡበት መስከረም 10 ቀን በሌላ ስያሜው አጼ መስቀል (የንጉሥ በዓል) እየተባለ ይጠራል፡፡ በአንድ ወር ለሁለተኛ ጊዜ የንጉሥ በዓል ማክበር አስቸጋሪ ስለሆነ መስከረም 25 ቀን ይከበር የነበረው የአበባ በዓል (ተቀጸል ጽጌ) መስከረም 10 ቀን ከአጼ  መስቀል በዓል ጋራ በአንድነት እንዲከበር ተደርጓል፡፡ ቁም ነገሩ÷ የመስቀል በዓል የሚከበረው አበቦች በሚፈኩበት የጥቢ ወራት መግቢያ በመኾኑ ጸሎቱም (መስቀል ኣብርሃ በከዋክብት አሠርገወ ሰማየ እምኵሉሰ ፀሐየ አርኣየ) ይኹን ሕዝባዊ ዜማው (ኢዮሀ አበባዬ÷ መስከረም ጠባዬ) የመስቀልን ክብር አለመልቀቁ ነው፡፡

የዘንድሮው የተቀጸል ጽጌ በዓል መስከረም 10 ቀን 2005 . በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተከበረበት ዕለት በቀድሞው ጊዜ የተቀጸል ጽጌ በዓል የሚታወቀው በቤተ  መንግሥት ሲከበር እንደነበር ያስታወሱት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል÷ ይኸውም ነገሥታት ምድርን የምታስተዳድሩ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና ዘመኑ ሲለወጥ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለማለት እንደ ነበር አስረድተዋል፡፡ ወርኀ ነሐሴ የሰዉ ልቡና በሐዘን የተሠበረበት የሐዘን ጊዜ ነበር ያሉት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል÷ በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙትን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ሊቃውንት መዘምራንና በርካታ ምእመናን እንኳን ከዚህ ዓመት፣ ከዚህ ሰዓት አደረሳችኹ ብለዋል፡፡

ዘመን የራሱ ሂደት አለውና በቤተ መንግሥት አደባባይ ይከበር የነበረውን በዓል ቃለ እግዚአብሔር በሚነገርበት፣ ታቦተ እግዚአብሔር በሚቆምበት በዐውደ ምሕረት በማክበር መስቀለ ክርስቶስን ማክበራችን የእግዚአብሔር መንክርና ኪን ነው - ብፀዕነታቸው እንደገለጹት:: ለዘንድሮው በዓል ተረኞች የነበሩት የርእሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም ጽዮን ማርያም ገዳም ሊቃውንት÷ “ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እለይፀውሩ አርዑተ መስቀሉ ለክርስቶስ እለ ሎሙ ሕግ ወሎሙ ሥርዐት፤ እምጽዮን ይወጽዕ ሕግ በአፈ ካህናት ምክረ ራትዓን አእምሮ ታኀድር ዲበ ብፁዓን ጳጳሳት” በማለት ወረብ አቅርበዋል፤ “ተቀጸል ጽጌ ናትናኤል ሊቀ ጳጳሳት” በማለት እያሸበሸቡም የበዓሉን ትውፊታዊ ሥነ ርእይ አሳይተዋል፡፡ በአጫብርና በቆሜ ስልት የቀረበው ሌላው የሊቃውንቱ ወረብ የተመልካቾችን ቀልብ የሳበ ሲሆን ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጡ ማዕከላውያን መዘምራንም ሊቃውንቱን መስለውና አኽለው ጣዕመ ዝማሬያቸውን አቅርበዋል፡፡

መስከረም 16 ቀን የሚከበረው የደመራ በዓል በሰቃልያነ ክርስቶስ አይሁድ እኵይ ተግባር የተቀበረውን መስቀል ለማግኘት ንግሥት እሌኒ ቁፋሮ ያስጀመረችበትና ከተገኘም በኋላ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ዋዜማና ቤተ ክርስቲያኑ የተባረከበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ምእመኑ በየአጥቢያው የመስቀል ደመራ ይዞታ ዕንጨቱን እያመጣ ይደምራል፡፡ ካህናቱም በደመራው ፊት ለፊት ጸሎት አድርሰው “መስቀል ኣብርሃ በከዋክብት አሠርገወ ሰማየ እምኵሉሰ ፀሐየ አርኣየ” እያሉ ደመራውን ይዞራሉ፡፡ ማታ ሕዝቡ በየደጁ ችቦውን እያበራ ደስታውን ሲገልጥ ያመሻል፡፡ በዐሥራ ሰባት ጠዋት ደመራው ይለኮሳል፡፡ ዐመድ እስኪኾን ድረስ ከተቃጠለ በኋላ ደመራው የተጸለየበትና የተባረከ ስለሆነ ሕዝቡ አመዱንና ትርኳሹን እየተሻማ ወደየቤቱ ይዞ ይሄዳል፤ ለሰውም ለከብትም መድኃኒት ነው፡፡ በአዲስ አበባና በአካባቢው ግን ደመራውን የሚያቃጥሉት ወዲያው ጸሎቱ እንዳበቃ ነው፡፡

መስከረም 17 ቀን ከመስቀሉ የመገኘት ብሥራት በኋላ ንግሥት እሌኒ በጎልጎታና በቤተ ልሔም ያሠራችው ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት የተፈጸመበት ነው፡፡ መስከረም 21 ቀን ለአጼ  ዘርዐ ያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” ተብሎ በራእይ በተነገራቸው መሠረት ከብዙ ድካም በኋላ ቅዱስ መስቀሉ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ መስቀለኛ ተራራ ገብቶ ያረፈበት በዓል ነው፡፡

በልዩ ልዩ ባህላዊ ሥነ ሥርዐት የሚከበረው የመስቀል በዓል ሥነ ርእይ ከኦርቶዶክሳዊነት ውጭ ባሉት ኢትዮጵያውያን ዘንድ “ሃይማኖቴም ባይኾን ባህሌ ነው” የሚያሰኝ ብሔራዊ እና አገራዊ ክብር የተጎናጸፈ ነው፡፡ በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ የመስቀል በዓል አከባበር ዐውደ ትርኢት ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የውጭ አገር ዜጎችን ሳይቀር የሚስብና የሚማርክ በመኾኑ በየጊዜው በክብረ በዓሉ ላይ የሚገኙት ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡

ከ1967 ዓ.ም በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ይከበር የነበረው የመስቀል ደመራ በዓል ይመራ የነበረው በከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ሓላፊነትና አስፈጻሚነት ሲኾን ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ንጉሠ ነገሥቱና ሚኒስትሮቻቸው በክብር እንግድነት ይታደሙ ነበር፡፡ ከ1967 ዓ.ም ወዲህ ግን ሥርዐቱን የመምራትና የማስፈጸም ሓላፊነት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኾኗል፡፡ ከ1967 – 1984 ዓ.ም በነበረው ጊዜ በመስቀል አደባባይ ይከበር የነበረው በዓል ወደ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ አካባቢ አሁን ለግንባታ በታጠረው ቦታ ላይ ተዛውሯል፤ መስቀል አደባባይ በመባል የሚታወቀውን ሥፍራችንንም “አብዮት አደባባይ” በማለት ሌላ ዐዋጅ ሲታወጅበት ቆይቷል፡፡ ከ1984 ዓ.ም በኋላ የመስቀል በዓል ወደ ቀድሞው ስፍራው ተመልሶ ቤተ ክርስቲያናችን የበዓሉ አከባበር ገጽታ በቀጥታ በብዙኀን መገናኛ እንዲተላለፍ ለመንግሥት ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት ከሞላ ጎደል እየተሰጣት ያለው ሽፋን ለበዓሉ ማማርና ለጎብኚዎች ቁጥር መጨመር የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉ አይካድም፤ አመርቂ ነው ለማለት ግን አይቻልም፡፡

የበዓሉን ከፊል ገጽታ በወለምታ ወይም በቆረጣ አሳይቶ (መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል እንደሚሉት እንደ ትል እሳት ብልጭ አድርጎ) በዓሉን ወደማይመለከት ሌላ ፕሮግራም ማምራት፣ ‹የብሔር ብሔረሰቦች› ዘፈን ማዘፈንና ዳንኪራ ማስረገጥ እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ከማሰኘት በቀር አያስመሰግንም፡፡ ሌሎች አብያተ እምነት ለሚያከብሩት በዓል ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ድረስ ሰፊ ሽፋን እየተሰጠ ለሀገሪቷና ለሕዝቧ ባለውለታ ለሆነችው ለጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙኀን መገናኛ የሚሰጡት የቀጥታ ሽፋን ግን አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ በሌሎች ሲደረግ በማይታይ አኳኋን በእኛ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ በዓላት የሌሎችን አብያተ እምነት በዓል አከባበር ቀላቅሎ ማሳየትም ቅሬታ ያሳድራል፤ ግራ አጋቢም ነው፡፡

በአጭሩ የመስቀልም ይኹን የጥምቀት በዓል ሲከበር ቤተ ክርስቲያናችን የምትፈልገው የበዓሉ ገጽታ አንዳችም ነገር ሳይቀላቀልበት በብቸኝነት እንዲታይላት ነው፡፡ የበዓላቱ ምንነትና ታላቅነት የሚገለጸውም አከባበራቸው ምንም ነገር ሳይቀላቀልበት ሲታይ ብቻ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ስለ በዓሉ ምንነትና አከባበር ግለሰቦችንና በተለይም የውጭ ዜጎችን አስተያየት እንጠይቃለን እያሉ ሊታይ የሚገባውንና ዓለሙን የሚያስደምመውን የበዓሉን ሥነ ርእይ ይሸፍኑታል፡፡ ከተራ ፕሮፓጋንዳ የጸዳ የበዓል ታዳሚዎች አስተያየት ያስፈልጋል ከተባለ ለብቻው ተቀርጾ በራሱ ጊዜ ቢቀርብ ይመረጣል እንጂ ስለ መስቀል ይኹን ስለ ጥምቀት በዓል ታሪክና ክብር ራሱ በዓሉ ቢናገር የተሻለ ነበር፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ እኮ የሀገርም ጉዳይ ነው፡፡

በዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር የመንግሥት ብዙኀን መገናኛዎች ያልተቆራረጠ ቀጥተኛ ሽፋን እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ ይኸው ያልተቆራረጠ የቀጥታ ሽፋን በመዲናዪይቱ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የመስቀል በዓል በድምቀት የሚከበረባቸውን የክልል ከተሞችንና ሌሎች አካባቢዎች እንደሚያካትት ተስፋ አለን፡፡ ይህን ማድረጉ በአንድ በኩል የመንግሥትን የገጽታ ግንባታ ጥረትና የአገርን ኢኮኖሚ ያግዛል፤ በዋናነት ግን “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” እንደተባለው የመስቀልን በረከት በተሟላ ገጽታው ለዓለም ሁሉ በማስተላለፍ የመስቀል ደመራን በዓል በብቸኝነት ለምታከብረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ አገልጋዮቿ እና ምእመኖቿ) ተገቢውን አክብሮትና ዋጋ መስጠት ነው፡፡

የበዓሉን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ በቤተ ክርስቲያናችን በኩል በተለይ በአዲስ አበባ ከ130 ያላነሱ ሰንበት ት/ቤቶች እንደተለመደው ከነሐሴ 24 ቀን ጀምሮ በየክፍለ ከተማቸው ሲያካሂዱት የቆዩትን የመስቀል ጥናት እያጠናቀቁ ይገኛሉ፡፡ ከ130 አጥቢያዎች የተውጣጡት ቁጥራቸው 2700 ያህል የሚኾኑ ወጣቶች በተለያዩ ወቅታዊ ጭብጦች ላይ ያተኮሩ ዐውደ ትርኢት በማቅረብ ለበዓሉ ድምቀት እንደሚሰጡት ተመልክቷል፡፡ ከዐውደ ትርኢቱ ክፍሎች መካከል በግእዝ የፊደል ገበታ የሚገኙ ሆሄያት “ይቀነሱ” በሚል ያላዋቂ/የስንፍና አስተያየት የሚሰጡ ምሁራንን በመቃወም ቤተ ክርስቲያናችንና መላው ሕዝብ አገልግሎታቸውን ዐውቆ እንዲጠብቃቸው የሚያሳስቡ፤ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ማሕሌታይ ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበትን 1500 ዓመት ምክንያት በማድረግ ንዋያተ ማሕሌትን በዐይነትና በጽሑፍ የሚታዩበት፤ በክበብ ቅርጽ ውስጥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በሕብረ ቀለም በማሳየት የተጀመረው የዕርቀ ሰላምና አንድነት ሂደት ከፍጻሜ እንዲደርስ የሚጠይቁ እንደሚገኙበት ከሠልጣኞቹ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

በተያያዘ ዜና የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት 40 ቀን ዛሬ በመላው አድባራትና ገዳማት በተለይም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ታስቦ እንደሚውል ታውቋል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

ከታሪክ ማስታወሻ፦ 
ታላቁ አባት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በአንድ ወቅት ካስተማሩት ትምህርት እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ 3ኛው ፓትርያርክ፣ ካስተላለፉት ቃለ ምዕዳን እነሆ!!!!5 comments:

Anonymous said...

vidiowin sayew yetesemagnin simet kemigelittsew belay new yabatochchin bereket yideribachihu endih ayenet video lelam gize bitasayun betam tiru new.

Anonymous said...

vidiowin sayew yetesemagnin simet kemigelittsew belay new yabatochchin bereket yideribachihu endih ayenet video lelam gize bitasayun betam tiru new.

Anonymous said...

vidiowin sayew yetesemagnin simet kemigelittsew belay new yabatochchin bereket yideribachihu endih ayenet video lelam gize bitasayun betam tiru new.

Anonymous said...

If you can post the video alone, it would be nice. Would you please do the same for other similar videos? The true holly fathers...Abune Teklehaimanot and Abune Gorgorios....Bereketachew yideribin...I watched and listened it with tears.

Anonymous said...

የበዓሉን ከፊል ገጽታ በወለምታ ወይም በቆረጣ አሳይቶ (መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል እንደሚሉት እንደ ትል እሳት ብልጭ አድርጎ) በዓሉን ወደማይመለከት ሌላ ፕሮግራም ማምራት፣ ‹የብሔር ብሔረሰቦች› ዘፈን ማዘፈንና ዳንኪራ ማስረገጥ እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ከማሰኘት በቀር አያስመሰግንም፡፡ ሌሎች አብያተ እምነት ለሚያከብሩት በዓል ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ድረስ ሰፊ ሽፋን እየተሰጠ ለሀገሪቷና ለሕዝቧ ባለውለታ ለሆነችው ለጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙኀን መገናኛ የሚሰጡት የቀጥታ ሽፋን ግን አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ በሌሎች ሲደረግ በማይታይ አኳኋን በእኛ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ በዓላት የሌሎችን አብያተ እምነት በዓል አከባበር ቀላቅሎ ማሳየትም ቅሬታ ያሳድራል፤ ግራ አጋቢም ነው፡፡


በአጭሩ የመስቀልም ይኹን የጥምቀት በዓል ሲከበር ቤተ ክርስቲያናችን የምትፈልገው የበዓሉ ገጽታ አንዳችም ነገር ሳይቀላቀልበት በብቸኝነት እንዲታይላት ነው፡፡ የበዓላቱ ምንነትና ታላቅነት የሚገለጸውም አከባበራቸው ምንም ነገር ሳይቀላቀልበት ሲታይ ብቻ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ስለ በዓሉ ምንነትና አከባበር ግለሰቦችንና በተለይም የውጭ ዜጎችን አስተያየት እንጠይቃለን እያሉ ሊታይ የሚገባውንና ዓለሙን የሚያስደምመውን የበዓሉን ሥነ ርእይ ይሸፍኑታል፡፡ ከተራ ፕሮፓጋንዳ የጸዳ የበዓል ታዳሚዎች አስተያየት ያስፈልጋል ከተባለ ለብቻው ተቀርጾ በራሱ ጊዜ ቢቀርብ ይመረጣል እንጂ ስለ መስቀል ይኹን ስለ ጥምቀት በዓል ታሪክና ክብር ራሱ በዓሉ ቢናገር የተሻለ ነበር፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ እኮ የሀገርም ጉዳይ ነው፡፡


በዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር የመንግሥት ብዙኀን መገናኛዎች ያልተቆራረጠ ቀጥተኛ ሽፋን እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ ይኸው ያልተቆራረጠ የቀጥታ ሽፋን በመዲናዪይቱ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የመስቀል በዓል በድምቀት የሚከበረባቸውን የክልል ከተሞችንና ሌሎች አካባቢዎች እንደሚያካትት ተስፋ አለን፡፡ ይህን ማድረጉ በአንድ በኩል የመንግሥትን የገጽታ ግንባታ ጥረትና የአገርን ኢኮኖሚ ያግዛል፤ በዋናነት ግን “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” እንደተባለው የመስቀልን በረከት በተሟላ ገጽታው ለዓለም ሁሉ በማስተላለፍ የመስቀል ደመራን በዓል በብቸኝነት ለምታከብረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ አገልጋዮቿ እና ምእመኖቿ) ተገቢውን አክብሮትና ዋጋ መስጠት ነው፡፡ .... tiru bilachihual deje selamoch joro yallew yisma. Melkam yemesqel ena yedemera beal yihunilin.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)