August 16, 2012

(UPDATED) የአቡነ ጳውሎስ ዜና ዕረፍት ጉዳይ ከተጨማሪ መረጃዎች ጋር

  •  READ THIS UPDATED NEWS IN PDF
  • በአንድ የመንግሥታዊው ባንክ ቅርንጫፍ ሦስት አካውንቶች ውስጥ በፓትርያሪኩ የተለያዩ ዘመዶች ስም ከ22 ሚልዮን ብር በላይ መከማቸቱ ተጠቁሟል፤
  • የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አስከሬናቸው ባለበት በዳጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ተገኝተው ሥርዐተ ግንዘቱን አከናውነዋል፤ ጥቅመኛዋ እጅጋየሁ በየነ “አልሞቱም፤ አስከሬናቸው ይመርመርልኝ” እያለች በማወክ ላይ ትገኛለች፤
  • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአህጉረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አለቆች በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ጥሪ ተደርጓል፤
  • የአቡነ ጳውሎስን ቀብር የሚያስፈጽም ኮሚቴ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ተቋቁሟል፤ መኖሪያ ቤታቸውና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ታሽጓል፤ በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና በሌሎችም ቦታዎች የሚገኙ ሙዝየሞች ለጎብኚዎች ዝግ ተደርገው ጥበቃው እንዲጠናከር ታዝዟል፤
  • ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ በማካሄድ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ይሾማል፤ ከቋሚ ሲኖዶሱም ጋራ እየመከረ ይሠራል፤ (ሕገ ቤተ ክርስቲያን)
  • “ውሉደ ጳውሎስ” /እነ እጅጋየሁ በየነ/ በፓትርያሪኩ ስም “ጳውሎስ ፋውንዴሽን” ለማቋቋም እየተሯሯጡ ነው፤ የሀብት ቅርምቱን ለማመቻቸት ይኾን?(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 10/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 16/ 2012/READ THIS UPDATED NEWS IN PDF):- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያሪክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዛሬ፣ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ንጋት ላይ በዳጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል በተወለዱ በ76 ዓመታቸው፣ በተሾሙ በኻያኛ ዓመት ዘመነ ፕትርክናቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ፓትርያሪኩ ከትናንት በስቲያ፣ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ገብተው ሕመማቸውን ለረጅም ጊዜ ሲከታተሉላቸው በቆዩት የሆስፒታሉ ዶክተሮች ሕክምና ቢደረግላቸውም በቆየባቸው በሽታ ዛሬ ንጋት 11፡00 ላይ መሞታቸውና አስከሬናቸውም ረፋድ ላይ ወደዚያው ባመሩት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሥርዐተ ግንዘት እየተከናወነለት እንደሚገኝ ተረጋግጧል፡፡

አቡነ ጳውሎስ የምንገኝበትን የፍልሰታ ለማርያም ጾም በድሬዳዋ ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ወቅድስት አርሴማ የሴቶች ገዳም የማሳለፍ ልማድ ቢኖራቸውም በዘንድሮው ሱባኤ ግን መሰንበቻቸውን ያደረጉት የፕትርክናው መንበር በሚገኝበት በአዲስ አበባ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ነበር፡፡

በቀደሙ ዘገባዎቻችን እንደገለጽነውና በሰሞኑ የሱባኤው ቅዳሴ ውሎዎች እንደተረጋገጠው÷ አቡነ ጳውሎስ የጀመሩትን ጸሎተ ቅዳሴ ለመጨረስ ተስኗቸው ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት /እነ ብፁዕ አቡነ ገሪማ/ እየተተኩ ጸሎተ ቅዳሴው እንዲጠናቀቅ ሲደረግ ነበር፡፡

የዐይን እማኞች እንደተናገሩት÷ ፓትርያሪኩ በጸሎተ ቅዳሴው መካከል በወንበር ላይ እንደተቀመጡ ሁለት እግራቸውን ፊት ለፊታቸው በሚገኝ ሌላ ወንበር ላይ ሰቅለው ታይተዋል፤ ወደ መኖሪያቸው ሲወጡም ይኹን ሲገቡ ዙሪያቸውን በረዳቶቻቸው ተደግፈው ነው፡፡ ከቆየባቸው የስኳር በሽታና ከፍተኛ የደም ግፊት ሕመሞቻቸው (hypertension and diabetes) መወሳሰብ ጋራ በተያያዘ ሁለቱም እግሮቻቸው ከአውራ ጣታቸው ጀምሮ እስከ ጉልበታቸው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ተጎድተዋል፡፡ እግራቸው እንዲቆረጥ ጤናቸውን በሚከታተሉላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሐኪሞች ሲነገራቸው ቢቆይም ፓትርያሪኩ ለሥልጣናቸው በመሳሳት [በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በአካል ጉዳተኝነት በፕትርክናቸው - ክህነታዊ ሥልጣን - መቀጠል አይችሉም] የሐኪሞቹን ምክርና ማሳሰቢያ ችላ ብለው በውጭ ምንዛሬ በሚገዟቸውና በመርፌ በሚወስዷቸው መድኃኒቶች ራሳቸውን ሲያስታምሙ ቆይተዋል፡፡ አባ ጳውሎስ ከትናንት በስቲያ ወደ ሆስፒታል የገቡት ታዲያ በእግራቸው ላይ በሚሰማቸው ከፍተኛ ጥዝጣዜ እየተሠቃዩ ባለበት ኹኔታ ነበር፡፡

በኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው አከባበርና ከዚያም ወዲህ ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያካሂዳቸው ስብሰባዎች ወቅት ጥልቅ የመቀዘዝ ስሜት ይታይባቸው የነበሩት አባ ጳውሎስ÷ ትምክህታቸውን በሚገልጹላቸውና እንደ አለኝታም በሚቆጥሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በጽኑ መታመም ክፉኛ መደናገጣቸውና ግራ መጋባታቸው፤ በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም በሃይማኖት ሕጸጽ ከተጠየቁ ወዲህ [በመጽሐፍ መልክ ባሳተሙት የዶክትሬት ጥናታቸው ሕጸጹ የተገለጸባቸውን አንቀጾችና ዐረፍተ ነገሮች አውጥተዋቸዋል] በአያሌው መጨነቃቸው፤ ከቅዱስ ሲኖዶሱ በላይ አመራር ሰጪ በመኾን የቀድሞውን ዐምባገነናዊ አሠራራቸውን ለመመለስ ከወርኀ ግንቦት ጀምሮ ሕገ ወጥ ቡድኖችን በማደራጀት ያደረጓቸው ጥረቶች መክሸፋቸው፤ ከዚህም ሁሉ ጋራ በሄዱበት ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብር የሚከተሏቸው በርካታ ጳጳሳት የሸሽዋቸው መኾኑ እዚህም እዚያም ከሚሰማው የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምእመናንና ወዳጆች ሐዘንና ጸሎት ጋራ ተደማምሮ የፈጠረባቸው አካላዊና መንፈሳዊ መጎሳቆል ለተመልካች በጉልሕ የሚረዳ እንደ ነበር የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምንጮች ለደጀ ሰላም ተናግረዋል፡፡

ሐምሌ 5 ቀን 1984 ዓ.ም የተሾሙትና ለኻያ ዓመታት በፕትርክና የቆዩትን የአቡነ ጳውሎስን የቀብር ሥነ ሥርዐት ለማስፈጸም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የአስተዳደር ጉባኤው ዛሬ ጠዋት ከመከሩበት በኋላ ‹‹የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ›› መቋቋሙ ተዘግቧል፤ የቀብር ሥነ ሥርዐት አፈጻጸሙም በተከታታይ እንደሚገለጽ ከፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት በብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ የወጣው የሐዘን መግለጫ አስታውቋል፡፡ የፓትርያሪኩ የሕዝብ ግንኙነት ጽ/ቤትና ፕሮቶኮል ሹሞችና ሓላፊዎችም በየአህጉረ ስብከቱ ስልክ በመደወል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአህጉረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አለቆች በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በርካታ አባቶች፣ አገልጋዮችና ምእመናን በመንበረ ፓትርያሪኩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ሐዘናቸውን ሲገልጹ የዋሉ ሲኾን ስለ ጸሎተ ፍትሐቱ እና የቀብር አፈጻጸም መርሐ ግብሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የሚያወጣው መግለጫ እየተጠበቀ ነው፡፡
የአባ ጳውሎስ ኅልፈተ ሕይወት በመጀመሪያው የደጀ ሰላም ዜና መገለጹን ተከትሎ÷ በርካታ ወገኖች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዓለማዊው አገራዊው ኹኔታ አኳያ በወሳኝ ወቅት ላይ እንደምትገኝ፣ በሹመታቸው ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት የከፈሉት አባ ጳውሎስ በሞታቸውም እንደይከፋፍሉን ይልቁንም ቀጣይ ርምጃዎች ያለፉትን ስሕተቶች የሚያርሙና እንዳይደገሙ የሚያደርጉ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎት መጠናከርም የሚያግዙ፣ ተቋማዊ ነጻነቷንና ብሔራዊ ክብሯን የሚመልሱ በመኾናቸው ላይ የተረጋጋና ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እንዲሠራ እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡

በፓትርያሪኩ ሞት ሰበብ ዘመዶቻቸው፣ የጥቅም ተጋሪ ቡድኖችና ግለሰቦች የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እንዳያሸሹ ማሳሰቢያ እየተሰጠም ነው፡፡ በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው፣ በቅርስና ቱሪዝም መምሪያ ሓላፊው ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ሓላፊነት የሚመራውና ከቀደሙት አራት ፓትርያሪኮች ጀምሮ በርካታ ቅርሶች የተከማቹበት ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት እንዲታሸግ ተደርጓል፡፡ እንደ እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና በሌሎችም ቦታዎች ያሉት ሙዝየሞች ለጊዜው ለጎብኚዎች ዝግ ተደርገው ጥበቃቸው እንዲጠናከር ከመንግሥት የተሰጠውን ትእዛዝ የአዲስ አበባ ፖሊስ በማስፈጸም ላይ ይገኛል፡፡

ይኹንና የተፈራውን ስጋት በሚያጠናክር አኳኋን የአባ ጳውሎስ ‹‹ቁም ተዝካር›› በተባለው የኻያኛው በዓለ ሢመታቸው አከባበር ወቅት የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የነበሩት ውሉደ ጳውሎስ (እነ እጅጋየሁ በየነ) በአቡነ ጳውሎስ ስም የሚጠራ ‹‹ጳውሎስ ፋውንዴሽን›› እናቋቋማለን በሚል እየተሯሯጡ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡

ለ‹ፋውንዴሽኑ› መቋቋም ያስፈልጋል የተባለውን ገንዘብም እንደተለመደው ከስፖንሰርሽፕ፣ ከአድባራትና ገዳማት እንዲሁም ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኢኮኖሚያዊ ምንጮች ለመሰብሰብ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን የገለጸው የመረጃ ምንጩ÷ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን፣ መልአከ ፀሐይ በቀለ ተሰማን (ቤቴል ቅዱስ ሚካኤል)፣ ሰሎሞን በቀለን (ቦሌ መድኃኔዓለም)፣ ቀሲስ ግሩም መልአክ ታዬን (ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልን (ጠቅላይ ቤተ ክህነት) በዋና አደራጅነት ጠቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ በመንግሥት የፀጥታ ኀይሎች በመታገዝ ጠንካራ ክትትል በማድረግ የወይዘሮዋንና ሌሎች አካላትን ችግር ፈጣሪነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማቆም እየሠራ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡

በተከታታይ ስለከናወኑት ተግባራት ለመወያየት የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ እንደሚካሄድ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መናገራቸው የተዘገበ ሲኾን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአባ ጳውሎስ እምቢተኝነት ሳይካሄድ በቀረውና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተለይም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከእምባ ጋራ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይፈረድ›› በሚል ሐዘናቸውን ከገለጹበት የሐምሌው ልዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መስተጓጎል በኋላ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው ሦስት አባላት የሚገኙበትና በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሚመራ ኮሚቴ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አባቶች ጋራ የተጀመረው የሰላምና ዕርቅ ንግግር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለአስታራቂ ኮሚቴው ሰባት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ እንደነበር ተነግሯል፡፡

የሰላምና ዕርቅ ንግግሩ እንዳይቀጥል ዕንቅፋት ሲፈጥሩ የቆዩት አባ ጳውሎስ ሞታቸው በሂደቱ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ገና የሚታይ ይኾናል፡፡

በ1991 ዓ.ም የወጣውና በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከፓትርያሪክ ድኅረ ዕረፍት ወይም ከሥልጣን መውረድ (አንቀጽ 16) በኋላ ስለሚሆነው ጉዳይ በአንቀጽ 17 ንኡስ አንቀጽ 1 - 3 ላይ የሚከተለውን ይላል፡፡

አንቀጽ 17 - ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ
1. ፓትርያሪኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያሪክ ምርጫም ይካሄዳል፡፡
2. የተተኪው ፓትርያሪክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደ ሥራው ኹኔታ እየታየ 40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይኾናል፡፡
3. የዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ተግባር-
) ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ጊዜያዊ ጉዳዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ እየመከረ ያከናውናል፡፡
) በፓትርያሪኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ኾኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡

የአባቶቻችን አምላክ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሰላም ይጠብቅልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡


23 comments:

Anonymous said...

ነፍስ ይማር! ላይቀር መሞት...........
ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን እግዚአብሔር ይጠብቅልን።

Anonymous said...

ነፍስ ይማር! ላይቀር መሞት

Anonymous said...

ልዑል እግዚአብሔር የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ነፍስ ይማር! እንደቸርነቱ ይሁን! ቀሪውን ጾመ ፍልሰታ /ሱባዔ/ እግዚእብሔር እንዲታረቀን፥ በሃይማኖት አባቶቻችን መካከል መግባባትንንና ፍቅርን እንዲሰጥልን፥ የቤተክርስቲያነችንን አንድነት እንዲጠብቅልን፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፍቅር፥ አንድነትና በሰላም ለመምራት መንፋሳዊ ብቃት ያለው ፓትርያርክ እንዲሾምልን፥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና ጸሎት እንዳይለየን እያለቀስን፥ ላለፈው እየተፀፀትን እንለምን። የማይጠቅመንን የሥጋዊ ጦርናት እንድንታውና የዲያቢሎስ መጫወቻ እንዳንሆን እግዚአብሔር ይጠብቀን።
አሜን!!

Anonymous said...

wiy dejeselamawyan egziabher amlak yesrachihu ystachihu maferyawoch... egzabher amlak yeqdus abatachin nefs ymar

Anonymous said...

Ye Abune Paulosin nefs Emebirhan tamaldilin. Be kibre tsomwa arfewalina diabilosin tasafililinina nesfachewun tasmirilin.

Anonymous said...

hi dejeselam write the good one . donot blame the dead body. The pope had positive side and negative side please write write the positive side.
from texas

Unknown said...

Last Anonym,

We are talking about the fate of our Church not about the patriarch's personal life. May be you are one of those who were enjoying the corruption operation of the past 20 years. You want to tell us still "to keep quite"? You are funny.

Anonymous said...

ኣይ ደጀሰላሞች - በሳቸው ኣመራር ላይ ጥያቄ ማንሳት ኣንድ ነገር ነው። ነገር ግን ስለ ሕክምናችው ስትፅፉ "ለሥልጣናቸው በመሳሳት" የሃኪም ትእዛዝ አልተቀበሉም ማለት ምን ኣይነት ስነ ስርዓት ነው? በምን ታውቃላችሁ? ሁለተኛ amputation አስፈላጊ ቢሆን እንክዋን እና ቤተክርስትያን በዚህ ምክንያት መቀጠል አይችሉም ብትል ይህ ሕግ መቀየር አለበት ትላላችሁ እንጂ እግር የሌለው ሰው መሪ ሊሆን አይችልም የሚል አሳፋሪ ሃሳብ ፅፋላችሁ?

Mercy said...

Dejeselam you became so nonesense and pharisee these days, what happened? you are blaming him even after death? wow just wow. We are talking about faith not poletics and you are such a pharisee, pharisee are not poleticians for the sake of God but you...
What is the MZ case doing here with Abune Paulos? that is for poleticians actually i dont even dare try to understand it. I see many people losing their mind these days and i think you are not different at all. The good thing is it is a choice to read DS. Have mercy God on all of us.

Anonymous said...

Loser

Anonymous said...

Dejeselam shame on you! He is died not went somewhere else. why do you criticize the dead????????? Is is realy Christianity????? we will all go to him some time indefinite

Anonymous said...

God bless u Deje selamoch ye Betekristian Tekorkariwoch

ልዑል እግዚአብሔር የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ነፍስ ይማር! እንደቸርነቱ ይሁን! ቀሪውን ጾመ ፍልሰታ /ሱባዔ/ እግዚእብሔር እንዲታረቀን፥ በሃይማኖት አባቶቻችን መካከል መግባባትንንና ፍቅርን እንዲሰጥልን፥ የቤተክርስቲያነችንን አንድነት እንዲጠብቅልን፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፍቅር፥ አንድነትና በሰላም ለመምራት መንፋሳዊ ብቃት ያለው ፓትርያርክ እንዲሾምልን፥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና ጸሎት እንዳይለየን እያለቀስን፥ ላለፈው እየተፀፀትን እንለምን። የማይጠቅመንን የሥጋዊ ጦርናት እንድንታውና የዲያቢሎስ መጫወቻ እንዳንሆን እግዚአብሔር ይጠብቀን።
አሜን!!

Anonymous said...

Excellent Job Dejeselam, Andadregen

Good response for the above anony
May GODbless u all Dejeselamoch

We are talking about the fate of our Church not about the patriarch's personal life. May be you are one of those who were enjoying the corruption operation of the past 20 years. You want to tell us still "to keep quite"? You are funny.

Berhanu z usa said...

*** ዳኛው መጣ ***
==============
ጮራ አይሉት መብረቅ በነሃሴ ነጸብራቅ
ዎፍ አይሉት አሞራ በሰማይ የሚፈልቅ፤
በጣም ግዙፍ ነው አንጋጥጭ ሳየው
መላእክት ያጀቡት ለካስ ፈጣሪ ነው
ሊፈርድ መጣ በቶሎ ስላስጨንቅነው፤
እሳት ይነዳል ከስሩ ቁጭ ካለበት ከመንበሩ
ጌታ መጣ ሊዘጋው ተከፍቶበት የገዳም ብሩ፤
ዝቅ በሉ እንስገድ ለእግዚአብሔር ለክብሩ
ገስግሱ ኑ እንግባ ከገዳሙ ሳይዘጋብን በሩ ፤
አትፍረዱ እግዚኦ በሉ ይገባል ለሰው ልጅ
በፍጥረቱ ጌታ ነው ሰው አይደለም ፈራጅ፤
ዋይ ዋይ እንበል ለወስዱት ሃላፊንት
ለሕዝብ መሪዎች ትእዛዙን ለረሱት
እናቱን እምየ ማርያምን ላቃለሉት
ያሳደግችውን በስደት ቀንና ሌሊት፤
ፍርዱ ለአምላክ ነው ዝም በሉ
በጋዜጣው በስልኩ ነገር አትብሉ።

ወስብሐት ልእግዚአብሔር ።

Anonymous said...

ሰላምደጀሰላሞች.Thank you for all the information you were given us.
Please keep informing us what is going in there and aware our responsibility for having a good religious leader.

Hailu said...

May God bless his soul.

What Aba Gerbremedihin did is a mixed bag situation. But most glaring is the division he has brought to the Ethiopian Orthodox Church and the recent complacence with the desecration of the age old monasty, Waldiba.

Any ways, God is the judge here. It is a relief for the church.

I pray to God to give the fathers of the church to use this opportunity to heal the division the late Aba Gebremedihin caused to the church. For the purpose of mending the splinter in the church, restoring the legitimate Patriarch, Abune Merkorios, is the best way. Unless God does his divine intervention, such a wise idea to solve the church's problem may be less likely as long as the Woyane will want to place another illegitimate cadre. Otherewise, the division in our church will unfortunately continue.

May God bless our church and Ethiopia. Nefis Yimar Lemotut.

wondy said...

I hate the way you present (deje selam) pleas be christian. GOD bless us and our church.

Anonymous said...

Amlak Nefsachewen Yemare.

We will never understand God's timimg and We should not try to reason out the whys, the buts, the yes, the no whatever it might be.

Let us all take time to reflect on life and our path in this life... And ask ourselves the mere question is this how God wants us to act? Is this how the person created in the likness and image of God should react when learning the truth or come across facts?

We get to witness things in this life not because we are a better creation than the next person but i beleive it is because God wants as to learn from the experience and serve Him through repetence and living his word.

My plea for all of us who is following this story is to remember that God created as in His image and likness for a purpose with a reason so just take a moment to just reflect on our life and focus on what we really want for our church, our people, our country and the world.

Please focus on praying so it will be God's willing to be merceful, forgiving, blessing to each one of us so we can be a blessing to all arround us.

This is the time God is watching over us for blessing or cursing according to our action and asking so let us not push God's blessing away!!!

Please pray hard.

Peace be upon all of us!

Anonymous said...

ልዑል እግዚአብሔር የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ነፍስ ይማር! እንደቸርነቱ ይሁን! ቀሪውን ጾመ ፍልሰታ /ሱባዔ/ እግዚእብሔር እንዲታረቀን፥ በሃይማኖት አባቶቻችን መካከል መግባባትንንና ፍቅርን እንዲሰጥልን፥ የቤተክርስቲያነችንን አንድነት እንዲጠብቅልን፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፍቅር፥ አንድነትና በሰላም ለመምራት መንፋሳዊ ብቃት ያለው ፓትርያርክ እንዲሾምልን፥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና ጸሎት እንዳይለየን እያለቀስን፥ ላለፈው እየተፀፀትን እንለምን። የማይጠቅመንን የሥጋዊ ጦርናት እንድንታውና የዲያቢሎስ መጫወቻ እንዳንሆን እግዚአብሔር ይጠብቀን።
አሜን!!

Anonymous said...

Nefs ymar. Gizew siders egziabher hulun yadergal! Egn gen Sile bet/n abizten entsely/kemingizewm yebelete/

Beza said...

We really thank you for the information u gave us! but, please try to respect even the dead body of our blessed Father. Remember that our church has taeched and is still teaching all of us to give the proper reputetion for those who deserve it. YEKIDUSAN ABATOCHACHEN AMLAK LEUL EGZIABHER HOY!!! YEABATACHENEN NEFIS BE GENET ANURELEN! AMEN

Anonymous said...

After z afew months death of pop sinoda of Alexandria and now our Father hi it is so mirucle; any ways may God put his soul at z hand of Abrham,Izac and Jacob and may z holy spirit choose z one who dies(strugle) 4 our religion beside him self! God bless us!

Anonymous said...

One of the greatest Ethiopian Orthodox Church learned me (Liq) Aleqa Ayalew Tamiru was martyred five years ago on 20 August 2012.

Aleqa Ayalew fought Aba Paulos ans Aba Girima and condemned both before he martyred for this great church.

Aba Paulos also passed away suddenly and did not even get a chance to repent for what he did.

Let this be a teaching to all these so called church leaders especially Aba Gerima who sacked Aleqa Ayalew from his post without any compensation and pension though he served the church for over 50 years.

This kind of inhumane action does have consequences.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)