August 25, 2012

የአቡነ ጳውሎስ ሥርዐተ ቀብር ሪፖርታዥ


  • READ THIS NEWS IN PDF.
  • መንግሥት - የፓትርያርኩ አብሮ የመኖርና መቻቻል እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል::
  • የውጭ እንግዶች - ፓትርያርኩ ለኢኩሜኒዝም ዓላማ የተጉ (Committed Ecumenist) እንደነበሩ ተናግረዋል::
  • በዐውደ ምሕረት መርሐ ግብር መቀመጫ ያላገኙ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሚኒስትሮችና ዲፕሎማቶች ነበሩ - መድረክ ዝግጅት አይዋጣልንም?
  • በቤተሰቦች ለቀረበው ቅሬታ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ “ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያን ናቸው” ሲሉ ምላሽ:: ሰጥተዋል፤ የቤተሰቡ አባላት ሥርዐተ ቀብሩ በአጭር ቀንና ጉዞ እንዲጠናቀቅ መደረጉ “ጥላቻና ተንኰል ነው” በማለት ይከሳሉ፡፡
  • ስለ አቡነ ጳውሎስ ዕድሜ የተጣረሱ መረጃዎች ቀርበዋል::
  • ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገብረ እግዚአብሔር በተሰኘው የክርስትና ስማቸው ተዘክረዋል::


 (ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 18/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 24/ 2012)፦  የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቀብር ሥነ ሥርዐት ትናንት፣ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም፣ 7፡30 ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ የሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መካነ መቃብር ከሚገኝበት ዐጸድ በስተቀኝ በተዘጋጀለት ሥፍራ በተፈጸመው የአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ግብአተ መሬት÷ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባሎች፣ የአኀት አብያተ ክርስቲያን አባቶች፣ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያን፣ የዓለምና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያን ምክር ቤቶች ተወካዮች፣ በርካታ አገልጋዮችና በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በቀብር ሥነ ሥርዐቱ ፍጻሜ እንደተናገሩት፡- “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ድንበሯ እንዳይጣስ፣ ሰንደቅ ዓላማዋ እንዳይታጠፍ በየጊዜው መሥዋዕትነት የከፈለች ናት፤ አፍሪካውያን የሚኮሩባት ናት፤ ይህ ካቴድራል ይህን መሥዋዕትነት የከፈሉ አባት አርበኞች መታሰቢያ ነው፤ ቅዱስ አባታችን ይህ ታላቅ ታሪካዊ ትርጉም ባለው ስፍራ ነው እንዲያርፉ የተደረጉት፤ ቅዱስ አባታችን የቤተ ክርስቲያን ናቸው፤ እዚህ መቃብር ላይ ቆመን የምንናገረው ስለ ሞትና መቃብር ሳይኾን ስለ ትንሣኤና ሕይወት ነው” በማለት ጥልቅ የማጽናኛ ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡


ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሥነ ሥርዐቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ድንገተኛ ሞት ልብ የሚሠብር አሳዛኝ ክሥተት እንደኾነና ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማቸው በመግለጽ ፓትርያርኩ በሁሉም ረገድ ባሳዩት ተሳትፎ ሁሌም እንደሚታወሱ ተናግረዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ÷ አቡነ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሚና ከአገሪቱ የዕድገት እንቅስቃሴ አንጻር በመቃኘት በእምነቶች መካከል የመቻቻል ባህል እንዲዳብር ውጤታማ ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል፤ አያይዘውም ትምህርትን በማስፋፋትና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከል፤ ከአገር አልፎ በአህጉር ደረጃ ባሳዩት ሰላምን የማስጠበቅ ጥረት፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ክብረ በዓላት በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ጥሪ በማስተላለፍ ፤ ከአገር የወጡ ቅርሶች እንዲመለሱና የቱሪስት መስሕብ እንዲኾኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ዘርዝረዋል፡፡ በይቀጥላልም የቤተ ክርስቲያኒቱ በሰላምና ግንባታ ዙሪያ በሰፊው እንደምትሳተፍ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰቦች ልባዊ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ሀገራችንን ከድኅነትና ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በራሳቸውና በሚመሩት መንፈሳዊ ተቋም በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በተወካያቸው በኩል የተናገሩት ደግሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ በአቶ አሰፋ ከሲቶ አማካይነት የቀረበው የፕሬዝዳንቱ መልእክት÷ አቡነ ጳውሎስ የሀገራችንን ሕዝቦች ከሌሎች የውጭ ወንድማማች ሕዝቦች ጋራ በማቀራረብ፣ በሕዝቦች መካከል የመልካም ጉርብትናና ወዳጅነት መንፈስን በማጠናከር እንዲሁም የሀገራችንን በጎ ገጽታ በመላው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ “በምሳሌነት የሚጠቀሱ ታላቅ መንፈሳዊ አባት ነበሩ” ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ቅዱስነታቸው የትምህርት ተቋማትን በመገንባት የመንግሥትን ጥረት ማገዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያን፣ አሳዳጊ አልባ ሕፃናትን በመርዳት፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከል የፈጸሟቸውን ተግባራት አስተውሰዋል፡፡ መንግሥት ለእኒህ የቅዱስነታቸው ቅዱስ ተግባራት አክብሮትና ዕውቅና እንደሚሰጥ ያስወቁት ከንቲባ ኩማ÷ የፓትርያርኩ አብሮ የመኖርና መቻቻል እሴት ፈለግ በአገልግሎትና ሓላፊነት ላይ በሚገኙት አባቶች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የአኀት አብያተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ልኡካን በየቋንቋቸው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎት አድርገዋል፤ መልእክትም አስተላለፈዋል፡፡ ከዐሥር ያላነሱ የኮፕት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የግብፅ መንግሥት ልኡካንን የመሩት 117ኛው ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ባለፈው የካቲት ወር ማረፋቸውን ተከትሎ ዐቃቤ መንበር ኾነው የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ናቸው፡፡

ብፁዕነታቸው በመልእክታቸው÷ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሞተ ዕረፍት ላይ ተገኝተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ማጽናናታቸውን አስታወሰዋል፤ “የተዋሕዶ እምነትን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም ለማጠናከር እና ለማስከብር የክርስቶስን መስቀል በመሸከም ብዙ መከራዎችን ተጋፍጠዋል” በማለትም በማኅበራዊ አገልግሎት (በትምህርት መስፋፋትና ምእመናን አገልግሎት)፣ ለኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያን ተቋማዊ ነጻነትና የአርስ በርስ አንድነት ታላቅ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በአባቶቻችን በአብርሃም፣ በይሥሐቅና በያዕቆብ እቅፍ እንዲያኖርም ጸልየዋል፡፡

ከአምስት ያላነሱ ልኡካን ይዘው የተገኙት የሕንድ /ማላንካራ/ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የአርመን/ ካቶሊኮስ፣ ኤክሊያቲክ/ አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች የቅዱስነታቸውን ዕረፍት የሰሙት በታላቅ ድንጋጤ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አብያተ ክርስቲያንን በመትከል፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን (social diakonia) በማስፋፋትና ሐዋርያዊ ተልእኮን በማጠናከር፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያን መካከል በሚካሄዱ ንግግሮችና ውይይቶች ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማድረግ ረገድ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የላቀ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው አብራርተዋል፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ ዕሥራ ምእት በአዲስ አበባ የተካሄደውን ሁለተኛውን የኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያን ጉባኤ በአስረጅነት አቅርበዋል፡፡ የአርመን ካቶሊኮስ ተወካዩ “የቅዱስነታቸው ኅልፈት ታላቅ ጉዳት ነው” ብለዋል፡፡ “ኢትዮጵያ በአንድ ሰሞን ሁለት ውድ ልጇቿን አጥታለች” ያሉት የሕንዱ ተወካይ÷ የእግዚአብሔር ሥራ ግን ልዩ በመኾኑ ቅዱስነታቸው በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጠራታቸውን አመልክተዋል፤ ከፍተኛ መጽናናትንም ተመኝተዋል፡፡


ከውጭ የመጡት እንግዶች በሥርዐተ ቀብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት አቡነ ጳውሎስ ለኢኩሜኒዝም ዓላማ መሳካት የነበሯቸውን ተሳትፎዎች አስታውሰዋል፡፡ ኢኩሜኒዝም በአብያተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ጥላቻና ክፉ አስተሳሰብ ለማስወገድና አብሮ ለመሥራት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ሲኾን አቡነ ጳውሎስን ለዚሁ የኅብረቱ ዓላማ የተጉ (Committed Ecumenist) በማለት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ስለነበራቸው ሚና አወድሰዋቸዋል፤ ኅልፈታቸውም በተለይም በዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት በነበራቸው የፕሬዝዳንትነት ሓላፊነት፤ 174 ዲኖሚኔሽኖችና ከ120 ሚሊዮን በላይ አማኞች ይገኙበታል በሚባለው በመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት ዘንድ ታላቅ ጉዳት እንደ ኾነ በዋና ጸሐፊዎቹ በኩል ተገልጧል፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰቦችም ጥልቅ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሁለቱም ኅብረቶች ም/ቤቶች መሥራች አባል ናት፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በ1998 ዓ.ም በብራዚል በተካሄደው ዘጠነኛው የዓለም አብያተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤትን በፕሬዝዳንትነት ከሚመሩ ስምንት የሃይማኖት መሪዎች መካከል አንዱ ኾነው ተመርጠው በመሥራት ላይ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ የፕሬዝዳንትነት ሓላፊነቱ በየሰባት ዓመቱ ምርጫ የሚካሄደበት ነው፤ በመጨረሻ ዓመት የሓላፊነት ዘመናቸው ላይ ይገኙ የነበሩት አቡነ ጳውሎስ እ.አ.አ በ2006 የካቲት ወር በሞስኮ እና በዚሁ ዓመት ነሐሴ ወር በዋሽንግተን በተከናወነው የዓለም እምነቶች መሪዎች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና አፍሪቃን ወክለው በመሳተፍ የዓለም ሰላምንና የአፍሪቃን ችግሮች የተመለከቱ መልእክቶች ማስተላለፋቸውን በሥርዐተ ቀብሩ ላይ ከመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት የወጣውና የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ዜና ሕይወትና ሥራዎች የሚዘረዝረው ኅትመት ያስረዳል፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ዜና ሕይወትና ሥራዎች በንባብ ያሰሙት ብፁዕ አቡነ ገሪማ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለኻያ ዓመታት በፓትርያርክነት የመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በትግራይ ጠቅላይ ግዛት፣ ዐድዋ አውራጃ፣ መደራ አባ ገሪማ ገዳም ተወልደው እምነትንና ሥርዐትን በተለይም ሥርዐተ ገዳማትን በአባ ገሪማ፣ በከሂና (ቸሂና) እና በአባ ሐደራ ገዳማት እያጠኑ ማደጋቸውን፣ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ የዲቁና፣ ከብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ የቅስና ማዕርግ መቀበላቸውን ገልጧል፤ የመነኰሱትም ከሕፃንነታቸው ጀምረው እየተማሩ ባደጉበትና ለ15 ዓመታት ባገለገሉበት በአባ ገሪማ ገዳም ነው፡፡

በ1957 ዓ.ም ቅዱስነታቸው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፈቃድ በአዲስ አበባ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ት/ቤት (አሁን መንፈሳዊ ኮሌጅ) በአዳሪ ተማሪነት ገብተው የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፤ በት/ቤቱም “የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ፣ ፀዋትወ ዜማ፣ የግእዝና የአማርኛ ሰዋስው፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተከታትለዋል” ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስና በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በተሰጣቸው የውጭ አገር ትምህርት ዕድል ከአሜሪካ - ኒው ዮርክ የቅዱስ ቭላድሚር የሩስያ ኦርቶዶክስ ሰሚናርየም በኦርየንታልና ምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቴዎሎጂ ዲፕሎማ (ሜይ፣ 1992)፤ በየል ኒውሄቨን የበርክሌይ ዲቪኒቲ ት/ቤት በኦርየንታል፣ ምሥራቅና ምዕራብ አብያተ ክርስቲያን መካከል ስላለው የነገረ መለኰት ልዩነት የመጀመሪያ ዲግሪ (ሜይ፣ 1966)፤ በነገረ መለኰት ሁለተኛ ዲግሪ እና የዶክትሬት ዲግሪ በፕሪንስተን የነገረ መለኰት ሰሚናርየም አግኝተዋል፤ ከአማርኛና ትግርኛ ሌላ በጣም ጥሩ እንግሊዝኛ የሚናገሩ ሲኾን በጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ዕብራይስጥና ግሪክ ቋንቋዎች ለምርምርና ንባብ በቂ የኾነ ችሎታ እንዳላቸው ተነግሯል፡፡

በፕሪንስተን የቴዎሎጂ ሰሚናሪየም የታሪክ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ትምህርታቸውን በየእርከኑ በንጽጽራዊ መንገድ የሠሩት አቡነ ጳውሎስ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያቸው የሠሩትን ጥናት ከኅልፈታቸው ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ በመጽሐፍ መልክ አሳትመው አስመርቀዋል፡፡ ለመጽሐፉ ዝግጅት በተጻፈው መቅድም ውስጥ እንደተገለጸው÷ አቡነ ጳውሎስ በተጨማሪ ምንጮች እጥረት የገቱትን የጥናቱን ተከታይ ሥራዎች /follow up work on the doctoral dissertation/ ለመቀጠል ያለባቸው ሓላፊነት ጫና ስላደረሰባቸው ለአሁኑ ጥናቱን ባለበት ማሳተም እንደመረጡ ተናግረው ነበር፡፡ ይኹንና በመጽሐፍ መልክ የወጣው ሥራና ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ያቀረቡት ጥናት በመቅድሙ እንደገለጹት አንድ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል የጥናቱ አጨቃጫቂ ክፍል የኾነውና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ውጭ÷ እመቤታችንን ጥንተ አብሶ /ጽነት፣ ጥላ/ እንዳለባት፣ ሞቷም የአዳማዊ ኀጢአት ውጤት ነው ብላ እንደምታምን÷ የቅብጥ ምንጮችን በመጥቀስ ያካተቷቸው ዐረፍተ ነገሮችና አንቀጾች በታተመው መጽሐፍ ውስጥ ተቆንጽለዋል፡፡ በተቺዎች አስተያየት መጽሐፉ ራሱን ችሎ እንጂ “አቡነ ጳውሎስ ለዶክትሬት ዲግሪያቸው የሠሩት ጥናት /ዲዘርቴሽን/ ነው” ተብሎ መቅረብ አልነበረበትም፤ ከኾነም ይህ ለውጥ ተለይቶ ተጠቅሶ ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባ ነበር፡፡ /የዲዘርቴሽኑን ገጽ 302 እና 306 ከመጽሐፉ ገጽ 349 እና ገጽ 353 ተመሳሳይ አናቅጽ ጋራ በማነጻጸር ይመልከቱ/

ማዕርገ ጵጵስና ከመቀበላቸው በፊት አባ ገብረ መድኅን ገብረ ዮሐንስ ይባሉ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ዲን ነበሩ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የታሪክ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ የወንጌል፣ የጋዜጣ፣ የኅትመትና የሬዲዮ መምሪያ በሓላፊነት መርተዋል፤ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትን፤ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን (ለሦስት ዓመታት) በዳይሬክተርነት መርተዋል፡፡ በኻያ ዓመታት የቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና እኒህ ዋነኛ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ መፈጸሚያ መዋቅሮች በሰው ኀይል፣ ዕቅድና በጀት አቅማቸው በምን ኹኔታ ላይ እንደሚገኙ መዘርዘር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ዘመነ ክህነት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ተጠናክሯል፤ ለሰበካ ጉባኤ የሥራ ሂደት መስፋፋት ክትትል ተደርጓል፤ የፈረሱ፣ የተጎዱ፣ የተጎሳቆሉ አብያተ ክርስቲያን ታድሰዋል፤ ተጠግነዋል፤ ታሪካዊ ቅርሶች ተጠብቀዋል” በማለት የዘረዘሯቸው የቅዱስነታቸው ‹ስኬቶች› በነባራዊና ወቅታዊ ኹኔታዎች ዐይን ጥብቅ ግምገማ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በደጀ ሰላም እምነት እኒህ የአገልግሎት መስኰች የፓትርያርኩ ዓለም አቀፋዊ ሰውነት በኢኩሜኒዝም መርሕ (የውጭ ግንኙነት) ጎልቶ በወጣበትና በመንበረ ፓትርያርኩ ቅጽር ይኹን በሌሎች ቦታዎች ሕንፃዎች በተገነቡበት መጠን በስኬት ሊጠቀሱ ይቅርና አሉ በሚባሉበት ደረጃ እንኳ ለመጠቀስ የሚበቁ አይደሉም፡፡ ጥቂቶቹንም ብፁዕነታቸው በአንድ የንባባቸው ክፍል እንዳሉት ለታሪክ ዘጋቢዎች መተው ሳይሻል አይቀርም፡፡

መስከረም 16 ቀን 1968 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ ተቀብለዋል፤ ከእርሳቸውም ጋራ ሌሎች ሁለት ብፁዓን አባቶች አብረው ተሾመው ነበር፡፡ ሹመቱ ከዕውቅናዬ ውጭ የተሰጠ ነው በሚል ለሰባት ዓመታት እስር ተዳርገው የቆዩት አቡነ ጳውሎስ በዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ስብሰባዎችን ተካፍለዋል፡፡ ከእስር ከተፈቱ አንድ ዓመት በኋላ ከዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት ባገኙት የውጭ ትምህርት ዕድል (ብዙ ጊዜ እንደሚባለው በስደት አይደለም) ወደ አሜሪካ አቅንተው በተለያዩ ግዛቶች /ስቴቶች/ አብያተ ክርስቲያንን ተክለዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስን፣ እምነትንና ሥርዐትን ያስተምራሉ የተባሉ ስድስት መንፈሳውያን ማኅበራትንም እንዳቋቋሙ በብፁዕነታቸው የተሰማው ዜና ሕይወታቸው ያስረዳል፡፡

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ከአንድ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ በንባብ ባሰሙትና በኅትመት በተሠራጨው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዜና ሕይወት የተጋጩ የሚመስሉና ከዚህ በፊት ከሚታወቀው የተለዩ መረጃዎች ቀርበዋል፡፡ ለዚህም በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የአቡነ ጳውሎስ የትውልድ ዘመን ነው፡፡ በኅትመቱ የእንግሊዝኛው ክፍል ገጽ አንድ ላይ አቡነ ጳውሎስ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓ.ም፤ በጎርጎሮሳውያን ዘመን አቆጣጠር ደግሞ ኖቬምበር 3፣ 1933 መወለዳቸው ተጽፏል፤ በአማርኛው ክፍል ገጽ 18 ላይ አቡነ ጳውሎስ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥቅምት 28 ቀን 1930 ዓ.ም፣ እ.አ.አ ደግሞ ኖቨምበር 3 ቀን 1938 ተወለዱ በማለት ፈጽሞ የማይገናኙ መረጃዎች ተጠቀስዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በንባብ ባሰሙት ታሪክ ደግሞ የጠቀሱት ጥቅምት 28 ቀን 1928 ዓ.ም የሚለውን ነው፡፡ ብፁዕነታቸው የጠቀሱትንና ሌሎችም የዜና ምንጮች በስፋት የተጠቀሙበትን የትውልድ ዘመን ይዘን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መዋዕለ ዘመን 76 ነው ብንልም የፓትርያርኩ ዕድሜ 80 ነው የሚሉ ሌሎች ምንጮችም አልጠፉም፡፡ በዕድሜ ጉዳይ የሚታየውን ልዩነት እንደ አብነት የጠቀስነው የቤተ ክርስቲያናችንን ስም ይዘው የሚወጡና እንዲህ በስፋት የሚሠራጩ ተቋማዊና ይፋዊ መሠረታዊ መረጃዎች ወደፊት ለታሪክ አጥኚዎች ዕንቅፋት እንዳይኾኑ፣ በግለሰቦች ውድና ፈቃድ ላይ እንዳይመሠረቱ ለመጠቆም እንጂ በምሳሌነት የቀረበው ስሕተት በጠንቃቃ የማጣሪያ ንባብ ሊታረም ይችል እንደነበር በመዘንጋት አይደለም፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር ወቅት አንድ ራሱን የቻለ ትዕይንት የነበረው በዐውደ ምሕረቱ ላይና ዙሪያ ይታይ የነበረው መገፋፋትና መጨናነቅ፣ ይህንንም ሥርዐት ለማስያዝ ሥነ ሥርዐት አስከባሪዎች ራሳቸው ከምእመናኑ፣ ከጋዜጠኞች፣ ከካሜራ ባለሞያዎችና ከእንግዶች ጋራ ሳይቀር ይፈጥሩት የነበረው ጭቅጭቅና ሁካታ ነበር፡፡ ይህም በዝግጅቱ ስክነት ላይ የራሱን ጫና እንዳሳደረ በመርሐ ግብሩ መሪ ጥድፊያና ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ በግልጽ የሚታይ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ መርሐ ግብሮች ከመታጠፋቸው አንጻር የፓትርያርኩ ታናሽ ወንድም ዶ/ር ተወልደ ገብረ ዮሐንስ የነጠቃ ያህል በወሰዱት ድምፅ ማጉያ ለመድረኩ የማይመጥን የቤተሰብ ታሪክ ማውራታቸው ብዙዎችን በኀፍረት ያሸማቀቀ ነበር፡፡

ማዕጠንት የያዙ ብፁዓን አባቶችና የውጭ እንግዶች ሳይቀሩ ወንበር አጥተው ቆመው ከኋላቸው ሊገለበጥባቸው ከደረሰው የሰው ብዛት ጋራ በግፊያ ሲታገሉ የታዩበት ኹኔታ አሳዛኝ ነበር፡፡ ድንኳን ከመትከል ያለፈ የካቴድራሉን ግቢ ስፋት ከሚመጡት እንግዶች፣ ከመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች ፍላጎትና ከተገኘው ሕዝብ ብዛት አኳያ በአግባቡ ከፋፍሎ የሚጠቀም የተቀናጀ የመስተንግዶ ሥርዐት ሊኖረን ይገባ ነበር፡፡

ምእመናንና አገልጋዮች ብቻ ሳይሆኑ በሃይማኖት የሚመስሉንም ኾነ የማይመስሉን የውጭና የሀገር ውስጥ እንግዶች የሚገኙባቸው መሰል የብዙኀን መድረኮች ምንም ዐይነት መነሻ ይኑራቸው÷ መስሕብ የኾኑትን ኦርቶዶክሳዊ እምነትን፣ ሥርዐትን፣ ትውፊትንና ሥልጡንነትን በሁለንተናዊ ገጽታው ከማስተዋወቅ አንጻር የሚፈጥሩትን ዕድል አሟጠን ለመጠቀም የሚያስችል የመርሐ ግብር ዝግጅትና የመስተንግዶ ብቃት ያሻናል፡፡ መድረኮቹ እንደ ትናንቱ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን በሚያገኙበት ኹኔታ ደግሞ አጋጣሚው የበለጠ ሊያስቆጨን ይገባል፡፡ ውጥኑ ቀርቶ ሐሳቡ ጨርሶ እንደሌለን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር አንድ ማሳያ ኾኖ አልፏል፡፡

አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ግብአተ መሬት ከቀኑ 7፡30 ላይ ተጠናቋል፡፡ እንግዶቹም ካቴድራሉን ያጨናነቀው ሕዝብም ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡ ለኛ የቀረልን ጥያቄ ፓትርያርኩ ካረፉ ጀምሮ በብዙዎች አእምሮ የተቀሰቀሰው የቀጣዩ ፓትርያርክ ማንነትና የት መጣ ጉዳይ ነው፡፡

ብዙዎች የቤተ ክርስቲያን አምላክ በመንፈሳዊ ሕይወቱና አቋሙ ነውር ነቀፋ የሌለበት÷ ካህኑም ምእመኑም ይደልዎ ብሎ የሚመሰክርለት፤ ቤተ ዘመድና ጥቅም ከመሰብሰብ ጸድቶ ሃይማኖትን የሚያጸና፣ ምግባርን የሚያቀና፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ የሚያስጠብቅ፣ በትምህርቱና አገልግሎቱ የተመሰገነ፣ በአስተዳደራዊ ልምዱና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቱ የካበተ አባት እንዲሰጣቸው ይጸልያሉ፡፡

ከዚህ ሁሉ በፊትና ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ቢያንስ ሁለት ወሳኝ ቅድመ ዝግጅቶች ያስፈልጋሉ - ሀ) የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የመመለስ፤ ለ) አንድነቱ በሚፈጥረው ድምር አቅም ከቤተ ክህነቱ ከፍተኛ መዋቅር ቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ተቋማዊ ለውጥንና መጠናከርን የሚያመጡ፣ ዘመኑን የዋጁ ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና ዝርዝር መምሪያዎች ዝግጅት፡፡ ይህን ለማድረግ ፍላጎቱም አቅሙም ከሌለን ቀጣዩ ጊዜ ከቀድሞው ፓትርያርክ ዘመን በእጅጉ የባሰ እንደሚኾን ለማወቅ ነቢይ መኾን አያሻውም፡፡

አዎ፣ እኛም ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ጋራ የምንተባበረው ከእንግዲህ በ‹መቃብሩ› ላይ ቆመን መነጋገር የሚገባን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ትንሣኤ ሊኾን ይገባል፡፡

የአባቶቻችን አምላክ የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነትና ሰላም ይጠብቅልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
 NOTE: Two colored pictures, courtesy of MK Website.

7 comments:

Anonymous said...

selamlehulachn yedres ena,
Er keahunu tensayewan yasayen belen letselot enensa mechewn ken bemulu letsom tselot enawelw betelyem betekristianeon ke mengerst leyeto be fiker yemebarken abat endnaye be zemnachn huulu tornet semten tawkenalena tensaten yasayen!
THE KEY FOR PEACE IS IN GOD HAND THROUGH PRAY TENEYEU LE TSELOT!

AMEN

Anonymous said...

የቅ.ፓትሪያርክ ምርጫ የመንፈስ ቅዱስ ምርጫ፤
የቅ. ፓትሪያርክ ምርጫ የእግዚአብሔር ፈቃድ፤ በየሕዝበ ክርስቲያኑ ፀሎትና፤
በተገባቸው አባቶች ብቻ የሚካሄድ ምርጫ እንደሆነ መቀበል ከሆነ....
በስጋ ዕይታ፤ አንዱ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ሲኮንን ሌላው ደግሞ ሲሻ፤ አንዳንድ የፖለቲከ ፓርቲና አማኝ አባ መርቆርዮስ አጋጣሚውን ተጠቅመው ወንበራቸውን እንዲይዙ ሲመኙ ሌላው ደግሞ "የምን እብደት" አይነት ልቦና ሲያሳይ፤ አንዳንዱ ቅድመ ዝግጅት "ግድ" ብሎ ሲለፋ ሌላው ደግሞ ለቅድመ ዝግጅቱ "ቅድመ ዝግጅት" ....
"ከዚህ ሁሉ በፊትና ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ቢያንስ ሁለት ወሳኝ ቅድመ ዝግጅቶች ያስፈልጋሉ - ሀ) የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የመመለስ፤ ለ) አንድነቱ በሚፈጥረው ድምር አቅም ከቤተ ክህነቱ ከፍተኛ መዋቅር ቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ተቋማዊ ለውጥንና መጠናከርን የሚያመጡ፣ ዘመኑን የዋጁ ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና ዝርዝር መምሪያዎች ዝግጅት፡፡"
.....
እንደምዕመን፣ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያናችንና ለእምነታችን ጥሩ አባት ይስጠን

texas

Anonymous said...

Dear Deje Selam,

I appreciate for your reporting in regard with Abune Paulos Funeral Ceremony.Yet you have stated the name of the younger brother of Abune Paulos wrongly as Dr .Tewolde Gebreyohanese.As far as i know him closely in Boston Medhanialem EOTC Church he does not have any doctoral degree or doctoral tittle.I am pretty sure.So i kindly inform you to check this matter from your end.

Demile yalew said...

God shows his power to clean our church by Him wisdom from hands of indirect catholic authority! Then to get the real fathers all synodos members the can ask to God whom is chose by God. Either even the law of 1991 have error from teaching of www.aleqayalewtamiru.org & www.ETHIOPIA THE KING-DOM OF GOD SERVICE . Saint Virgin Mary chalenge peace for our church Amen!!.

Anonymous said...

Egziabher Yimesgen! Kebru yihn yimesl never:-

http://youtu.be/TLJ8kf_LPZU

Unknown said...

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገብረ እግዚአብሔር በተሰኘው የክርስትና ስማቸው ተዘክረዋል::
እውነት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ንስሐ ገብተዋል???

Anonymous said...

"የሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መካነ መቃብር ከሚገኝበት ዐጸድ በስተቀኝ በተዘጋጀለት ሥፍራ..." እሚለው አካባቢ ስደርስ ደከመኝና ማንበቤን ተውኩት። ምናልባት ጥቂት እልፍ ብሎ እንዲህ የሚል ጥቅስ ይኖር ይኾን፦ "በመካነ ጻድቅ ህየ ረሲእ"

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)