August 23, 2012

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ሥርዐተ ቀብር ዛሬ ይፈጸማል


  • የኮፕት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበር ይገኛሉ።
  • አቶ መለስ ዜናዊ (ገብረ እግዚአብሔርበጸሎተ ቅዳሴው ታስበዋል።
  • ጊዜያዊ ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ይገኛሉ።
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 17/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 23/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሥርዐተ ቀብር ዛሬ፣ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም በ6፡00 በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡ ትናንት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ቅዳሴ ተከናውኗል፡፡ በዚህ ወቅት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እንደተናገሩት÷ “የቤተ ክህነቱም የቤተ መንግሥቱም መሪዎቻችን በአንድ ቦታ እንገናኝ ብለው የተቃጠሩ ይመስል በአንድ ወቅት ተጠርተው ሄደዋል፡፡ ሁለቱንም መሪዎች ተራ በተራ እንሸኛቸዋለን፤ ተራ በተራ ነው የምንሸኛቸው፤” ብለዋል፡፡


ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከሌሊቱ 5፡40 በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የተነገረው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በጸሎተ ቅዳሴው ላይ ታስበዋል፡፡ በትግራይ ዐድዋ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን /ደብርኪ/ ሰበካ ተወልደው ማደጋቸው የተነገረው አቶ መለስ ዜናዊ÷ በጥምቀተ ክርስትና መጠሪያ ስማቸው ገብረ እግዚአብሔር እንደሚባልም ተገልጧል፡፡

የቅዱስነታቸው አስከሬን ትናንት 8፡30 ላይ በልዩ ሠረገላ ላይ ኾኖ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተነሥቶ ወደ ካቴድራሉ ሲያመራ፡- ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጡ መዘምራን፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማርሽ ባንድ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የቅብጥ፣ ሶርያ፣ ሕንድና አርመን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን፣ የግሪክ ኦርቶዶክስና ቫቲካን ተወካዮች፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት እንግዶች እንዲሁም በርካታ ምእመናን - በተጠቀሰው ቅደም ተከተል - አጅብውታል፡፡ የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ የክብር ዘብም የብረት ሰላምታ ሰጥቷል፡፡

አስከሬኑ በካቴድራሉ እንደ ደረሰ የሠርክ ጸሎተ ኪዳን ተደርሷል፡፡ ዐቓቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ አጭር ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ሲናገሩ፡- “የቤተ ክህነቱንም የቤተ መንግሥቱንም መሪዎቻችንን በአንድ ወቅት አጥተናል፡፡ እግዚአብሔር ሰጠ፣ እግዚአብሔር ነሳ ብለን መጸለይ ይኖርብናል፤” ብለዋል፡፡ ሌሊቱን ጸሎተ ማሕሌቱ ሲከናወን አድሯል፤ ቅኔዎችም ቀርበዋል፡፡

በዛሬው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር አፈጻጸም ከንጋቱ 12፡00 ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተጀመረው ጸሎተ ቅዳሴ ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳትና የአኀት አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች ባሉበት ተከናውኗል፤ በአሁኑ ሰዓት ጸሎተ ፍትሐቱ እየተጠናቀቀ ይገኛል፤ በይቀጥላል የአኀት አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች በየቋንቋቸው ለቅዱስነታቸው ጸሎት ያደርጋሉ፡፡ ይኸውም የቅብጥ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበር ከአምስት ልኡካን ጋራ፣ የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ከአምስት ልኡካን ጋራ፣ የአርመን ተወካዮች ከሦስት ልኡካን ጋራ፣ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ ጸሎት የሚያደርጉት ጸሎት ነው፡፡ ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት የቅብጥ፣ የሕንድና የአርመን መንበረ ፓትርያርክ ተወካዮች ጸሎት አድርገዋል፡፡

በውስጥና በዐውደ ምሕረቱ በርካታ አገልጋዮችና ምእመናን ተገኝተዋል፤ በዐውደ ምሕረቱ ላይ በተወሰነ መልኩ መገፋፋትና መጨናነቅ ይታያል፡፡ የውስጥ ሥርዐቱ እንደተጠናቀቀ የቅዱስነታቸው አስከሬን በክብር ታጅቦ ወደ ዐውደ ምሕረት ወጥቶ በተዘጋጀለት ቦታ ያርፋል፤ የሊቃውንቱ ያሬዳዊ ወረብ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዝሙሮች፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅኔዎች ይቀርባሉ፡፡ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የተዘጋጀው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ዜና ሕይወትና ሥራዎች ይደመጣሉ፡፡

ከመንግሥት - የኢ... ፕሬዝዳንት ተወካይ፣ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የአኀት አብያተ ክርስቲያን አባቶች፣ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች - የሩስያ፣ የግሪክ፣ ሊባኖስ፤ የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ተወካይ የፖንቲፊካል ካውንስል ካርዲናል የኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያን /ቤት ዋና ጸሐፊ፣ የዓለም ሃይማኖቶች /ቤት ለሰላም ተወካይ፣ የሁሉም የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያን /ቤት ዋና ጸሐፊ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ጉባኤ ተወካይ ንግግሮች ያደርጋሉ፡፡

ልዑል እግዚአብሔር የቅዱስነታቸውን ነፍስ ያሳርፍልን፤ ከማኅበረ ቅዱሳን ይደምርልን፡፡
ተጨማሪ ዜናዎችን ይከአታተሉ፤
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)