August 22, 2012

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ኾነው ተመረጡ

  • ቋሚ ሲኖዶሱን የሚያጠናክሩ ብፁዓን አባቶች ተመርጠዋል::
  • ሕገ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያር ምን ይላል? (ከዜናው መጨረሻ ላይ ያንብቡት)
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 14/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 20/ 2012/ PDF)፦ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ፣ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በፊት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ አድርጎ መርጧል፡፡ ስለዚህም ጉዳይ ዛሬ በ9፡00 ሰዓት በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ለመሠየም ምልአተ ጉባኤው ባካሄደው ምርጫ ሦስት ዕጩዎች ቀርበው እንደነበር የጉባኤው ምንጮች ለደጀ ሰላም ተናግረዋል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 17 መሠረት ለምርጫ የቀረቡትና በሹመት ቀደምትነት ያላቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡


በአሁኑ ወቅት የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከሚከናወን ድረስ ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ እየመከሩ ሲሠሩ እንዲቆዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡ በ1991 ዓ.ም የወጣውና በሥራ ላይ በሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በተተኪ ፓትርያርክ ምርጫ ጊዜም ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር በመኾን ምርጫውን ያስፈጽማሉ፡፡ እርሳቸው ግን ምርጫ ውስጥ አይገቡም፡፡

ብፁዕነታቸው በ1971 ዓ.ም በሦስተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ከተሾሙትና ዛሬ በአገልግሎት ላይ ከሚገኙት 16 አንጋፋ ብፁዓን አባቶች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊም ኾነ ማኅበራዊ ተግባር ዘርፈ ብዙ ነው ያለው የምልዓተ ጉባኤው መግለጫ ቋሚ ሲኖዶሱን ማጠናከር አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋራ አብረው የሚሠሩ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት ሠይሟል፡፡ እነርሱም፡- 1) ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ 2) ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ 3) ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ 4) ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ 5) ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ 6) ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ 7) ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ 

ቅዱስ ሲኖዶስ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ለመምረጥ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር ፍጻሜ በኋላ ቀጠሮ ይዞ የነበረ መኾኑን በማስታወስ ምርጫው ዛሬ ለምን እንደተደረገ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ÷ “መንበር ያለ ሓላፊ አንድም ቀን ማደር ስለሌለበት ለሥርዐተ ቀብሩ ከውጭ የሚመጡትንም ይኹን በሀገር ውስጥ ያሉትን ምእመናንና እንግዶች የሚናዝዝና የሚያሰናብት አባት አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ምልዓተ ጉባኤው ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ በአስቸኳይ ሠይሟል፤” ብለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው እንዲህ ይበሉ እንጂ ዛሬ ምልዓተ ጉባኤው በአስቸኳይ ተስብስቦ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩን እንዲመርጥ ያስገደዱት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር ቀን እንዲለወጥ በመንግሥትና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተሰብ “ግፊት ተደርጓል” ከመባሉ አንሥቶ ሌሎችም ምክንያቶች ሳይኖሩ እንደማይቀር የዜናው ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ


ሕገ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያር ምን ይላል?
አንቀጽ 17
·         ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
1.    ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫም ይካሔዳል፡፡
2.    የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደሥራው ሁኔታ እየታየ 40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይሆናል፡፡
3.    የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ተግባር
. ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉደዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር እየመከረ ያከናውናል፡፡
. በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ሆኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም::

ምንጭ፦ ሕገ ቤተ ክርስቲያን 1991 .

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)