August 17, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ ይካሄዳል፤ መግለጫም ይሰጣል


  • የፓትርያርኩን ቀብር የማስፈጸም ጉዳይ ቅድሚያ ጉዳይ ይሰጠዋል፤
  • ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ እስኪመረጥ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ተወክለው ይሠራሉ፤
  • የአቡነ ጳውሎስ አስከሬን ከተገነዘ በኋላ ግንዛቱ ተፈቶ ዳግመኛ ምርመራ ተካሂዷል፤

(ደጀ ሰላም ነሐሴ 11/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 17/2012/ READ THIS IN PDF)፦ የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ ዛሬ፣ ነሐሴ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት፣ 3፡00 ጀምሮ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፤ ጋዜጣዊ መግለጫም ይሰጣል፡፡ ለአስቸኳይ ጉባኤው በርካታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ሲኾን በተገኙት አባቶች የፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር አፈጻጸም በቀዳሚ አጀንዳነት እንደሚታይ ተነግሯል፡፡


ትናንት ጠዋት በአዲስ አበባ በተገኙት 12 ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ ጋራ ባደረጉት ስብሰባ በአምስት ንኡሳን ኮሚቴዎች የተከፋፈለና 15 አባላት የሚገኙበት ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት ሰብሳቢነት፣ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ሓላፊው ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል ምክትል ሰብሳቢነትና በሊቀ ትጉኃን ኀይለ ጊዮርጊስ ዳኜ ጸሐፊነት የሚመራው ዐቢይ ኮሚቴ የመስተንግዶ፣ የእንግዶች አቀባበል፣ የሚዲያ፣ የአዳራሽ ዝግጅትና የትራንስፖርት ንኡሳን ኮሚቴዎችን በበላይነት ያስተባብራል፡፡

ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እስኪመረጥ ድረስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ቋሚ ሲኖዶሱን በመሰብሰብ በሐላፊነት ይቆያሉ፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 17 ንኡስ አንቀጽ አንድ መሠረት ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ መሾም ነበረበት፡፡

ይኹንና “ድንገተኛ ነው” በተባለው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሞት ሳቢያ በሀገር እና በውጭ አህጉረ ስብከት የሚገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እስኪሰበሰቡ መጠበቅ በማስፈለጉ፣ በይቀጥላልም ከሚመረጠው ፓትርያርክ አስቀድሞ መፈጸም ከሚገባቸው የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያስጠብቁ፣ መሠረታዊ ችግሯቿን ከሚፈትሹ የጥናትና ለውጥ ተግባራት አኳያ ቅዱስ ሲኖዶስን በጊዜያዊ ሊቀ መንበርነት ለሚመራው ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ምርጫ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መወያየት አስፈልጓል፡፡ በዛሬው የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባም የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ምርጫ ከቀብር ሥነ ሥርዐቱ ፍጻሜ በኋላ እንዲኾን ይወሰናል ተብሎ ተገምቷል፡፡

ይህም ኾኖ ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነት የሚመረጡት ብፁዕ አባት በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንደመኾኑ መጠን÷ ዛሬ በሓላፊነት ላይ የሚገኙትና በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ1971 ዓ.ም የተሾሙት አባቶች፤ ከሀገር ውስጥ፡- ብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፤ በውጭ ሀገር በሓላፊነት ላይ ከሚገኙት ውስጥም ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፤ በስደት ከሚገኙትና የዕርቀ ሰላም ንግግር ከሚያካሂዱት ብፁዓን አባቶች ውስጥም አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ናቸው።

በተያያዘ ዜና ትናንት አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ተገኝተው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን አስከሬን ከገነዙ በኋላ “አሟሟታቸው አጠራጣሪ ነው” በሚል በተነሣው ጥርጣሬ ግንዛቱ ተፈትቶ የአስከሬን ምርመራ መካሄዱንና ዳግመኛ ሥርዐተ ግንዘቱ መፈጸሙን የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ለምርመራው መካሄድ ወደ ሆስፒታሉ መጥተው የነበሩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ትእዛዝ ሳይኖርበት እንደማይቀር ተመልክቷል፡፡ ለጥርጣሬው መነሻ የኾነው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከመሞታቸው አስቀድሞ ወስደውታል ከተባለው መድኃኒትና ከዕለቱ ቅዳሴ በኋላ የተመገቡት ምግብ አልተስማማቸውም በሚል የሆድ እጥበት ተደርጎላቸው የነበረ መኾኑ ነው ተብሏል፡፡

ትናንት ጠዋት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በመንበረ ፓትርያርክ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለተገኙት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ምእመናንና ጋዜጠኞች የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ዜና ዕረፍት አሰምተው ሌሎች ጉዳዮች በቀጣይ እንደሚገለጹና ዕለቱኑ ፈጥኖ የሚደረግ ነገር አለመኖሩን በመናገር ካሰናበቱ በኋላ በቅጽሩ የቆየችው እጅጋየሁ በየነ ታሰማው በነበረው ልቅሶ “አባቴን ገድለውብኝ ነው፤ ለጅቦች ሰጥተውኝ ሄዱ፤ አስከሬኑ ይመርመርልኝ” በማለት ታሰማው የነበረው ‹ልቅሶ› በአካባቢው የነበሩትን ሐዘንተኞች አበሳጭቷልም፤ አሳዝኗልም፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)