August 17, 2012

ስለ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ቀብር ከተጨማሪ መረጃዎች ጋር

·  የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ነሐሴ 17 ቀን በ6፡00 በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከናወናል::
·        የቅዱስነታቸው አስከሬን ነሐሴ 16 ቀን ወደ ካቴድራሉ የሚያመራው መንግሥት በሚመድበው ሠረገላ ነው::
·        የመንግሥት፣ የአኀት አብያተ ክርስቲያንና የዓለም አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች ይገኛሉ::
·        ከሥርዓተ ቀብሩ በኋላ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ይመረጣል::
·        ኅብረትን አጠንክሮ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራት ጸሎትን የሚጠይቅ ነው፤ ምእመናንን አንበትንም፡፡” /ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል/
 (ደጀ ሰላም ነሐሴ 11/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 17/2012/ READ IN PDF)፦ የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቀብር ሥነ ሥርዓት÷ ኀሙስ፣ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ በ6፡00 በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲከናወን ወሰነ፡፡


“ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የእገሌ ወእገሌ አይደሉም፤ የሁሉም አባት ናቸው፤” ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ የቀድሞው ፓትርያርክ አስከሬን ሲቀድሱ ባደጉበት፣ ከእስር ከተፈቱም በኋላ ባገለገሉበት፣ ማዕርገ ጵጵስናም ማዕርገ ፕትርክናም በተሾሙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጎን በተዘጋጀለት ሥፍራ እንደሚያርፍ፣ እስከዚያው ድረስ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ እየተገኙ ሐዘንን ለመግለጽ የሚቻል መኾኑን አስታውቋል፡፡

ስለ ሥርዓተ ቀብሩ አፈጻጸም በወጣውና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት [ሕገ ወጥ ተግባራት ሲፈጸሙበት የቆየው ይህ መዋቅር ከፓትርያርኩ ሞት በኋላ ያለው ተገቢነት አጠያያቂ ነው] ጋራ በሚያስተባብረው መርሐ ግብር÷ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አስከሬን አሁን ከሚገኝበትና እስከ ቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ ከሚቆይበት የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተወስዶ ጸሎት ይደርሳል፤ ጸሎተ ቅዳሴም ይቀደሳል፡፡

ከዚያም በዕለቱ ከቀኑ በ7፡00 ላይ መንግሥት በሚመድበው ሠረገላ ተጭኖ፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ታጅቦ በክብር ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያመራል፤ በካቴድራሉም ጸሎተ ፍትሐት ሲደረግለት አድሮ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም ማለዳ በ12፡00 ሰዓት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መሪነት ጸሎተ ቅዳሴው ይከናወናል፡፡

ይህም ጠዋት 3፡00 ላይ እንደተጠናቀቀ የዐውደ ምሕረት መርሐ ግብሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት፣ የአኀት አብያተ ክርስቲያንና የዓለም አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የሌሎች አብያተ እምነት እንግዶች በተገኙበት ሥነ ሥርዓቱ ይቀጥላል፤ የቅዱስነታቸው ሕይወት ታሪክ ይነበባል፤ የሐዘን መግለጫዎችም ይሰማሉ፡፡                                                                                                                                                                       
የዐውደ ምሕረት ሽኝት መርሐ ግብር ቀትር 6፡00 ላይ ከተካሄደ በኋላ የቅዱስነታቸው አስከሬን ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መካነ መቃብር ጎን በተዘጋጀለት ሥፍራ በክብር እንዲያርፍ ተደርጎ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ፍጻሜ ይኾናል፡፡

ዛሬ ተሲዓት ላይ በመንበረ ፓትርያርኩ የተሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ የመሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ንጋት 11፡00 ላይ በተወለዱ በ76 ዓመታቸው ማረፋቸውን አረጋግጠው ተናግረዋል፤ አሟሟታቸው ድንገተኛ መኾኑንና ድንጋጤ መፍጠሩን የተናገሩት ብፁዕ ዋና ጸሐፊው÷ አቡነ ጳውሎስ ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል በተወሰዱበት ምሽት “አብረን አስቀድሰን፤ ቢሮም አብረን ቆይተን ነበር፤ ድንገት አሞኛል ብለው ማክሰኞ ማታ ወደ ሐኪም ቤት ከተወሰዱ በኋላ ዕረፍት እንዲያደርጉ አዝዘዋቸው ነበር፤ በስኳር ሕመም ይታወቃሉ፤ የስኳር ሕመሙ ጠንቅ ኾኖባቸዋል፤ ጾሙም ሕመማቸውን ሳያከፋው አልቀረም፤ እርሳቸው ግን ታመምኹ አቅኑኝ ሳይሉ ፃዕር ጋዕር ሳይበዛባቸው፣ ቅዳሴውንም ሳያቋርጡ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደዋል፤” ብለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በቀጣይ ከፍተኛ አመራሩ ስለሚጠበቅበት ሓላፊነት ያለውን ዝግጁነት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “ኅብረትን አጠንክሮ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራት ጸሎትን የሚጠይቅ ነው፤ ምእመናንን አንበትንም” በማለት የአባቶች፣ አገልጋዮችና ምእመናን አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ መኾኑን በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡

ከምልዓተ ጉባኤው ከግማሽ በላይ ብፁዓን አባቶች የተገኙበትን የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ የመሩት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ተፈጽሞ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እስኪመረጥ ድረስ የያዙት ሓላፊነት እንደተጠበቀ ኾኖ የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስን ስብሰባዎች በመምራት በሓላፊነት እንደሚቆዩ ተገልጧል፤ ከሥርዓተ ቀብሩ በኋላ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እንደሚመረጥ ተመልክቷል፡፡

በ1991 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን ምዕራፍ 3 አንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ (2) መሠረት እንደተደነገገው÷ “የቋሚ ሲኖዶስ ሰብሳቢው ፓትርያርኩ ነው፤ ፓትርያርኩ በማይኖርበት ጊዜ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ተወክሎ ሰብሳቢ ይኾናል፡፡ አባላቱም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተመረጡ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ወይም ኤጲስ ቆጶሳት ይኾናሉ፡፡”
በአሁኑ ወቅት ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስና የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ጋራ የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በመኾን የሚሠሩት ብፁዓን አባቶች÷ አቡነ ኤልሳዕ፣ አቡነ ዮናስ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ እና አቡነ ኤጲፋንዮስ ናቸው፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

2 comments:

Anonymous said...

Dear Dejeselam

When I wake up in the morning the first priority job is checking ur website.

You are the eyes and ears of The Ethiopian Orthodox Church. Excellent job even before any mass media got the news u are the first blog who broke the news to the world.
Well done.

That shows how you are very close to the church. Your website is visited by a millions of we TEWAHEDO sons and daughter.

May GOD bless u all.

Anonymous said...

Thanks for the update, DS.

These days, you are posting a lot of updates as new articles. I don't know what your reason is, but i think it is better if you just updated the original post instead. You can use different fonts (e.g. bold, or different color) to highlight the changes.

Just my personal view.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)