August 11, 2012

ቅ/ሲኖዶስ የ”ጉባኤ አርድእት” ነን ባዮቹን እንቅስቃሴ “ተቀባይነት የሌለው ነው” በሚል እንዲታገድ ወሰነ


  • በመሥራችነት ከተጠቀሱት ግለሰቦች መካከል ስለ እንቅስቃሴው ምንም የማያውቁና በፓትርያርኩ ስም አስገዳጅነት የተሰባሰቡ ይገኙበታል።
  • እንቅስቃሴው ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ብሎጎች ጋራ ያለውን ግንኙነት ይፋ አድርጓል።

(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 5/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 11/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት መጽናትና ለአስተዳደራዊ አንድነቷ መጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ውሳኔዎች መጠናቀቁን ተከትሎ÷ የአባ ጳውሎስን ዐምባገነናዊ አሠራር ለማጠናከርና ቡድናዊ ጥቅሞቹን ለማሳካት ከፓትርያርኩ ባገኘው ቀጥተኛ ፈቃድ ራሱን “ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ብሎ በመጥራት ኅቡእ እንቀስቃሴ ሲያካሂድ የቆየው ቡድን በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ታገደ፡፡


በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ፊርማ በቁጥር 486/836/2004 በቀን 25/11/2004 ዓ.ም ወጥቶ÷ በአድራሻ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በግልባጭ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት፣ ለፌዴራል እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው÷ ራሱን “ጉባኤ አርድእት” ብሎ የሚጠራውን ቡድን ዓላማና ፍላጎት የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አያውቀውም፡፡ የቡድኑ መቋቋም የቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና የሌለው ከመኾኑም በላይ የቅዱስ ሲኖዶሱን ፈቃድ ሳያገኝና ሳይፈቀድለት በኅቡእ መንቀሳቀሱ “ተቀባይነት የሌለው ነው” ብሏል ጽ/ቤቱ፡፡ በመኾኑም ቡድኑ በተጠቀሰው ደብዳቤ መታገዱንና ይኸው የእግድ ውሳኔም ለሚመለከተው ሁሉ እንዲገለጽ አስታውቋል፡፡

የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደተናገሩት÷ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት “ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ነን ባይ ግለሰቦች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ የእግድ ውሳኔ ያስተላለፈው ጥያቄው ለቋሚ ሲኖዶስ በአጀንዳነት ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበትና አባ ጳውሎስም ሳይቀሩ “አላውቀውም” በሚል ከተገዘቱበት በኋላ መኾኑ ተገልጧል፡፡

የቡድኑ ዋነኛ አመራሮች (አባ ሰረቀ፣ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን፣ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን፣ አእመረ አሸብር) “የጠሯችኹ ቅዱስነታቸው ናቸው” በሚል ስልክ እየደወሉ በፓትርያርኩ ስም ያስፈራሯቸው አንዳንድ ግለሰቦች÷ በኅቡእ ይደረግ በነበረው ስብሰባ ላይ ተገደው መሳተፋቸውን፣ የቡድኑ ዓላማ የሚታመንበት ከኾነ እኛ ብቻ ሳንኾን ሁሉም የቤተ ክህነት ሠራተኛ በአዳራሽ በተገኘበት ስለምን እንደማይደረግ መጠየቃቸውን ተናግረው እንደ ነበር ተዘግቧል፤ ሌሎቹም ቡድኑ ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባቀረበው ሰነድ ላይ በመሥራችነት ስማቸው ስለመጠቀሱ እንኳ እንደማያውቁና ጉዳዩን በሕግ እንደሚከታተሉት ተናግረዋል፡፡

ደጀ ሰላም ምንጮች እኒህን በመምሪያ ሓላፊነትና በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የሚገኙ ቅሬታ አቅራቢ ግለሰቦች ስም ዝርዝር ያደረሱን ቢኾንም ለሥራ ዋስትናቸውና ለማኅበራዊ ደኅንነታቸው ስንል ከመግለጽ ተቆጥበናል፡፡ ቁም ነገሩ ግን÷ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ብሎጎች ጋራ ቁርኝት የፈጠሩት “ጉባኤ አርድእት” ነን ባይ ግለሰቦች ማኅበረ ቅዱሳንን የሚያርዱና የሚያንቀጠቅጡ መኾናቸው ይቅርና የራሳቸውን ህልውና በቅጡ ማቆም የተሳናቸው ለዐምባገነንት ያደሩ ጥቅመኞችና የተርእዮ ሰዎች መኾናቸው መጋለጡ ነው፡፡  

“ጉባኤ አርድእት” ነን ባዮቹ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የ”ዕወቀኝ” ጥያቄ ያቀረቡት÷ “ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለማሻሻል እና ስለ ማኅበራት የቀረቡትን ጥናቶች ተግባራዊነት ለማገዝ” በሚል ሰበብ አባ ጳውሎስን ከቅዱስ ሲኖዶስ በላይ አመራር ሰጪና ወሳኝ ለማድረግ፤ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን፣ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበርና የመሳሰሉትን አዳክመውና አፈራርሰው የግልና የቡድን ጥቅሞቻቸውን ለማሳካት አስበውና ተስማምተው በኅቡእ ሲያካሂዱ የቆዩት እንቅስቃሴ ከመጋለጡ ጋራ ተያይዞ ነበር፡፡ ይህም ኾኖ በአንድ በኩል የጀመርነው ማኅበር ጉባኤ ነውእያሉ በሌላ በኩል ደግሞአቋማችንን በአንድነት ለማራመድ ኅብረት አስፈለገን እንጂ ራሳችንን እንደ ማኅበር አንቆጥርም በሚሉና በመሳሰሉት እርስ በርስ የተምታቱ አንቀጾች የታጨቀውና ሰኔ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የቀረበው የቡድኑ የ”ዕወቀኝ” ጥያቄ ቀደም ሲል ስለ ኅቡእ እንቅስቃሴው የተገለጡትን ሐቆች የሚያረጋግጥ መኾኑ ተዘግቧል፡፡

ቡድኑ ጥያቄውን ባቀረበበት ደብዳቤ ላይ የሚታየው አስገራሚ ጉዳይ በአድራሻ ለቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራር አካል የጻፈውን ማመልከቻ በሌለው ዕውቅናና ባልተሰጠው ፈቃድ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ውጭ ለኾኑ መንግሥታዊ አካላት ጭምር ግልባጭ ማድረጉ ነው፡፡

ቡድኑ ጥያቄውን ካቀረበ አራት ቀናት በኋላ (ሰኔ 26 ቀን 2004 ዓ.ም) የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ለጥበቃ አገልግሎት ክፍል በሰጠው ትእዛዝ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ መሰብሰብ እንደማይችል በዚሁ የጡመራ መድረክ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ይህም እግድ አባ ጳውሎስ ቡድኑ በኅቡእ የወጠነው እንቅስቃሴ ለሚፈጥረው ነውጥ ሓላፊነቱን እንደሚወስዱ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ከተሰጣቸው በኋላ የተላለፈ ነበር፡፡ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ካስተላለፈው እግድ በኋላ ዋነኞቹ የእንቅስቃሴው አመራሮች አባ ሰረቀ ለስሙ የያዙትንና ነገር ከመጎንጎን በቀር የረባ ቁም ነገር ያልፈጸሙበትን የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ቢሮ መስተዋት ዙሪያውን በወረቀት በመከለል መሰብሰባቸውን ቀጥለው እንደ ነበር የዜናው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

“የጾምና ሱባኤ ወቅት አይመቻቸውም” የሚባሉትና የመንፈሳውያን ማኅበራትን የውጭ እንቅስቃሴ “ሽባ እናደርጋለን” ብለው መዛታቸው የሚነገርላቸው አባ ሰረቀና ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን÷ መንፈሳውያን ማኅበራትንና ኦርቶዶክሳውያን የጡመራ መድረኮችን ለማዘጋት ሰሞኑን በሚዶለትበት ሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ሲኾን÷ አባ ሰረቀ በመምሪያ ዋና ሓላፊነታቸው አጋጣሚ በእጃቸው የገቡና በተለይም ማኅበረ ቅዱሳንን የሚመለከቱ ሰነዶችን ጭነው መውሰዳቸው ተመልክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የቡድኑ አመራሮች የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያስተላለፈባቸውን የእግድ ውሳኔ አስቀድመው በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ብሎጎች ላይ በማውጣት ከቀድሞም ያላቸውን የዓላማና ጥቅም ግንኙነት በራሳቸው ጊዜ ይፋ አድርገውታል፡፡

የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትንና ንጹሐን ግለሰቦችን ስም ከማጥፋት ጀምሮ ከወቅቱ የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ አንጻር የመንግሥትን ቀልብ ስቦ በመንፈሳውያን ማኅበራት ላይ (በዋናነት ማኅበረ ቅዱሳንን ዒላማ በማድረግ) የኀይል ርምጃ ያስወስድልናል ያሏቸውንና ሌሎችም የሐቅ ጠረን የማይገኝባቸውን አሉባልታዎች እያናፈሱ ይገኛሉ፡፡ እንደ ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን ያሉት የ“ሬማ ቸርች” ቆራቢዎች ደግሞ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር ጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ሥልጣንና ሌሎችም ተባባሪዎቻቸውን ተጠቅመው የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር በኮሌጁ የሚገኘውን ቢሮውን እንዲያጣ አድርገዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ሀብት በሚያባክንና ገጽታዋን በሚያበላሽ አኳኋን የአባ ጳውሎስን 20 ዓመት በዓለ ሢመት ለማድመቅ የተንከላወሱትን “ውሉደ ጳውሎስ”ን በግብር በመተባበር ከአካዳሚያዊ ዲሲፕሊን ውጭ የአባ ጳውሎስን የዶክትሬት ጥናት ጽሑፍ እንደ ድርስ መጽሐፍ ኤዲት በማድረግ ሕጸጻቸውን ለመሰወር የሞከረው ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል÷ ማኅበረ ቅዱሳን በተለያዩ ጭብጦች ላይ ጥናታዊ መድረክ ለማካሄድ የሚያቀርባቸውን የአዳራሽ ጥያቄዎች፣ በቅርስ ዙሪያ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮች ላይ ራሱን በብቸኛ ተጠሪነት በመሠየም ቢሮክራሲያዊ ዕንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በዋና ሓላፊነት ተቀምጦ “መምሪያውን እየገደለው ነው” የሚባለው አእመረ አሸብር ኦርቶዶክሳዊነታቸው ለተመሰከረላቸው ቀናዒ ሰባክያነ ወንጌል ተልእኮ አስተዳደራዊ ድጋፍ በመንፈግ እንደ አሰግድ ሣህሉ ያሉ የለየላቸው መናፍቃን እስከ ክብረ መንግሥት ድረስ የሚፈነጩበትን ፈቃድ ይሰጣል፡፡

ይህንና ይህን የመሳሰሉ የማን አለብኝነት አካሄዶች ቀደም ሲል እንደገለጽነው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደር ከመሠረቱ ለመለወጥ በቢሮክራሲው ውስጥ ማካሄድ የሚገባንን ዘርፈ ብዙ ተጋድሎ ያጠናክረው እንደኾነ እንጂ አያላላውም፡፡ ለዚህም አሁን ቋሚው ቅዱስ ሲኖዶስ በመከረበት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የሕገ ቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለማስከበር እንደ “ጉባኤ አርድእት” ባሉ ሕገ ወጥ ቡድኖች ላይ የወሰዳቸው ርምጃዎች ያላቸው ፋይዳ አጠራጣሪ አይኾንም፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)