July 29, 2012

የአቡነ ጳውሎስ የማዕረግ ስም ላይ “ዓለም አቀፍ የሰላም አምባሳደር” የሚል ተጨመረ


  • READ THIS NEWS FEATURE IN PDF.
  • ስለ አቡነ ጳውሎስ ኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመት በክራውን ሆቴል ለሦስተኛ ጊዜ ይደገሳል።
  • የመንበረ ፓትርያርኩ ሙስና ለጥቅመኛ የውጭ ቡድኖች ‹መስሕብ› ኾኗል - ራእይ ለትውልድ አንዱ ነው።
  • የጠቅ/ቤ/ክህነቱ “የምግባረ ሠናይ አጠቃላይ ሆስፒታል” ኦዲት ተደርጎ አያውቅም።
  • ሰሞናዊው ድግስ “ለመጨረሻው የአቡነ ጳውሎስ በዓለ ሢመት የቁም ተዝካር” በሚል እየተነገረለት ነው።
  • “የሰውዬው [አባ ጳውሎስ] መታወሻ (legacy) አውዳሚነታቸው ነው። እርሳቸውም፣ እኛም እየበላን ያለነው ቀደምት ፓትርያርኮች ያስቀመጡትን ሀብት ነው።” (የቤተ ክህነቱ ታዛቢዎች)
  • ሐምሌ 22ን - እንደ አቡነ ጳውሎስ ወይስ እንደ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ አቡነ ጴጥሮስ?

(ደጀ ሰላም፤ ሐምሌ 21/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 28/ 2012)ቀደም ሲል ባስነበብናቸው ዘገባዎቻችን እንደጠቆምነው ሐምሌ አምስት ቀን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የፍሰስ ተፋሰስ፣ ብላ - ጠጣ ወጪ (extravaganza) የተጀመረው የድግስ ጋጋታ የአባ ጳውሎስን ግለሰባዊ ጥቅም እና ዝና በሚያጠናክር አኳኋን ቀጥሎ ይገኛል፡፡ የፓትርያርኩን ከንቱ ውዳሴ፣ ዝናና ጥቅም ወዳድነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በበዓለ ሢመታቸው አከባበር ዙሪያ ከተሰለፉት መካከል÷ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ታዋቂ ሰዎችን ስም ከፊት እያሳየ ጥቅም በማጋበስ የሚታወቀው “ራእይ ለትውልድ” የተባለው ድርጅት፤ እንደ እጅጋየሁ በየነ፣ ቀሲስ ግሩም መልአክ ታዬ (ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት)፣ “ጉባኤ አርድእት” ነን የሚሉት እነ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ በሃይማኖት ሕጸጽ ጥያቄ የሚጠብቀው በጋሻው ደሳለኝ፣ አሰግድ ሣህሉና መሰሎቻቸው እንደየሚናቸው ግላዊና ቡድናዊ ጥቅሞቻቸውን እና ባለሟልነታቸውን እያዳበሩበት ይገኛሉ፡፡

የአባ ጳውሎስን ኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመት ምክንያት በማድረግ እሑድ ሐምሌ 22 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት በክራውን ሆቴል “የእንኳን አደረሰዎ” የምሳ ግብዣ እንደሚካሄድ ታወቀ። የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፍ ተልእኮ በመዘከር ስም ግለ ሰብእናቸውን በሚያጎላ መንገድ የተዘጋጀ “መጽሐፍ”ም ይመረቃል ተብሏል፡፡ የክራውን ሆቴሉ ምሳ ግብዣ ለድግስ አፍቃሪው ፓትርያርክ የስጦታ ጋጋታ እና የውዳሴ ዝናም ከማዝነም ባለፈ ኢትዮጵያ የመንበረ ፕትርክናውን ነጻነት ከ53 ዓመት በፊት ስትቀዳጅ ከተያዙት “መሠረታዊ ራእዮች” አንዳቸውን በመለስተኛ ደረጃ እንኳ ለማሳካት የማገዝ ፋይዳ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

በተሰራጨው የጥሪ ካርድ ላይ እንደተመለከተው÷ የምሳ ግብዣውን የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤቱ “ውሉደ ጳውሎስ” ከተሰኙት የአቡነ ጳውሎስ ቤተ ዘመዶች - ጥቅመኞቹ እነእጅጋየሁ በየነ - የ‹ጉባኤ አርድእት› አመራሮች - አርባና ኀምሳ ሺሕ ብር የአድባራትንና ገዳማትን ገንዘብ በፖስታ እያሽጉ በአቡነ ጳውሎስ ዘመዶች ስም በተከፈቱ የባንክ ቋቶች ውስጥ የሚከቱ ሹመት አስጠባቂና ሹመት ፈላጊ አለቆችና መነኰሳት ነን ባይ ‹ቆሞሳት› - ሕገ ወጦቹ እነበጋሻው ደሳለኝ ጋራ የሚያዘጋጁት እንደኾነ መገለጹ÷ በዓለ ሢመቱ በግላዊና ቡድናዊ የጥቅም ትስስሮች የቤተ ክርስቲያናችን ሀብት የሚባክንበት፣ የሚዘረፍበት ለመኾኑ ዐይነተኛ ማሳያ ነው፡፡

በዋናነት ‹ውሉደ ጳውሎስ› የተሰኘው ቡድን እንዳዘጋጀው ለተገለጸው ለዚሁ ምሳ ግብዣ ጥሪ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይኹንታ ያለበት ለማስመሰል በጥሪ ካርዱ ጀርባ ላይ የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ማኅተም እንዲያርፍበት ቢደረግም÷ ለሼራተኑ ራት ግብዣ ቀርቦ የነበረውን የገንዘብ ወጪ ጥያቄ ውድቅ ያደረጉት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሕመም ሳቢያ ይህን ለማወቅና ለመፍቀድ በሚችሉበት ኹኔታ ውስጥ እንዳልኾኑ የደጀ ሰላም ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ይልቁንም የጥሪ ካርዱን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ስምና ማኅተም ማጀባቸው ሳያንስ የመምሪያና የክፍል ሓላፊዎች ያለፍላጎታቸው እየፈረሙ እንዲወስዱ በማድረግ በኩል መዝገብ ቤቱን፣ የአስተዳደር እና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያዎችን የተቆጣጠረው የአቡነ ጳውሎስ ፈቃድና ጥቅም አስጠባቂ መዋቅር ሲዋከብ መታየቱ ተገልጧል፡፡

በጥሪ ካርዱ ሽፋን ላይ ከሚታየው የአቡነ ጳውሎስ ሥዕለ ገጽ ሥር ፓትርያርኩ በሃይማኖት ሕጸጽ ያስጠየቃቸውን ‹ንጽጽራዊ ጥናት› ሠርተው የተቀበሉት የነገረ መለኰት ዶክትሬት ማዕርግ ለፓትርያርክነት (ለካህናትና ምእመናን መንፈሳዊ አባትነት) ካበቃቸው የብፁዕ ወቅዱስ ማዕርግ አስቀድሞ ተጽፏል - “ዶክተር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ” ይላል፡፡ የጥሪው መልእክት በሰፈረበት ጽሑፍም ከረጅሙና ብዙዎች እያምታቱ በመጥራት ከሚቸገሩበት የአቡነ ጳውሎስ ‹አስማተ ማዕርጋት› ቀጥሎ “ዓለም አቀፍ የሰላም አምባሳደር” /Internatinal Ambassador for Peace/ የሚል አዲስ ሥያሜ ተጨምሮ ይነበባል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 14(1) ፓትርያርኩ ከተሾመበት ቀን ጀምሮ በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚጠራበት የማዕርግ ስምና መንበር “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እገሌ [ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ] ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት” የሚል ብቻ እንደ ኾነ ተደንግጓል፡፡ ብዙዎቹ ብፁዓን አባቶች እንደሚያስረዱት አሁን በጥሪ ካርዱ ላይ የሚታየውን ጨምሮ በሕጉ ከተደነገገው ውጭ በተውሳክ የገቡት የአቡነ ጳውሎስ መጠሪያዎች በገዛ ፈቃዳቸው የተጨመሩ፣ ለቤተ ክርስቲያን ክብር የማይበጁ፣ ስመ ማዕርግ ለመኾንም የማይመጥኑ ናቸው፡፡

የበዓለ ሢመቱ አከባበር በዚህ መልኩ በቀጠለበት ኹኔታ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞችና አንዳንድ ሓላፊዎች እየባከነና እየተዘረፈ ባለው የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ሐዘናቸውን፣ ምሬታቸውንና ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ሐዘናቸው በቀደሙት ፓትርያርኮች ዘመን ምንም እንዳልተሠራና በእርሳቸው ዘመነ ፕትርክና ግን “ትንሽ ነገር ሲሠራ ብዙ ሥራ እንደተሠራ ያስመስላል” በሚል በበዓለ ሢመታቸው ቀን የተናገሩት ቃልና በአንጻሩ የሚታየው ዘረፋና ብኩንነት ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ አባ ጳውሎስን ክፉኛ የሚተቹት ሠራተኞቹ እና ሓላፊዎቹ÷ “የሰውዬው [አባ ጳውሎስ] መታወሻቸው (legacy) አውዳሚነታቸው ነው፤ እርሳቸውም እኛም እየበላን ያለነው ቀደምት ፓትርያርኮች ያስቀመጡትን ሀብት ነው፤” በማለት ከዚህ ያለፈ ዝክረ ነገር እንደማይኖራቸው በመግለጽ ራሳቸውንም ፓትርያርኩንም ይገሥጻሉ፡፡

ለቤተ ክህነቱ ማኅበረሰብ ከልማታቸው ይልቅ አውዳሚነታቸው፣ እልከኛነታቸውና በቀለኛነታቸው አመዝኖና ከፍቶ  በትውልዱ ዘንድ የቀረላቸው በጎ ትውስታ እንደማይኖራቸው የሚነገርባቸው አባ ጳውሎስ÷ ወጪው እየጨመረና አሳሳቢ እየኾነ ከመጣው ጤናቸው [እርሳቸውም ቅሉ ለመመጻደቅ ይኹን ለማማረር እንደሚናገሩት “የበሽታ ጎሬ ነኝ” ይላሉ] አንጻር÷ በብዙዎች ዘንድ ‹የመጨረሻ ይመስላል› የተባለውን በዓለ ሢመታቸውን ለማድመቅ “በውጭ ኮበሌዎችን እየሰበሰቡ መደገስ” መምረጣቸውን ሠራተኞቹና ሓላፊዎቹ ነቅፈው አጸይፈው ያስረዳሉ፡፡ ይህንኑ ‹የመጨረሻቸው ሊኾን ይችላል› በተባለው በዓለ ሢመታቸው የሚታየውን የድግስ ጋጋታ “ስም አጠራርን (ቀብርን) ማሣመርያ፣ ወዳጅነትን መግዣ የቁም ተዝካር ነው” ሲሉ ያላገጡበትም አልጠፉም፡፡

የሠራተኞቹና ሓላፊዎቹ ምሬት ደግሞ የአቡነ ጳውሎስ ኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመት በሕገ ቤተ ክርስቲያን በማይታወቀው የልዩ ጽ/ቤት መዋቅራቸውና “ራእይ ለትውልድ” በተባለው አካል አዘጋጅነት ለሁለተኛ ጊዜ በሼራተን አዲስ በተከበረበት ዕለት ‹በስጦታ› የተበረከተላቸውንና በስማቸው የሚሠራውን “የካንሰር፣ ቲቢ እና ኤድስ የሕክምና እና ማገገሚያ ማእከል” ግንባታን ወጪ ይመለከታል፡፡ ይህ ማእከል ብር 200 ሚልዮን እንደሚጠይቅና ለሥራው ማስጀመሪያ ብቻ ግማሽ ሚልዮን ብር እንደሚያስፈልግ ያሬድ ግርማ የተባለው የ”ራእይ ለትውልድ” ተወካይ በዕለቱ ባሰማው ዲስኩር ውስጥ ተገልጧል፡፡ ምሬቱ ታዲያ ተፈጻሚነቱ ብቻ ሳይኾን ጤናማነቱ አጠራጣሪ ለኾነው የሕክምናና የማገገሚያ ማእከል ግንባታ ካህኑና ምእመኑ በኑሮ ውድነት ውስጥ በመዋጮ ጥያቄ ሊሠቃይ የሚችልበት ኹኔታ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ግዴታውን የተወጣው ካህኑና ምእመኑ÷ ለአኵስም ጽላተ ጽዮን ማደርያ እድሳት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ 425 ሚልዮን ብር ያወጣል ለተባለው የቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ግንባታ ያለፈቃዱ የአጥቢያው ሙዳየ ምጽዋት በእነ ንቡረ እድ ኤልያስና ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን እየተመዘበረ እንደሚገኝ ሠራተኞቹ አስታውሰዋል፡፡

የሠራተኞቹና ሓላፊዎቹ ስጋት ደግሞ የ”ራእይ ለትውልድ” አመራሮች የኋላ ማንነትና አቡነ ጳውሎስ የፈጠሩት ትስስር ነው፡፡ የደጀ ሰላም ምንጮች እንደሚገልጹት እንደ ያሬድ ግርማ ያሉት የ”ራእይ ለትውልድ” አመራሮች ቀደም ሲል በ”ኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላምና ልማት ፎረም” ስም ተደራጅተው በርዳታ ካገኙት እስከ ሁለት ሚልዮን ብር /በዋናነት ከሼኽ መሐመድ ሑሴን አላሙዲ/ ውስጥ ጥቂት የማይባለውን ለግል ጥቅማቸው ውለዋል ተብለው የሚነገርላቸው ናቸው፡፡ አሁን በሕይወት የሌሉትን ፕሮፌሰር ክንፈ አብርሃምን የበላይ ጠባቂ በማድረግ ከፖለቲካም ከሃይማኖትም አድሏዊነት ነጻ ኾነን በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሴት ተማሪዎችን እየደገፍን ነው የሚሉት እነ ያሬድ ያገኙት ፋይናንሳዊ ድጋፍና በተጨባጭ ያሳዩት የሥራ ውጤት ራሳቸውን ከመጥቀም በቀር ስማዊ ብቻ ኾኖ መቅረቱ ነው የተገመገመው፡፡

አሁን ደግሞ እንደሚሰማው በእነ እጅጋየሁ በየነ ‹ባለሟልነት› ከፓትርያርኩ ጋራ ከተገናኙ በኋላ በፓትርያርኩ አማካይነት ደግሞ “የካንሰር፣ ቲቢና ኤድስ ሕክምናና ማገገሚያ ማእከል” በመገንባት ስም የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን የበላይ ተቆጣጣሪ በማድረግ ለመፍጠር የታሰበው ቁርኝት በመጨረሻው ሰዓት የ”ራእይ ለትውልድ” አመራሮች የግልና የቡድን ጥቅማቸውን አካብተው ለመጥፋት የሚወጣጡበት እርካብ እንዳይኾን ከሚነሡ ጥርጣሬዎች የጸዳ አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር÷ በዓለምና በአገር ደረጃ ለሰላም ጥረት በማድረግ ዓለም አቀፍ ፓትርያርካዊ ሰውነት አላቸው የሚባሉት አቡነ ጳውሎስ፤ ፓትርያርኩ ለማእከሉ ግንባታ የበላይ ተቆጣጣሪ ያደረጓቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የቲቢን፣ ኢች.አይ.ቪ/ኤድስንና ወባን መስፋፋት በመግታት ባገኟቸው ዓለም አቀፍ ሽልማቶች እንዳላቸው በሚነገረው ከፍተኛ ተቀባይነት የለጋሾች ፈንድ ለማግኘት አያዳግት ይኾናል፤ በታዳሚነት ከተጋበዙት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልኾኑት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ሓላፊዎቻቸው አማካይነት የተወከሉት እነ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ባለሥልጣን፣ ሚድሮክ፣ ሰን ሻይን፣ ተክለ ብርሃን እምባዬ፣ ሠራዊት ፍቅሬ የመሳሰሉት የቢዝነስ አካላትና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች የፈቀዱትን ያህል ይወረውሩ/ይደግፉ ይኾናል፤ በአናቱም በማእከሉ ግንባታ ስም ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከአድባራትና ገዳማት እንዲሁም ከልማት ተቋማት የሚወሰድ ገንዘብ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፤ መሬቱም እንደ ሕጉ ከሊዝ ነጻ ሊገኝ ይችላል፡፡ ጥያቄው ግን÷ የሚገኘው ገንዘብ ተጠብቆ በሚቆይበትና በሚንቀሳቀስበት ወቅት መደረግ የሚገባው የቁጥጥር አግባብ ነው፡፡

ከዚህ ጋራ በተያያዘ በዲዛየኑ ላይ እንደሚታየው ሄሊኮፕተር ሳይቀር ያሳርፋል የተባለው የሕክምናና ማገገሚያ ማእከል÷ በአቡነ ጳውሎስ ስም ከመሠየሙ ጀምሮ በተቀራራቢ ስያሜ ያሉ ሌሎች የሕክምና ማእከላት ከመኖራቸው አኳያ አወዛጋቢ ሊኾን ይችላል መባሉ አንድ ነገር ኾኖ÷ ሌላው የምዝበራ ሰበብና ማእከል እንዳይኾን ስጋቱ አለ፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የሚጠቀሰው በሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ሥር የሚገኘውና ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረጃ ያደገው የምግባረ ሠናይ ክሊኒክ ነው፡፡

ይኸውም ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት፣ በአስከፊ የኑሮ ኹኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጤንነት ይጠበቅበታል በሚል ቀላል የማይባል ገንዘብ የሚገኝበት ይኸው አጠቃላይ አባ ጳውሎስና የጥቅም አቀባባዮቻቸው ከሚገለገሉበት በቀር ለአንድም ጊዜ እንኳ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ተመርምሮ የማያውቅ መኾኑ ነው፡፡ በሼራተኑ የራት ድግስ የ”ራእይ ለትውልድ” አመራር ያሬድ ግርማ ሲናገር÷ የሕክምናና የማገገሚያ ማእከሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ምንም ዐይነት ቁጥጥር በማታደርግበት ኹኔታ ለአቡነ ጳውሎስ መታሰቢያነት መሰጠቱ “ኢትዮጵያውያን ያለብንን መሪዎችን ያለማክበር፣ የመጎተት ባህል” ለመለወጥ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብሏል፡፡ በአንጻሩ ም/ጠ/ሚኒስትሩ አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ አባ ጳውሎስን እያወደሱም ቢኾን “ለኻያ ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በሓላፊነት መምራት ከባድ ነው” ብለዋል፤ ቁም ነገሩም ያለው እዚሁ ላይ ነው፡፡ እውን አቡነ ጳውሎስ ለኻያ ዓመታት በፓትርያርክነት የቆዩት አቶ ኀይለ ማርያም እንደተናገሩት “ጥሪያቸውን እያዳመጡ” ነው ወይ?

ለሐቀኛ የእግዚአብሔር እና የሕዝብ ሰዎች ስንኳን ለኻያ ዓመት የዚህ ሩብ ለኾነ ጊዜ የተጠሩበትን ሓላፊነት በአግባቡ ሳይወጡ በሥልጣን ላይ መሰንበት እንደ መርግ ይከብዳል፤ እንዲህ ላሉት ‹መሪዎች› ክብር መስጠትም የክፉ ሥራቸው ተባባሪና ሽፋን መኾን ነው - እንደ ጥቅመኞቹ የ“ራእይ ለትውልድ” አመራሮች ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ያሬድ ግርማ እንደተናገረው “ኢትዮጵያውያን መሪዎችን አለማክበርና መጎተት ባህላችን ነው” አያሰኝም፡፡ በቀላሉ ለማስረዳት ያህል አቡነ ጳውሎስ የግል ጥቅምና ዝናቸውን በሚገነባ መልኩ የድግስ መርሐ ግብር በሚያካሂዱበት እሑድ ሐምሌ 22 ቀን በፀረ ፋሽዝም አቋማቸው የኢጣልያን ‹ክርስቲያንነትና ሥልጡንነት› ፈተና ውስጥ በመክተታቸው በመትረየስ ተደብድበው መሥዋዕት በመኾን “ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ” የተሰኙትን አቡነ ጴጥሮስን ታቦት ቀርጸን ቤተ ክርስቲያን አንጸን የምናከብርበትን መንገድ ማስተዋል ብቻ ይበቃል፡፡

አዎ! ትውልድ ለአሁን ይኹን ለዘላለም የሚያከብራቸውና የሚዘክራቸው፣ ሊዘክራቸውና ሊያከብራቸውም የሚገባው ከእምነታቸው ታላቅነት የተነሣ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በታደላቸው የጥብዐት መንፈስ (የመንፈስ ልዕልና) ታግዘው÷ ለጽድቅ፣ ፍትሕና ነጻነት በመቆም፤ ፋሽስቶች በገጸ በረከትነት ያቀረቡላቸውን ሀብትና ሥልጣን በመናቅ፤ በምትኩ ለፋሽስታዊ ግፋቸው፣ በደላቸውና ጥቃታቸው ስንኳን ሕዝቡ ምድሪቱ እንዳይገዛላቸው በመገዘት የሰማዕትነትን ጽዋ ጨክነው የተቀበሉትን ሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስንና በሥራ የሚመስሏቸውን ብፁዓን አባቶች ነው፡፡

አቡነ ጴጥሮስ ለሃይማኖታቸው ባላቸው ጽናት (መንፈሳዊ ወኔ)፣ ለአገራቸውና ለወገናቸው ባረጋገጡት ፍቅርና ታማኝነት ዐይን አቡነ ጳውሎስ ሲመዘኑ “ጴጥሮሳዊነት” በእጅጉ ጎድሏቸው ይታያል፡፡ በአንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን አገላለጽ÷ ጴጥሮሳዊነት “በአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ላይ የተመሠረተ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ” ሲኾን÷ በሃይማኖት መሪዎች ላይ የሚታየው “የጴጥሮሳዊነት” ጉድለት ምንጩ “ለዚህ ዓለም ሕይወት ካላቸው ጉጉትና ከመንፈሳዊ ኀይል ይልቅ በአካላዊ ኀይል ላይ ያላቸው ትምክህት” ነው፡፡

መቼም ሐውልትን በቁም ማሠራት፣ ድግስንና ውዳሴ ከንቱን መውደድ፣ በሚልዮን የሚቆጠር ብር በዘመድ አዝማድ ስም በየባንኩ ማድለብ፣ የአባቶችን በር በሌሊት እያስደበደቡ በያዙት አቋም ማሸማቀቅ (ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው ላይ ይደረጋል እንደሚባለው)፣ ከጥቅመኛ አካላትና ሕገ ወጥ ቡድኖች (ቅዱስ ሲኖዶስ በመናፍቅነት ያወገዛቸው እንደ እነ አሸናፊ መኰንን ጋራ ሳይቀር) የጥቅም ትስስር መፍጠር፣ . . . ወዘተርፈ ይህን ዓለም መውደድን፣ በአካላዊ ኀይል መመካትንና ክሕደትን ከሚያሳይ በቀር በአቡነ ጳውሎስ የበዓለ ሢመት ፖስተርና መጽሔት ላይ እንደተገለጸው የ”ኻያ ውጤታማ ዓመታት” ምስክርነት ሊኾን አይችልም፡፡

ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራስዋን ለመቻል በጀመረችው ጥረት ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ከሌሎች ሦስት ኢትዮጵያውያን አባቶች ጋራ ካይሮ ላይ ጵጵስና ከተሾሙት የመጀመሪያዎቹ ጳጳሳት አንዱ ናቸው፡፡ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አገላለጽ “ታሪካቸው ለኢትዮጵያ ክርስቲያን መመኪያ” ከኾኑት ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ጋራ በግፈኛው ፋሽስት እጅ የተገደሉት አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘጎሬ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እኒህ ብፁዓን አባቶቻችን ከወራሪው የኢጣልያ ሠራዊት ጋራ ፊት ለፊት ተዋግተው የሞቱትን ክርስቲያኖች ሳይጨምር በደብረ ሊባኖስ፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ አኵስም እና ዝቋላ አድባራትና ገዳማት ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው መሥዋዕት በመኾን÷ ከነጻነት በኋላ ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ፕትርክና ራሷን ለመቀዳጀት እንድትደርስና ከዚያም ወዲህ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኦርቶዶክሳዊነት “መሠረታዊ ራእዮቿን” ለመያዝ እንድትበቃ ያደረጉ ባለውለታዎቻችን ናቸው፡፡

እነ ያሬድ ግርማ ለራሳቸውና ለአቡነ ጳውሎስ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በመሥራት ‹ራሳቸውን እንደሸጡበት› በሚታመነው የሼራተኑ የራት ግብዣ ለሰነዘሩት አጉል ትችት ይህ የማይበቃቸው ኾኖ ቢገኝ ወርኀ ሐምሌ እንደኾን የብዙ ቅዱሳን ሐዋርያት ዕረፍታቸውና መከራቸው የሚታሰብበት በመኾኑ እርሱን ልናስታውሳቸው እንወዳለን፤ “የሐምሌ ሐዋርያት” እንዲሉ፡፡ በስንክሳሩ ዕረፍታቸውና መከራቸው ከሚታሰብላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ሐምሌ 2 (የቅዱስ ታዴዎስ ዕረፍት)፣ ሐምሌ 5 (የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ የሰማዕትነት ዕረፍትና የ72 አርድእት መታቢያ)፣ ሐምሌ 6 (የሐዋርያው ቅዱስ በርቶሎሜዎስ መታሰቢያ)፣ ሐምሌ 7 (ከሐዋርያውያን አበው አንዱ የኾነው አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ - ሊቀ ጳጳሳት ዘሮሜ - ዕረፍት)፣ ሐምሌ 10 (የሐዋርያው ናትናኤል የሰማዕትነት ዕረፍት)፣ ሐምሌ 14 (የቅዱስ አብሮኮሮስ - የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የሰማዕትነት ዕረፍት)፣ ሐምሌ 18(የጌታ ወንድም የሚባለው የቅዱስ ያዕቆብ ዕረፍት)፣ ሐምሌ 29(የሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ የሥጋው ፍልሰት ከከሶርያ አገር ወደ ቁስጥንጥንያ)፣ ሐምሌ 30 (ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያው ቅዱስ ማቲያስን ሰውን ከሚበሉ የበርባሮስ(ስኩቴስ) ሰዎች/በላእተ ሰብእ/ ከ123 እስረኞች ጋራ ከወኅኒ ቤት ያወጣበት) መታሰቢያ ነው፡፡

አቡነ ጳውሎስ በበዓለ ሢመት ኅትመቶቻቸው ላይ በተመዘገበውና አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን ሐምሌ 5 ቀን 1985 ዓ.ም ሲያከብሩ አስተላለፈውት ነበር በተባለው መልእክታቸው ስለተጠሩበት የፕትርክና ሓላፊነት ሲናገሩ÷ “አደራው ይከብዳል፤ ኾኖም የእግዚአብሔር ጥሪ ነውና እርሱ እስከፈቀደ ድረስ እርሱ ይወደዋል የሚባለውን ሥራ እየሠሩ መጓዝ ነው፡፡ ይህ ሥልጣን ከእግዚአብሔር ጋራ ቃል ኪዳን የተገባበት ስለኾነ የራስን ፈቃድ የሚፈጽሙበት አይደለም፤ በጥልቀትና በማስተዋል ሲመለከቱት የበለጠ ምናኔ ነውማለታቸው ተገልጧል፡፡ ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ከሚገኙበት ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር በአንድ ዓመት ዘመነ ፕትርክናቸው አተኩሬበታለኹ ያሉትን ዐቢይ ቁም ነገር ሲያብራሩም “ሰላምን መስበክ፤ ሰውን ከኅሊናውና ከፈጣሪው፣ ሕዝብን ከሕዝብ ማስታረቅ፤ ሰላም በሰዎች ልቡና፤ ሰላም በሀገርና በጎረቤት እንዲሰፍን ማድረግ ነው፤” ብለው ነበር፡፡

ከኻያ ዓመታት በኋላስ? እውን አቡነ ጳውሎስ ሰውን ከኅሊናውና ከፈጣሪው አስታረቁ ወይስ በአድሏዊ፣ ሙሰኛና ዐምባገነናዊ አሠራር ለብዙዎች (በ1990 ዓ.ም በተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት መሠረት በ90 ከመቶ አገልጋይና ሠራተኛ ላይ) መሰናክልና ጥርጣሬ ፈጠሩ? ሕዝብን ከሕዝብ አስታረቁ ወይስ የጎሰኝነትንና የጥቅመኝነትን ነገር በማበረታታት አበጣበጡ? ሰላምን በሰዎች ልቡና አሳደሩን፤ በሀገርና በጎረቤትስ ሰላም እንዲሰፍን አደረጉን ወይስ ቤተ ክርስቲያን በአገራዊ፣ ኅብረተሰባዊ ሰላምና ዕርቅ ያላትን ሚና በጭፍን ወገንተኝነትና እልክኝነት በመለወጥ፤ ለሰላምና ዕርቅ ንግግር የቅ/ሲኖዶሱን ጥረት ሳይቀር በተንኰል በማጓተት ኀፍረትን፣ መከፋፈልንና ጥላቻን አትርፈውልን እስከ መወገዝ ደረሱ?

ታሪካዊ ማስታወሻ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ951 ዓ.ም ጀምሮ በራስዋ ፓትርያርክ መመራት የጀመረችበት 53 ዓመት ሐምሌ አምስት ቀን 2004 ዓ.ም ተከብሮ መዋሉ ይታወሳል፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ቅዱስ ፍሬምናጦስ (ከሣቴ ብርሃን ሰላማ) በእስክንድርያ ከቅዱስ አትናቴዎስ ተሹሞ በ330 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን ተከትሎ ለዓመታት ግብጻውያን ጳጳሳትን ከዚያው ማስመጣቱ ቀጥሎ ነበር፡፡

ይኹንና በአንድ ግብጻዊ ጳጳስ አገሩን በአገልግሎት ለማዳረስ እንዳልተቻለ በመታየቱ ከመንግሥቱ ስፋት፣ ከሕዝቡ ብዛት ጋራ የሚመጣጠኑ ኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ከ11ው መ/ክ/ዘ ጀምሮ በንጉሥ ቅዱስ ሐርቤ የተነሣውና በ1921 ዓ.ም አራት ኢትዮጵያውያን አባቶችን ጵጵስና በማሾም ተጀምሮ፣ በ1943 ዓ.ም ኢትዮጵያዊውን ጳጳስ ሊቀ ጵጵስና በመቀባት የቀጠለው የነጻነቱ ጉዞ÷ በንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያላሰለሰ ጥረትና ተጋድሎ ሠምሮ በ951 ዓ.ም ለኢትዮጵያዊው ሊቀ ጳጳስ የፓትርያርክነት ማዕርግ በማቀዳጀት (Autocephalous and Independent Church) ፍጻሜ አግኝቷል፡፡

ሐምሌ አምስት ቀን ለ53ኛ ጊዜ የተከበረውን የነጻነት በዓለ ሢመተ ፓትርያርክ አስመልክቶ በተሠራጨው ኅትመት ውስጥ እንደተገለጸው÷ ከ34 ዓ.ም ጀምሮ የእግዚአብሔር ልጅነትን በጥምቀት የተቀበለችው ቤተ ክርስቲያናችን ሀብተ ክህነት ሳይቋረጥባት ዘመናትን ብታስቆጥርም ከቅብጥ የሚላክላትን ሀብተ ክህነት ለማስመጣት እልክ አስጨራሽ ደጅ ጽናት፣ አድካሚና ፈተና የበዛበት ጉዞ እንዲሁም ከፍ ያለ ስጦታ ማበርከት የመሳሰሉትን ተሸክማ ለ1600 ዓመታት ዘልቃለች፡፡ አንድ ሊቀ ጳጳስ አልፎ ሌላውን ሊቀ ጳጳስ ለመተካት አባቶቻችንን ይጠይቃቸው የነበረ ተጋድሎ ከባድና ውስብስብ ነበር፡፡ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በ1951 ዓ.ም የፓትርያርክነት ማዕርግ በመቀዳጀት ያረጋገጠችው የክህነት መብቷ እንዲሁ ያለ ራእይ አልነበረም” የሚለው መጽሐፉ÷ የቤተ ክርስቲያን “መሠረታዊ ራእዮች ነበሩ” ያላቸውን ሲያስረዳ÷ በራስዋ ቋንቋና በራስዋ ልጆች ተከታዮቿን በማስተማር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት፤ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሟን በማጎልበት ለሕዝብዋ በቂ አገልግሎት ማበርከት እንደ ኾኑ ይገልጻል፡፡

አያይዞም እንደ አንድ የኮፕት ሀገረ ስብከት ትቆጠር የነበረችው ኢትዮጵያ የፓትርያርክነት ማዕርግ ከተቀዳጀች 53 ዓመታት በኋላ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ወደ 70 ያህል አህጉረ ስብከትን ማደራጀቷን፣ ከሀገራዊነት ወደ ዓለም አቀፋዊነት በመሸጋገር ዓለም አቀፋዊ ልዕልና መጎናጸፏን አመልክቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ሐዋርያዊ ግዳጃዋን ሙሉ በሙሉ ተወጥታለች ለማለት ባይቻልም ለሐዋርያዊ ሥራ የሚያገለግሉ የጠነከሩ መሠረቶች መመሥረታቸውን መጽሐፉ አመልክቶ÷ በይቀጥላል “በዓለም ዙሪያ የተጣሉ የሐዋርያዊ አገልግሎት መሠረቶቻችንን የማጎልበት ሥራ” መሠራት እንዳለበት ይመክራል፡፡ በመንበረ ፕትርክና ራሳችንን የቻልንበት 53 ዓመት የቤተ ክርስቲያን በዓልም የቀደመውን “የአባቶቻችንን ጥረትና ተጋድሎ በማስታወስ የቀረንን ሐዋርያዊ ሥራ ዳር ድንበር ለማድረስ ቃላችንን የምናድስበት በዓል ነው፤” ብሏል መጽሐፉ፡፡

የበዓሉ ታላቅነትና የቤተ ክርስቲያን በዓል ለመኾኑ የተነገረው በመጽሐፉ ብቻ አይደለም፡፡ በዕለቱ (ሐምሌ አምስት ቀን 2004 ዓ.ም) የተከበረላቸው አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾነው የተሾሙበት ኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመት የተከበረላቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም “ይህ በዓል የግለሰብ በዓል አይደለም፤ ይህ በዓል የቤተ ክርስቲያን የነጻነት በዓል ነው፤ ይህ በዓል ታላቅ ነው፤ ታላቅ ያደረግነው እኛ ነን፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይኹንና በተለይም ከሐምሌ አምስት ቀን 2004 ዓ.ም ምሽት ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያለው ኹኔታ÷ በአሁኑም ይኹን በቀጣዩ ጊዜ የበዓለ ሢመቱን “መሠረታዊ ራእዮች” በመከተል ለአገራዊው - ሉላዊው ተግዳሮቶች ራስን ለማዘጋጀት ይቅርና ተጠብቀው የቆዩ ሀብቶችን (እሴቶችን) እንኳ ለማስጠበቅ ተስፋ የማይጣልበት ነው፡፡

ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ፤
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

10 comments:

Anonymous said...

ahunes zenachu hulu were honebegn betam new metastelut. yesemachutin lemasaweq becha sayhon men madereg endaleben lemin atenegerunem?????? abat endi bichemalekim ayenekam yemil temehrt kale asetemirun ahunem zem belachu were atabezu mefetehewenem negerun

Anonymous said...

Thank you very much Deje Selam! You are doing a highly blessed job! I wonder how you are devoted for this spiritual work. Let the blessing of God be with you!
It is really sad and heart-breaking to hear and understand the depth of corruption found in our Mother Church. I see many corrupted people are running behind this diabolic business. I think it is time to look for ways to defend our church from these corrupted groups who are not religious at all! I am crying....

Anonymous said...

yale sera sem birezem men yetekmal sasebew gen ketenesh gize buhal yegnih seweye sem metsehaf endaihonena charashun endaigermen
selamen lemayak sew yeselam ambasador arif faze new
metsehafu endemilew lekfuwoch selam yelachewem selezih yelelachewen selam felega rasachewen yeselam ambasador yelalu

Anonymous said...

lebochena yeleboche degese!!!!!


egiziabehere yegelagelene

Demile yalew said...

Hope..... Kirstin tesfa aykortm.... Wondinet atche beenba tekche: keto echil yhon medemet agignche: enderahel enba demewoz belche: emeta yhonal musen astekche: yemenfesn sira kesga asleyiche: endihuma alkerm bewore selichich: emetalehu enj PETROSN agigniche: Petern agigniche: one thing for man immpossible are, but for God all things possible... For THIS let near to God and ask for to support us by him own WISDOM!!

Anonymous said...

Deje Selam Beale Simetu Sew Alneberewim Bilachihu Mewashetachihu Lemndinew ? yasazinala ethiopia yalew Hizib Abune Pawlosin mewdedun yayehut You tube Lay Yetelekekewin Bale Simet Temelkiche new yewededachew hulu bidegis- biyabela -Biyatsetsa -binager- minalebet Atiwashu Ewnet Tenager Sewm Yitazebachihal Deje selam Melakm neger yemizegib bemehonu Kemesimeru atiwtsu

Anonymous said...

ጽድቅም፤ ክብርም፤ በቲፎዞ! የሚሆንበት ዘመን ላይ የደረሰን ይመስላል፡፡ ከላይ ስለ ጳውሎስ፤ ከታች ስለ ጎርጎርዬስ፤የተጠለጠፈውን ሳይ የተሰማኝ ይኸው ነው፡፡ ካጠፋሁ እቅርታ፡፡

Anonymous said...

You guys are late now. This guy is the devil messenger.He did all bad things on the name of the church. He celebrate his day on celebrated hotels just to defuse the talks of the nation about the death of his right hand notorious man, meles. If he were a true believer, this kind of celebration is for people like meles, not for him. Because it is for the world happiness. if he really needed it, where was supposed to be done ?

Anonymous said...

መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንዲሉ

Anonymous said...

is he became an ambassador for peace. he has to find a place to represent his own. he never represent peace. instead he represent corruption, heresy, nipotism, Racism, unwanted luxury for a monk, and more of his badness and the desire to be a celebrity. he can represent those no peace and its element like kindness, equalness, spirituaality, and so on. by the way all Melese cadires are start fleeing the country. is he going to where? Hell or Heaven. i dont think he will ran away like others instead he will taste what his god (meles zenawi) tasted. he assumed he is cheated by him and he want to see what Meles did. for our church no one will abuse you anymore.
mulu

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)