July 16, 2012

በጀርመን ስለ ዋልድባ ተጠርቶ የነበረ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሄድ በፓትርያርኩ ታገደ


(ደጀ ሰላም፤ ሐምሌ 9/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 16/ 2012/ READ NEWS IN PDF)፦ በዋልድባ ገዳም ክልል ውስጥ መንግሥት እሠራዋለሁ ያለውን የስኳር ፋብሪካ ግንባታ በመቃወም በጀርመን ያሉ ማኅበረ ካህናት እና ማኅበረ ምእመናን በፍራንክፈርት ከተማ ሐሙስ ሐምሌ 12/2004 ዓ.ም (ጁላይ 19/2012) በኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ተገኝተው የተቃውሞ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ በጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ኃላፊ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ  አስተላለፈውት የነበረው የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ አግባብነት እንደሌለው እና ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ ሰልፉ እንዲወጣ የማድረጉ ጥረት እንዲገታ ቅዱስ ፓትርያርኩ  ጥብቅ መመሪያ አስተላለፉ።

 በቅዱስነታቸው በተፈረውና ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸውን የሚያወሳው ይኸው ደብዳቤ “ሁሎችም የዚሁ ሰላማዊ ሠልፍ ተባባሪዎች እንዲሆኑ በልዩ ልዩ መንገድ እያስገደዱ መሆንዎን ከደረሰን ሪፖርት መረዳት ችለናል፤ ይህም ኢ-ቀኖናዊ የአሠራር ሒደት ዲሞክራሲያዊ አሠራር እንዳልሆነ ልንገልጽልዎ እንወዳለን በማለት ሌሎቹ ካህናት በነፃ ያሰቡበት ሳይሆን በሊቀ ካህናቱ አስገዳጅነት እየሆነ ያለ እንቅስቃሴ መሆኑን ፍራንክፈርት ከሚገኘው የቆንስላ ጀነራል ጽ/ቤቱ የደረሳቸው መረጃ እንዳለ አመልክቷል። 
ሊቀ ካህናት መርዓዊ
ከአምባሳደር ፍሥሓ ጋር

ሊቀ ካህናት መርዓዊ በዋልድባ ገዳም ጉዳይ ወደ ቤተ ክህነቱ ደብዳቤ ጽፈው ምላሽ ባለማግኘታቸው ምክንያት ሰልፉን መጥራታቸውን በአካባቢው በተበተነ በራሪ ወረቀት ላይ መገለጹ ሐሰት መሆኑን እና ቅዱስ ሲኖዶሱን ጨምሮ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ሆነ የውጭ ጉዳይ መምሪያው በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ምንም ዓይነት ደብዳቤ እንዳልደረሰው የጠቆመው ይኸው ደብዳቤ በገዳሙ ላይ ደረሰ የተባለው ነገር በሙሉ ከእውነት የራቀ ነው ሲል ገልል። ከውጪ ሀገር አንቶ ከተለያዩ የኅብረተሰቡ አካላት የተውጣጡ ሰዎች በአካባቢው ተገኝተው ግንባታው ገዳሙን በአደጋ ላይ እንደማይጥል መግለፃቸውን በማተት ሊቀ ካህናቱ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪውን እንዲያነሱ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑንም እንዲያረጋጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ደብዳቤው ከቤተ ክህነቱ አካላት በተጨማሪ ለኢፌድሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በጀርመን ለኢትዮጵያ አምባሳደር እና በፍራንክፈረት ለሚገኘው ለቆንስላ ጄነራሉ ጽ/ቤት ግልባጭ ተደርጓል።

ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ በወርኃ ፋሲካ በደብረ ዘይት እለት በየአጥቢያው እንዲነገር ከላኩት ከስር ካለው መልእክት ባሻገር በግንቦት 26 (ጁን 2/2012) በበርሊን የቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር የተከበሩ አምባሳደር ፍሥሓ አስገዶም በተገኙበት ስጋቱ በዚህም የሚኖሩ ማኅበረ ካህናት እና ምእመናን እንደሆነ መንግት ይረዳ በማለት በቅርብ ቀናት ውስጥ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ እንደሚያደርጉ አሳስበው ነበር።


ታዲያ የፓትርያርኩን ደብዳቤ ተከትሎ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ቅዳሜ ሐምሌ 7 (ጁላይ 14) በኑረምበርግ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴን ዓመታዊ በዓል ለማክበር ከተገኙት ካህናት ውስጥ የተወሰኑትን እና ከየአካባቢው የሰበካ ጉባኤ አባላት የተውጣጡ ምእመናንን አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት አነጋግረዋል። በምሽት በተጠራውም በዚሁ ስብሰባ የሰልፉ ዝግጅት ይቀጥል ወይስ ይሰረዝ በሚል የተወያዩበት ሲሆን በገዳሙ እየደረሰ ያለው ችግር የማይካድ ቢሆንም ትዕዛዙ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ከመምጣቱ አኳያ፤ ይህንንም ባለማክበር የምንወሰደው እርምጃ ከእናት ቤተ ክርስቲያናችን ጋር እንዳይለየን ጥንቃቄ ሊደረግበት ይሻል የሚል ሃሳብ ተነቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ምንም እንኳን ገዳሙ ያለበት ሁኔታ አስጊ መሆኑ እና የምእመናኑንም ትብብር መሻቱ ግልጽ ቢሆንም ሊቀ ካህናቱ እዚህ ጀርመን ሀገር በርሳቸው አስተዳደር ር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ከገንዘብ ብክነት ጀምሮ የባዕድ ትምህርት ሰለባ መሆናቸውን ዝም ብለው እያዩ ነገር ግን በቀጥታ ውሳኔ ሊሰጡበት የማይችሉበትን የዋልድባ ገዳም ጉዳይ ላይ ያላቸውን ተቆርቋሪነት ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረት በምእመናኑ ዘንድ አመኔታን እና ተቀባይነትን እንዳላገኘ በስብሰባው ላይ ተጠቅሷል። እንደ ሦስተኛ ሃሳብ ተነቶ የነበረው ሰልፉ መካሄድ አለበት የሚለው ሲሆን ከረጅም ንግግር በኋላ ባሉት ሃሳቦች ላይ ድምፅ ተሰጥቶ ከፓትሪያርኩ የተላከው ደብዳቤ በነጋታው እሑድ ከሥርዓተ ቅዳሴው በኋላ ለምእመናኑ እንዲነበብ ተወስኖ ስብሰባው አብቅቶ ነበር

በዚሁ በማታው ሰበር ስብሰባ ላይ በቦታው ተገኝተው ከነበሩት ካህናት መካከል የፍራንክፈርቱ ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አባ ሲራክ ወልደሥላሴ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ቀደም ብለው ነገ ቀዳሽ ስለሆንኩኝ መሰብሰብ አልችልም በምትወስኑት ሳብ ላይ ግን እስማማለሁ ብለው የወጡ ሲሆን ይህ አወጣጣቸው ስልታዊ መሆኑ በተሰብሳቢዎቹ ተነቷል። ለሊቀ ካህናቱ በግልጽ አቋማቸውን ማሳወቅ ያልፈለጉት አባ ሲራክ ከአንዳንድ ደጋፊዎቻቸው ጋር በፍራንክፈርት በቆንስላ ጄነራሉ ጽ/ቤት ግንቦት 20 ላይ በነበረ ስብሰባ ሊቀ ካህናቱ ያለ ሕዝበ ክርስቲያኑ ፍላጎት የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ እያስተላለፉ ነው የሚል ነገር መናገራቸው በተቃራኒው ሊቀ ካህናቱ ጋር ሲቀርቡ ጉዳዩን አደባብሰው ለማለፍ የሚሞክሩበት አካሄድ ሆን ብለው የሚያደርጉት ማፈግፈግ እንደሆነ፤ ለፓትርያርኩም ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት እና በሊቀ ካህናቱ እና በቤተ ክህነቱ ከሚፈጠረው ግጭት ለትረፍ የሚጠቀሙበት ስልታዊ አካሄድ እንደሆነ በርካቶች ይስማሙበታል።

አባ ሲራክ በሚያስተዳድሩበት ደብር በፈጠሩት ግልነት በሌለው እና ተጣያቂነት በጎደለው የአስተዳደር እና የስብከተ ወንጌል ችግር ከዓመታት ጀምሮ የሚነሱባቸውን ጥያቄዎች ሆን ብለው በአንድ ብሔር ላይ የሚነሳ ጥያቄ በማስመሰል በምእመናኑ መካከል አመኔታ እንዳይኖር ከመጣራቸውም በተጨማሪ ነገሮች ፖለቲካዊ መልክ እንዲይዙ የሚያደርጉ፤ እነዚህንም ጥያቄዎች የሚያነሱ ምእመናንን አልቃይዳዎች የሚል ኢ-ክርስቲያናዊ እና ተገቢ ያልሆኑ ስሞች እየሰጡ የሚጠሩ ሰው ናቸው። ከአሥር ዓመት በላይ በሆነው የአስተዳዳሪነት ቆይታቸው አንድም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ግዢን ነገር አንሰተው የማያውቁ ሲሆን ከዚሁ ከላይ ከተጠቀሱት ግልፅነት ከሚጎለው የአሠራር ችግሮቻቸው ጋር በተያያዘ ባለፈው ታኅሣሥ ወር 2004 ዓ.ም በሙኒክ በነበረው የካህናቱ እና የምእመናን ስብሰባ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ብፁ አቡነ እንጦንስን ሽቅብ ወጥተው ኃይለቃል ከተናገሩ በኋላ በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት ውጪ የሊቀ ጳጳሱን ስም ፍጹም መጥራት አቁመዋል። ታዲያ በዚህ ዓይነት ብልጣ ብልጥነት የቅዳሜ ማታው ስብስባ ላይ ያልተገኙት አባ ሲራክ በነጋታው እሑድም በጉዳዩ ላይ ምንም ያሉት ነገር አልነበረም።

እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ከፓትርያርኩ የተላከው ደብዳቤ በኑረምበርግ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለተገኙ ምእመናን ከተነበበ በኋላ ውይይት ተደርጎበታል። በመጀመሪያ የደብዳቤው ይዘት ምእመናኑን ያስቆጣ በሰልፉ እንወጣለን ወደሚለው አዝማሚያ ያዘነበለ ቢሆንም በውይይቱ ሂደት የተነሱ ሃሳቦች በተቃራኒው በሊቀ ካህናቱ አራር ላይ ጥያቄ ሳያስነሱ አላለፉም። በተለይም የመናፍቁ የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ አለቃ ጉዳይን በሚመለከት ላለው ችግር መፍትሄ ለመስት ዋስትና የምትገቡልን ከሆነ እናንተ በጠራችሁት የሰላማዊ ሰልፍ ላይ ለመገኘት ችግር የለብንም አሊያ ግን ከእናንተ ጋር አብሮ ሰልፍ ላይ ለመገኘት ያዳግተናል የሚል ሳብ ከመነቱም ባሻገር ሊቀ ካህናቱ ከዚህ በፊት በርካታ ውሳኔዎችን ሲወስኑ ምእመናንን ያማከሩበት ጊዜ እንዳልነበረ በማሳሰብ አሁን ጭንቅ ሲመጣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር አቤት ማለታቸው እንዳሳዘናቸውም የተናገሩ ነበሩ።

አንዲት ምእመን በተለይ እውነቱን ልንገርዎት ብዙ ሰው በዚህ ሰልፍ ላይ ቢገኝ ደስ ይለዋል ነገር ግን እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችንን እንዳንወጣ ያደረገን ይህ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ በእርሶ መተላለፉ ነው ብለዋል። ይህ ሳብ በእርግጥም ብዙዎችን የሚያስማማ መሆኑ ሃሳቡን ተከትሎ የነበረው ጭብጨባ አመላካች ነው። ሊቀ ካህናቱ እንደዚህም ዓይነት አስተያየት ተሰጥቷቸው መናፍቁን የቪዝባደን አለቃ ከመከላከል ወደ ኋላ አላሉም። በግለሰቡ ዙሪያ በቀጥታ ለተነሱትም ጥያቄዎች ፍጹም ከእውነት የራቁ መከራከርያ ሳቦችን በማንትና አላስፈላጊ እና አሰልቺ የሆኑ ታሪኮችን በማተት ሰውን ለማሰላቸት ሲሞክሩ ታይተዋል። በንግግራቸውም ለቪዝባደኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አለቃ ክህነታቸውን የመለሱላቸው አቡነ ዮሴፍ እንደሆኑ እሳቸውም ክህነታቸውን አልመለስኩላቸውም ብለው የገለጹበት ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።

ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ይህን ይናገሩ እንጂ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በሐምሌ 2 ቀን 2003 ዓ.ም ለሚመለከተው ሁሉ በሚል ርዕስ በጻፉት ደብዳቤ ከላይ የተገለጹት መናፍቁ አለቃ ከስህተቴ ተመልሻለሁ ባሉ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መጠቀም የሚችሉት እንደማንኛውም ማኅበረ ምእመናን ነው ከማለት በስተቀር በቤተ ክርስቲያን በክህነት አገልግሎት ተመድበው እንዲሠሩ በቃልም ሆነ በጽሑፍ ያስተላለፍኩት ምንም ዓይነት ትዕዛዝ የሌለ መሆኑን ማለታቸው ይታወሳል።

በእርግጥም ሊቀ ካህናቱ በዋልድባ ጉዳይ ሌላ ትርፍ ለማትረፍ የሚያደርጉት አካሄድ እንደሆነ አጠራጣሪ አይደለም። በእሑዱ ውይይት የነበሩ አስተያየት ለመስጠት እጃቸውን አውጥተው እድል ያላገኙ አንዳንዶች ከውይይቱ በኋላ ዋልድባ ገዳሙ ይጠበቅልን ስንል እኮ በገዳሙ፤ በበረሃው ዋዩን ቁሩን ችለው፣ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው፣ ግርማ ሌሊቱን ጸብአ አጋንንቱን ታግሰው የኖሩ ቅዱሳን አባቶቻችን ዘወትር በጸሎታቸው የሚያስቧት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓቷም ጭምር ካልተጠበቀልን ምኑን ጥያቄያችንን አቀረብነው? ሥርዓቷን እየጣሱ፤ መቅደሷን ምእመኗን እያሳለፉ ለከሃዲ እየሰጡ ለዋልድባ እሃለሁ ቢሉ ጩኸቱ አይሰማንም ከነሱ ውጪ በራሳችን የሰላማዊ ሰልፍ ብናዘጋጅ ይመረጣል ሲሉ የተሰሙ አሉ።

ሊቀ ካህናት መርዓዊ ከሥርዓት ውጪ ሲሠሩ የመናፍቁ ቄስ ገዳሙ ደምሳሽ ጉዳይ የመጀመሪያው አይደለም። እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2007 በጀርመን ማግደቡርግ ከተማ በተካሄደ የፕሮቴስታንት እና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ አሥራ አንድ የተለያዩ የእምነት ተቋማትን ባገናኘ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ፍጹም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሠረተ ሃይማኖት ውጪ በሆነ መልኩ አንዱ የሌላውን ጥምቀት እንዲቀበል በሚል ሰነድ ላይ በመፈረም ከባድ ስህተት የፈፀሙ ሆኖ ሳለ በመፈራረሜ የፈፀምኩት ስሕተት ባለመኖሩ አልፀፀትም ይቅርታም አልጠይቅም፣  የምፀፀተው ስፈራረም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ባለመጠየቄ ነው፤ እንዲህ ሰዎችን የሚያሳዝን መሆኑን አላወኩም፡፡ ፈቃድ ብጠይቅ ትልቅ ቁም ነገር ነበረው ብቻ በማለት ነገሩን በማቅለል እና ስህተትም አልፈፀምኩም በማለት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በኅዳር ወር፣ ቅጽ 19 ቁጥር 236 እትም ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ መናገራቸው የሚታወስ ነው። በዚህ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ ወደፊት በሰፊው የምንመለስበት ይሆናል።

በጀርመን ያሉ ምእመናንን ያሳዘነው ሌላው ነገር ግን የቤተ ክህነቱን አሠራር ይመለከታል። በጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውስጥ የሚታየውን የአስተዳደር ብልሹነት ጨምሮ በቪዝባደን ያለውን የመናፍቁን ቄስ በሚመለከት፤ በግለሰቡም ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን እየተው የሚወጡት የዋሃን ምእመናን ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው በተደጋጋሚ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለሚገኙ አካላት የምእመናንን ኅብረቱ ቢያሳውቅም እስካሁን ድረስ ምላሽ ሳይሰጠው ቆይቶ አሁን ግን ገና ለገና ሰላማዊ ሰልፍ ሊወጣ ነው ተብሎ በተሰማ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሰልፉን የሚከለክል ከቅዱስነታቸው ቀጥታ ደብዳቤ መጻፉ ብዙዎችን አስገርሟል። ሁኔታው በእውነትም እንጠብቃታለን ለሚሏት ቤተ ክርስቲያን ቅንጣትም ታክል ጉዳይ እንደማይሰጣቸው ይልቁንም ከመንፈሳዊው ይልቅ የፖለቲካው ነገር እንደሚያሳስባቸው ያሳየ ሁነኛ አጋጣሚ ነው።

ቸር ወሬ ያሰማን።
አሜን።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)