June 23, 2012

በሙስና የሚታሙት የላፍቶ ደ/ትጉሃን ቅ/ሚካኤል አስተዳዳሪ አባ አእምሮ ሥላሴ ታከለ የአ/አ ሀ/ስብከት ም/ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተሾሙ


·         የደብሩ ሰበካ ጉባኤ በአስተዳዳሪው ላይ ያቀረበው የሙስና ክስ በመጣራት ላይ ነበር::
·         ወርቅ፣ የውጭ ምንዛሬና የሌሎች ነዋያት ግምት ሳይጨምር በጥሬ ብር ከ200,000 በላይ መዝብረዋል::
·         የአስተዳዳሪውን ሹመት በማስፈጸም የእጅጋየሁ በየነ ሚና አለበት::
·         የሀ/ስብከቱን ገዳማትና አድባራት ሓላፊዎች ለዐመፅ ለማዘጋጀት አባ ጳውሎስ ያሰቡት ዕቅድ አካል ይኾን?
(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 15/2004 ዓ.ም፤ ጁን 22/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF):- ሰባኬ ወንጌል ከነበሩበት የመርካቶ ደብረ ኀይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ወደ ላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተዘዋውረው በአስተዳዳሪነት ከተሾሙ ሁለት ዓመታትን  ብቻ ነው ያስቆጠሩት - አባ አእምሮ ሥላሴ ታከለ፡፡ በሁለት ዓመት የደብሩ ቆይታቸው ግን ካራታቸው በመዝገብ ላይ ያልሰፈረ የወርቅ እና የውጭ ምንዛሬ ስርቆትን ጨምሮ ለተፈጸሙ ሕገ ወጥ የነዋየ ቅድሳት ሽያጭ እና የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ እንዲሁም ያለ ደረሰኝ ገቢ የመሰብሰብ ድርጊቶች ዋነኛ ተጠያቂ መኾናቸው በሰፊው ይነገራል። በደብሩ የአንድ ወገን የጎጠኝነት አስተሳሰብ እንዲስፋፋና ሌሎች በርካታ አስተዳደራዊ ችግሮችም እንዲከሠቱ ምክንያት የመኾናቸው ጉዳይ አደባባይ የወጣ ምስጢር መኾኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ።


በድንገት ተነሥተው ከሄዱበት ገዳም በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ምንኩስና ከተቀበሉ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ የላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የኾኑት አባ አእምሮ ሥላሴ÷ ይህን ሹመት ለማግኘት ለቀድሞዎቹ የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ሓላፊዎች እስከ 2ዐ ሺሕ ብር ገደማ መማለጃ መስጠታቸው ተጠቁሟል፡፡ አባ አእምሮን በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች ሰውዬው ገንዘብ አምላኩ፣ ቤት ለመሥራትና መኪና ለመግዛት የሚቋምጡ፣ የመጠጥ ሱስ እና ከምንኩስና ሕይወት ይኹን ከጥሩ ምእመን ጋራ የማይጣጣሙ እኵይ ጠባዕያትን የተላበሱ ስለመኾናቸው ይመሰክሩባቸዋል፡፡ ከዕድሜያቸው አለመብሰልና ምግባር ጉድለት አኳያም የአስተዳዳሪነት ይኹን አሁን በአባ ጳውሎስ የተቸራቸው ሥልጣን በጭራሽ እንደማይገባቸው በመግለጽ ይተቿቸዋል፡፡

ምንጮቹ አያይዘው እንደገለጹት÷ አስተዳዳሪው ወደ ደብሩ ከመጡ ከአንድ ዓመት በኋላ አዲስ የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ ከእርሳቸው ጋራ በነበረው የአንድ ዓመት ቆይታ ተግባብቶ መሥራት አልቻለም፡፡ እንደሌሎቹ ጥቅመኛ አለቆች በቃለ ዐዋዲው መሠረት መሥራትም ኾነ መመራት ማይፈልጉት አባ አእምሮ÷ የጋራ ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የግል ፍላጎታቸው ጎልቶ የሚወጣባቸው አጋጣሚዎች በርካታ እንደነበሩ የዜናው ምንጮች ያደረሱን መረጃ ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታ ከሰንበት ትምህርት ቤቱ፣ ከስብከተ ወንጌል እና ልማት ኮሚቴዎች ጋራ ተግባብተው መሥራት ብቃት ይኹን ፍላጎት እንዳልነበራቸው ነው ዘገባው የሚጠቁመው፡፡

አባ አእምሮ በተለይም ከቀድሞው የደብሩ ጸሐፊ ጋራ በመተባበር የፈጸሟቸውን ሕገ ወጥ ድርጊቶች በተመለከተ ሰበካ ጉባኤው ከሁለት ወራት በፊት ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በዝርዝር ማመልከቱን ተከትሎ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን በግንቦት ወር ተልኮ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ይኹንና አጣሪ ቡድኑ ችግሩ ለማጣራት ወደ ደብሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጣበት ወቅት÷ የአስተዳደር /ቤቱ ማኅበረ ካህናቱ ተሟልተው እንዳይገኙ ለማድረግ የሞከረ ቢኾንም ሰበካ ጉባኤው ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በመጠየቁ፣ የአጣሪ ቡድኑ ሰብሳቢ ንቡረ እድ አባ ዮሐንስ ገብረ ዮሐንስ በሰጡትም ማሳሰቢያ ስብሰባው ከሳምንት በኋላ የአስተዳደር /ቤት ሠራተኞች፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት /ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባላት እና የጥበቃ አባላት ተሟልተው በተገኙበት ተካሂዷል፤ ሀገረ ስብከቱም በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥበት በተገለጸው የአጣሪ ቡድኑ ሰብሳቢ ማሳሰቢያ መሠረት አቤቱታው ፍትሐዊ ውሳኔ እንደሚያገኝም ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡

በዚህ መካከል ከሰኔ ሦስት ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከእጅጋየሁ በየነ ጋራ ያላቸውን የቀደመ ወዳጅነት ማጠናከራቸው የተገለጸው አባ አእምሮ÷ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት እና የሰንበት /ቤት ሥራ አስፈጻሚዎች የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እንደ ኾኑ፣ እርሳቸውን በሐሰት እንደ ከሰሷቸውና ሥራም አላሠራ እንዳሏቸው አድርገው ስሞታ እንዳቀረቡላቸው ነው የተጠቆመው። እንደ ቅርብ ምንጮች ከኾነ ታዲያ÷ ወይዘሮዋ አስተዳዳሪው ምንም ዐይነት ችግር እንደማይገጥማቸው በማደፋፈር ጉዳዩን ለፓትርያርኩ እንደሚያሳውቁ ነግረዋቸው ተለያይተዋል፡፡

ይህ በኾነ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነበር ለአባ አእምሮ ሥላሴ ታከለ አቤቱታው ሹመት ኾኖላቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት /ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው ስለ መመደባቸው የተሰማው፡፡ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብሩ በተከበረበት ሰኔ 12 ቀን 2004 ዓ.ም ከሀገረ ስብከቱ የተላኩትና የዕለቱን ትምህርት የሰጡት የአጣሪ ቡድኑ ሰብሳቢ ንቡረ እድ አባ ዮሐንስ፣ ከእርሳቸው በማይጠበቅ አኳኋን አስተዳዳሪውን ሲያሞካሹ እና የሹመታቸውን ‹የምሥራች› ሲናገሩ ከነፋስ ጋራ እንጂ አባ አእምሮን አሣምሮ ለሚያውቀው የላፍቶ ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ምእመን የሚናገሩ አይመስሉም ነበር - እየሠሩ ያሉት መልካም ሥራ በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ብቻ ተወስኖ እንዳይቀርና መልካም ሥራቸው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሁሉ እንዲስፋፋ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት /ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው እንዲያገለግሉ በቅዱስ አባታችን በአቡነ ጳውሎስ ተሹመዋል፡፡” መቼም ‹ማፈር ድሮ ቀርቷል›ና ተሿሚው አባ አእምሮም በታቦተ ሕጉ ፊት ሰዎች  ወደ ላይ ሄደ ይሉኛል፤ እኔ ግን አልሄድኩም፤ ይህን ቦታ ገና እናለማለን” በማለት ሲዘርፉት በነበረው አገልጋይና ምእመን ላይ አላግጠዋል፡፡

ይህን ድራማ መሳይ አሳፋሪና አሳዛኝ ኹኔታ በቁጭት የተከታተሉት የደብሩ ማኅበረ ካህናት÷ ንቡረ እድ አባ ዮሐንስ ለአጣሪነት መጥተው በነበሩበት ወቅት በስብሰባ ላይ የተናገሩትን አጽናኝ እና መልካም ቃላት እያስታወሱና በዕለቱ የተናገሩትን በማነጻጸር÷ አይ አንቺ ቤተ ክርስቲያን! ከቶ ማን ይኾን በዚህ ዘመን የሚታመንልሽ?” በማለት እጅጉ ማዘናቸው ተዘግቧል፡፡ አንዳንዶቹም ንቡረ እዱ በፊት የተናገሩትን አስተባብሉ በሚል ተገደው እንደ ኾነ እንጂ በጤናቸው እንዴት በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ይናገራሉ?” በማለት ሲጠይቁም ተደምጠዋል፡፡

ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል ፍትሕ ሲጠባበቁ ነገሩ ግራ ያጋባቸው ምእመናን የሀገረ ስብከቱ ፍትሕ ሲጠባበቁ የነበሩ ታላላቅ አባቶችና እናቶች ምእመናንም “ውርደታቸው ክብራቸው (ክብራቸው በነውራቸው) ይኾናል የተባለው ዛሬ ተፈጸመሲሉ ሌሎች ሰዎች ደግሞጭራሽ አያፍሩም ወይ? ለማፈርም እኮ ኅሊና ያስፈልጋል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የክሱን ጉዳይ የያዘው አጣሪ ቡድን የደረሰበት ውሳኔ ሳይታወቅ ለአስተዳዳሪው የተሰጠው ሹመት፣ የአጣሪው ቡድን ሰብሳቢ እርስ በራሳቸው የሚጋጩ አስተያየቶች እና ያልተጠበቀ ሙገሳ እንዲሁም ሰሞኑን አስተዳዳሪው በተደጋጋሚ በየሰፈሩ በእኔ ላይ የሚወራውን አትስሙ፤ አትመኑ፤ እንደሚባለው ከዚህ ቦታ የተነሣኹት በቀረበብኝ ክስ አይደለም፤ ይልቁንም በሠራኹት መልካም በቅዱስ አባታችን ተሹሜያለኹ፤ እውነታውም ይህ ብቻ ነው፤በማለት በዐውደ ምሕረት እየተናገሩ የሚገኙት [ማስታዋወቂያ] ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን አሠራር በሚገባ የሚያውቁቱ “ድሮውንስ ምን ተጠብቆ ኖሯል?” ቢሉም ለአጥቢያው ምእመናን ÷ የአባ አእምሮ የምክትል ሥራ አስኪያጅነት ሹመት የአባ ጳውሎስን አስተዳደራዊ ፍትሕ በተጨባጭ የፈተነበትንና በሩቅ ሲሰ የቆየውን በቅርበት ያረጋገጠበትን አጋጣሚ ፈጥሮለታል፤ የቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓልም ውደ ምሕረቱን በተቆጣጠሩት ግለሰቦች ሐሰት የተሰበከበት እና እውነት ለጊዜውም ቢኾን አንገቷን የደፋችበት የማይረሳ ቀን ኾኖ አልፏል።

ቀደም ሲል ባሰፈርነው ዘገባችን እንደተጠቆመው÷ በእጅጋየሁ በየነ ባለሟልነት ከአባ ጳውሎስ የተገኘው የአባ አእምሮ ታከለ ሹመት የፓትርያሪኩን ዐምባገነንት፣ የተጠያቂነት መጥፋት እና በወይዛዝርቱ አቅራቢነት እየገነገነ የመጣውን የሥልጣን መቆናጠጥ አባዜ ከማስረገጡም ባሻገር የሀ/ስብከቱን አድባራትና ገዳማት አስተዳደር ሓላፊዎች በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ለዐመፅ የማዘጋጀት ደባ አካል ሊኾን እንደሚችል አስተያየት እየተሰጠበት ይገኛል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)